አካላዊ ጥቃቶች (physical violences)
ባል ሚስቱን ደብድቦ ገደለ፣ ሚስት ባሏን ገደለች (የአቅምም ሁኔታ ታክሎበት ነው መሰል፥ ይሄ ብዙም አይሰማም። ሲሰማም ሞቱ እንኳን ለህብረተሰብ ጆሮ ወንጀሉን ለሚፈፅሙት ሴቶችም ድንገቴና አስደንጋጭ ነው የሚሆነው።) ፣ ልጅ አባቱን ገደለ፣ ልጅ እናቱን ገደለ፣ ባል ሚስቱን አቆሰለ፣ ሚስት ባሏን አቆሰለች፣ አሲድ ደፋባት፣ አሲድ ደፋችበት፣ ዐይኗን አጠፋት፣ ከፎቅ ወረወራት፣ በስለት ወጋችው….ሌላም ሌላም በተለያዩ ምክንያቶች ተፈፀሙ የተባሉ የተለያዩ ዓይነት ጥቃቶችን በተለያዩ ጊዜያት ስንሰማ ኖረናልና፥ ነገሩን ጆሮአችን ለምዶታል። ያም ሆኖ እንዲህ ያሉትጥቃቶች ብዙ ጊዜ በደፈናው ይድበሰበሱና ‘ፆታዊ’ በሚል ስም ይጠቀለላሉ። ‘ህፃን ደፈረ’ማ ተነግሮንም ሳይነገረንም የሚገጥመንን የመብራት ፈረቃ ያህል እንኳን የማያስገርመን ነገር ሆኗል።
በወቅቱ ወሬውን ስንቀባበል፣ ስንሰበሰብ፣ ስናራግብ፣ስንፅፍ፣ ስናነብ፣ ነገሩን ስናወግዝ፣ “እግዚኦ” ስንባባል እንከርምና ወዲያው ወከባ በበዛበት የኑሮ ባህራችን ውስጥ እንደ አንዳች ነገር ጠብ ብሎ ይረሳል።ይደክመናል። ወይም ደግሞ ተከትሎ የሚመጣውን የፍርድ መጠን እንገምተውና ወሽመጣችን ቁርጥ ብሎ ጉልበታችንን ይወስነዋል። ያም ሆኖ… ድንጋጤና ሀዘኑ ባይሆን እንኳን ወሬ መቀባበልና ነገሩን ማውገዙም ቢሆን ብዙ ጊዜ በአድልዎና በቲፎዞ የሚደረግ ነው።ብቻ ግን የአንድ ሰሞን ጉድ ሆኖ ይከርማል። ወዲያው ደግሞ ይረሳል። ህይወት ትቀጥላለች።ምናልባት በሌላ የከፋ የወንጀል ዓይነት እየተተካና “የባሰ አታምጣ” እያስባለን። – የሞተ ቀረበት!
እንዲህ ያለውን ነገር በፊት ፖሊስና ህብረተሰብ ፕሮግራም ላይ ሲተላለፍ እናቴ “ቅጣቱን አብረው ካልነገሩ ባያወሩት ይሻላል። ካልሆነ አዲስ ዘዴ ነው የሚያስተምሩብን።” ትል ነበር። እውነት ነው። አንድ ዓይነት የወንጀል ዘዴ በዜና ሰበብ ለህብረተሰቡ ከተዋወቀ በኋላ በቀጣይ ተመሳሳይ የወንጀል ዓይነቶች ሲፈፀሙ እንሰማለን። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን አሲድ በመድፋት ጥቃት ማድረስ ነው። እንደ ቀልድ ተፈፅሞ (ምናልባት መጀመሪያ የደፋው ሰው ‘ይሁን’ ብሎም ሳይሆን በአቅራቢያው ስላገኘው ብቻም ሊሆን ይችላል።) እንደ ጉድ ተወራ፣ ከዚያም አሲድ መደፋፋት ተለመደ። ጆሮአችንም ለመወደው። እንዲህ ነን እኛ።
የቤት ሰራተኛዋ አሰሪዋንና ሁለት ልጆቻቸውን ገደለች
