የ “በሚመጣው ሰንበት” እንቆቅልሾች?!

ከቀኑ ትርምስ መለስ ስል. . . ባለፈው ከአንድ ወዳጄ ጋር ምሳ ለመብላት ወጥቼ የገዛሁትን፣ በወቅቱ ከወዳጄ ከሰሚር ጋር ሆነን በጨዋታ መሀል ገረፍ ገረፍ አድርጌው፣ በሙሉ ትኩረት ለማንበብ በመሻት ጥሩ ሙድ ሳመቻችለት የነበርኩትን የታገል ሰይፉን “በሚመጣው ሰንበት” የግጥም መድብል. . . ቆይቼ ፉት አደረግኩት። እንዲያው እንደ እሳት ማራገቢያ ከፊፍ ጥራዝ በመሆኑ ሲነበብ ጊዜም አይፈጅ።

ከመደበኛ የምስጋና ገፅ ቀጥሎ፥ ፀሀፊው መፅሀፉን ለ3 ልጆች መታሰቢያ አድርጓል። እንዲህ ብሎ. . .
– አባታቸው ለሚወዳቸው ልጆቹ ፍቅር የሚሰጥበትን ጊዜ ያጣ ሙሉ ዕድሜውን ለህዝብ /ለሃገር/ የሰጠ ነበር
– መታሰቢያነቱም ለእነሱ : – ለሰምሃል፣ ለማርዳ፣ እና ለሠናይ ይሁን።
ስማቸውን አበጥሮ ማወቁም ይገርማል። በእውነት ለመደበኛ ኗሪ የተጠቀሱት ሰዎች ማንነት የሚገለጠው ምናልባት መፅሀፉን ከጨረሰው በኋላ ነው። እግርጌ ደርሶ መለስ ቀለስ ካለ በኋላ። ሃሃሃ. . .

በእኔ አመለካከት፥ የተካተቱት 27 ግጥሞች እንደ ግጥም ደህና የሚባሉ ናቸው። የታገልን ግጥም አዋቂነት ይናገራሉ። አወራረዳቸው፣ ምጣኔያቸው፣ ዜማ አጠባበቃቸው፣ የሀሳባቸው ጥልቀትና የሚቀመጡበት መንገድ. . . ከሞላ ጎደል ጥሩ የሚባሉ ናቸው። ምርጥ ግጥም ለተጠማ (በተለይ የኤፍሬም ስዩምን ‘ፍቅር እዚህ ቦታ ፈገግ ብሎ ነበር’ን በጉጉት ጠብቆ የሁለት እዮሽ ለተበሳጨ – በጥበቃው ዳፋና፣ የጠበቀውን በማጣት. . . ) ምስኪን የጥበብ አፍቃሪ. . . ከቁጥራቸው ማነስ የተነሳ (የቁጥራቸው ማነስ ከዋጋው ጋር ባለመመጣጠኑ) ‘ጥም ይቆርጣሉ’ ባይባልም እንኳን፥ ከጥራታቸው የተነሳ አፍ ማርጠቢያ ይሆኑ ዘንድ አያንሱም። — ያው በገለልተኛነት ቢነበቡ ማለት ነው። ቅሉ እርሱ እንደዚያ እንዲሆን አላደረጋቸውም።

ይህም ቢሆን ግን ከነድክመቱ ነው። ሌላ ሌላ ሞያዊ እክሎች ቢቀሩ እንኳን እንዲያው ማንም አንባቢ በወፍ በረር የሚታዘባቸው ስነፅሁፋዊ ሳንካዎችም አሉት። ለምሳሌ: – ምንም ሳልወጣ ሳልወርድ፣ ይህን ታይፕ በማድረግበት ቅፅበት፣ (ለማሰብ ጊዜ ሳልወስድ)… ያነበብኩትን በማስታወስ ብቻ ትዝ ከሚሉኝ መሀል. . . — ባለቤትን ለመጠቆም ‘ህ’ መጠቀም ሲገባው፥ ብዙ ቦታ ላይ ‘ክ’ ይጠቀማል። እንኳን ያልሆነና — ለነገሩ ቢሆን እንዲህ አይሆንም ነበር — ታገል የእኛ ቤት ልጅ ቢሆን ኖሮ፣ በዚህ ምክንያት ከአባቴ ጋር ሁሌ ይጣሉ ነበር።

አባቴ ‘በላክ?’. . . ‘ጠጣክ?’. . . ‘መጣክ’. . . ሲባል በጣም ይበሳጫል። ተበሳጭቶም ዝም አይልም። መልሶ ያበሳጫል። ስህተቱ በተፈፀመበት ቅፅበት ሁሉ ተከታትሎ ያርማል። ሲያርም እንደ ሰባኪ — “‘በላህ?’. . . ‘ጠጣህ?’. . . ‘መጣህ?’. . . ነው የሚባለው።” ብሎ አይናገርም። . . . ይልቅስ ‘በላክ?’. . . ‘ጠጣክ?’. . . ‘መጣክ’. . . ብሎ የመጨረሻዋን “ክ” አጥብቆ ንግግሩን ይደግማል። በዚያም የነሩንም አካሄድ ያስታጉላልና ያበሳጫል። መበሳጨቱ የከፋውም ስህተቱን አይደግመውም። – ቢያንስ የእኔ አባት ፊት።

