የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ እያለን…ትምህርት፣… ጥናት፣… የቤት ስራ፣… ትምህርት ቀረህ፣… አረፈድክ… ምናምን ጭቅጭቁ ሲመረን… ባልተገራ የልጅ ዜማ እንዲህ እንል ነበር፡፡
“ሀይማኖት የግል፣
ሀገር የጋራ፣
ትምህርት የፋራ”
መቼም በዚያ እድሜያችን እንዲያ የምንለው የሀይማኖት – የግልነትና… የአገር – የጋራነት ዘይቤ በወጉ ገብቶን አልነበረም፡፡ ያው እንደ ልጅ ጉጉቱ ሁሉ… ማደግ፣ ታላላቆች ላይ መድረስ ነበርና…ብዙው ከሚለውና፣ ‘ይስማማበታል’ ብለን ካሰብነው ነገር ጋር የእኛን ነጥብ አጣብቀን ለማስተላለፍ የተጠቀምንበት ነገር ይመስለኛል። — የእኛ ነጥብ ‘ትምህርት የፋራ!’ የምትለዋ ነበረች፡፡
ሀይማኖት የግል?!
ሀይማኖት የግል መሆኑ እየተነገረ፣ ህገ መንግስቱም ላይ ሳይቀር መንግስትም ሆነ ማንኛውም ግለሰብ በሀይማኖት ላይ ጣልቃ እንዳይገባ፣ የግለሰቦችን የእመነት ነፃነት እንዲያከብር በግልፅ የተቀመጠ ቢሆንም እውነታው ግን መንግስትም ሆነ ግለሰቦች በሀይማኖት የግልነት በሀሳብ (በመርህ ደረጃ) እንጂ በተግባር የሚስማሙ አይመስልም። ‘ሀይማኖት የግል ነው’ ይልና፣… ሁሉም የራሱን እምነት ሌላው ላይ ለማጋባት የመኳተን ዝንባሌውን ይቀጥላል፡፡
እንኳንስ በስም ተለይተው ታውቀው በህብረት የሚያመልኩት ይቅሩና ‘የእምነት ተከታዮቹ በህብረት ማምለክ ነዋሪውን ጎድቶታል፣ …በድህነት እንድንመላለስ ሰበብ ሆኗል፣… የስራ ባህላችንና ተጠያቂነታችንን ጨቁኖታል፣….’ ሌላም ሌላም ብለው የእግዚአብሔርን መኖር የማያምኑ (ኢ-አማንያን – athiests) ሳይቀሩ ህብረታቸውን ማጠንከርና ብዙ ሰዎችን መሳብ ይፈልጋሉ። ሁሉም ባይሆኑም… አማኞቹን ካለአግባብ መንቆርና ‘ቅዱስ’ ብለው የሚያክብሯቸውን ማንቋሸሽ ላይ ይበረታሉ፡፡ (የሌላ እምነት አማኞችንም ይጨምራል፡፡)
እንግዲህ ይህ የሚሆነው ‘የለምና አላመንነውም’ ብለው የተውት ቦታ ጋር በሀሳብ ተመልሰው ነው፡፡ እንቆቅልሹም እዚህ ጋር ነው። – ‘በህብረት ማምለኩ ጎድቶናልና በህብረት ሆነን የተመላኪን አለመኖር እናሳይ’ አይነት ነገር፡፡…ምናልባት በሂደት የራሱ መተዳደሪያ ደንቦች ተቀርፀውለት፤ዲስኩሮችና ስብከቶች ይዘጋጁለትም ይሆናል። (እስካሁንም ይኖር እንደሆን እንጃ!) — በሀይማኖቶች ሀልዮት ተበሳጭቶ ራሱን የወለደ ተመላኪ-አልባ ሀይማኖት እለዋለሁ፡፡ (ምናልባት ይሄን ሀሳቤን ፈታ አድርጌ መፃፍ ካማረኝ ራሱን አስችዬ ሌላ ቀን እመለስበት ይሆናል፡፡ — ያው በመሰለኝ ነውና ‘ሲመስለኝ’ ብዬ! )
ሰው ስለራሱ ሀይማኖት ጥንካሬና ውበት፣ መልካምነትና ሰማያዊነት፣ ዘላለማዊነትና ፍፁምነት… ቢናገር ስለሌላው ሀይማኖት ድክመትና አስቀያሚነት፣ መጥፎነትና ምድራዊነት፣ ወቅታዊነትና ከንቱነት መናገሩ ነው ማለት አይደለም። ብዙ ሰው ግን እንደዚህ አይረዳውም፡፡ ወዳጁ እውነት ያለውን ነገር መስማት ያሳምመዋል፡፡ ‘ከእኔ ሌላ እውነት ላሳር’….በሚመስል ሽለላ፡፡
