የልደት ወግ: 125 vs. . .

አንተዬ በማለዳው ልቤን አንድ ነገር ቢያስጨንቀው ጊዜ፥ ልጠይቅህ ረፋዱ ላይ ብቅ አልኩኝ። እንዲያው የትናንት የልደት ሻማ ገበያ እንዴት አዋለህ? — ድካሙ? ዋጋው?… ‘እድሜ ሲገፋ ከኬኩ ዋጋ ይልቅ የሻማው ዋጋ ነው የሚወደደው’ ምናምን የሚባል ወሬ ሰምቼ እኮ. . . “ወይኔ ወንድሜን እንዴት ሆኖ ይሆን?” ብዬ ስጨነቅ ነው ያደርኩት። እንዴት አረገህ ባ’ያሌው? አዪዪ. . . የኬኩን ነገርማ ትናንት ጨረስነው እኮ። ቢረክስስ በምን ጥርስ ሊበላ?– ጥርስ ድሮ ቀርቶ! –አያ!. . . እድሜ በልቶት! ሀሀሀ. . .

እድሜው ለገፋበትና እርጅና ለተጫነውስ፥ ሻማው ሲረክስ ነበረ ጥሩ፤ እንዲያ ሲሆን የደከመ እይታንም ያግዛል ምናምን ይላሉ። መቼስ የእኛ ነገር በ‘ይላሉ’ ነው።. . . እንጂማ ምኑን አይተነው? ምኑን አውቀነው?. . . ብለህ?! — ስታየን! ሰታውቀው!… ኸረ ገና ብላቴኖች ነን!…ብቻ ግን ሻማው ቢረክስ ከሞት ወዲያ ሌጋሲውን አጠናክሮ ለማስቀጠልም ጠቃሚ ግብአት የሚሆንይመስለኛል። ህልምና ራዕይስ ቢሆን በሻማ ይበልጥ ደምቆ ይታይ የለ?!…መሰለኝ! ሁሁሁ. . .

ዝም ብዬ ሳስበውግን. . .“ኧከሌ. . . ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል በፀሀይና በሻማ ሲሰራ ኖሮ”…ምናምን ተብሎ፥ በሻማ የመድመቅ ታሪኩ ታክሎ ወሬ ቢጀመር ሌላ ነው የሚሆነው። ስንቱን ሰምተህ የለህ… ‘እንትን ተደግፎ መፅሀፍ ሲያነብ… ኖሮ… ኖሮ… ሞተ’ ተብሎ ገድሉ ሲወራ…. ሌላው ቀርቶ ሻማና ምግባሩን መዝዘን እንኳን. . . “እንደ ሻማ ቀልጦ” ብለን ጨዋታ ብንጀምር የስንቱን አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪ ጆሮ እንስበው ይሆን? አዪ. . . አዲስ አበባ ስል ደግሞ ልደቷ ብልጭ አይልብኝ መሰለህ?! – (ነገርን ነገርም አይደል የሚያነሳው?) ሙት! ከሆኑስ አይቀር ከተማ መሆን ነው ኧረ። ሂሂሂ. . .
ከዚያም ልደትን ዓመት ሙሉ ማስከበር። በዘልማዳዊ ዘይቤም ይባላልሀል — “የወዳጃችንን ልደት ለየት የሚያደርገው ከአዲስ አበባ ልደት ጋር አብሮ መዋሉ ነው።”. . . ልክ “የዘንድሮውን አዲስ ዓመት ለየት የሚያደርገው ከሚሊንየሙ ጋር አብሮ በመዋሉ ነው።” እንዳሉት. . . ሃሃሃ. . . ውይ አዲስ አበባ፣ ውይ አራዳ ሆይ… (ወይ አላልንም ልብ አርግ!) እንዲያው ጭርጭስ ብላ፣ በአልሞትባይነት ስትታገል – ስታታግል፣ ስታስወጣ – ስታስገባ፣ ስትወድቅ – ስትነሳ፣ ስትጥል – ስታነሳ፣ ስትፈርስ – ስትገነባ. . . 125 ዓመቷን ደፈነች። አይዞን አንተም እኮ ደርሰህባታል፣ ብዙም አልቀረህ! ሃሃሃ. . .

