የግልብ ዘመን ግጥሞች…

‘ዓሳ ጎርጓሪ….’

በትዝታ ፈረስ ጭኖ፣ ወደኋላ አሳፍሮኝ ያለፈውን እያስቃኘኝ፣ ብቻዬን ሲያዝናናኝ የዋለ ደስ የሚል እሁድ። ‘ዓሳ ጎርጓሪ ዘንዶ ያወጣል።’ እንዲሉ የጠፋብኝን አስፈላጊ ወረቀት ፍለጋ ከማለዳው አንስቶ፥ ሳጥኔን ስበረብር ስንትና ስንት ወረቀቶች አግኝቼ ከራሴው ጋር ስጫወት፣ አንዳንዶቹን ለእህቶቼ እያነበብኩላቸው አብረን እየሳቅን፣ በየመሀሉ ደግሞ በዋናነት የምፈልገውን ነገር እየረሳሁት ስባዝን ዋልኩ። ወይ ጉድ! ምን ያላገኘሁት ነገር አለ? ደብዳቤ (የተፃፈልኝ፣ የፃፍኩት፣ ያልጨረስኩት፣ ያልላኩት…)፣ ግጥም፣ መጣጥፍ፣ ልብወለድ….መሳይ ነገሮች (ለአቅመ እነዚያ ስያሜዎች ያልደረሱ።)

ልጅነት እንዴት ደስ ይላል? በተለይ የ2ኛ ደረጃ ተማሪ ሳለሁና ከዚያ በፊት የፃፍኳቸውን ነገሮች ስመለከት የነገሮች ብስለትና የአገላለፅ ችሎታ ላይ የጊዜ ሚና ፍንትው ብሎ ታየኝ። በጣም የሚያስቁ አገላለፆች። ቤት ከቤት በመምታት ላይ ብቻ ያተኮሩ ዝም ብሎ ግጥሞች። እንደ ነገሩ የተደረደሩ የቃላት ትርምስ የተሞላባቸው አረፍተ ነገሮች። በሽቅድምድም የተፃፉ የሚመስሉ ያልበሰሉ ሀሳቦች። ቤት አመታታቸው በሳቅ የሚያፈርሱ መስመሮች። (ልክ ‘ነው። ነው።’ ወይም ደግሞ ‘እና፤ እና’ ብለው ሁለት መስመሮች በተከታታይ እንደሚዘጉ ዓይነት…) ዜማ የማይሰሩ ለዛ ቢስ ድርድሮች። ለዛ ባለው የቤት ምት የተሸፈኑ ተራ ሀሳቦች።… እያሳቁኝ። እያስገረሙኝ። በራሴው ፊት እያሸማቀቁኝ። (እንዲያው ጨዋታ እንጂ በጉርምስና ሀሳቤና ድርጊቴ በጉልምስናዬ እሸማቀቅ ዘንድስ ሀይማኖቴ አይፈቅድልኝም።:)) [ዛሬ መሀመድ ሰልማን ከልጅነት የግጥም ዝንባሌ ጋር በተያያዘ የፃፈውን status update ብንመለከትም በተያያዥ የሚነግረን ነገር አለው።]

ያኔ በልጅነት እንደሰዉ የልብ ልብ ተሰምቶኝ አሳትሜያቸው፣ ለሰው ጆሮ አድርሻቸው ቢሆን ኖሮ ምንስ ይውጠኝ ነበር? ሆ… ማርያም ተፍታኛለች አቦ! ማርያምን!:) በርግጥ እንዲህ ያሉ ተራ ፅሁፎች ተሰባስበው በመፅሀፍ ሲታተሙ እና ለአደባባይ ሲውሉ ማየት አዲስ አይደለም። ዛሬም ብዙ የምንታዘበው ሞልቷል። ከሙላቱ የተነሳም ነገሩን እየለመድነው ነው። መፅሀፍ እስኪሆኑ ድረስ ሳንጠብቅ እንኳን በየግድግዳዎቻችን ላይ የምንለጣጥፋቸው ግጥሞች በአብዛኛው የግጥምን ደረጃ አይጠብቁም። ቤት ከቤት ከማማታት፣ ቃላት ከመደርደር አይዘሉም። ከዚህም ጋር ተያይዞ ይመስላል የአገራችን የግጥም መፅሀፍ ገበያ በጣም ቀዝቃዛ ነው። እንደዚህ ምሽት ቀዝቃዛ።:) ግጥምን ብዙዎች ይፈልጉታል፥ ግን ደግሞ ብዙዎች አይገዙትም። (ብዙዎች አይፈልጉትም።) ለጨዋታው እጥረትና ቀጥተኛነት በዋናነት ስነ ግጥምን ይዘን እንዝለቅ…

