እንዴት እንተማመን?

ሰሞኑን ከባቡር መንገድ ስራው ጋር በተያያዘ የአቡነ ጴጥሮስና የአፄ ምኒልክ ሀውልቶች ይነሳሉ፡፡ የሚል ያልጠራ ወሬ ይዘን ብዙ ስንልና ስንባል ነበር የከረምነው፡፡ እግዜር ይስጣቸው፣ ብስጭቱ ስኳር ደማችንን ከፍ አርጎት ሳይደፋን በፊት ብቅ አሉና… የአንዳንድ ፀረ ልማት ሀይሎች አሉባልታ ወሬ ነው፡፡ ለደህንነቱ ሲባል መንገዱ እስኪያልቅ ድረስ የአቡነ ጴጥሮስ ሀውልት ይነሳና፣ መንገዱ ሲያልቅ ይመለሳል፡፡ የእምዬ ምኒሊክ ሀውልት ግን ጭራሽ አይነካም፡፡ ምናምን… ብለው አረጋጉን፡፡

ከዚያም በኋላ ቃላቸውን እንደሚጠብቁ እንዴት እናውቃለንና እንመናቸው? የሚለው የብዙ ሰው ስጋት አዘል ጥያቄ ሆነ፡፡ እኔም ደገምኩ! – እንዴት ነው የምናምናቸው? ማንም ጤናማ አዕምሮ ያለው ኢትዮጵያዊ መንገድ በመሰራቱ፣ አገር በመልማቱ፣ ብልፅግና በመምጣቱ…ቅር አይለውም ብዬ አስባለሁ፡፡ እኛው ኗሪዎቹ ነን በመንገዱ የምንሸልልበት፡፡ እነሱ እንደው አንዴ ተሸፋፍነው ከመረቁት ወዲያ፣ ሞተው (የሰይጣን ጆሮ ይደፈን) አስከሬናቸው ካልሆነ በአዲስ አበባ መንገድ አይምነሸነሹም፡፡

ምናልባት አንዳንዴ መውጫና መግቢያ መንገድ ሲሆን (እንደ ቦሌ) በዝጉ ላስ ላስ የሚሉበት ሁኔታ ይኖር ይሆናል እንጂ፡፡… መንገድ ማዘጋታቸውም ቢሆን አመል ሆኖባቸው ክባድ ሲፈጥሩ እንጂ፣ ኑሮና እነሱ ተባብረው ዐይናችንን ጋርደውት፣ የአገሩ መንግስት ይለፍ የእድሩ ዳኛ መንግስቱ መች እንለይና? – መሰለኝ!

ያም ሆነ ይህ ግን በአቡነ ጴጥሮስ ሀውልት ተነስቶ መመለስ ጉዳይ ዙሪያ፣ እንዴት እንመናቸው? ነው ጥያቄው፡፡ ሲጀምር የሰዉ አፀፋ ምን ሊሆን እንደሚችል በመገመት (አሉባልታም ሆን ምን ከመስማታችን አሊያም ከመፍጠራችን በፊት) አካሄዱን የተመለከተ ነገር በዚያ ቆርቆሮ ወቆረቆራም ቲቢ በኩል ሰው ወክለው ሊያሳውቁን ይገባ ነበር፡፡ የነሱ ዝምታ ነው እኛን ያስቀባጠረን፡፡ በዝምታቸውም አሸበሩን! ቅሉ ንጉስ አይከሰሰ….

ሲቀጥል ደግሞ ከዚህ በፊት ብዙ ቁማሮች ላይ ያፈሩብን እፍርታሞች ናቸው፡፡ ሌላ ሌላውን ብተወው እንኳን ሁለት ነገሮችን አይረሱኝም፡፡ ያኔ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት ስንትና ስንት ወንድምና እህቶቻችን ደማቸውን ካፈሰሱ በኋላ (እኛም ሆ….ብለን በነቂስ ወጥተን፣ በሞራልና በወኔ ሞልተን ሸኝተን ለፈሰሰው ደም ከተባበርን በኋላ)፣ ጦርነቱንም ማሸነፋችንም ታውቆ ድህረ ድልም (post victory) ሸልለን … ‘ባድመ እኮ belongs to ‘em’ ብለው አረዱን፡፡

የኢትዮጵያችንን የሰው ዘር መገኛነት ጮክ ብላ የምታቀነቅነው ሉሲም (ሰላም መጥታ እስክትቀናቀናት ድረስ) አሜሪካ ለስድስት ዓመታት ጉብኝት ፈታ ብላ ትምጣ ተብሎ ከሄደችበት መመለሷን አልሰማንም፡፡ ጥገኝነት ጠይቃ ነው መሰል በዚያው የውሀ ሽታ ሆና ቀረች፡፡ ስድስት ዓመቱ ባለፈው ጥቅምት ደፍኗል፡፡ እንዲያውም ‘አሜሪካ ሄደሽ፣ አወቅሽ፣ ነቃሽ…ሀሳቤን የመግለፅ መብቴን ምናምን አልሽ…’ ተብሎ የአሸባሪ መዝገብ ምናምን ሊከፈትላትም ይችላል፡፡

እንግዲህ ጎብኚዎች እንዳይጉላሉ በማሰብ ተጎብኚውን ቦታቸው ድረስ በማድረስና የተቀላጠፈ አገልግሎት በመስጠት ረገድ እኛን ማን አህሎን?…. ደግሞስ ማን ያውቃል? – አቡነ ጴጥሮስ ሰማዕትነትን በጭካኔውና በላዩ ላይ፣ በታላቅ ኩራት የተቀዳጁበትን ፋሽስት ጣልያን ሄደው ይሸልሉበት፣ ህዝቡንም ይቅርታ እያስጠየቁ ያስገብሩት (ያባት እዳ ለልጅም አይደል?) ምናምን ተብሎ መንገዱ እስከሚያልቅ ድረስ ደርሰው ይመለሱ ቢባልስ ምን እናውቃለን?