እንዴት መታደል ነው ግን አንተዬ?… 125 ዓመት ሙሉ በግንባታ ላይ።125 ሙሉ መቀባባት። 125 ዓመት ሙሉ መኳኳል። 125 ዓመት ሙሉ መጊያጊያጥ። 125 ዓመት ሙሉ መሽሞንሞን፡፡ 125! — ግን እንዲያው በብላሽ! – አንዴም ሳያምርባት! በስሜት “ኧረ እሷን ባረገኝ’ እልና. . . ደግሞ ወዲያው ታሳዝነኛለች። ስታገባ፣ ስትፈታ በወጉ ለደህና ባል ሳትዳር እድሜዋ እብስ ማለቱ ፊቴ ይደቀንና አንጀቴን ትበላዋለች። ውይ ወላጅ እናቷ ጣይቱና አባቷ ምንሊክ የዛሬን ባላይዋት። መቼስ ከሄዱበት መንገድ መመለስ ቢፈቀድ “ውይ እንዳስቀመጥናት” ምናምን ሳይሉ ይቀሩ ብለህ? ኧረ ወዲያ ህንፃው መች ሆነና ቁምነገሩ?!… የእኔ መኳንንት – በዓሉ እኮ ሁሉን ጨርሶታል —-

ከጎራው ዘልቄ እስኪ ልነጋገር፣
ያለሰው ቢወዱት ምን ያደርጋል አገር፣
ህንፃው መች ሆነና የድንጋይ ክምር፣
መንገድ መች ሆነና የድንጋይ አጥር፣
ህንፃው ምን ቢረዝም ምን ቢፀዳ ቤቱ፣
መንገዱ ቢሰፋ ቢንጣለል አስፓልቱ፣
ሰው ሰው ካልሸተተ ምንድነው ውበቱ
የኔ ውብ ከተማ የኔ ውብ አገር፣
የሰው ለጅ ልብ ነው. . .
. . . የሌለው ዳርቻ፣ የሌለው ድንበር፡፡
/በዓሉ ግርማ/

ብቻ እልሃለሁ 125 ዓመቷን ፉት አድርጋ ለማክበር ደፋ ቀና ስትል፥ የኬኩን ጉዳይ በአንድ አንድ ድፎ ዳቦ ስትሸውደው የሻማው ነገር ግን ኪሷን ሲንጠው ነበር የከረመው አሉ።125 ሻማዎች? ዓመቱን ሙሉ –እግዚአብሄር ያሳይህ… በዚያ ላይ በየቦታው ነው የሚበራው።እኔስ ቀድሞ ያሰብኩት. . . ዓመቱን ሙሉ ከተማዋ ላይ መብራት በማብራት (የኤሌክትሪክ አገልግሎት ባለማቋረጥ)፣ ኗሪዎቿን በሙሉም ዓመቱን ሙሉ ኬኩ ቀርቶ ሽልጦ በማብላት ይከበርላታል ብዬ ነበር። አይጠብቁትን ነገር ጠብቄ ተገረምክብኝ? ውይ እሱስ. . . የማይሆን ጠይቆ ሲቀርስ ድርብ በደል ነው። ይሁና . . .

ትዝ ትልህ ዬል ባለፈው በጨዋታ. . . ‘ሄዋን ገጣሚ’ ምናምን ብለን የጫርናት? አዳምሄዋን፣ ያው በለው! ጠይቆ መከልከሉ ነው ጉዳዩ. . .