‘ፍቅር ሲደቁሰው ሁሉም ሰው ገጣሚ ይሆናል…’

ሥነግጥም ለስሜት ቅርብ የሆነ የፅሁፍ ዓይነት በመሆኑ በተለያዩ ጊዜያት ብዙዎች ወደው ይሞክሩታል። በአንፃሩ ደግሞ ሥነግጥም በሥነፅሁፍ ስር ያለ አንድ ዘርፍ ነውና፥ የራሱ ህግጋቶች (ደንቦች) እንዲሁም ለዘርፉ የተሰጡ የራሱ አዋቂዎች አሉት። ማንም ሰው ተነስቶ ሱቅ ከፍቶ መነገድ ሊፈልግ ይችላል። መነገድ የፈለገ ሁሉ ግን ነግዶ ለማትረፍ የሚያበቃ የገበያ ገድ ወይም የንግድ ክህሎት ሊኖረው አይችልም። ለንግድ ስራው በጣም ፍቅርና የተወሰነ የንግድ ስራ ያለው ቢኖር ግን በልሂቃን ድጋፍና ምክር ሊሻሻልና የበቃ ነጋዴ ሊሆን ይችላል። ለዚህም ለኪሳራ ራሱ ሀላፊነቱን (risk) ወስዶ ነው። በእኔ መረዳት፥ ሥነግጥምም እንደዚሁ ነው።

ከዚህ ጋር በተያያዘም ታላቁ የግሪክ ፈላስፋ ፕላቶ at the touch of love everyone becomes a poet’ (‘ፍቅር ሲደቁሰው ሁሉም ሰው ገጣሚ ይሆናል…’) ይላል።  ፍቅር ሲደቁስ የጀመረ የመግጠም አባዜ ግን ለሁሉም ሰው እስከመጨረሻው ድረስ ዘልቆ መሄድ ስላለመቻሉ የብዙ ሰው ታሪክ ነውና የመግጠም ፍላጎት በሰዎች ህይወት ውስጥ የሆነ ቦታ ላይ ሊከሰት የሚችል ነገር መሆኑን እንረዳለን። ሆኖም በተለያየ ስሜት ውስጥ ሆነን የፃፍናቸውን ግጥሞች ለሚመለከታቸው (በቀጥታ ለጉዳዩ  ባለቤቶች) ካልሆነ በቀር ለሌሎች በትኩሱ አናጋራቸውም። አንድም ስሜታችንን በመደበቅ ሰበብ፣ ሌላም የግጥማችንን ደረጃ ማወቅ ባለመቻላችን፥ የፃፍናቸውን ለማንም ሳናሳይ በፊት እኛ ጋር ይቆያሉ። ከርሞ… ስሜቱ ሸሽቶን ከእኛ ጋር የቆዩት ግጥሞች ግን ጣእምና ውበታቸው ሲያብለጨልጭብን ጊዜ፥ የፃፍነውን ለሰዎች ስለማጋራት እናስባለን።

