ወይ ጂጂ…! (2)

ዛሬ እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) ስለ አባይ የተጫወተችውን ሙዚቃ አዳምጬ እንደ አዲስ ብገረምና የምለው ግራ ቢገባኝ…. ከዚህ በፊት በ ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አብርሀምና ሰርፀፍሬ ያዘጋጁት የነበረው የጣእም ልኬትፕሮግራም ላይ የሰጡት ትንታኔ ትዝ አለኝ፡፡ ከዚያም ቅጂው ያለበትን ፋይል ከማህደሬ በርብሬ አግኝቼ ወደ ፅሁፍ ገለበጥኩት፡፡ ያኔ በጣእም ልኬት ፕሮግራም መቋረጥ የተነሳ ከሸገር ሬድዮ ጋር የነበረኝን ቂም መርሳቴ ትዝ ቢለኝ ደግሞ፣ ወርቅ ላበደረ ጠጠር እንዲሉ ባለፈው ክረምት በደል ሳይቆጠር በደመቀ ሁኔታ የተፈፀመ የሆነ አገራዊ ክስተት ቢገርመኝ የጫርኳት ግጥም መሳይ ነገር እንዲህ ትዝ አለችኝ…

ሆደ ሻሽ ሀገሬ ቂም አለመያዙን ዛሬ ባየ ኖሮ፣
ያንገራገጨውን፣ የገላመጠውን የናቀውን ቆጥሮ፣
ከልቡ ባዘነ፣ ይቅር በሉኝ ባለ፣ በደሉን ዘርዝሮ፡፡

ሆ…. ‘ምን አገናኛቸው?!’ ኸረ ምንም! ግን እንደው ነገሩ ትንሽ ቢነካካ ለሸገርም ይሆን ነበር በማለት እንጂ፡፡ የምር ግን ሸገሮች ከልባቸው ተፀፅተውና በደላቸውን ዘርዝረው ይቅር ሊሉን በተገባ ነበር፡፡ ባወቁ…

ለማንቻውም እነሆ የጣእም ልኬት ትንታኔ በአባይ የዘፈን ግጥም ላይ….

ይህ ግጥም የአገራችንን ታላቅ ወንዝ አባይን በርዕሰ ጉዳይነት የሚያነሳ የዘፈን ግጥም ነው፡፡ ይህ የዘፈን ግጥም በእኔ እምነት እስከዛሬ ስለ አባይ ከተቀነቀኑት ዘፈኖች ሁሉ እጅግ የተለይ፣ ጥልቅና ምጡቅ ስራ ነው፡፡ አንዳንዶች በጓን ለማድነቅ ፍየሏን ማረድ አያስፈልግም ይላሉ፡፡ ይህ አባባል እውነትነት ያለው ነው፡፡ አተረጓጎም ላይ ችግር ካልተፈጠረ በስተቀር፡፡

አንዱን ለማድነቅ ሌላውን ማብጠልጠል መዝለፍና አንዱን ለሌላው ክብር መስዋዕት ማድረግ ፈፅሞ ያልተገባ ነገር እንደሆነ እሙን ነው፡፡ ይህ ማለት ግን አንዱ ከሌላው በሆነ ጉዳይ መሻሉን፣ በሌላ ነገር ደግሞ መድከሙን መግለፅ አያስፈልግም ማለት ከሆነ እጅግ አደገኛ አነጋገር ይሆናል፡፡

በህይወት እጅግ በርካታ ነገሮች አንፃራዊ ከመሆናቸውም በላይ በበጎ እይታ የአንዱን ከአንዱ መሻል ማውሳት ለጥበቡ በእድገትና በመሻል ጎዳና በርትቶ መግፋት እጅግ ረብ ያለው ግብአት ነው፡፡ በመሆኑም ይህ አባይ የተሰኘው የእጅጋየው ሽባባው ግጥም ከእስከዛሬዎቹ አባይ ነክ ግጥሞች ሁሉ የረቀቀ ነው ስንል እንናገራለን፡፡ የስራዋን ግሩምነት ማስተጋባት ከገጣሚዋ ዋና አምሀዎች አንዱም ጭምር ነውና፡፡ ይህንን ለማለት ያስቻሉንን ምክንያቶች እንደሚከተለው እንጠቅሳለን፡፡

