ያልተዘመረለት – ‘የተረገመው ባለቅኔ’!!

ሁሉም ቢያገኘው፣ሁሉም ቢያነበው፣ ሁሉም ቢረሰርስበት፣ ሁሉም ቢማርበት፣ ሁሉም ቢያውቀው፣ ሁሉም ቢደመምበት፣ ሁሉም ቢያከብረው፣ ሁሉም ቢዘምርለት…ብዬ ብጓጓ፤ምድር በጥበቡ ከመረስረሷ ባሻገር፣ ነፍሱ ባለችበት ሀሴት ታደርጋለች፣….ብዬ ባስብ…. ከትናንት በስትያ (ወዳጄ አብዲ ሰይድ “ወፍዬ”ን ለጥፎ ቢቆሰቁሰኝ) ያልተዘመረለትና በወጉ ሳይታወቅ ያለፈው ታላቅ ገጣሚ ሙሉጌታ ተስፋዬ የባለቅኔ ምህላ መፅሀፍ ድጋሚ ይታተም ዘንድ ስንዱ አበበን ስጠይቃት፣ (ኮፒው በእጄ ቢኖርም፣ ቢያንስ የህትመት ወጪዋን አንባቢው ይጋራ ዘንድ፣ የርሷን (የአሳታሚዋን) ፈቃድና መብት እንዳልጋፋ በመፍራትና… መፍራቴን በመግለፅ…)

(እዚህ ጋር አብዲ በአበበ ተካ ወፍዬ ተቆስቁሶ…የተዘነጋ ገፅ በሚል ርዕስ የከተባት ማስታወሻ ብዙ ትጨምራለች፡፡ እኔም ይህችን እከትብ ዘንድ በእጅጉ ወስውሳኛለች፡፡)

በመጀመሪያ ህትመቱ ብዙ ብር በመክሰሯ ድጋሚ እንደማታሳትመው፣ ሶፍት ኮፒውን ግን ለኢትዮጵያ ህዝብ ነፃ ስጦታ ይሆንላት ዘንድ በመሻት ለወዳጆቼ ባካፍልላት ደስታዋ መሆኑን ገለፀችልኝ፡፡  በፊት ከነበራት በሚጠልቅ ደግነት፡፡ ቀድሞ በአሳታሚ ድርጅቷ በኩል ካሳየችን በሚልቅ ርህራሄ፣ ፍቅርና ቅርበት፡፡ለነገሩ ወትሮም የርሷ ጉዳይ ጥበቡን መዝራት፣ ተሸጦ ገቢ ቢኖረው በትርፉ ሌላ ያልተዘመረለትን አንስታ ለማዘመር እንጂ መች ሌላ ሆኖ….፡፡

መቼም ጉኖዬን (ሙሌክስ እንደሚጠራት) አለማመስገን በብዙ ፍቅር አለማክበርና ስለርሷም  አለመዘመር አጉል ስስት ነው የሚሆነው፡፡ አድሮ የሚቆጠቁጥስስት፡፡ ከሄዱ በኋላም የሚያሸማቅቅ፡፡ እነሆ የመፅሀፉን ኮፒ ከዚህ ጋር ተያይዞ ይገኛልና ረስርሱበት፡፡ ፍቅርና ክብራችሁን ለፀሀፊው ለሙሉጌታ ተስፋዬ እና ለአሳታሚዋ (እንዲሁም አሳታሚዋ አመስግኑልኝ ላለቻቸው) እያበረከታችሁ አንብቡት፡፡ አንብባችሁ ስትወዱት ደግሞ ባላችሁበት ዘምሩለት፡፡ ሌሎችም ይዘምሩለት ዘንድ አስተላልፉት፡፡

Yebaleqine-Mehela

እኔ ሙሌን ሳስበው እንባ ይቀድመኛል፡፡ ሳላውቀው የቆየሁበት (በዘፈን ግጥሞቹ ተወስኜ) ጊዜ ይቆጨኛል፡፡ መሀላችን አለመኖሩ ያንገበግበኛል፡፡ በኖረና ብዙ በፃፈ….በኖረና ቋጠሮዎቹን በፈታ…. እያልኩ፡፡ እንደ አዲስ ዳስ ጥሎ፣ ንፍሮ ቀቅሎ ለቅሶ መቀመጥ ያምረኛል፡፡ ግና መፅሀፉን ከመደርደሪያዬ ላይ አንስቼ ጠረግ ጠረግ አድርጌ ማንበብ ስጀምር እንባዬ ይታበሳል፡፡ ብዙ መኖሩ ይሰማኛልና ቁጭቴን ሁሉ በደፈናው “ከንቱ” እለዋለሁ፡፡ ከንቱ ሀዘን፡፡ ደርሶ በጥበቡ የሚበርድ፡፡አንዳንድ ጊዜ ስቃዥ ደግሞ ቆሪጡን ማግኘትና ማናዘዝ ያሰኘኛል፡፡