ስለሆነም ሀሳባችንን በግጥምም ሆነ በሌላ ዓይነት የስነፅሁፍ ዘርፍ ብንገልፅ ‘ይበል!’ የሚያሰኝ ነገር ነው። የፃፍነውን ነገር ለሰው ስለማካፈል (ስለማሳተም) ስናስብ ግን ራስ ጋር ከማቆየት ባሻገር ሞያዊ አስተያየትን መጠየቅ አግባብ ነው። እኛንም የተሻለ የእድገትና የመረዳት እርከን ላይ ያስቀምጠናል። – ቢያንስ መስመሩን በውል እስክንለየው ድረስ! ልክ ለወዳጅ ዘመድ የተፃፈ ደብዳቤ ሁሉ ተሰብስቦ እንደማይታተም፤ ነገር ግን ለወዳጅ ዘመድ ከተፃፉ ደብዳቼዎች መሀል ስነፅሁፋዊ ፋይዳቸው ተስተውሎ ሊታተሙ እንደሚችሉ ሁሉ ስሜትን ለመወጣት በማሰብ የሞከርነውን በሙሉ ሰብስበን ብናሳትም ግን ሀላፊነት የጎደለው ተግባር ነው የሚሆነው። ተራና ጊዜያዊ እርካታን ከማጎናፀፍ አያልፍም። ሲቆይም በራሳችን ፊት ሊያሸማቅቀን ይችላል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ የባለሞያዎች (እንዲሁም የግጥም አንባቢዎች) ግድየለሽነትና ሀላፊነትን በአግባቡ ያለመወጣት ነገር ከግጥሞቹ ያለመመጠን ሁኔታ እኩል የሚያሳፍር የሚያሳስብ ነገር ነው።  ያም ሆነ ይህ ግን “ይህ ሌላ፣ ያ ሌላ” አሉ አፄ ቴዎድሮስ እንዲል ብርሀኑ ዘርይሁን (በታንጉት ምስጢር መፅሀፉ) ግጥም መግጠም ሌላ፣ የገጠሙትን ለሰፊው ህዝብ ማቅረብ (ማሳተም) ሌላ! መሆኑን ሁሉም ባለድርሻ (ገጣሚም አንባቢም) ሊያስተውለው የሚገባ ጉዳይ ነው።

ስነ ግጥምና የሂስ ባህል…

ሥነ ግጥም የሰው ልጅ በቋንቋ አማካይነት ስሜቱንና ሀሳቡን የሚገልፅበት የቋንቋ አጠቃቀም ስልት ነው። ደስታ፣ ሀዘን፣ ጥቃት፣ ብቸኝነት፣ በግጥም ይገለፃሉ። ፀሎት፣ ምህላና ምስጋና በግጥም ይደርሳሉ። እንጉርጉሯችን፣ ፀሎታችን፣ ዘፈናችን፣ ሆታችን፣ ቀረርቷችን፣ ምህላችን፣ ምርቃታችንና እርግማናችን፣ ግጥማዊ የንግግር ስልቶች ናቸው።  (ብርሀኑ ገበየሁ (1999), ‘የአማርኛ ስነግጥም’) በዚህም መሰረት ሀሳብን ከመግለፅ እና ከመግባባት አንፃር ከተመለከትናቸው የግጥሞች ጥራትና ደረጃቸውን መጠበቅ አለመጠበቅ ጉዳይ ገጣሚያኑን አያስወቅሳቸውም።

ሆኖም እርሱን ተከትሎ የሚግተለተሉ የአስተያየት ዓይነቶችና ገጣሚያኑ አስተያየቶቹን የሚመለከቱበት ዐይን ሁኔታ ግን፥ በጠቅላላው የጥበቡንና በተናጥል የገጣሚውን የነገ የብስለት ደረጃ የመወሰን አቅማቸው ብዙ ነው። በመሆኑም አስተያየት አሰጣጣችን ላይ ስሜት፣ እንክብካቤና ቸልተኝነት ካመዘነ ጉዳቱን ዘመን ተሻጋሪ (intergenrational) ያደርገዋል። ይህንን ሀሳብ ሲያጠነክርልንም ሌሊሴ ግርማ “ዘመን አልፎት የሚሄድ ጥበብ ጥልቅ አይደለም።” ይለናል። ግልፅ የሂስ ባህል ከሌለም ለመሻሻልና ለመለወጥ ማሰብ ብሎም ራስን ለማሳደግ መጣር የሚታሰብ ነገር አይሆንም።

