ደኔን አትነካኩት!!

የዘራ’ዝመራ ብቃይ ኩራት፣ ግንድ ማንነት ታቅፌ፣
ማደሪያ ደኔን ስፈልግ፣ መሀል መንገድ ላይ ሰንፌ፣
ስደናበር፣ ስንከላወስ፣ ሸክም ኮተቴን ሸክፌ፣
ስባክን! ስማስን! ኖሬ. . .
ከገደል፣ ጢሻ፣ ከዱሩ፣
ከጋራው ከሸንተረሩ፣. . .
ብቅ አለልኝ የእኔ መሲህ፥ forest-beautiful-places-13747456-1920-1080
. . . ማንዘራሹ አርበኛዬ፣ ወፍ ዘራሽ ዘዴ ሰንቆ፣
አርነቱን ሊያስታጥቀው፥ ዘሬን ከግንዴ ፈልቅቆ፣
ሞልቶለት አንድ ላያገኝ. . .
ቋሚ ግንዴን ሰነጣጥሮ፣ቅርንጫፌን ሰነጣጥቆ፣
ዘሬን ለቀማ ባከነ፣የእኔ ጀግና ባ’ጭር ታጥቆ።

‘ኦ ዘርህ. . . ክቡር ነውሳ ጃል!. . .
የሚታይ ከግንድህ ልቆ፣
ከቅጠል ቅርንጫፍህ ደምቆ፣
ልዩ ውበቱን አምቆ. . .
እምቢኝ ለዘርማንዘርህ!. . .እምቢኝ!. . . ’
ብሎ ተመመ፣…
የማላውቀውን ሊያውቅልኝ…
የማይረባኝን ሊያይልኝ።

በውብ የዜማ ቀመር፣. . .
. . . በሽለላ በቀረርቶ፡ መወድስ ፉከራ ሞልቶ፣
ከግንዴ ጋር የናቀውን፣ ዛሬ ሊያስከብረው ሽቶ፣
ሲሸርብልኝ መሽጎ፣ ዛፍነቴን ቀድሞ ስቶ፣
ዘሬን ከግንዴ ለይቶ፣ሊያስታፍር እቅድ ዘርግቶ. . .
ህገ – ልቡና፣ ወንጌልን፣ ህገ-ስብ’ናን ገርስሶ፣
ልህልናዬን ደፍጥጦ፣ ልሳን ኩራቴን ጠርምሶ፣
ጥቅጥቅ ጫካዬን አሳስቶ፣ ማደሪያዬን በእጁ አፍርሶ፣
አዱኛ ተርፎት ተርቤ፣ ቆጥሮኝ ሳያውቅ ከጥፍጥሬ፣
ይህው ዛሬ. . .

ያዋጅ ነጋሪ አስነግሮ፣ መለከት እምቢልታ አስነፍቶ፣forest_road_picture_mystery
ድቤ፣ ከበሮ  አስደልቆ፣ ድብ-አንበሳ አስመትቶ፣
ቦታ ሰይሞ፣ ቀን ቆርጦ፣ ቁሳቁሱን አስከትቶ፣
ዳስ ጥሎ፤ -ክራር በገና፣ አታሞውን አዘጋጅቶ፣
አልባሱን ሽቶ ነስንሶ፣ ባ’ይነት ባ’ይነት አሰናድቶ፣
ስልቻ፣ ጎተራ፥መርጦ፤ ዘር ሰብስቦ፣  አስከትቶ፣

ይህው ዛሬ. . . ይህው ዛሬ ቀኔ ሆነ
ሊያስከብረኝ ላይታች አለ፣
ህግ ከመረ፣ ቆለለ
ዛቻ ፈተለ፣ ሸለለ. . .

ደግሞ ሌላውም ቀጠለ. . .
‘ጫካነት ይከበር!’ . . . ሊል ሲችል፣ ግንዴን ከጫካው ለይቶ፣
‘ህገ-መሲሁ ይከበር!’ እያለ ካውላላ ጮኧ፣ በቃሉ ባ’ሳቡ ዋትቶ፣
ግንድነቴን መርጦ አጉልቶ፣
ለምቾቱ የጫረውን፣ ሲሻው ነገ ‘ሚያድሰውን – የመሲሁን ህግ አንስቶ፣
ቃል አጣቅሶ፣ ቃል ፈትፍቶ፣ ቃል አስውቦ፣ ቃል አጣፍጦ፣
ቀን ሰይሞ ላይ ታች አለ፣
ወኔ ከመረ፣ ቆለለ፣
በምድረ በዳ ባተለ፣. . .

ግን ምናል ሁሉም ቢተዉኝ? ሊበጣጥሱኝ ባይጥሩ፣
በዘር ለቀማ ሰበብ፣ በዘር ስብሰባ ሰበብ፣. . .
. . . ጫካው ልቤን ባይነካኩት፣ሊበትኑኝ ባይዳክሩ?

/ዮሐንስ ሞላ/

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s