ግጥሙ ሲጀምር የሚያነሳው ስለ አባይ አፈጣጠርና አመጣጥ በመተረክ ነው፡፡ እናም የራሱን ምናባዊ ብየና ይሰጣል፡፡ ወደሚቀጥሉት የሀሳብ ድሮቿ ከመሸጋገሯ በፊት ገጣሚዋ መሰረቷን አጥብቃና አፅንታ ለመሄድ በመሻት ስለአባይ የመነሻ ቦታ አመጣጡን እና አፈጣጠሩን የምናብ ነፃነቷን ተጠቅማ ትበይናለች፡፡ ትተርካለችም፡፡ ስለታላቁ ወንዝ ስታወጋን ስለአመጣጡ ማውሳቷን እፁብ የሚያደርጉት አንዳንድ ምክንያቶች አሉ፡፡

አንደኛ የምታጫውተን ስለወንዝ ከወንዝም ከዓለም ረጅም ስለሆነው ስለአባይ ነውና፤ ወንዝን አንስቶ፣ ወራጅ ውሀን ጠቅሶ ስለመነሻና መድረሻ አለመናገር ግጥሙን ስነኩል ያደርገው ነበር፡፡ ስለዚህ ይህ ድንቅ ብየና ለግጥሙ ፅኑ መንደርደሪያና ልዩ ምልአት ሰጥቶታል፡፡ ሁለተኛ የገጣሚዋ ብየና የወንዙ መነሻ ያደረገው አንዱን ክፍለ አገር፣ አህጉር ወይም ግዛት በመጥራት አይደለም፡፡ የትኛውም ቀበሌና ጎጥም አልተጠቀሰም፡፡ ይልቅስ…

የሀሳብ አድማሷ ወዲያ ተመንጥቆ፣ ምድርን ተሸግሮ፣ ዓለምን ዘቅዝቆ እያየ….አባይ ህይወት እንድትቀጥል ለምድር ከገነት የተቸራት ቅዱስ የጠበል ውሀ መሆኑን ታበስረናለች፡፡ ባናውቅበት ነው እንጂ…የምትልም ይመስላል፡፡ እነኚህን ሀሳቦች ሁሉ የምናገኘው እንግዲህ በዘፈኑ የመጀመሪያ ክፍል ማለትም አዝማች ላይ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ይህንን ሁሉ ግዙፍ ፍልስፍና፣ እነኚህን ሁሉ አበይት ሀሳቦች የተሸከመ የስንኞች ህብር ሌሎች ተከታይ ስንኞችን ለማዝመት ብቁ በመሆኑና መንደርደሪያነቱም የጎላ በመሆኑ አዝማች የሚለው ስም ያንስበት ይሆናል እንጂ አይበዛበትም፡፡ አባይ ከ እንጂ እስከ እንደሌለው አበክረው ይሰብካሉ….

የማያረጅ ውበት…. የማያልቅ ቁንጅና…፣
የማይደርቅ፣ የማይነጥፍ፣ ለዘመን የፀና፣
ከጥንት ከፅንሰ አዳም….
ገና ከፍጥረት…
የፈሰሰ ውሀ… ፈልቆ ከገነት፡፡
ግርማ ሞገስ፣
የአገር ፀጋ፣ የአገር ልብስ…
ግርማ ሞገስ…አባይ፣
ግርማ ሞገስ፣
የአገር ፀጋ፣ የአገር ልብስ…
ግርማ ሞገስ….አባይ….
የበረሀው ሲሳይ፣ (4X)

ብነካው ተነኩ!…. አንቀጠቀጣቸው፣
መሆንህን ሳላውቅ፣ ስጋና ደማቸው፣
የሚበሉት ውሀ፣ የሚጠጡት ውሀ፣
አባይ ለጋሲ ነው… በዚያ በበረሀ…
አባይ… አባይ… አባይ… አባይ…
አባይ ወንዛወንዙ፣
ብዙ ነው መዘዙ…
አባይ… አባይ… አባይ… አባይ…
አባይ ወንዛወንዙ፣
ብዙ ነው መዘዙ…

አዝማች፡-

አባይ የወንዝ ውሀ፣ አትሆን እንደሰው!
‘ተራብን፣ ተጠማን…’ ተቸገርን ብለው፣
አንተን ወራጅ ውሀ….ቢጠሩህ አትሰማ፣
ምን አስቀምጠሀል ከግብፆች ከተማ?
አባይ…አባይ…አባይ…አባይ…
አባይ ወንዛወንዙ፣
ብዙ ነው መዘዙ…
የበረሀው ሲሳይ፣ (3X)

Oh, Gigi…!!

3 thoughts on “ወይ ጂጂ…! (2)”

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s