ዋ… ሄዋን መበደሏ፣ ሄዋን መታለሏ፣
የማይሆን ጠይቃ፣ አልችልም መባሏ፣
የማይችል ጠይቃ፣ አይሆንም መባሏ፣
ስድ ፅሁፍ ሆኖባት ሰንካለው እድሏ፣
ገጣ ስትፈልግ፣ ፍቺኝ ሲላት ባሏ፣

/ዮሐንስ ሞላ/

ውይ ሳልነግርህ?! ባለፈው ከወደ መርካቶ ምናለሽ ተራ እሳት ተነስቶ ወደ 40 ሱቆችን ቢያወድም ጊዜ የአካባቢው ቧልተኞች. . . ‘ለሸገሪና የሚለኮሱ አሮጌ ሻማዎች ስለሌሉን 125 ቤቶችን ለማቃጠል እቅድ ይዘን ገና 40 ገደማው ከመቃጠሉ የከተማዋ የእሳትና ድንገተኛ አደጋ መከላከል ሰራተኞች እንደ አሞራ መጥተው እሳቱን ተቆጣጥረው፣ ራዕያችንን አደናቀፉት’ ብለው ሲያስቁን ነበር።’ አሮጌ ተራም አይደል? ነገር ካላረጀ አገልግሎት ላይ አይውልም። ታዲያ ማን አሮጌ ሻማ አውጥቶ ይሸጥ ብለህ? – ማንም ካልሸጠስ፣ ማን ሊገዛ? የመብራቱ ብልጭ ድርግም መላ ካላገኘ ግን በቅርቡ ቆራሊያዎች — ‘ቆራሌዮ… አሮጌ ሻማ አሌዮ…’ ይሉ ይሆን?! ህህህ. . .

እውነት ግን. . . ይሄኔ ለሌላ ነገር (ለሌላ ዓላማ) ቢሆን እኮ የተቃጠለው ከርመው ነበር የሚመጡት። –ተዘንቦ! ተባርቆ! ነፋስ መጥቶ አመዱን ቡን ማድረግ ሲጀምር! ምቀኞች. . . ምናል ለእናት አዲስ አበባ ክብር እንኳን 125 ሺ ቤት ቢቃጠል? ደግሞ ለሚፈርሱ ቤቶች፤ ተቃጥለው እሳቱን መሞቅ ሳያተርፍ ይቀር ነበር ብለህ? ሄሄሄ. . . አንተዬ ‘ድንገተኛ አደጋ’ ስል ደግሞ እንትን ትዝ አይለኝ መሰለህ ‘አዲስ አበባ እኮ በዚህ እድሜዋ የግሏ መኪና ማንሻ – ክሬን – የላትም’ አሉ። አይገርምም?. . . (አይኔን ‘ባላየሁም’ ስብር አድርጌያለሁ፡፡)

ውይ ሳልነግርህ?! ባለፈው ከወደ መርካቶ ምናለሽ ተራ እሳት ተነስቶ ወደ 40 ሱቆችን ቢያወድም ጊዜ የአካባቢው ቧልተኞች. . . ‘ለሸገሪና የሚለኮሱ አሮጌ ሻማዎች ስለሌሉን 125 ቤቶችን ለማቃጠል እቅድ ይዘን ገና 40 ገደማው ከመቃጠሉ የከተማዋ የእሳትና ድንገተኛ አደጋ መከላከል ሰራተኞች እንደ አሞራ መጥተው እሳቱን ተቆጣጥረው፣ ራዕያችንን አደናቀፉት’ ብለው ሲያስቁን ነበር።’ አሮጌ ተራም አይደል? ነገር ካላረጀ አገልግሎት ላይ አይውልም። ታዲያ ማን አሮጌ ሻማ አውጥቶ ይሸጥ ብለህ? – ማንም ካልሸጠስ፣ ማን ሊገዛ? የመብራቱ ብልጭ ድርግም መላ ካላገኘ ግን በቅርቡ ቆራሊያዎች — ‘ቆራሌዮ… አሮጌ ሻማ አሌዮ…’ ይሉ ይሆን?! ህህህ. . .

