የጊዜን ቡቱቶ አሳር፣ የዘመንን ውድቅዳቂ፣
የኑሮን ስንክሳር መዝዞ፣ የህይወትን ብጭቅጫቂ፣
ከ’ነ ዝብዝቡ ጎትቶ፣ ከ’ነ ኮተቱ ጎልጉሎ፣
ከ’ነ ተሳቢው ስቦ፣ ከ’ነ ጓዙ ካንቺ ጥሎ፣
እድል ስቃይ አሸክሞሽ፣
ህመምን ዱሎ ከአምሮሽ፣
ነጋ ጠባ ሲያስጨንቅሽ፣ ነጋ ጠባ ስትማቅቂ፣
በነገር ብዛት ስትዝዪ፣ በሀሳብ ብዛት ስትደቅቂ፤
ኦ ያ’ንቺስ….
የተጫነሽን መከራ፣ ማንም ላይጥለው ነቅሎ፣
ሁሉን በራስሽ ችለሽው፣ ለሌላ ሰው ላታስነኪ፣
ሁሉን በልብሽ ይዘሽው፣ ተስፋን በኑሮሽ ስትሰብኪ፣
ስኬትን – በልጆች ደስታ፣ በጥጋባቸው ስትለኪ፣
እርካታን – በውጣ ውረድ፣ ሥራን – በጥረት ስትሰፍሪ፣
የኑሮን ግለት ለማብረድ፣ ባ’ሳብ ላይ ታች ስትቧትሪ፣
ሀዘንን በልብሽ ይዘሽ፣ ተስፋን በፊትሽ ስትዘሪ፣
ልጅ ብቻ ጉልበት ሆኖልሽ፣ በእናትነት ስትዳክሪ፤
ኦ አንቺስ….
ወገብሽን እያለፋሽ፥ እለት በመሸ በነጋ፣
መባተል ሆኖብሽ እዳ፣ ሸክም ሆኖልሽ ጸጋ፥
ከቀን ትብስ ስትታገይ፥ የቀን ትሻልን ፍለጋ፥
መቼ ተስፋ ልትቆርጪ? መቼ እምነትሽ ሊናጋ?
ዙሪያ ገባው ሲያደናግዝ፣ ‘ሚያዝ ‘ሚጨበት ሲጠፋ፣
ህይወት ጣእሯ ጠንክሮ፣ ነገር ዓለሙ ሲከፋ፣
በሸክም ቤትሽን ልትጠግኝ፣ የኑሮን ቁስል ልታክሚ፣
ማልደሽ ከጫካ ገብተሽ፤ ጭራሮ፣ ቅጠል ልትለቅሚ፥
ስቃይሽን ታሰፊያለሽ፥ የኑሮን ክፍተት ልትደፍኚ፤
አካልሽን ትሰብሪያለሽ፥ ስብራትሽን ልትጠግኚ።
ኦ አንቺስ!
ልጅ – ዓለም ብለሽ ወስነሽ፣ ቤትን በልጅ ስትገድሚ፣
ለምሰሶው ፀንቶ መቆም፣ ለዓለምሽ ውበት ስትደክሚ፣
የሴት ወግ፥ የጓዳ ሥራ፣ የማጀቱ ጉድጉድሽ፣
ባልን ለመርዳት ከጓሮ፣ በእርሻ ሥራ መጠመድሽ፣
ሳይበቃሽ፣ አርፈሽ ሳታውቂ፤
ለአፍታ እንኳ’ አምረሽ፣ ሳትደምቂ፣
የመከራን ጥምር ሸክም፥ ከጫንቃሽ ላይ ልትንጂ፣
ለልጆችሽ ቀንቶ መቆም፣ ዘመንሽን ልትማግጂ፣
ራስሽን ታጎብጫለሽ – ካለቦታሽ በቦታቸው፤
ሰውነትሽን ታለፊያለሽ – ካለእረፍት ለ’ረፍታቸው፤
ኦ አንቺስ!