የግጥምቆሪጡን፡፡  የቅኔዛሩን፡፡ ማስለፍለፍ….ማስቀባጠር…ማናዘዝ… ከስር ከስሩ እየተከተሉ መቃረም…. ወደኗሪውማጋባት… አይ ሙሌክስ፣ …እርሱን ሳስብና ሳገኝ(እድሜ ለስንዱ) እንዲህ ብቻ አይደለም የምሆነው፡፡ የቃላትን ስንፍና የሚያሳይ ብዙ የማይገለፅ ነገር፡፡ በቃላት ለመጫወት መፍጨርጨሬን (ግጥም መፃፍ መሞከሬን)ማ ስንት ጊዜ እንደሚኮረኩመው፡፡ ስንት ጊዜ እንደሚያሸማቅቀው…. የተረገመ!! ዛሩንባገኘው ኖሮ ግን ስንት ነገር አናዝዘው ነበር…. ስንት ነገርስ እቃርም ነበር…. እግሮቹ ስር ቁጭ ብዬ፣ ቢፈቅድ ፀጉሬን እየደባበሰ…. ቲሽ! አጉል ቅዠት!!

በመግቢያው ላይ ስብሀት ገ/እግዚአብሔር (ነፍሱን ይማረውና) እንዲህ ብሎ ነበር… (አቤት…ከሙሌክስ ጋር ሲገናኙ ግን እንዴት ሆነው ይሆን? … ምናልባት ለስንዱ ደብዳቤ ከላኩላት ታስነብበናለች፡፡ እርሷ እንደው ደግነቷ ብዛቱ…፡፡)

ሙሉጌታ ግን ከቅዳሴ እስከ ቅኔ፣ ከዛም ተሻግሮ ቁርአን፣ ሀዲስንና መንዙማን የሚያውቅ ምሁር ነው፡፡ ይህም ባንዳንዶቹ ግጥሞቹ ውስጥ ይታያል፡፡ እግዜርንም ሸይጣንንም በእኩል ንቀት እየገረመመ ሲያናግራቸው እንደ ዳኛ ነው፡፡ ምንም ምክንያት ሳላገኝለት እውስጤ የሰረፀ ጥርጣሬ አለኝ፡፡ በሞተበት ቦታና ሰዓት ከሰይጣን ጋር እየተፋጠጠ፣ እየተናነቀ ነበር ይሆን…

እዝጌርም ሰይጣንም የለም የሚሉ አንባብያን ሁሉ፣ እዝጌርም ሰይጣኑም የመለሱለት የራሱ ህሊና የፈጠረቻቸው ህልም ወይም ቅዠት ናት በሉ፡፡ ሌላ ማለት ብትፈልጉም መብታችሁ በህገ-መንግስቱ የተጠበቀ ነው፡፡

ስንዱዬ ደግሞ በምናቧ ከሙሌ ያስላከቸው ደብዳቤ ደግሞ እንዲህ ይቀነጨባል፡፡….

በምድር ስኖር ለግሌ ብዬ ያከማቸሁት ምንም ነገር አልነበረም፡፡ እንግዲያውስ በእርዳታ ድርጅት ውስጥ ከመስራት እስከ ኢህዴን – ብአዴን – ኢህአዴግ ድረስ ታገልኩ! በግሌ ያገኘሁት ነገር፣ መናቅ፣ መዋረድ፣ ለዐይን አለመሙላት ሆነ፡፡ ዋጋና ችሎታዬን ያወቁና የተረዱ ‹‹ጓዶች›› እንኳን የሚፈልጉኝና የሚያስፈልጉኝ ‹‹የድል በዓል›› በሚል ሰበብ ቅኔ እንድቀኝ፣ ግጥም እድገጥም፣ በአጭሩ የድግሳቸው አድማቂ፣ ተራ ‹‹አዝማሪ›› የሆንኩ እስኪመስለኝ መጎሳቆል ተሰማኝ፡፡