እውነት ግን. . . ይሄኔ ለሌላ ነገር (ለሌላ ዓላማ) ቢሆን እኮ የተቃጠለው ከርመው ነበር የሚመጡት። –ተዘንቦ! ተባርቆ! ነፋስ መጥቶ አመዱን ቡን ማድረግ ሲጀምር! ምቀኞች. . . ምናል ለእናት አዲስ አበባ ክብር እንኳን 125 ሺ ቤት ቢቃጠል? ደግሞ ለሚፈርሱ ቤቶች፤ ተቃጥለው እሳቱን መሞቅ ሳያተርፍ ይቀር ነበር ብለህ? ሄሄሄ. . . አንተዬ ‘ድንገተኛ አደጋ’ ስል ደግሞ እንትን ትዝ አይለኝ መሰለህ ‘አዲስ አበባ እኮ በዚህ እድሜዋ የግሏ መኪና ማንሻ – ክሬን – የላትም’ አሉ። አይገርምም?. . . (አይኔን ‘ባላየሁም’ ስብር አድርጌያለሁ፡፡)

ግን ምናለ ከገቢያችን ቢቀር፣ ጠግበን ሳንበላ… ከጎረስናት፣ ካየናት ሁሉ 15 መቶኛውን ‘ተጨማሪ ጃዝገለመሌ ግብር’ ብለው ሲሰበስቡ እንዲህ የሚያስፈልጋትን ነገር ቢገዙላት? ለአንድ ከተማ የድንገተኛ አደጋ መከላከያ መኪና የላትም ማለት እኮ አንዲት የደረሰች ልጃገረድ ግልገል ሱሪ የላትም እንደማለት ነው፡፡ ይሄ ቢቀር እንኳን. . . በአንድ ጊዜ ሁለት ሶስት ቦታ እሳት ቢነሳ በተራ በተራ ነው የሚያጠፉት። በጥቂት መኪናዎች የአደጋ መከላከል ድርጅት አቋቁመው የጉድ ቀን ሲመጣ. . . ‘ቆይ የያዝኩትን ጨርሼ መጣሁ ቢሉህ ምን ይሰማ ይሆን?’ በዚያ ላይ መንገዶቹ ሁሉ በልማት ሰበብ ተቆፋፍረው መኪናስ እንዴት ሊገባ? ብቅ ብለው ሲመሱም አይተናል። ብቻ ግን የሸገር ሰው ‘ተለያየ’ ሲሉት በእንዲህ ያለ ጊዜ ህብረቱ ያስቀናል። በምራቅና በእንባውም ያጠፋዋል። – እግዚአብሔር ይጠብቅ እንጂ!

የቆሻሻውን ነገርስ አለማንሳት ነው የሚሻለው። ሰዉ በማህበር – በጥቃቅንና አነስተኛ – ተደራጅቶ በየቅያሱ የሚሸና እና ቆሻሻ የሚጥል ነው እኮ የሚመስልህ። እንዲያውም ባለፈው ጎጃም በረንዳ ዋናው አስፓልት ላይ 10 ጎረምሶች በአንድ ቱቦ አፍ ላይ ሲሸኑ አይቼ ጉድ ነው ያልኩት። ኸረ እንዲያውም ሽንቴን አስመጡት፡፡ እንክት 10! ቆጥሬያቸው ነበር ስልህ። የሰዉን ሁኔታ ስታየው ሽንት ቤት ሆነው ሽንታቸው ቢመጣባቸው ራሱ ውጪ ወጥተው የሚሸኑ ነው የሚመስልህ። በየመንገዱ እንደዚያ ነው። ሰዉ ቆሻሻ የትም ይጥላል። መንገዱ ሁሉ ይሸታል።– 13 months of sunshine እንዲሉ 13 months of ጉንፋን! ያሰኝሀል፡፡ ቅቅቅ. . .

