ጨዋታ ዘግንቦት

ክረምቱ ተገፋ፣ ፀሀዩ በረደ፣ ቀዘቀዘ ስንል… ወርሀ ፅጌ ከማለፉ፣ ፀሀዩ በህዳሩ እንደ ግንቦት ከርሮ ሲቀጠቅጠንና፣ ዝንቦቹም ሲፈለፈሉ ብናይ ጊዜ ባለፈው ያመጣናት ጨዋታ ትዝ ብላን ድጋሚ መዘዝናት፡፡  ግንቦት መጨረሻ ላይ እንዳለን ሁሉ በታሳቢ ይነበብ…

እሽሽ….ቆይ ….የት ትሄድ መስሎሃል? ….አገኝሃለሁ! …. (እዝዝዝ….እያለ ሄደ።…. ዝንብ መሰለኝ። በዝንብኛ እየሳቀባቸው። በዝንብኛ እያለመጠባቸው። በዝንብኛ ሙድ እየያዘባቸው….) ወቸው ጉድ! በግንቦት እንዲህ ተፈልፍለው መጫወቻቸው አረጉኝ እኮ።…. ወይስ እርጅና ይሆን?…. ኤድያ! ዝንብ ድሮ ቀረ እቴ! የዛሬ ዝንብ እንደው ዓይነ ደረቅ ነው። ሂድ ቢሉት አይሰማ፣ ቢያባርሩት ተመልሶ እዛው። አሳበዱኝ እኮ። ኧረ ጨርቄን ሊያስጥሉኝ ነው። እኔ ለነርሱ ስል ቆዳዬን አልገፍ ነገር፤ ምን ተሻለኝ ይሆን?…. (የልጅ እግር ሴት ልጅ ሳቅ ይሰማል)

ምን ያስቅሻል? ጥርስሽ ይርገፍ እቴ! ለነገሩ የዛሬ ልጅ ምን ቆዳ አለውና ምን ይሰማዋል ብለሽ? ቆዳ ድሮ ቀረ እቴ! ኧረ እንኳን ዝንብ አርፎብሽ ጅብ ግጦሽ እንኳን ህመሙ ከሰማሽ ልቀጣ! (ይሳሳቃሉ…) ተባብረው ሲበቀሉልሽማ ደስታሽ ነው። ሙች! እውነቴን እኮ ነው…እስኪ እያቸው አፈር ስሆን… ድሮ የበደልኳቸው ነገር እንዳለ ሁሉ ለበቀል የመጡ ነው የሚመስሉት። የማይሆኑት የለም እቴ…..እንደ ወይዘሮ – ኩሽና ነው….እንደ አባወራ – ሳሎን ነው…. እንደ ባለሞያ – ላብስል ነው…. እንደ ምኡር – ላንብብ ነው….እንደ ፈላስፋ – ልተንትን ነው…. እንደ ውሻ – ልንከስ ነው …እርጎው ሳይኖር በባዶ ሜዳ የማይጠልቁበት የለም …

እርጎስ በእኛ ጊዜ ቀረ እቴ። ወተቱ ከጓዳ… ልግዛህም ቢሉት የት ጠፍቶ? ሁሉ በእጅ ሁሉ በደጅ። አዪዪ….ይብላኝ ለዛሬ ልጅ፣ ለወተት ብርቁ!….ግን ዝም ብዬ ሳስበው እናንተ የምትወልዷቸው ልጆች ወተትን በአማርኛ ትምህርት ክፍለ ጊዜ ‘ለምሳሌ’ ቢያውቁት ነው። ኧረ ወዲያ…እርሱስ አማርኛው ከኖረ  አይደል? አማርኛ በእኛ ጊዜ ቀረ እቴ….! ነገሩን ሁሉ በምሳሌ እያወራርድን፣ ጠጁን ሁሉ በብርሌ እየኮመኮምን ባንድ ‘ዝም ባለ አፍ ዝንብ አይገባም!’ ምሳሌ ብቻ የስንቱን የጨዋ ልጅ አፍ እንዘጋው ነበረ መሰለሽ?! ቢሻን ደግሞ ‘ካለመናገር ደጃዝማችነት ይቀራል’ን መዝዘን እናናግረው ነበር፡፡ ዛሬ ግን ይኧው ዝንብ እንኳን ጊዜ ሰጥቶት፣ አፋችንን ፈልቅቆ ሊገባ ይጠብቃል… ደጃዝማችነቱንም ጠቅልለው ይዘውታል ስልሽ….