“እውነተኛ የሂስ መንፈስ የሌለበት ቦታ የህዝቡ ሂስ የጥበብ ደረጃን ያወጣል። ያወጣው ይፀድቃል። ህዝብ የወደደው ሁሉ እውነተኛ ነው።” (ሌሊሴ ግርማ (2004), ‘አፍሮጋዳ’) ይሄ እየኖርን ያለንበት ግልብ ዘመን ሀቅ ነው። በተድበሰበሱ እውነቶች ተከብበን በብዥታ እንመላለሳለን። ብዥታንም እንፈጥራለን። ብዙ ነገር ስላየን ብዙ ነገር ያወቅን ይመስለናል። ብዙ ነገራችን የለብለብ ነው። የተጠበሰና የበሰለ ነገር አናውቅም። ብናውቅም ዙሩን ያጠነክርብናልና አንፈልግም። ሌሊሴ ዘመኑን በአንድ ቃል ሲጠቀልለውም “አፍሮጋዳ” ይለዋል። “ለእኛ የዘመኑ ታዋቂነት መንፈስ “አፍሮ” እና “ጋዳ” ተጠቃሽ ናቸው። የአፍሮጋዳ አስተሳሰብ የሚመነጨው ጥልቅነትን ከማለዘብ ነው።” በማለት እያብራራ….

ምናልባት ዛሬ የተመለከትናቸውን ችግሮች፣ በተሰማን መልኩ ነቅሰን በማውጣት ሂስ ብንሰጥ፥ ፀሀፊው ለሚሰራቸው ቀጣይ ስራዎች እናግዘዋለን እንጂ አንጎዳውም። ገጣሚውም የምሩን በጥበብ የተቃኘ ወይም የመቃኘት ፍላጎት ያለው ከሆነ እገዛችን ከምን ፍላጎት የመነጨ መሆኑን ቀድሞ ያውቀዋልና ስለምንፈጥርበት አሉታዊ ተፅህኖ ብንጨነቅ፥ – በእውነት በከንቱ ነው። የሰላ ሂስ መስጠትም የሚችለውን (ለዘርፉ የተሰጠውን) ሲያበረታው፥ የማይችለውን (ለዘርፉ ያልተሰጠውን) ሰው ደግሞ በማይሆን ነገር ላይ መድከሙን ትቶ መክሊቱን ፍለጋ ይተጋ ዘንድ ያነቃዋል።

መቅረዝ የኪነ ጥበባት አፍቃሪያን ህብረት

መቅረዝ የኪነ ጥበባት አፍቃሪያን ህብረት በቀድሞ ደቡብ ዩኒቨርስቲ (ዲላ፣ ወንዶገነትና ሀዋሳ ግቢዎች) ውስጥ የተመሰረተ እና እስካሁንም ያለ የስነፅሁፍ አፍቃርያን ስብስብ ነው። የቀድሞ የህብረቱ አባል መምህር ሆኖ ሰመራ ዩኒቨርስቲ በሄደበት አጋጣሚም መቅረዝን በሰመራም አቋቁሟል። ያው ከነሙሉ ክብሩና መታወቂያው – በተለይ የሂስ ባህሉ – ማለት ነው። የቀድሞ የህብረቱ አባላትም ከሁለት ዓመት በፊት በአዲስ አበባ ተሰባስው ፈቃድ በማውጣት ህብረቱን ወደ አገር አቀፍ ማህበርነት  አሳድገውት የነበረ ቢሆንም፥ በተለያዩ ምክንያቶች ለጊዜው ይህ ነው የሚባል እንቅስቃሴ እያደረገ አይደለም። በዩኒቨርስቲዎቹ (አሁን ለሁለት ተከፍለው ዲላ እና ሀዋሳ ተብለዋል) ውስጥ ግን አሁንም ድረስ የድሮ መልክና ቅርፁን እንደያዘ አለ። ወደፊትም እንደሚኖር እናምናለን።

ርእሱን ያነሳሁት ስለ ህብረቱ ልናገር አይደለም። ይልቅስ ያተረፍኩበትን አውቃለሁና ህብረቱ ስለሚታወቅበት ጠንካራ ባህርዩ – የሰላ ሂስ – ጥቂት ለማለት ነው። ይሄን የመቅረዝ መታወቂያ የሆነውን ሂስ አሁን ያሉት (ከእኛ ቀጥለው የመጡ) አባላት “ግጀራ” ይሉታል። ግጀራ፥ ገጀራ ከሚል የአማርኛ ስም የረባ ግስ ነው። የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማእከል (2001) ያዘጋጀው መዝገበ ቃላት ደግሞ “ገጀራ”ን “ቆንጨራ” ብሎ ይተረጉመዋል። እንግዲህ በዚህ መሰረት ግጀራ ማለት “በቆንጨራ ቆርጦ መጣል።” የሚል ትርጉም ይይዝልናል።