ሽታው ሲያማርረኝ ምነው የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ በጠራና መንግስታቱ አዲስ አበባ መጥተው ባንቀላፉ ነው የሚያሰኘኝ። ፓ ያኔ እኮ አስባፓልት ሳይቀር ይታጠባል። ኧረ ምን እሱ ብቻ? የጎዳና ተዳዳሪም ይደበቃል። — ሰው እንደ ቆሻሻ። ኧረ እነሱስ በትንሽ በትልቁ ነው የሚደበቁት። ‘የምን ጎዳና ተዳዳሪ? አሉ ወይ?’ ኧረ. . . አንተ ደግሞ! ዛሬም ድረስ አሉ ስልህ። መኖሩንስ ይኑሩ። – ዋናው ቤት ቦታ ከታጣላቸው ጎዳናውም እኮ አንዱ ክፍሏ ነው።

ግን ቆሻሻ ለበሱ ብላ አፍራባቸው እንግዳ በመጣ ቁጥር መጋረጃ አበጅታ ከጀርባ ማስቀመጧ ሰርክ ያስተፋፍረናል እንጂ! – ግን ምናለ እንግዳ ሲመጣ አንድ አንድ ካናቴራ ብትገዛላቸው? ብትፈልግ እንግዶቹ ሲሄዱ መልሳ ተቀብላ ስቶር ታስቀምጠው፡፡ ደግሞ ምን… በኮንትሮባንድ ሰበብ በየጊዜው ከነቦንዳው ለሚቃጠል ካናቴራ. . .

አሁን አውንማ እናቶችም ወደ ጎዳናዎች ብቅ እያሉልህ ነው። – ነጠላ ለብሰው ሊለምኑ። ‘የሰው ፊት አያሳይህ’ ይሉት ምርቃት ትልቅነት የሚገባህ እነሱን ስታይ ነው። እንዲያው ሲያሳዝኑ። አይናይንህን ነው የሚያዩህ. . . አይናይንህን እያዩ አንጀት አንጀትህን ይበሉታል፡፡ ሲፈሩ ሲቸሩ በደንብ በማይከፈት አፍ ‘እርዳኝ ልጄ’ እያሉህ፡፡ እንደዚያ ዓይነት ሰው ይለምናል ብለህ ስለማታስብ ያስደነግጥሀል . . ግን ምን ታደርገዋለህ? – ከገባህ ሳንቲም መስጠት ነው።

ደግሞ ብዙዎቹ ስማቸው እንዳይጠፋ ፈርተው ከሰፈር ርቀው ነው የሚለምኑት። እና በታክሲ ስትመላለስም ያጋጥሙሀል። እንዲያው ጎንህ ቁጭ ያሉ ገራገር እናት ከወያላው ጋር ቀንስ አትቀንስ እንደሚከራከሩ እቅዳቸውን ቀድመው ያማክሩሃል። “ኧረ ወዲያ፣ ዝም ስንል አበዙት እኮ. . . ብር ከአርባ? ኧረ እኔስ ከ1 ብር በላይ አልሰጠውም። ታያለህ፡፡ መንግስት የሌለበት አገር አደረጉት እኮ፡፡” ምናምን ምናምን ይሉሀል. . .

አዲስ ሆኖባቸው አይደለም። ዋጋው ዛሬ ተወዶም አይደለም። ካንተ በላይ ያውቁታል፡፡ ለምደውታል። ስራ እንዳለበት ሰው ማልደው ወጥተው አምሽተው ይመለሳሉ። (ነገሩን ሳስበው፣ ለልጆቻቸው (ካሏቸው) እና ለጎረቤት “ስራ” ብለው ይሆን የሚወጡት? የሚል ጥያቄ ሁሌ ይጭርብኛል።) ለሆድ በሰው ፊት እሳቱ ተገርፈው የቃረሟትን ጨርሰው እንዳይከፍሏት አሳዝናቸው ነው። ከገባህ ትሞላላቸዋለህ። ከዚያም ትለምደዋለህ፡፡ ህምምም. . .

ግን ምናለ ‘ግብር’ ተብሎ ከገቢያችን የሚቆረጠውን ትተውት ቢያንስ ከአፋችን የቆጠብናትን 15 ፐርሰንት ግማሽ ያህሏን ምግብ ፍለጋ ጎዳና የወጡት ሰዎችን መቀለቢያ ቢያደርጉት? አዛውንቶቹን ቢጦሩበት? ተ.እ.ታ. ስንከፍል… ልክ መቶ ጉርሻ ስንጎርስ 15ቱን ለእነሱ እንዲያጎርሱልን ቀኝ እጃችንን እንደሰጠናቸው ቢያስቡት? እንዲያ ቢሆን ማን ፆሙን ያድር ነበር ጃል?!