ማድያት ፊትሽን ወርሶት፣ ፀአዳው ገፅሽ ወይቦ፣
በጢስ፣ በጥላሸቱ፥ ገላሽ እንደጨርቅ ነትቦ፣
ቅጠልሽን ተሸክመሽ፥ ከመዝለቅሽ ከመንደሩ፣
እንስራ አዝለሽ ትርቂያለሽ፥ ውሀ ለመቅዳት ከጥሩ፤
ረፍዶ ልጅ ለማባበል፥ ባ’ንቀልባ አዝሎ ‘እሽሩሩ’፣
ቀን መሽቶ የባልን ዱላ፣ ከጀርባሸ ፥ ጦም ከማደሩ፣
ደግሞ በገበያም ቀን ሸክም፣ ሸጦ ለመግዛት መጣሩ፣
ልጅ አድጎ ተነሳ ሲባል፣ በቦታው ሌላ ሊመጣ፣
አንቀልባው ከመታጠፉ፣ ‘ሳጥን ሳይገባ ሊወጣ፤
አቤት ያንቺስ አበሳ፣ እግዚኦ የጀርባሽ ጣጣ።
ጭነትሽን ላያግዙሽ፣ ልጆችሽ ላያቀሉልሽ፣
በመሳሳትሽ ተገፍተው፣ በመጫን ማውረድ ላይረዱሽ፣
ወልደሽ – የወላድ መሀን፣ አፍርተሽ – አልቦ ፍሬ ዘር፣
ሰጥተሽ አዱኛ ብላሽ፣ ወርቅ ሰጥቶ፥ ወሳጅ ጠጠር፤
ዘርሽ የትም ተበትኖ፣ በየወደቀበት ባክኖ፣
ለስንት ብቅል ሲጠበቅ፥ በየደረሰበት መክኖ፣
ያልመከነውም ተለቅሞ፣ በወፎች መንጋ ተወስዶ፣
ከአድማስ ወደዚያ ተሻግሮ፣ ከባህር ወዲያ ተሰድዶ፣
ኦ ያ’ንቺስ!
ከቶ ምን ልበልሽ እቴ፣ ‘አሻም!’ ነው እንጂ ስትመጪ፣
የኑሮን ሸክም ልትንጂ፣ ሸክም ሸክፈሽ ስትወጪ፣
የኑሮን ሸክም ልታቀይ፣ ሸክም ጠፍረሽ ስትወርጂ፣
በህይወት ያ’ሳብ መንገድ ላይ፥ ከ’ነ ጭነትሽ ስትነጉጂ፣
ገና ከሩቁ ሳይሽ፥ ከ’ነ ጭንቀትሽ ስትደርሺ፣
___ሌላማ ምኑን ችዬበት? ‘አሻም!’ ልበልሽ እንጂ፤
አሻም እቴት! አሻም፣ አሻም፣ አሻም እ’ቴ!
የት አውቄበት ልረዳሽ? የት ችሎት ሸክሙን ጉልበቴ?
ላበርታሽ በቃል፣ በሃሳቤ፤ እስኪ ልርዳሽ ባንደበቴ፤
አሻም! አሻም! አሻም እቴ!
ግን ተስፋ አለኝ…
ከያሉበት ተጠራርተው፣ ልጆችሽ ሲሰባሰቡ፣
ተንጠራርተው ሲደርሱበሽ፣ ትጋት ልፋትሽን ሲያስቡ፣
‘ሆ. . .’ብለው ደጅሽ ሲመጡ፣ ማጀት ጓዳሽን ሲከ’ቡ፣
ተስፋ አለኝ እቴት፣ . . . ይህም ያልፋል፤
ጀርባሽም ከሸክም ያርፋል፡፡
/ዮሐንስ ሞላ/
(ማስታወሻ: ይህ ግጥም ከዚህ በፊት በተደረገ የ”በጥበብ እንኑር” የስነ-ፅሁፍ ውድድር ላይ ተሳትፎ በ3ኛ ደረጃ ተሸላሚ ነበር።)
Erkatachin ke elet wede elet eyechemere yimetal yalew. shi amet yanurilign yatsifilign…
It’s nice, pls keep it up!
Asham Guade! I have to tell you this is your Masterpiece!
ውብ! ውብ! ውብ! ብቻ..!
ተስፋ አለኝ እቴት፣ . . . ይህም ያልፋል፤
ጀርባሽም ከሸክም ያርፋል፡፡ ጆዬ በርታልን