ይህንን ይሁን ብዬ ጓዶቼን ፈትቼ፣ ህዝቤንም አምኜ፣ ችሎታዬን ለዘፋኞች ልሰጥ አልኩና ተነሳሁ፡፡ ገበያው እጅግ የደራ ከመሆኑ የተነሳ እንኳን ሌላ ነገርሽን ከዐይንሽ ላይ ኩልሽን ሊሰርቁሽ የሚችሉ ሰዎች የበዙበት ሆነ፡፡ ይህን ትልቅ የገበያ ስፍራ ለመቀላቀል ስንት አሳር እንደቆጠርኩ ዛሬም ሳስበው ይዘገንነኛል፡፡ በቃ የስልጣናቸው የመጨረሻ ዳር ድንበር አሁን ትዝ አለኝ! ‹‹የኢኮኖሚው ባለቤት የፖለቲካውም ዋና ባለቤት›› እንደሆነው ሁሉ የስራው ባለቤቶች ነጋዴዎች ብቻ ሆኑ፡፡

‹‹እኔ እበላ – እኔ እበላ›› እያሉ ከሚሻሙት ጋር ለጨው፣ ለበርበሬ፣ ለውሎ ለአዳሩ እንኳ ብዬ አብሬያቸው ለመቆየት አቃተኝ፡፡ ይልቅ ጠጋ ያሉኝ ጋር በማርያም መንገድ፣ በማተብ፣ በክርስትና ለየግል ተነጋግረን፣ ቀኑን አሳምረንን ዱአ እያደረግን፣ ተፈጥሮንና ፈጣሪን ሳይቀር እየተፋጠጥን አብረን ጎጆ ልንወጣ ሰርተን ፈረንካው ሲገኝ ዐይኔን ለማየት እንኳ ይፀየፋሉ፡፡ አልፈው ተርፈው ብኩርናዬን ሳይቀር እንድሸጥላቻ ሁሉ ጠየቁኝ፡፡

ጉኖዬ – እንጂማ እኔ ወንድምሽ፣ ጥንቅቅ፣ ጥንፍፍ ያልኩ ጀግና ነኝ፡፡ ቅሱስም ንጉስም እሆናሁ አላልኩሽም ነበር… ካልሆንኩ ኋላ ትታዘቢኛለሽ፡፡ ለጊዜው ‹‹ብርዕ በደም ዕንባ››፣ ‹‹አንተሙሽር››፣ ‹‹ከመንበርህ የለህማ››፣ ‹‹ከነዓን ነው ዘንድሮን›› ግጥሞቼን ብቻ እንኳ ልጥቀስልሽ፡፡ እያደር እንደምትሰሙኝ ተስፋ አለኝ፣ ታዲያ እኔ እንዴት አባቴ አድርጌ ብኩርናየን ልሽጥ?!

ወደ ሁለት ሺህ የሚጠጉ ግጥሞችን፣ ሁለት ቲያትሮችን (ደጀ ሰላምንና ግምሻን) እና በርካታ ዘፈኖች ሰርቻለሁ፡፡ ውድነሽ በጣሙ፣ አማራ ነኝ ያውም ደሜ አረንጓዴ (ራዲዮ ፋና ሰነበው ቀድቶኛል፣ ጠይቀሽ ስናፈቅሽ ደግመሽ ስሚው፡፡ ‹‹ከመንበርህ የለህማ›› ኢትዮጵያ ሬድዮ ነበር፡፡ …እና ታዲያ ጉኖዬ አንቺ ግን ‹‹ጉዳዬ ሞተብኝ!›› ብለሽ በጣም ያዘንሽው ለእኔ ነው?

ይልቅስ ለሁሉም ሰው ይቅርታ መድረጌንና ይህ አካሄድ በእኔ ቢያበቃ ደስ እንደሚለኝ ንገሪልኝ፡፡ የሰራሁትን፣ ሀቄን፣ ገንዘቤን አንድጄ ብሞቀው እንኳ የሚያገባው እንዳልነበረ ደሞ መንገር እንዳትረሺብኝ!!