ካለምንም ማብራሪያ አዲስ የወጣለት ስያሜ የሂሱን ሂደትና ዓይነት የሚያሳይለት እንቅስቃሴ በመቅረዝ ይደረጋል። ከ “ይሄን ግጥም ብለህ ፃፍክ?!” እስከ ግጥሙን ለማሻሻል “እንዲህ አርገው፣ ይህን አውጣ…” ምናምን እያሉ ጣልቃ ገብቶ እስከማገዝ የሚደርስ ሂስ በውስጥ ስብሰባዎች ላይ ይደረጋል። – ጥበቡን አፍቅረዋልና ለገጣሚውም ይሳሱለታል። በመቅረዝ ባለቤቱ ጥበብ ነው። አባላቱ ግን አገልጋዮች ናቸው። ማንም ግጥም ቢፅፍ ለራሱ ብሎ ሳይሆን ጥበብን አፍቅሮ ፃፈ የሚል ያልተፃፈ ስምምነት አለ። ነገሩ የገባቸውና በስነፅሁፍ ፍቅር የተለከፉ አባላት ፀንተው ቆይተው፣ በብዙ አትርፈው፣ የካምፓስ ቆይታቸውን አድምቀው ይመረቃሉ።

መቅረዝ በዚህ በግልፅ የመነጋገር ባህሉ አባላቱን ፍፁም ስለሚያስተሳስብ የቤተሰብ ዓይነት ቅርርብ ይፈጥራል። የመቅረዝ አባል እስከሆነ ድረስ መቼም ይመረቅ መቼ ከሌላ የመቅረዝ አባል ጋር ዞሮ ሲገናኝ መግባባቱ የግድ ነው። ከሁኔታዎች አንፃር አለመገናኘት ቢኖር እንኳን በተገናኙ ጊዜ ያለው ፍቅር የሚገርምና ፍፁም ቤተሰባዊ ነው። የመቅረዝ አባላት ከግቢ ከወጡ ከብዙ ጊዜ በኋላም “ሀዋሳ” ወይም “ዲላ” ነበር የተማርኩት የሚል ወዳጅ ቢገጥማቸው ስለመቅረዝ መጫወታቸው አይቀርም። – ይገርመኛል። ምናልባት ሌሎችም እንዲህ ያሉ የስነፅሁፍ ክበቦች ይኖራሉ። እንዲህ ያለ የሂስ ባህል የሌላቸው እንደሆነ ግን ይህንን ባህል ከመቅረዝ ቢወርሱ ትርፋቸው የሁለት እዮሽ ነው። – የተሻለ የስነፅሁፍ እውቀትና ፍፁም ወዳጅነት!

ደረኮ (የመፅሀፍ የጀርባ አስተያየት) 

ብዙ ጊዜ ታዋቂ የስነፅሁፍ ባለሞያ ለማይመጥን የስነፅሁፍ ስራ፥ ደረኮ (የጀርባ አስተያየት) ሲፅፍ በይሉኝታና አግባብነት በሌለው መልኩ በከንቱ እያወደሰና እየመሰከረ መሆኑን እንታዘባለን። “እንዲህ ሲል አይደብረውም?!” ለሚል ታዛቢ ራሱንና ክብሩን፣ እንዲሁም እውቀቱንና ሞያውን አሳልፎ እየሰጠ። ግን የምር አይደብረውም?! ምናልባት እንዲህ ያለው ግድየለሽነትና ከንቱ ውዳሴ፥ ለፀሀፊዎቹ አጉል ከመሳሳትና ለስሜታቸው ከመጨነቅ የሚመጣ እንደሚሆን እገምታለሁ።

አንዳንዴ ነገሩ በጣም ሲመረኝ ደግሞ ነገሩን ከስግብግብነትና እነሱ ብቻ ጎልተው ለመታየት ካላቸው ፍላጎት ያመነጩት መሆኑን አስቤ እበሳጫለሁ። (እንዲያው በልጅነት ሀሳብ እንጂ የምሩን ለሞያው የተሰጡት ሰዎች ያንን ያደርጋሉ ብዬስ አይደለም።) በዚህ ላይ በ1996 ዓ/ም ገደማ ለማይረባ መድብል የተሰጠን ውዳሴ አምላክ የመሰለ ደረኮ አንብቤ ብበሳጭ እንዲህ መግጠሜ ትዝ አለኝ….

