ለአገር ጉዳይ ስብሰባ ላይ ነበርኩኝ….

መንደርደሪያ…

የመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርቴን ከጨርስኩኝ ጊዜ ጀምሮ በመምህርነት ሞያ አገልግያለሁ። (‘ሳይማር ያስተማረንን ማህበረሰብ ሳንማር እናስተምር’ በሚል ግነት መርህ ቢጤ ተደጋግፌ…) በመጀመሪያ መምህር ለመሆን ስወስን ስራ ስፈልግ አግኝቼው (ሌላ አጥቼ) ሳይሆን ለግልም ሆነ ለህብረተሰብ እድገት ጉልህ አስተዋፅኦ ለማድረግ ጥሩ ሞያ ነው ብዬ መርጬው ነበር። መምህርነት ሰው የማምረት ሞያ እንደመሆኑ የሰው ልጆችን የአስተሳሰብ አድማስ የማስተካከልም ትልቅ ሀላፊነትን ይሰጣልና ስራውን በፍፁም መነቃቃት እና ጉጉት ውስጥ ሆኜ ነበር የምሰራው።

አንዳንድ ጊዜም በሚጠበቀው መልኩ ችግሩን መርዳት አለመቻሌን ሳስብ ጥረቴ እና ጉጉቴ ከንቱ ይሆንብኛል። ስራው ከእኔ በተሻለ የእውቀትና የእድገት ደረጃ ላይ ያለ ሰው እንደሚያስፈልገው ሲሰማኝም ብዙ ጊዜ የስራ መልቀቂያ ደብዳቤ እፅፍና ስጨርስ፥ ከራሴ ጋር ተሟግቼ ሀሳቤን ቀይሬ ቀድጄ እጥለዋለሁ። ይህን የማደርገው ስራውን ላለመተው በመፈለግ አልነበረም። ይልቅስ ተማሪዎቹ ያሳዝኑኛል። ስራውን ብተወው በቦታው የሚተካው ሰው ማንነት ያስጨንቀኛል። ከንቱ ጭንቀት። ቢያንስ ችግሩን (ጉድለቴንም ጭምር) አውቀዋለሁና እስከ ጊዜው ድረስ መቆየቱን እመርጥና ሀሳቤን እለውጣለሁ። ፀዳ ያለ ትምክህት።

ያም ሆነ ይህ ግን እንደ መምህር የሞውን ደረጃና ክብር ለመጠበቅና ራሴን ከጊዜው ጋር እያደስኩና (update እያደረግኩ) ጎዶሎዬን ለመሙላት እየጣርኩ፣ ብቁ ለመሆን በመጓጓት ማድረግ የምችለውን ነገር ሁሉ አደርግ ነበር። እንደ ወጣት መምህርነቴም በዚህ ረገድ በብዙ ተሳክቶልኝ ነበር ማለት ይቻላል። ከተማሪዎቹ ጋር የነበረንም ግንኙነት እንደ እድሜያችን መቀራረብ ሳይሆን፣ በፍፁም ፍቅርና መከባበር ውስጥ የነበረ የአባትና የልጅ ዓይነት ነበር። ያም ማስተማሩን ይበልጥ ደስ እያለኝ እንድሰራው ረድቶኛል። – ያው በመማረርና በመመራመር  መሀል ውስጥ እየዳከርኩኝ

የእኔ ነገር… ልናገር ያሰብኩትን ረስቼ ነገር አበዛሁኝ። ለነገሩ ይሄን የምቀባጥረው የገጠመኝ (ከታች እንደሚነበበው) ከለመድኳቸው ወጣ ያለ ተማሪ መሆኑን ጠቆም ለማድረግም ነው፡፡ – ነገሩን ይበልጥ እንድትገነዘቡት፡፡ እነሆ ወደ ገደለው….

የገጠመኝ…

ከእለታት በአንዱ ቀን የተማሪዎች የሴሚስተር አጋማሽ ፈተና ወቅት ሆነ። እኔ የማስተምረው ትምህርትም ፈተና ጊዜ ደርሶ ተማሪዎቹን ፈትኜ፣ በመነጋው ቢሮ ቁጭ ብዬ የፈተና ወረቀታቸውን በማረም ስራ ላይ ተጠምጄ ነበር። አንድ ግድየለሽ ተማሪ ወደ ቢሮዬ ዘው ብሎ ይገባል። ፊቱ ላይ ፍፁም መረጋጋትና ኩራት ይታይበት ነበር። ስሙን ጠርቼ ሰላምታ ከሰጠሁት በኋላ ምን እንደፈለገ ጠየቅሁት።

እርሱ: “ትናንት ፈተና አልተፈተንኩምና እንድተፈትነኝ ነው።” አለኝ።

እኔ: (የምሬን አሳዝኖኝ እንዲሁም መረጋጋቱ ገርሞኝ) “ምነው በሰላም? አሞህ ነበር? አይዞህ! በቃ የሀኪም ማስረጃህን ታመጣና እፈትንሀለሁ።”

እርሱ: የትዝብት ፈገግ ብሎ “አይ ቲቸር አሞኝ አልነበረም።”

እኔ: “አሃ… ምነው? ሀዘን ምናምን?”….ስፈራ ስቸር። (ሟርተኛ ላለመሆንም፣ ላለመባልም)

እርሱ:  “ኧረ አይደለም።”….ሳቅ ብሎ ።

እኔ: “እንግዲያው በሀዘንና በህመም ምክንያት ያልተገኘ ተማሪ ብቻ…እርሱም መረጃ ሲያቀርብ ነው ድጋሚ የሚፈተነው።”

እርሱ: ምንም አልተረበሸም። በትኩረትና በትዝብት ተመልክቶኝ…ፀጉሩን እያሻሸ …በድጋሚ ፈገግ ብሎ… አስረግጦ – “ትፈትነኛለህ! ለአገር ጉዳይ ስብሰባ ላይ ነበርኩኝ።” አለኝ…

(እንግዲህ የተማሪ አባልነቱን ተጠርቶ  መሆኑ ነው)

😀 😀 😀

ያመናቸው ከደተውት (ወይም ከአቅማቸው በላይ ሆኖባቸው) አለመፈተኑ ግድ ሆኖ… ለተመሳሳይ ኮርስ በዓመቱ ክፍል ሲመጣ የመጀመሪያው ቀን ላይ አቀርቅሮ ነበር…

“ሰውን ከማመን እግዜርን መለመን” ~ እናቴ

😀 😀 😀

☞ እንግዲህ ይሄ  ፍንትው አድርጎ የሚያሳየው ትልቅ አገራዊ ጉዳይ መኖሩን ልብ ይሏል።