ቀብሬን ለማከናወን በእጅጉ የተባበሩሽን ጓዶቼን፣ መላ ጓደኞቼንና ቀባሪዎቼን አመስግኝልኝ፡፡ በምድር ሳለሁ አብረን የተሽከረከርናቸው ሰፈሮች የማስታውሳቸውን የምድር ጀለሶቼን አለምገናዎችን፣ ተረት ሰፈርን፣ ፈረንሳይ ለጋሲዎኖችንና ስድስት ኪሎዎችን፣ ቅድስት ማርያሞችን፣ ዶሮ ማነቂያዎችን፣ ሀብተጊዮርጊስ ድልድዮችን፣ አጠና ተራዎችን፣ ሰንጋ ተራዎችን….መላውን ወዳጆቼን ‘እንገናኛለን እኔ አልቆርጥም ተስፋ!’ ብሏል በይልኝ፡፡

ከልጆቼ ቀጥሎ የወለድኳቸውን ስራዎቼን እያስታወሳችሁ ‹‹አደራ ልጄን አደራ›› የሚለውን የብፅዓት ስዩምን ዘፈን እንድትሰሙልኝም ጋብዘዤያችኋለሁ፡፡ ጉኖዬ – ሆድ ሲብስሽ ደግሞ የሀና ሸንቁጤን ‹‹ሆዴ ባለአብሾ››ን ስሚ፡፡ በጣም ደግሞ የአበበ ተካን ‹‹ወፍዬ››ንም ስሚ!

ስሚ እንጂ …አንድ ቀን ‹‹ያንተን የተለያዩ ዘፈኖች መደዳውን ዛሬ አራት በኤፍ ኤም ሰማሁ›› ብለሽ በልብሽ ያጨበጨብሽልኝን ዕለት አስታውሼ ምን ትዝ አለኝ መሰለሽ… ያወጣሁላቸው ስሞች! ታምራት ‹‹ሀኪሜ ነሽ››፣ መሰረት ‹‹ጉም ጉም››፣ ፀደንያ ‹‹ገዴ››፣ ብፅአት ‹‹ገዳዬ››፣ ሸህ አብዱ ‹‹ሀዋብስል›› ኸረ ስንቱን አድምቄዋለሁ አያ!…ምንስ ቢሆን ሙሉጌታ ተስፋዬ ወዲ ሀለቃይ! ተጋዳላይ ነኝ እኮ!…

ከመፅሀፉ ላይ አሟልታችሁ ድገሙት፡፡ (ገፅ 133 – 135)

እስኪ ‘እውነት ከመንበርህ የለህማ’ን ፣ ቀንጭቤ ነገሬን ልቋጭ፡፡ወትሮም ለአመሌ ነው መቀባጠሬ እንጂ፣ መፅሀፉንካ ወረደ በኋላ ማን ይሰማኛልና?!

ምነዋ መንግስተ ሰማይ! የምህረትሽ ቀን ራቀ?
ምነው ትንግርትሽ ረቀቀ?
ምነው ኪዳንሽ ታጠፈ….ወዝሽ ወዘናሽ ነጠፈ?
እንደ ዳጉሳ ድፍድፍ….ላቦትሽ ተንጠፈጠፈ
አሳርሽ ጠሎ አሰፈፈ

ምነው እርሾው ተሟጠጠ….ጎታው ጎተራው ታጠጠ
ረሀብ ላንቃው ፈጠጠ….ያዳም ልጅ አፅሙ ገጠጠ
ምነው ጭር አለ ቀየው! ሀሩር ነዲዱ በረታ
ኮርማው ጥማዱ ተረታ

ምነው ነበልባሉ አየለ! ማሳው ተንቀለቀለ?
ነቀለ ሞፈር ሰቀለ! ተገድራ ደቀለ
ምነው ምድር ጨነገፈች….ዝላ ተርገፈገፈች?
ካስማ እንደተደገፈች ምነው ሳታብብ ረገፈች፡፡

ምነው የናት ጡት ደረቀ…..አራስ ልጅ ተስረቀረቀ?
ምነው አንጀቱ ታለበ….በውኑ ተለበለበ?
ኮሶ ስንብቱን ለለበ
ምነው ወላድ ተነስለሰለ….ልሳነ ቃሉ ሰለለ
በቁሙ ቆስሎ ከሰለ፡፡

አቤት የርግማን ቁርሾ…
በንጣይ እርሾ መነሶ
ምነው ላይፀድቅ በቀለ
የሰው ልጅ ዋጋ ቀለቀለ
ትቢያ አፈር ተቀላቀለ፡፡
ሆድና ጀርባው ተጣብቆ
አንጀቱ በራብ ተሰብቆ
እንደፈረሰ ክራር ቅኝት
ሰርቅ እንዳነቀው ድብኝት….

ከመፅሀፉላይጨርሱት፡፡ (ገፅ 11)

One thought on “ያልተዘመረለት – ‘የተረገመው ባለቅኔ’!!”

  1. many more, much more, zillion, gazillion times thanks …. be urs Yohannes, Abdi, Sinidu, and of course Muleeee. Areseresachihugn

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s