ምናምን ጫጭሬ፣ ሰብስቤ ብሰጠው፥ አርምልኝ ብዬ፣

አድጌ እንዳልበልጠው፣ ስህተቴን አርቄ፣ ሂሱን ተቀብዬ።

ሸንግሎ ሰደደኝ፣ ‘አባቴ’ ነው ያልኩት፣ ትልቁ ሰውዬ፣

/ዮሐንስ ሞላ/

የልብን እንደማይናገሩ በሚያውቁበት ጊዜ ግን ምንም አለመፃፍ እያለ እንዳልሰብረው በሚል ስስት በባዶ ሜዳ ማሞካሸትና በከንቱ ማወደሳቸው ራሳቸውን ከማስወቀሱም ባሻገር የግለሰቡንም የእድገት ደረጃ ይወስነዋል። ለስነፅሁፍ እድገት የሚኖረውንም አስተዋፅኦ ያቀጭጨዋል። ከባለሞያ ውጪ ያለ አንባቢም ችግሮቻችን በግልፅ አይነግረንም። እኛም የሚሰጡንን ሂሶች ለመቀበል ፈቃደኞች አንሆንም። (በግል ስራዎቻችን ይቅርና አንዳንዶቻችን የምንወደው ታዋቂ ሰው (ለምሳሌ ቴዲ አፍሮ) ተተቸ ብለን እሪ እምቧ በማለት ራሳችንን ለአደባባይ ትዝብት ከመጣላችን ባሻገር ከወዳጆቻችን ጋር እስከመቆራረጥ (block መደራረግ) ድረስም እንደርሳለን።) አንድ ጊዜ የሞከሩን ደጎች ቢኖሩ እንኳን ያለመቀበል ችግራችንንና ቆራጥ እርምጃችንን ሲመለከቱ ሂስ በመስጠት አይቀጥሉም። ይሄ ግን መለወጥ ያለበት ባህል ነው። ጥሩ ስራ ሲመለከቱ ማድነቅ እንዳለና አግባብ እንደሆነ ሁሉ፣ ጥሩ ያልሆነ ነገር ሲመለከቱም እርሱን መጠቆም፥ የቀደመውን አድናቆት ልባዊነት ይበልጥ ያሳያልና ወዳጅነትን ቢያጠነክር እንጂ አይጎዳም። በመሆኑም ሊዳብር ይገባዋል።

ሥነግጥም በዘመነ መፅሀፈ – ፊት (Facebook)

Facebook እንደማህበራዊ ግንኙነት መረብነቱ የዓለምን ማህበረሰብ በማቀራረብ ረገድ እየተጫወተ ያለው ሚና ትልቅነት ግልፅ ነው። ተጠቃሚዎቹም ሀሳባችንን በደግነትና በነፃነት እንድናካፍል ‘ረድቶናል። የማያቋርጠው የ’what is in your mind…?’ ጥያቄውን በመመለስ ሰበብም አህምሮአችንን ለመረዳት እና ሀሳባችንን ለመግለፅ የምንሞክር ብዙ ነን። ሰዎች በፃፉት ነገር ላይም ሀሳባችንን እንሰጣለን። ከዚህም ባሻገር አገርን፣ ባህልና ችሎታን ከማስተዋወቅና ለሌሎች ከማጋራት አንፃርም facebook ያለው አስተዋፅኦ ይህ ነው አይባልም።