ዛሬ በጠዋቱ ከሸገር 102.1 የሬድዮ ጣቢያ የሰማሁት ጉድ ደግሞ ለጆሮዬ እንደመርግ የከበደ ነው። ምናልባት ከመሰል የሰራተኛ አሰሪ ጥቃቶች ጋር እስክንላመድ ድረስ። በርግጥ ሰራተኛ አሰሪን ሲበድል የመጀመሪያ አይደለም። ሆኖም ከዚህ በፊት የተለመደው ልጆችን ማጥቃት እንጂ እንዲህ ቤተሰብ መፍጀት አልነበረም። ወይም እኔ ስሰማ ይሄ የመጀመሪያዬ ነው። ፈፃሚና ተፈፃሚው ዞሮ ያው ሰው መሆኑ ከከዚህ በፊቶቹ ወንጀሎች ባይለየውም የጥቃት አድማሱ እንዴትና ወደየት እየሰፋ መሄዱን አጉልቶ ያሳየናል። ሸገር ላይ የተሰማው ወሬ “የቤት ሰራተኛ አንዲት ሴት ወይዘሮንና ሁለት ልጆቻቸውን ገደለች።” ብሎ ይጀምርና እንዲህ ያብራራል።…
“በሻሸመኔ ከተማ አንዲት የቤት ሰራተኛ በደመወዝ ጨምሩልኝ ሰበብ በተነሳ ጭቅጭቅ አሰሪ ወይዘሮዋንና ሁለት የአራት ዓመትና የሰባት ዓመት ልጆቻቸውን በተኙበት በመጥረቢያ ደብድባ ገደለቻቸው። ድርጊቱን ፈፅማ ለጊዜው ተሰውራ የነበረ ቢሆንም በፖሊሶችና በአካባቢው ነዋሪዎች ክትትል በወላይታ ሶዶ ከተማ ውስጥ ከተደበቀችበት ተገኝታለች።” (ቃል በቃል አልፃፍኩትም።)
የደቡብ ሰዎች (ወላይታዎች መሰሉኝ) እንዲህ ያለ፥ ለጆሮ ከባድ ነገር ሲገጥማቸው (ሲሰሙ) ‘ጎንዶሮ!’ ይላሉ። ‘አያድርስ’ እንደማለት ነው። አያድርስ ቢባልም ግን እነሆ ደርሶ የቤተሰቡ ህይወት ተቃርጧል። መቼስ ሁሉም በራስ ደርሶ ይታይ አይባል። ሆኖም… – ጎንዶሮ!
ምን ሰይጣን አሳታት?
መቼስይሄምድርጊት ማብራሪያ አያጣም ይሆናል። ምናልባት ወንጀለኛዋ የመክፈል አቅምና ፈቃድ ያለው የቅርብም ሆነ የሩቅ ቤተሰብ ካላት የሚቆምላት ጠበቃም አታጣም። ሰብአዊ ተቆርቋሪ ነን ባይ ኗሪዎችም ድርጊቱን በጓሮ መንገድ አዙረው ከሰራተኛ አያያዝና ከአሰሪዎች በደል ጋር አያይዘውት፥ ትንታኔ ሰጥተውበት ቢያንስ ለኗሪ ህሊና የወንጀለኛውን አጢሀት ሊያቀሉ ይሞክሩ ይሆናል። ወይ ደግሞ የወንጀለኛዋን የትምህርት ደረጃና የማሰላሰል ሁኔታ ተንትነው፣ ቢያንስ ልባቸውን አሳምነው በልባቸው ምህረት ያደርጉላትም ይሆናል። (ለነገሩ ይሄ በፍርድ ቤትም ቢሆን ዓይነተኛ የፍርድ ማቅለያ መሆኑን በተለያየ ጊዜ ታዝበናል።)
ከዚህ የሚተርፈው አብዛኛው የማህበረሰብ ክፍል ግን እንዲህ ያለው ነገር ሲከብደው “ምን ሰይጣን አስቶት/ቷት ነው?” በሚል ቆራጣ አረፍተ ነገር ጠቅልሎት፥ አጢሀቱን ሁሉ ሰይጣን ላይ ነው የሚያላክከው። ይሄ ነቢይ መሆን ወይም ጥናት አያሻውም። ይልቅስ ያለፉ የወንጀል ታሪኮችንና ህብረተሰባዊ ትንታኔዎቻቸውን ማስታወስ በቂ ነው። ሰይጣን ግን ፈረደበት። የምር አንጀቴን ነው የሚበላኝ።