እኛና ጣልያን እንደው ድንጋይ በመወራወር ስር የሰደደና ዓለምን ያስናቀ ልምድና ታሪክ ነው ያለን፡፡ ያኔ…አያቶቻችን በዘመናዊ ጦር የታጠቀውን ቡርቂ ጡርቂ የጣሊያን ሠራዊት በድንጋይ፣ በጦርና በጎራዴ ቂጥ ቂጡን እያሉ አባረሩት፡፡ ጣሊያንም ድል ማድረግ አልሆን ሲለው፣ አገሩ ሲመለስ ባዶ እጁን እንዳይሆን ብሎ…የከበረና ታሪካዊ ድንጋይ ይዞ ፈረጠጠ፡፡ ወደ ሮም፡፡

(እዚህ ጋር የአክሱም ሀውልትን ክብርና ዋጋ በማሳነስ ሳይሆን የተቀረፀበት ቁስ ድንጋይ መሆኑን በማሰብ ብቻ ያልኩት መሆኑ ይታወቅልኝ፡፡ የጨዋ ልጆች ነን፡፡ ሀውልትን – ‘ድንጋይ’፣ ባንዲራን – ‘ጨርቅ’ አንልም፡፡)

‘ከቅንፍ ስንወጣ’ – አለ አቤ ቶኪቻው፣….ከቅንፍ ወጥተን ሌላ ቅንፍ ውስጥ ብንገባስ? – መብታችን ነው፡፡ ህገ – መንግስታዊ መብታችን፡፡ እናም ሌላ ቅንፍ ውስጥ ገባን… ምሽግ መሆኑ ነው፡፡ (ያኔ የጣሊያን ሰራዊት መጀመሪያ ከጀግኖች አርበኞቻችን የተዘነዘረበትን ጥቃት ለመመከት፣ እንደ ጦር መሳሪያ ሊጠቀምበት አስቦ ነበር… ከቦታው የነቀለውና ይዞ መሮጥ የጀመረው፡፡ ኋላ ላይ ግን ነገሩ ከግምቱና ከአቅሙ በላይ ሆኖበት በእኛው አንበሶች ቀኝ ኋላ ዙር ሲባል ጊዜ፣ በዚያው ይዞት ሮም ገባ፡፡ (በደመነፍስ ሮጦ…) ከዚያም የቅሌትና ልክን የማወቅ ዘመኑን ያስተውሰው ዘንድ አደባባይ ላይ ተከለው፡፡ ምናምን ብለን እናሽሟጥ እንዴ፡፡

ከዚያም በኋላ….ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ምክንያቶች ሮም ሲሄዱ ሀውልቱን ተደግፈው ፎቶ ሲነሱ ኖረው ኖረው…. ከዕለታት በአንዱ ቀን በፀሀዩ መንግስታችን የአክሱም ሀውልት አስመላሽ ብሔራዊ ኮሚቴ ተዋቀረና አክሱማችን ወደ ጦቢያችን ተመልሳ ዳግም ከመንበሯ ላይ ተሰየመች፡፡ ደስም አለን፡፡ በልባችን ዘንባባ ዘንጥፈን እንደ አዲስ ጨፈርን፡፡ በልጅነት ቀልባችንም፣ ይሄ የድንጋይ ቅብብል (ቅልብልቦሽ ልንለውም እንችላለን፡፡) ቢያስገርመንና ቢረቅብን ጊዜ…. በኩልትፍና እንዲህ ብለን ነበር….

የስልጣኔ ጥግ…
ድንጋይ ከአገር አገር
ያግዝ ያንሸራሽር፣
ያወራውር ጀመር፡፡

/ዮሐንስ ሞላ/

ተሽከርክረን ወደ ዋናው ጉዳይ ስመለስ…በበኩሌ፣ ጉዳዩ መንገድ አይሰራ ሳይሆን፣ እንድናምናቸው አድርገው አላሳደጉንምና እንዴት እንመናቸው? የሚለው ነው፡፡

One thought on “እንዴት እንተማመን?”

  1. ጥገኝነት ጠይቃ ነው መሰል በዚያው የውሀ ሽታ ሆና ቀረች፡፡ ስድስት ዓመቱ ባለፈው ጥቅምት ደፍኗል፡፡ እንዲያውም ‘አሜሪካ ሄደሽ፣ አወቅሽ፣ ነቃሽ…ሀሳቤን የመግለፅ መብቴን ምናምን አልሽ…’ ተብሎ የአሸባሪ መዝገብ ምናምን ሊከፈትላትም ይችላል፡፡ hahaha

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s