ሰዉ ግን ምን ነካው?!

ሰሞኑን ኢንተርኔት ቤቴ ስለሌለኝ ኢንተርኔት ካፌዎች እየሄድኩ ነው የምጠቀመው። ትናንት አመሻሹ ላይም ከወዳጆቼ ጋር ፒያሳ የማንኪራን ቡና አጣጥመን…. መኪና ስለነበራቸው ወደ ሰፈር ገፋ አድርገውኝ ስንለያይ በአቅራቢያው (ከሰፈር ትንሽ ራቅ ብሎ) ወዳለ ኢንተርኔት ካፌ ጎራ አልኩኝ። ካፌው እንደ ደንበኛ የደህና ደሀ መኖሪያ ቤት ሳሎንና ጓዳ አለው። ጓዳ ያሉት ምትሀተ ሳጥኖች (computers) ዌብ ካምና መብራት አናታቸው ላይ ተገጥሞላቸዋል። (መብራቶቹ ዌብ ካሞቹ የጠራ ምስል እንዲያሳዩ የሚያግዙ ናቸው።)

Tበዚያም ክፍል ውስጥ ስካይፕ (skype) ላይ በድምፅ ቻት የሚያደርጉ ይበዛሉ። የቤቱ ሁኔታ ስራ እንደሚበዛበት ቴሌ-ሴንተር ነው። – የወዲያኛው ጫፍ የማይሰማበት፣… የአንድ እዮሽ ንግግር ድምፅ ብቻ የሚስተጋባበት። ቁርጥራጭ ወሬዎች የሚተራመሱበት ጠባብ ክፍል። ወሬ የጠማውና በመሀል እንደ እኔ ለአፍታ ስራ የፈታ የዚያኛውን ጫፍ በግምት እየሞላ ይሰማል። በየመሀሉ ከሳሎን በሚመጣው የሚካኤል በላይነህ የሙዚቃ ድምፅ ታጅቦ። – ‘በማር ሰራሽ’ ወይ ይላል፤ የወሬ ሱሱን የተገኘውን የወሬ ዓይነት እንደ ማር እየላሰ፡፡

በክፍሉ ውስጥ ያሉ አብዛኛው ተጠቃሚዎች ጆሮአቸው ላይ ማዳመጫቸውን ተክለው እየጠበቁ ያወራሉ። እየቆዩ የጎንዮሽ ሰረቅ እያደረጉ እየተመለከቱ፡፡ …

“እሺ…”… “አዎ…”…. “እኔም” (እውድሻለሁ ተብላ ይመስላል፡፡) …. “እምጷ!…. ቀላል ናፍቀሽኛል?” (በአካል ያገኛት ይመስል ተስገብግቦ) … “ኢንሻ አላህ!”….“እግዚአብሄር ይጠብቅሽ…”… “እቴትዬ፣ ብሩ ደርሶኛል… ቴንኪው”…. “ኧረ የትምህርት ደመወዝ ደረሰ።…በልደታ ካልከፈልኩ መባረሬ ነው።”… “በርቺ! አይዞሽ…ስለራስሽ አስቢ! አትጨነቂ ስለእኛ!”… “አዎ በዌስተርን ላኪልኝ…”…. “ነገ 1 ሰዓት ላይ ኦንላይ ሁኚ።”…“እሺ” “እፅፍልሻለሁ”…. “ሁሉም ሰላም ብሎሻል” “አታስቢ ሁሉም ደህና ነው፡፡” አሁን ደህና ነው። መድሀኒቱን እየጨረሰው ነው። ግን ምግብ በደንብ መብላት አለበት።”

…..ብዙ ዓይነት ንግግሮች። — የናፍቆት። የስስት፡፡ የፍቅር፡፡ የእሮሮ። የተማፅኖ።

በዚያ ዓይነት በድምፅ የማውጋት (voice chat) ሁኔታ ላይ ሳይሆን ቀርቶ፣ ዝም ብሎ ገፅ ገፁን ኢንተርኔት ለሚጠቀም የእኔ ቢጤ… ትርምሱ ገበያ መሀል እንደ መሆን ነው።