መቼስ ታምር አያልቅም!…. ‘ሰው ከጦጣ መጣ’ ሲባል ሰምተው፣ ምናልባት ከዝንብነት ወደ አውሬነት ለማደግ ሲታገሉ ይሆን እንዲህ ድርቅ የሚሉት? ሆሆሆ…. (ሳቅ ይሰማል…) ኡኡቴ….አሁን በእኔ ድንቁርና መሳቁ ነው? ወግ ነው!… የናንተ እውቀት እንደው ነገር ማጣመምና ቦታ ማገላባበጥ ነው። የዝንቡን ፍሊት ከኔ ደብቀሽ ለገላሽ ስታርከፈክፊ አንድ ቀን እዚያው እንዳትደፊ እንጂ….(‘ዶዶራንቱን ነው እኮ’ እያለች ትስቃለች) ድንቄም! ከፈረንጅ ሴጣን ጋር አማሽኝ ማለት ነው? አማርኛማ ዳገትሽ ነው… ነገሩን ሁሉ እያደባለቀሽ በእግሩ እያስኬድሽው…. የኔታው ብርቅ ሆኖ አስኳላ የማንም መጫወቻ ሆና ቀረች! ቱቱቱ….

(የረሱት ነገር ድንገት ትዝ እንዳላቸው ሁሉ መንጨቅ ብለው) እስኪ የዝንቡን ብዛት እዪማ! አቆናጠጣቸው ብትይስ? እንደ ሆነ ነገር አይደል ሚመዘልጉት እንዴ? ሆሆ… እኔማ ድንጋይ ይዞ ከነሱ ጋር መሯሯጥ ነው የቀረኝ። ዱላውንማ ቆየ ከጀመርኩት። ታዲያ ምን ያደርጋል?! እቃ ብሰባብር እንጂ ዝንቦቹ ከኔ ጋር አባሮሹን ለምደውታል። ‘የባሰ አታምጣ!’ ማለት ነው የሚሻለው….እንጂማ የመጪውን ማን ያውቃል?  ምናልባት ዝንብ መግደል ከጀግንነት ተቆጥሮ ያሸልም ይሆናል። (አሁንም ሳቅ ይሰማል…) ሙች ስልሽ… (ሳቁ ይቀጥላል…)

ኤድያ! ለነገሩ ጊዜ ሰጥቶሻል….በደንብ ሳቂ! ጊዜ እንጂ ብርቱ፣ ሰውማ ደካማ ነው። ምኑንም ችዬ አላሳይሽ። ጊዜ ያሳይሻል….አንሙት ብቻ! ሰው ዛሬ የያዘው የመሰለው ነገር ሁሉ ከእጁ እየተፈተለከበት ሰዶ ሊያሳድድ ይሰደድም ይሆናል።… ደግሞስ ማን ያውቃል? በዝንብ ተማርረን ጫካ የምንገባበት ጊዜም ይመጣ ይሆናል። (አሁንም ይሳቃል…) ሥራ መፍታት እንዲያ ነው! ታየኝ መቼስ…. ለዝንብ ቦምብ ሲጠመድ….. ለዝንብ ምሽግ ቆፍሮ ሰው ተሸሽጎ  ሲዋጋ…..ግን ምን ያተርፈኝ ተብሎ? ለነገሩ ሰውስ ምን ያተርፈኝ ብሎ ነው ከሰው ጦር የሚማዘዝ? እንዲያው ቢፈርድበት  እንጂ… ‘በዚህ ብላ! ላብ ይሁንህ’ ቢባል እንጂ!… ይሁና! ነገ ሰኔም አይደል?… የወቅቱስ ዝንብ ያልፋል!… ብቻ የባሰ አታምጣ! ተመስገን!….

ትናንት ጠዋት አልጋዬ ላይ ሆኜ በሰመመን የሰማሁት ነው። በህልሜ ይሁን በእውኔ እንጃ። ሴትዮዋም ማን እንደ ሆኑ በትክክል አልለይም። …አንድ ነገር ግን አውቃለሁ….ዛሬ ሰኔ ነው….ግንቦት አልፏል….ዝንቦቹም ቀስ እያሉ ይሄዳሉ። እኛን ለብርድና ለቁር አቀብለውን.። ዞምቢዎቹስ?