እንደ እኔ ግን ማንም እውነት አለኝ ሲል…ሌላውን ሳያስታክክ ይመስክር። ሌላውንም ሰው በሀሳቡ አይናቀው። ‘አይ…ይሄማ ሀሰት ነው፡፡’ የሚለው ተቃዋሚ ቢኖር… ተቃውሞውን ከዘለፋና ከንቀት የፀዳ ያድርገው፡፡ ያ ካልሆነ ግን የሚከራከርለትን እውነት አቅም ውሱንነት ቀድሞ ማመን ሊመስል ይችላልና አያተርፍም፡፡ አያስታፍርም፡፡ ምናልባት ቢያስተፋፍር ነው፡፡
መቼም ከቁስ ጣዖት አምላኪዎች በቀር በሌሎች እምነት ውስጥ የሚገኙ ሰዎች አምላክን በመለኮዊ ረድኤቱ እንጂ በገፁ ያየው የለም፡፡ ያም ነው እምነት ማለት፤ – ያላዩትን ነገር መኖሩን አውቆ መረዳት፡፡ በዚያም ውስጥ ለግብሩ ይመጥናል ተብሎ የሚታሰበው ነገር ሁሉ እየተደረገ ለህግጋቱ መገዛት ይመጣል፡፡ ያመለክነው እንዲረዳንም በተስፋ እንማፀናለን፡፡ …ከዚህ የዘለለ ነገር የለውም።
ሆኖም ግን በተለያየ ጊዜ የምናየው ነገር ከዚህ በጣም የተለየ ነው። ሰዎች ስለሚያመልኩት (ስለሚያምኑት) ነገር እርግጠኛነቱን ማግኘት የሚፈልጉት ከልባቸው ሳይሆን በአካባቢው ከሚመለከቷቸው ሰዎች ነው። በተለይ ሰዎቹ ታዋቂ ሲሆኑ ፍለጋው ይበረታል፡፡ ብዙ ሰው አዋቂነትን እና ታዋቂነትን ለመለየት ይቸገራልና ልቡ ሲጠገንም… ሲሰበርም ወዲያው ነው፡፡ (እዚህ ጋር ብዙ ነገር ማለት ይቻላል፡፡ ሆኖም ግን ነገሩ እንዳይንዛዛም ሀይማኖታዊ ዲስኩር እንዳይመስልም ተውኩት…)
የሌላው እምነት (እውነት) ሲንቆላጰስ የእኛ እንደተብጠለጠለ አድርጎ ይሰማናል። በዚህም ሳናውቀው የተመላኪያችንን (የእውነታችንን) ባህርይ ሳንረዳ እንደ ደካማ እናሳየዋለን። እርሱ ግን ቤቱን ይጠብቃል። መንጋውንም ይንከባከባል። በአምሳሉ የፈጠረው ሁሉም መንጋው ነው ብለን እንናገራለን፡፡ – በሌላ ጎን። ሲመስለኝ ግን…. ማንም የፈለገውን ያድርግ። ማድረጉ ግን ለእግዚአብሄርና በእግዚአብሄር ይሆን ዘንድ መጠንቀቅ ነው ያለበት።
ሀገር የጋራ?!
የአገር የጋራነት ጋር ስንመጣም ከዚህ የተለየ ነገር አናይም፡፡ አንዳንዶች ከእኛ የተለየ የሚቆረቆሩልን፣… ለእድገታችን፣ …. ለመውጣት መግባታችን፣… ለመብላት መጠጣታችን፣ ….ለመጠለል መተኛታችን፣ ….ለማንበብ መስማታችን፣… ለመናገር መፃፋችን… ከእኛ በላይ የሚጨነቁ ይመስል፣ ጣልቃ ይገቡና፣ ‘እንወስንላችሁ’ ይሉናል።
በቀላሉ በሚነሱ የውይይት ሀሳቦችና በእንድ ወቅት ብልጭ ድርግም በሚሉ ጉዳዮች ዙሪያ እንኳን ብዙ እንደምንባባልና እርስ በርስ እንደምንተዛዘብ ዘወትር የምናየው ነገር ነው። ለገዛ አገራችን እየሰራን፣ ልክ ለኤርትራ (ወይም ለሌላ አገር) የሰራን ይመስል የሚያሳቅቁን የሚያሸማቅቁን ብዙ ናቸው። እንደ ምስኪን እናት ከአፋችን ቆጥበን የከፈልነውን (የተነጠቅነውን) የግብር ገንዘብ እንኳን ምን እንደተሰራበትና እንዴት እንደዋለ መጠየቅ እስከማንችል ድረስ አፋችን ይሸበባል፡፡ – አንዳንዴ በፍርሃት! አንዳንዴ ደግሞ በጉልበተኞች ጉልበት!