እዚህ ጋር ከዚህ በፊት የሰማሁትን ተረት (አፈታሪክ) ላንሳ…
የሆነ ገዳም ውስጥ ነው። የፆም ወቅት ላይ አንድ መነኩሴ እንቁላል ጥብስ ክፉኛ ያምራቸዋል። ሊያረሳሱት ቢሞክሩም ጭራሽ የሚባረር ዓይነት አምሮት አልሆነባቸውም። ከዚያም ዘየዱ። ሰብረው ቢጠብሱት አንድም እሳት የላቸውም ሌላም ደግሞ ሽታው በገዳሙ ቅፅር ውስጥ ተሰምቶ የሚያስቀጣቸው ይሆናልና እንቁላሉን ሳይሰብሩት ቅርፊቱን በጧፍ ለብልበው መጥበስ አሰቡ። ከዚያም ጧፉን ለኩሰው መጥበስ ጀመሩ። በመሀል ከየት መጡ ሳይባል የገዳሙ አበምኔት ወደመነኩሴው ማደሪያ ዘው ብለው ሲገቡ ድርጊቱን ተመልክተው ደነገጡ። ገሰፅዋቸውም። መነኩሴውም ጥፋታቸውን አጠር ባለች ማብራሪያ ይቅርታ ለመኑ። “ይቅር በሉኝ አባቴ። ሰይጣን አሳስቶኝ ነው።” ለካስ ቀድሞም አምሮቱን ሊያሳድርባቸው ቤት መጥቶ ኖሮ “ኧረ አባቴ ይህን ዘዴ፥ እኔም ካለዛሬም አላየሁት” ብሎ ሰይጣን ራሱ መልስ ሰጠ። ይባላል።
እንግዲህ ይሄ የሚያሳየን ነገሮችን በሰይጣን ላይ የማላከክ አባዜያችንን ጥልቀት ነው። ጥቅም የለውም እንጂ ብዙዎቻችን ሰይጣንን እንበልጠዋለን።
‘እናቱምገበያየሄደችበትእኩልየሚያለቅስበት’ – የእኛ ፍርድ ቤት
በተለያዩ ጊዜያት፥ በዝርዝር የማላስታውሳቸውን ወንጀሎች፣ ጭራሽ ከማይመጣጠኑ ቅጣቶቻቸው ጋር ሰምቼ አንገቴን፥ ወንጀሉን በፈፀሙት ግለሰቦች ላይ ብቻ ሳይሆን በወንጀለኛ መቅጫ ህጋችንና በፍርድ ቤታችን ላይ ደፍቼያለሁ። ፊቴ ከማይጠፉት እንደምሳሌም፡- ባንድ ጎን፥ የሚስቱን እጆች በመጥረቢያ የቆረጠው 19 ዓመት ተፈረደበት፡፡ ሲባል እንሰማና፤ በሌላ ደግሞ፥ የ6 ልጆቹን እናት (ሚስቱን) አንዱን ልጅ ከኔ እንዳልወለድሽው በራእይ ታይቶኛል ብሎ የገደላት 6ዓመት ተፈረደበት ሲባል እንሰማለን።
ይህ ገርሞን ሳያባራ፣ ሚስቱ ላይ ግልፅ የሆነ ጥቃት አድርሶ ልጆቹ እንዳይመሰክሩበት አባትነቱ አራራቸው የተባለለት አባወራ ደግሞ፣ በነፃ ተለቀቀ እንባላለን። ሁሉንም የሚያደርሱን ቴሌቪዥንና ሬዲዮዎቻችን ናቸው፡፡ እንግዲህ ይህ ነው የኛ ፍርድ ቤት። አመክሮው፣ ጉቦውና ዝምድናው ተደማምረው የፍርዱን መጠን የት ሊያደርሱት እንደሚችሉም መገመት ልብ ላላ ሰው ቀላል ሂሳብ ነው። ታዲያ የኛን ፍርድ ቤት፣ “እናቱም ገበያ የሄደችበት እኩል የሚያለቅስበት” ብለው አሳነስኩት እንጂ አበዛሁት ይባል ይሆን?
ከዚህ በላይ ሽብር ከወዴት ይገኛል?