“እልል በል አበሻ…. የ30 ብር ጌታ በ10 ብር”…. “ያይጧን ያይጧን”….”የወለሏን ማፅጃ በ20 ብር”…”ሰምተሻል! ቤት ያለሽ…ባል ያለሽ….የወጥ ማውጫዋን በነፃ…” ….”ፓሳ አራት ኪሎ”… “ጎርጊስ ጎርጊስ”… “አንሶላ፣ ብርድልብስ፣ የውጪ አልጋ ልብስ”… “የሞባይል ቻርጀሯን ባስር  ብር”…. “ ልጅ ያለው በ40… ልጅ ያለው… ልጅ ያለው”

…ብዙ ዓይነት የንግድ ድምፆች እየተንጋጉ ጆሮን እንደሚደበድቡ፡፡ አይንን እንደሚጎትቱ፡፡ አይንን የሳበው ጆሮ እንደሚገባ፡፡ …የማታው የኢንተርኔት ገበያም እንደዚያ ነበር። እልል ያለ ገበያ። የድምፅ ገበያ። የቻት ገበያ። የናፍቆት ገበያ። የጠበሳ ገበያ። የፈለጣ ገበያ፡፡ የማፅናኛ ገበያ፡፡

ስራዬን እየሰራሁ ዙሪያውን በጆሮዬ ቃኘት ቃኘት፣ ወሬ ቃረም ቃረም ሳደርግ… ወዲያው ከጎኔ የተቀመጠ የአንደኛው ድምፅ የጆሮዬን ቀልብ ሳበው። የምፈልገውን ዓይነት ወሬ አውርቶ አይደለም። እንዲያው ነጎድጓድ ድምፅ ነው። ለዛ የሌለው ነጎድጓድ ድምፅ። እንኳን ሌጣውን የቀረ ጆሮ ይቅርና ማዳመጫ የተደረገለትንም ጆሮ ሳይቀር ትኩረት የሚስብ ረባሽ ድምፅ። ድምፅህን ዝግ አርግ እንዳይሉት የወሬው ሁኔታ የሚያጓጓ።

በቴሌቪዥን የሚበሳጩበትን ነገር አፍጥጦ እንደማየት ነው። በዚያ ላይ እየተበሳጨና እየተወራጨ ነው የሚያወራው፡፡ ድምፁ  ጆሮ ሲገባ የወሬው ይዘት ዓይንንም የመግፋት አቅም አለው። በጆሮዬ የተገፋው ዓይኔም ሰረቅ እያደረገ ያየዋል። በግርምትና በብስጭት። በተለይ ሲቆጣ ድምፁ  ከጣሪያ በላይ ይሆናልና ጤነኛ ጆሮ ይሰማው ዘንድ፣ የሰማው ጆሮ ባለቤት ዓይንም አካባቢው ሰላም መሆኑን ያጣራ ዘንድ ዞር ብሎ መመልከቱ የግድ ነው።

እርሱ

በጎን እንደተመለከትኩት…አንዳንዴም በቁጣ ሲወራጭ ሙሉ ገፁን ገረፍ አድርጌ እንዳየሁት…– ቀላ ያለ መልከ መልካም ነው። እድሜው ከ35 – 40 ቢሆን ነው፡፡ ፈርጠም ያለ ሰውነት አለው፡፡ የሰውነቱ ሁኔታ ከአለባበሱ ጋር ሲታይ ዓይንን በቀላሉ የመያዝ አቅም አለው። ለመግባት እያቅራራ ያለውን ፀጉሩን በጄል ነክሮት በጣም ያብረቀርቃል። የግንባሩ ጫፍም ለጥ ያለ ነው። ሸርተቴ ቢሉበት ይዞ የሚያዳልጥ ይመስላል።

ፊቱ ደህና ባልቴት በሰም ያሳመረችው የጣውላ ወለል ይመስል ያንፀባርቃል። ክሬም ካለልክ እንደተደፋበት ይለያል። የሽቶው ልስላሴና መዓዛም ሳይረብሽ ቀልብን ይይዛል፡፡ እንዲያው ሲሽሞነሞን ቤቱ ምንም መዋቢያ ያላስተረፈ የሚመስል ጥንቁቅ ሽሙንሙን ነው። ከላይ ታች በውድ ያብለጨለጨ ፋራ ሽሙንሙን። መሽሞንሞን ብርቁ። እንደወረደ። ንግግሩን ሲከታተሉት ደግሞ መሽሞንሞኑ ይረሳና ፋራነቱ ብቻውን ይቀራል። — ግጥጥ ፍጥጥ ብሎ። እልም ያለ ፋራ!