በfacebook ብቻ የሚተዋወቁ ሰዎች ከfacebook ወዳጅነት አልፈው ብዙ ነገር ሲሰሩ፣ ወዳጅነታቸውን ሲያጠነክሩ ተመልክተናል። አሁንም ብዙ ነገሮች እየተሰሩ ነው። ከዚህም ሌላ የተለያዩ የስነፅሁፍ ስራዎችን በማዳረስ ረገድ facebook ትልቅ ስራ እየሰራ በመስራቱ በተለይ የስነፅሁፍ ፍቅር ያለንን ሰዎች ወደ አንድ ማእድ እያሰባሰበን ነው። እንደመሰባሰባችን ግን ስነፅሁፉን ለማሳደግ ጥረት ስናደርግ አንታይም። የስነፅሁፍ ስራዎችም እንደመብዛታቸው መለወጥና መንጠር አልቻሉም። በጎዶሎ ሀሳብ የምንዳክር ግልቦች እንበዛለን። ግልብነታችንም የሚፈጥረው ዘመን የማይሻገሩ ግልብ ስራዎችን ነው።

በርግጥ ፅሁፍ በመፃፍ ተግባር ውስጥ የፀሀፊው ዋናው ጉዳይ (ጭንቀት) የሚሆነው በወቅቱ ያለውን ሀሳቡን ከአህምሮው ጨምቆ  ማውጣቱ ነው። ከዚያ በኋላ ለሌሎች ማድረስ አለማድረሱ ደግሞ ከፀሀፊው ፈቃደኝነት በመቀጠል በሚኖረው የማዳረሻ መንገድ ምቹነት ይወሰናል። ፈቃደኛ ለሆኑ ፀሀፊዎች facebook ዓይነተኛ መንገድ ነው። ለአጠቃቀም ቀላል ከመሆኑ ባሻገር ብዙ ሰዎችን ለመድረስ ይረዳልና በተለይ ገጣሚያን ስራዎቻችንን ለሌሎች ለማጋራት እየተጠቀምንበት ነው። በቀላሉ መገኘት ከመቻሉ (accecibility) ጋር ተያይዞ ግን ግጥሞችን እንደፃፍናቸው (እንደወረዱ) እንድናጋራ ስለሚያረገን ቢያንስ እኛ ጋር ቆይተው እንዲበስሉ አንፈቅድላቸውም።

ከዚህም ሌላ ግጥሞቻችንን ስንለጥፋቸው የሚኖሩ አስተያየቶችም አንዳንዶቻችንን ወደኋላ ስለሚጎትቱን፥ ሁሉን ነገር ግጥም የማድረግና በግጥም የመግለፅ አባዜ ውስጥ እንወድቃለን። በመሀሉም መብሰልና መለወጥ ይጠፋል። ግልብ ሆነን ላይ ላዩን እንኖራለን። አካባቢያችንንም በአግባቡ እንዳንመለከትና ነገሮችን እንዳንመረምር እንጋረዳለን። በዚህም መሀል የምንፅፈው አብዛኛው ነገር ከአፍላፊ የማይተናነስ ግልብ ነው። ዝም ብሎ ቤት ለመምታት ብቻ እንፅፋለን። ለዚህም አፀፋው ከወዳጆቻችን በደግነት የሚቸሩን ልብን የሚያቀልጡ የአድናቆትና የውዳሴ ቃላቶች ብቻ መሆኑ ነገሩን ይበልጥ አሳሳቢ ያደርገዋል።