ያም ሆነ ይህ ግን ወንጀሎች በብዛትና በዓይነት እየተፈፀሙ ዘወትርጆሮአችንን ይደርሳሉ። ሰጋት ላይም ይጥሉናል። ከትንንሽ የቀበሌ ትኩረት ከተነፈጋቸው ጥቃቶች እስከ ትልልቅ አገራዊ ሽፋን እስከሚሰጣቸው ጥቃቶች ድረስ ብዙ እንሰማለን። በሞባይል ቀፎ ቅሚያና ኪስ በማውለቅ ሳቢያ በየቅያሱ የሚነሱ አምባጓሮዎችና በሰላማዊ ኗሪዎች ላይ የሚደርሱ አሰቃቂ ጥቃቶች ብዙ ናቸው። ‘በሩ ላይ ተወጋ። በሩ ላይ ተዘረፈ። በሌሊት የቤተሰብ ቤት ተሰብሮ ተሰረቀ።…’ የሚሉ ወሬዎች በተለይ በአሁኑ ወቅት በየቀበሌው ገነዋል። ‘ሌባና ዱርዬም በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅቷል እንዴ?’ እስኪያስብል ድረስ። (ቢያንስ በእኛ ቀበሌ ውስጥ ታይቶም ተሰምቶም በማይታወቅ መልኩ ተበራክተውና ተጠናክረው እየተፈፀሙ ነው።)
ይህንንም ሽሽት ሰዉ ወደቤቱ ለመግባት የሚጣደፈው ገና ጀምበር ስታዘቀዝቅ ነው። የቤቱን አጥር ቢጠነክርልኝ ብሎ አጥር የሚያስቀይረውም ብዙ ነው። ሲሆን የስልክ ቀፎም ይቀየራል እንጂ፣ በወርቅማ ማን ያጌጣል? ዱላው ይቀራል እንጂ ዝርፊያና ንጥቂያው በጠራራ ፀሀይ፣ በፖሊሶች ምስክርነት ሳይቀር ይፈፀማል። በየታክሲ ቦታው፣ በየመንገዱ፣ በየካፌው፣ በየጎዳናው፣ በየጥጋጥቁ…. አሸባሪው ብዙ ነው። ሰዉም ጥላውን ሳይቀር ይጠራጠራል።
‘የአበራሽን ጠባሳ ያየ በእሳት አይጫወትም’ና የሰማውን አስታውሶ ራሱን ለመጠበቅ ይጨነቃል። በለመደውና ይሆናል ብሎ ባሰበው ሲጨነቅና ራሱን ለመጠበቅ ሲሞክር፥ ጭራሽ ያልሰማው ዓይነት ንጥቂያ ይገጥመዋል። ያልገመተው ዓይነት ጥቃት ይደርስበታል። ታስረው ሳይቆይ ስለሚፈቱ የከፋ ጥቃት ያደርሱብኛል ብሎ ስለሚፈራ ማንም ማንም ላይ መጠቆም አይፈልግም። ይፈራል። እንግዲህ ከዚህ በላይ ሽብር ከወዴት ይመጣል? (ለስንቱስ ነገር ይሆን ይሄን ሀረግ የምንመዘው?)
እንግዲህ በማንም ልገደል የምችልበት ሁኔታ እንዳለ ነው እና እየተማርኩ ያለሁት ከእንግዲህ አልፈራም። (ለነገሩ ድሮም አልፈራም ነበር።) እናም እላለሁ። የእኛ ፍርድ ቤት ነገሩን እንዴት ይመለከተው ይሆን? ‘አሸባሪ’ በሚል ታርጋ ቃሊቲ የታጎሩትና በስደት ያሉት የሚያማምሩ አዕምሮዎች በቴሌቪዥን፣ (ለዚያውም ክሱ ተጠናቅቆ ፍርዳቸው ሲነገር – በዜና ወይ በዶክመንተሪ) አደረጉ ተብሎ ከምንሰማው ነገር ባለፈ ምንም ሲያደርስብን አላየንም።
ማወቅ፣ መጠየቅ፣ መፃፍና ማንበብ በሚያሸብሩበት አገር እንደምን እንዲህ ያሉ ጥቃቶች ችላ ተባሉ? ነው ወይስ ወንበር እንዳይነቀንቁ አያሰጉምና?! ባትሰማንም ቅሉ እንላለን – ቃሊቲ ሆይ በርሽን ከፍተሽ ውስጥ ያሉትን ሰላማዊ ዜጎች አስወጪና የሚያሸብሩንን አስገቢልን።
ጎንዶሮ!
“ቅጣቱን አብረው ካልነገሩ ባያወሩት ይሻላል። ካልሆነ አዲስ ዘዴ ነው የሚያስተምሩብን።” እናቴ in law
‘ጎንዶሮ!’