እርሷ

በመነፅሬ ተከልዬ፣ ዓይኔን ወደ ምትሀተ ሳጥኑ ወርወር እያደረግሁ በትግል ላያት እንደሞከርኩት…. — ቀይ ነች። የገረጣች ቀይ። የእንቅልፍ ሰዓት የደረሰባት ይመስል ዓይኖቿ ቡዝዝ ፍዝዝ ያሉ ይመስላል። – በማየትና ባለማየት ትግል ውስጥ የሚዳክሩ።….. ቆንጆ ደመ ግቡ ትመስላች፡፡ ሰጋጋ አንገቷ ሲታይ ረዥም ትመስላለች። ልጅነቷ ቀልጭልጭ ዓይኗ ላይ ይታያል። የሆነ የቤተሰብ መልክ ነው ያላት። የምታሳሳ። የምታሳዝን። የማይቆጧት ዓይነት ነች። – ብታጠፋም በርሷ ምትክ የሚያብራሩላት።

እንባዋ ደግሞ ቅርብ ነው። ወይም የኑሮዋ ሁኔታ እንደዚያ አድርጎ  አስቀርቷታል። ይጨቃጨቁ ይጨቃጨቁና በመሀል እንባዋ ዱብ ዱብ ይላል። ደግሞ ትጠርገዋለች። ወዲያው እስኪረጥብ ድረስ። የሆነች ነፍሰ ስሱ ስታለቅስ ደስ ትላለች። ማለቴ ፊቷ ቲማቲም ይመስላል። ደግሞ ስትስቅ ከዚያ በላይ ነው። ፍልቅልቅ ስትል ምኑንም አትቆጥበውም። እኔን ግን ከአሳሳቋ ውበት ይልቅ ምን እንደሚያስቃት ነበር የገረመኝ። እርሱ ሲያምባርቅባት ታለቅስና ደግሞ ትንሽ ቆይቶ ገገማ ቀልድ አይሉት ቀንድ ሲለቅባት ትስቃለች።

እኔ

መጀመሪያ ስገባ እንዲያው ሱስ ለማብረድና አንድ ጥብቅ ዶክመንት ለወዳጅ ለመላክ በማሰብ ብቅ ጥልቅ እላለሁ ብዬ በማሰብ ነበር። ኋላ ላይ ግን የሰውየው ንግግር አስሮ ያዘኝ። መሀል ላይ ወዳጄን ቻት እያደረግኩኝ ከዚህ በፊት በ1997 ዓ/ም ፅፌያት የነበረች ግጥም ትዝ አለችኝና እርሷን እያሽሞነሞንኩ፣ እያቀናበርኩ ቆየሁ። ጆሮ ስጠባ…. ወሬ ስቃርም… ስጬስ ስቃጠል። ‘ከዚያስ?’ የሚለውን ለመመለስ ስጓጓ… መላክ የፈለግኩት ዶክመንት በአግባቡ ያልተሰናዳ መሆኑን አይቼ ቤት ሄጄ አስተካክዬ መቀየር እንዳለብኝ አውቄ ተበሳጭቼያለሁ። ግን መሄድ አልሆነልኝም።  አጥብቆ ጠያቂ (ጠባቂ) እንዲሉም…ጥጉ ድረስ ደርሼ ልቤን ሰብሬ ቤቴ ገባሁ። እንዲህ ነበር….