ምናልባት ጎበዞች፣ – ራሳቸውን ሆነው፣ ጫናውን ለመቋቋም ድፍረቱንና አቅሙን ያገኙ ሰዎችን ስናይም እናሸማቅቃቸዋለን። ‘መግባት ፈለግሽ እንዴ?’ … ‘በል ቃሊቲ ስመላለስ አልገኝም።’ ምናምን ምናምን …. መንግስትም ቢሆን ይሄንን ስሜት የሚጠላው አይመስለኝም። በጋዜጣ አቅም እንኳን አንድ ጋዜጣ በስርዓቱ መነበብ ሲጀምር ተሯሩጠው ይዘጉታል። – እንዳናውቅ?… ሳስተውልን – እንዳናልቅ?… ብቻ ግን ማንም ከውዳሴ በቀር የሚያጣጥል ነገር እንዲናገር አይፈለግም። በዚህም በሀሳብ ደረጃ እንበለው እንጂ የአገር የጋራነት በተግባር አለመስረፁን እንረዳለን።
ትምህርት የፋራ?!
ሌላው የትምህርት የፋራነት ነው። እዚህ ጋር ስለትምህርት ጥራት ጉዳይ አንስተን አንጥልም። ስለተማሪዎቹ ለትምህርት ተነሳሽነት አንተነትንም፡፡ ሆድ አደርነት ወይም ህሊና አክባሪነታቸውንም አንስተን አንነጋገርም። ሆኖም ግን ‘ተማርን’ የምንል (ቢያንስ ‘computer operate’ ማድረግ የምንችልበት እውቀት ያለን)፣ …ወይም በጣም አጥብበነው መፃፍና ማንበብ የምንችል ሰዎች ጋር ያለው የውይይት ባህል አሳፋሪ ነው። ‘መማር ምን ይሰራል?!’ እስኪያስብል ድረስ ያሸማቅቃል።
ሆድ ሆዳችንን እያየን ላይ ላዩን እንኖራለን፡፡ – ህሊናችንን እያፈንነው፡፡ ከእኛ ሀሳብ ልዩ የሆነ ነገር ሲነሳ ስድብ ይቀናናል። ሀሳብን በሀሳብ መቃወም በማንችልበት ቦታ ላይ መሰዳደብን እንመርጣለን። ሰውየውን እንዳንሰድበው… ትንሽ የቀድሞ ማክበራችን ሲቆነጥጠን፣ ወይም ደግሞ ‘ተሳዳቢነት ግብራችን አይደለም’ ብለን ስናስብ…. ከውይይቱ እናሸሸዋለን፡፡ (ውይይቱን እንዳይከታተል ለይተን እናግደዋለን፡፡) እስከ ዛሬ ብዙ ተዛዝበናል፡፡
እንኳን ስለራሳችንን… ስለምንወደው (ስለምናከብረው) ሰው ድክመት ሲነገር ብንሰማ ወዲያው ስሜታችን ይጎዳል፡፡ መቻቻል አርጧል፡፡ የውይይት ነገር ዜሮ ገብቷል። መደማመጥማ አይታሰብም፡፡ – ታዲያ መማሩ ምኑ ላይ ነው? ‘መማር የፋራ’…ብንለው በዚህ ደረጃ ቢበዛበት እንጂ ያንስበታል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የንባብ ባህላችን ሊነሳም ይችላል፡፡
ምናልባት ብዙዎቻችን የመጨረሻዋን መፅሀፍ ያነበብነው ት/ት ላይ እያለን…ለዚያውም ለት/ት አጋዥ የሆነን የመማሪያ መፅሀፍ። ከዚያ ከፍ ሲል ግን ብዙዎቻችን በ’ዴርቶጋዳ’ ተጠምቀናል። አንድ እርሱን ይዘን ምሁራዊነትን እናቀነቅናለን፡፡ አገራዊነትንና አዋቂነትን እንሰብካለን፡፡ የምሁራኑን ጎራ በአንድ መፅሀፍ ንባብ ለተቀላቀለ ምሁር መደማመጥና መከባበር የተራራ ያህል ከባድ ሲሆን እንመለከታለን፡፡ – ‘ትንሽ እውቀት ያጠፋል!’ እንዲሉ አበው ወእመው፡፡
ሁሉም መናገር ይፈልጋል። ሁሉም የርሱ እንደሚበልጥ ይሰማዋል፡፡ መልስ ባጣበት አጋጣሚም…ሲችል ይሳደባል! ሳይችል ደግሞ ጠያቂውን ይሳደባል፡፡ ያልገባው ነገር ላይ ማብራሪያ መጠየቅማ ታምር ነው፡፡ ሳት ብሎት ደግሞ ከቀድሞ – ‘አዲስ ነገር’ና ‘ፍትህ’… ከአሁን ደግሞ – ‘አዲስ ታይምስ’ እና ‘አዲስ ጉዳይ’ የቃረመማ… በቃ! በስማ በለው ከነጠቃቸው ጥራዞች እየመዘዘ፣ በብዥታ የሚያውቀውን በብዥታ ይተነትናል፡፡ – ባትንኩኝ ባይነት! እርሱ ምሁር በመሆኑ ራሱን ከጥቂት እውቀት ከተላቆጡ የስድብና ንቀት ግንብ አጥሮ… ቀድሞስ ማን ሊነካው ይቻለዋል? ማንስ ሊጋፋው ያይችላል?
— አሳፋሪ እውነት!