(ማስታወሻ፡ ሰኔ 1/2004 የተፃፈ)

አዪዪ…

☞ ORION BANANA ማስቲካ ከ1996 ዓ/ም ጀምሮ (በግምት) ጥቂት ከሚባሉ ጊዜያት በቀር ከኪሴ ተለይቶኝ አያውቅም ነበር። ተመሳስሎ ሲሰራም ከአስመጪው ከአልሳም ትሬዲንግ ሁሉ ቀድሜ የማውቀው እኔ ነኝ ብል ማጋነን አይሆንም። ሃሃሃ… ስንቱን እንደከተብኩለት ቢያውቅ ኖሮ ተቆራጭ ያስብልኝ ነበር። (ተቆራጭ ኬክ ነው? ብሎ መቀለድ አይቻልም። ሄሄሄ…) ባለፈው የሀዘኑ ጊዜ ‘በየመንገዱ ማስቲካ ማኘክ አይቻልም።’ የሚል ተባራሪ ወሬ ሰምቼ የተውኩት፥ ይሄው እስከዛሬ አፌ ገብቶ አያውቅም።

Oh my Orion, I missed u so much!:D

 

☞ በ1993 ዓ/ም የ11ኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ በ1 ብር ከስሙኒ (1:25) የገዛሁትን ጥፍር መቁረጫ ነው እስከዛሬ ድረስ የምጠቀመው። ውይ ደጉ ዘመን… ብር ከስሙኒ የሚባል…እቃ የሚገዛ ብር ነበረን። ምናምን ብለን እናማር እንዴ? ሃሃሃ… የምር ግን በየመሀሉ ለአፍታ ከዐይኔ እየተሰወረች ሳጣት ሌላ ብገዛም ሳይቆይ ይሰበርብኛል። ያኔም ጥንካሬና አለመሰልቸቷን ውለታ እየቆጠርኩ እወለውላታለሁ። ምናልባት ለልጄ አወርሳት ይሆናል እያልኩ።…ሃሃሃ (ሰው ጠብመንጃ ሲወለውል፣ ቤት ሲያወርስ አይተሀል።’ ብሎ መቀለድ አይቻልም።) ተመስገን! እነሆ እኛም ድሮ ቀረ እያልን ያለበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡

Oh my nail cutter, I owed a lot to you! :p

 

☞ በ1997 ዓ/ም የ3ኛ ዓመት ተማሪ ሳለሁ በ35 ብር የገዛኋት አንዲት የምታምር ነጭ ቲሸርት አለችኝ። በጣም ስለምወዳት ብዙ ጊዜ እለብሳታለሁ። እርሷ ግን ለመጣል ፈቃደኛ አይደለችምና ዛሬም ያኔ በነበረችበት ይዞታ ላይ ሆና ታባብለኛለች። ሰሞኑን (ከ3 ወር ወዲህ) ባመጣሁት ክብደት የመጨመር ፕሮግራም መሰረት ያቀድኩትን ያህል በመጨመሬ ምክንያት እርሷም እንደሌሎቹ ልብሶቼ እየጠበበችኝ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው። እንዴት ነው እናጫርታት? ወይስ መልሰን ክብደት የመቀነስ ስራ (z other way round) እንጀምር?:) (ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ’ ብሎ መተረት ከቅናት ይቆጠራል። ሄሄሄ…)

Oh my t-shirt, I don’t wanna lose you!;)

 

☞ በ1992 ዓ/ም የአስረኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ ጋሽ ዓለሙ የሚባሉ ባዮሎጂ መምህራችን (አዲስ ከተማ የተማሩ ያውቋቸዋል። ወይም ደግሞ በትርፍ ጊዜያቸው የመስመር ዳኝነት (አራጋቢነት) ስራ ስለሚሰሩ ምናልባት ስታዲየም የሚያዘወትሩ ወዳጆች ያውቋቸው ይሆናል።) በትምህርት መሀል ‘ጉንፋን ሊጀምር ሲል (ስሜቱ ሲመጣ) አፍንጫን በቀዝቃዛ ውሀ በመታጠብ ጉንፋኑን ሳይመጣ በፊት ድራሹን ማጥፋት ይቻላል፡፡ ያው ክትባት በሉት።’ ብለው ነገሩን። እነሆ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ እኔም ምክራቸውን ተግባር ላይ እያዋልኩ (ለሰውም እየመከርኩ) ጉንፋንን እከላከላለሁ።:) በመሆኑም ከዚያ ወዲህ ጉንፋን ይዞኝ የሚያውቀው በጣም ጥቂት ጊዜ ነው። እርሱም ክትባቴን ስረሳት! (‘ውሀ በመንደሩ ሲጠፋ ሲጠፋ…’ በል እንጂ ብሎ ማላገጥማ አይቻልም። ሃሃሃ…)

Oh common cold, where are you?:-/