– “እርሱን ምናባሽ አውቅልሻለሁ?
– ….አቦ እንግዲህ አትልዘዢ!
– ቆይ…. የማትሰሚኝ ከሆነ ለምን ትደውያለሽ? ለምንስ ደውል ትይኛለሽ?
– ወዲያ….አልቅሰሽ ልታስፈራሪ ነው? አብረን እንኖራለን ብለሽ ነው። ለራስሽ ብለሽ ያደረግሽው ነው።
– ደላላ የነበርኩ አስመሰልሽኝ እኮ፡፡ (ይስቃል… የለበጣ ሳቅ)
– እንግዲህ ሴት ስለሆንሽ ያገኘሽው እድል ነው እንጂ በቦታሽ በሆንኩኝ አሳይሽ ነበር። ደግሞ እንደተጎዳ ታካብጂያለሽ?
– ዝተት! 16 ዲጂት ቁጥር እኮ ነው የላክሽው። ቀበሌሽን ጠየኩሽ እንዴ?
– ወይ ደግሞ ብሩን መላክ ካልፈለግሽ መናገር ነው። ደግሞ ስሚ። እዚህ ለራሳችን ነው ብሻሻል። አስተካክለሽ ትልኪያለሽ ላኪ፣ ካለዚያ ዓይኔን አታይም ከእንግዲህ።
– (የለበጣ ሳቅ…) ….ቆይ ግን ግኑኝነትሽ ከእኔ ጋር ነው? ወይስ ከቱልቱላዎቹ ጋር? እነሱ ወሬ ፈጥረው ባወሩልሽ ቁጥር አትነዝንዥኝ። ካላመንሽኝ ማቆም እኮ ነው። እጅሽን ያዝኩሽ? …ምን አድርግ ነው የምትይኝ…. ሆሆሆ……
– በቃ የራስሽ ጉዳይ! ራስሽን ስለማታምኚ ነው። ቀድሞ መታመን….
– ኦፋ! ልጅ አይደለሁም። አታምሽ ምናምን…
– ምናውቅልሻለሁ? እዚያ ያሉትን አሳያቸው። ሰውዬሽ አይነግርሽም? እርሱ ይንገርሽ። ደግሞ ከርሱ ጋር አንድ ነገር አደርጋለሁ ትይና የማላውቅ እንዳይመስልሽ። (ትስቃለች)
– አግጥጪ! ቀልድ መስሎሽ…
– እና ነገ ትልኪያለሽ አትልኪም?  ሳምንትም ቆንጥረሽ ላክሽ። ዝም ብለሽ መላኪያ ከምታባክኚ እኮ አንዴ መላክ ነው የሚሻልሽ።
– እርሱንማ ማንም ይላል።…. ከወደድሽ በተግባር ነው።
– ኤጭ እንግዲህ….. (ይወራጫል)
– ቆይ አንቺ ካለመጠራጠር ሌላ ስራ የለሽም እንዴ? እዚያ ጥርጥር ነው የሚያስተምሩሽ?
– በቃ እኮ ስትመጪ ሁሉንም ታያለሽ። የእኔ ከሆነ እውነቱ የእነሱ ከሆነ እውነቱ መለየት ነው።
– 2 ዓመት  ምናላት?
– ሃሃሃ…..ሴትነትሽ አሁን ነው ትዝ ያለሽ? ሴት ብትሆኚማ ከዚህ ችግር አመለጥሽ እኮ። ( ሌላም ነገር ያጉተመትማል)

….. (ቃል በቃል አይደለም፡፡ እንዳስታወስኩት ነው፡፡)

438089-Cartoon-Black-And-White-Outline-Design-Of-A-Businessman-Running-And-Talking-On-A-Cell-Phoneብዙ ብዙ ሲባባሉ ቆዩና በቅጡ ቻዎ  ሳይባባሉ “በቃ ልሄድ ነው ሆዴ።” (ጆሮዬ ሆዴን ሰምታ ማመን አልቻለችም ነበር፡፡) ብሏት ስካይፑን ድርግም አድርጎት ተነሳ። እኔም ወዲያው ቻት የማደርገውን ወዳጄን መምሸቱን አሳውቄው… በአጣዳፊው ተሰናብቼው ተነሳሁ። ሳላውቀው 2 ሰዓት ቁጭ አልኩኝ። ሳሎን ወጥቼ ገንዘብ ልከፍል ሂሳብ ሳሰላ (120 ሲባዛ በ20)  ሰውየውም ከብዙ ብሮች መሀል መቶ ብር ሰጥቶ መልስ እየጠበቀ ወደ በሩ ወጣ ብሎ ስልክ ደወለ።

– “ሃሎ የኔ ቆንጆ…
– ቆየሁ አይደል?
– ቤት ነበርኩኝ ኧረ። ከእንቅልፌ ነቅቼ ልተጣጠብ ብዬ ነው።
– እህ የት ነሽ አሁን?
– እሺ የእኔ ፍቅር…
– በረንዳው ላይ ጠብቂኝ። የፈለግሽውን አዘሽ…
– Of course, ከእራት ውጪ፣ ቀይ ወይን እቀጣለሁ።
– በቃ መጣሁ። …መጣሁ.. መጣሁ…
– Me too…”

እኔም ‘ኢቲቪ ከስንት ጣእሙ’ እያልኩ ቆሽቴ እየነደደ፣ ብዙ ነገር እያሰብኩ ቤቴ ገባሁ፡፡