በርግጥ ፀሀፊው ነፃነቱን ተጠቅሞ የፃፈውን አንባቢውም ነፃነቱን ተጠቅሞ ባተረፈበት ልክ ቢያመሰግን፣ ቢያወድስና አስተያየቱን ቢሰጥ አግባብ ነው። ፀሀፊዎቹ የሚሰጠውን አስተያየት የሚመለከቱበት ዐይን ግን የራሳቸውን ብሎም የስነፅሁፍን እድገት ይወስነዋል። አንባቢውም ቢሆን በግልፅ የሚመለከተው ችግር እያለ፣ እየጎረበጠውና ቅር እያለው….ባለበት ሁኔታ ላይ ችግሩን ደፍሮ መጠቆም ባይችል እንኳን፥ ዝም ብሎ በከንቱ ቢያወድስ የተሻለ ማደግ የሚችል ወዳጁን ያቀጭጨዋልና ይሄ ባህል ሊለወጥ ይገባዋል። ቢያንስ የአድናቆት መጠናችንን ከግጥሙ የልቀት ሁኔታ ጋር አጣጥመን ከፍ ዝቅ ብናረገው ገጣሚውም ግጥሙን በተመለከተ፥ ‘ወተት ነጭ፣ ጨለማ ጥቁር’ ሳይባል በራሱ የሚረዳው ነገር ይኖራል። ልክ ባህርይውን በደንብ የምናውቅለት የቅርብ ወዳጃችን ዝም ስንል ምን ማለታችን፣ ለአድናቆት ቃላት ጠፍቶን ስንንተባተብ ምን ማለታችን እንደሚገባው ሁሉ፥ በfacebook ግጥሞቻችን ላይም ያንን የመግባባት ደረጃ እና ስምምነት መፍጠር  ብንችል የግልብ ዘመን ግጥሞቻችን በተሻለ የግልብነት ይዞታ ላይ እንዲገኙ ይረዳናል።

በተለይ ራሳችን ግጥም የምንሞክር ሰዎች ለሌሎች አስተያየት ስንሰጥ በሀላፊነት ሊሆን ይገባዋል። እርስ በርሳችን ብንተራረም (በአደባባይ ቢከብደን በውስጠ ሳጥን (inbox) ስነፅሁፍን ከማሳደግ በተጨማሪ ጥቅሙ ለራሳችን ነው። ማንኛውም ዓይነት ሂሶች ሲደርሱንም ከልብ አመስግነን በመቀበል ቆም ብለን ማሰብ ብንለምድ ለስነፅሁፍ እድገት ብሎም ለግል ስብእናችን ይረዳናልና ቢንለማመደው መልካም ነው ብዬ አምናለሁ። በዚህም የዘመንን ግልብነት መለወጥ ባይቻለን እንኳን ከህሊና ወቀሳ እንድናለን።

ሁሉም በእኔ እምነት ነው። እስኪ የእናንተን አክሉበትና እንጨዋወት።

5 thoughts on “የግልብ ዘመን ግጥሞች…”

  1. እውነትም አሳ ጎርጓሪ እንኳን እቃክ የጠፋ አንተ ብታተራምስ እንዲህ በቁምነገር እያዋዛክ ታጫውተናለህ ግን እንዴት አሳምረከ ጻፍከው ጃል?ልልክ ብዬ ውይ ደሞ አጉል ውዳሴ ይለኛል አሁን ተናግሮ ብዬ ግን ደሞ እሱን ምተችበት ምን አቅም አለኝ እውነቴነ ነው ወድጄዋለው አልኩ!!

  2. behulum aqtacha ketsehafiwum,ke’anbabiwum ke asteyayet sechiwum ateyay adrgeh yasnebebken hasab mirt new.letekebelew ena tegbarawi lemyadergew ende “his” liwesdewum yichilal.yibel byalew.

  3. ወዳጄ፤ መልእክትህን ያስተላለፍክበት አቀራረብ “ቀልድ-ቅብ ቁም-ነገር” ማረኮኛል፡፡
    አንጀቴን ነው ያራስከው፡፡ በጥቂት ሂስ ብትንትኑ ከሚወጣ የአድናቆት ቅርፊት ድርርቦሽ ውስጥ ላለነው ፣ መልእክትህ የብረት ጡጫ ነው፡፡ ታዲያ በነካ እጅህ የሌላውን ግጥምን ታከው ስለሚፃፉ የጨረቃ ግጥሞች /ተለጣፊ ግጥሞች/ ሃሳብህን ብታካፍለን…?
    በግጥም መመላለስ የብቃት መለኪያ መሆን አለበትን… ? ምላሽህን እናፍቃለሁ

  4. ጆ አሪፍ ምልከታ ነው በአጓጉል አድናቆት ገበያላይ ወጥተው የውሃ ላይ ኩበት ከመሆን ያድናል ዞር ብሎ የጫሩትን መገምገም ማስገምገም ትችትን መቀበል እያደር የበሰለ ሥነ-ጽሁፍ እንዲወጣው ይረዳል እና ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡
    ሰላም ይረፉ 14/06/2006

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s