ኧረ የሸዋስ ጉድ መች ተወርቶ ያልቅ ብለህ? ደግሞ ከዚህ ሁሉ ኮተቷ ጋር ‘ከዐለም መታየት ካለባችው ከተሞች አንዷ ሆና ተመረጠች’ ይሉሀል ካስመረጧት ትሩፋቶቿ መሀል ዋናው የካፌዎቿ ብዛት መሆኑን ሲነግርህ ደግሞ ሳቅ ያፍንሀል…. (ስለሱ ሌላ ጊዜ አጫውት ህ ይሆናል) የስዋ ነገር ግን እንዲያው ጉንጭ አልፋ ነው። እኔም በወሬ ሰቅዤ በልደትህ ማግስት አደረቅሁህ አይደል?

ውይ ሳልነግርህ ደግሞ፥ ትናንትና እናቴን “ዛሬ እኮ የዮሐንስ ልደት ነው።” ስላት ምን እንዳለች ታውቃለህ? “ዮሐንስ፣ ዮሐንስ… ዮሐንስ የዐይን አባትህ?” ሃሃሃ… ዐይኔ እስኪጠፋ ነው የሳቅኩት። እኔ የታወቅሁልህ ታዲያ? ግን አዲስ አበባ የዓይን አባት አላት እንዴ? ማለቴ መጎሳቆሏን የሚያይላት የዐይን አባት። መውጣት መግባቷን በስስት የሚመለከት የዐይን አባት? አዪዪ. . . የዐይን አባት ትርጉሙ እንደዚያም አይደል ለካ? ሃሃሃ. . .

በል አንተዬ ንግስቲቱ መጥተው online ሳይፈነክቱኝ፣ እንተንም “አንበሳ ሲያረጅ”ን ለንጉስ ሳላስተርትህ በፊት ከትናንት በስቲያ ወዳጄ ያደረሰችኝን የበዕውቀቱ ስዩም “ወይ አዲስ አበባ” ግጥም ልልቀቅብህና ልሰናበትህ፡፡ ኧ ማነው ዝንብ አንተ?. . . ዝንብማ ከቆሻሻዋ አዲስ አበባ ማደሪያ ቦታ አታጣም። ሃሃሃ… ይብላኝ ለእኔ – ለ40/60 ተስፈኛ. . . ሆሆሆ. . .

ወይ አዲስ አበባ. . .
ወይ እመ ፊንፊኔ. . .
ንቅሳትሽን ስታሳይኝ፣ ጠባሳሽን አያለሁ እኔ፡፡
የሴቶችሽ ውበት – የገባኦን ጸሀይ
ሲወጣ ነው እንጂ፤ ሲጠልቅ የማይታይ፡፡

በረንዳ ላይ ሆኜ
ቁስል ለበስ ለማኝ. . .
ማየቱ ቢቀፈኝ፣ አይኖቼን ጨፍኜ
ስንት አንገት፣ ስንት ጡት. . .
ስንት ዳሌ አለፈኝ?!

ወይ አዲስ አበባ . . .
ወይ እመ ፊንፊኔ. . .
ሴቶችሽ እርጉሞች ሀሳባቸው ክፉ፣
ቀስተ ደመና ላይ ቡትቶ እየጣፉ፣
ውበት አስጠየፉ፡፡

ወይ አዲስ አበባ. . .
ወይ እመ ፊንፊኔ፤
የብረት አበባ – የማይረግፍ ፔታሉ፣
የሚዝግ ነው እንጂ የማይደርቅ ቅጠሉ፤
የአዱኛ ሽራፊ፣  የመከራ ግንጥል፣
አልኖርብሽ ባ’ማን፤ አልለይሽ በጥል፤
በዕንባ በሳቅ መሀል እንደተቸነከርኩ
. . . አብሬሽ ልቀጥል፡፡

/በዕውቀቱ ስዩም/