ታገል ግን ይላል – ‘ተስፋክ’. . . ‘ዋሸክ’. . . ‘በሸሸክ’. . . የፅሁፍ ስህተት ነው እንዳይባል መደጋገሙ ያስፎግራል።. . . የፆታ አለመጣጣምም ሌላው ስነ – ፅሁፋዊ ችግር ነው። ለምሳሌ “አቤቱ ፀጋን የተመላሽ” ይለናል ስለአገር በፃፈው ግጥሙ ላይ። እንግዲህ “አቤቱ” የምንለው ለወንድ ሲሆን “ፀጋን የተሞላሽ” ደግሞ ለሴት ነው። ይሄም ዓይነቱ የፆታ መጣረስም የሚጠበቅ አይደለም። የገጣሚነት መብቱን (poetic license) ሲጠቀምም ትርጉም ማዛባት በሚያስችል መልኩ ቸልተኝነትም ይታይበታል። ብቻ እንዲህና እንዲያ ዓይነት ስህተቶች ተበታትነው አሉ። ከነርሱ ጭምር ግን፣ ከአንድ ግጥም እስኪወጡ ድረስ የግጥሞቹን ደረጃ አያሳንሳቸውም።

ከዚያ ሌላ ደግሞ ለ27ቱም ግጥሞች ሳይታክት የግርጌ ማብራሪያ ይሰጣል። “ለ ኧከሌ” እያለ። አንዱም ላይ ተቀባይ ሳይጠቅስ ባለመቅረቱ “ለምን በ27 ብር ከሚሸጥልኝ በየአድራሻቸው አይልክላቸውም?” ያስብላል። (በማሳዘንና በማበሳጨት መሀል ሆኖ) ከዚያም ሌላ ደግሞ የተወሰኑት ግጥሞች ‘ተቀባዮች’ ማንነት መታወቅ. . . ለሁሉም ተቀባይ ከመሰየሙ ባሻገር፣ የግጥሙንም አቅጣጫ ከአንድ በዘለለ እንዳይታይ ሳንካ ይሆናል። ይህም የገጣሚውን የመረዳት ነፃነት ይገፍፈዋል። በነፃነት (እንደልቡ) የገጠመ ሰው ይሄን ነፃነት ገፈፋ ካለምንም ፋታ ማድረጉ ይበልጥ ያበሳጫል። ከዚያም በነፃነት መፃፍ አለመፃፉ ጥያቄ ያጭራል። ይልቅስ በሆድ ተፅህኖ ስር መፃፋቸው ይታያል።

እንግዲህ ይህ በእንዲህ እንዳለ ግጥሙን. . . ‘አገር አማን’ ብሎ ማንበብ የቀጠለ ሰው፥ ምርጥ የ27 ግጥሞች ስብስብ እያነበበ እንዳለ ይሰማውና በአቅራቢያው ላለ ለማንም “አንብቡት” ብሎ ሊጠቁም ይችላል። …በግማሽ ልብ ሆኖ። ገና መጨረሻው ሳይደርስ በተመለከተው. . . 27 ብቻ ናቸው። 1ግጥም በ1 ብር?! ተወደደ። 27ቱም ተቀባይ ግለሰቦች ተመድቦላቸዋል። የአጀብ መንኳተት ሊደብረው ይችላል። የግጥሞቹ ደህና መሆን ደግሞ ከአጀባው ጋር አልጣጣም ይለዋል። ማህበርን ወይም ፓርቲን አያወድሱም። ግለሰብን አያንቆላጵሱም። ታዲያ ለምን መደጎሻው በዛ? – ሊጠይቅ ይችላል። አሁንም የገጣሚው ሆድ ይታየዋል!

አንባቢው የእኔ ቢጤ (ነገር በሰልስቱ የሚገባው) ከሆነ ቆም ይልና ጥያቄውን ወደ ላይ ያወጣዋል። ሲገባ መታሰቢያ የተደረገላቸው ልጆች ትዝ ይሉታል. . . መለስ (ይላላልኝ። ሆሆሆ….) ብሎ ያነበውና ሊጠይቅ ይችላል።
– አባታቸው ማነው?
– እናታቸውስ? (ስሟ አለመጠቀሱን ልብ ይልና ሸፍጥ እንዳለ ያስባል። በልቡ – ‘ሆ . . . ኋላ እንዳያወቃቅሰው!. . . የለሁበትም!’ – ይልና ብቻውን ይስቃል። – ነገር እየበላ! 🙂 . . .)
– ለምን ከነአባታቸው ስም አልተጠቀሱም? ምናምን ምናምን. . .– ሌሎች ጥያቄዎች። ሌሎች ነገር መብላቶች። – ለዚያውም ችሎ ቆም ካለ ነው።

ለነገሩ ታገልን “ፍቅር” በሚለው የግጥም መድብሉ እና በአጭር ልብ ወለድ መፅሀፉ (ርእሱን ዘነጋሁት እንጂ. . . አፌ ላይ ነበር፣ ግን ጠፋኝ! ሃሃሃ. . . የምር ግን ያሁኑን መንግስትን ደህና አድርጎ የሚነቁር ነገር እንደነበረው አስታውሳለሁ። ወይም በጎረምሳ አዕምሮዬ እንደዚያ ነበር የገባኝ።. . . እስኪ የምታስታውሱት!) የሚያውቀው ሰው ግን የፈለገውንና ሊያነበው ወፍራም ቡና ከጥሩ ሙድ ጋር የሚገጥሙለትን ቀን የጠበቀ ሰው ግን የሆነ ነገር ፍለጋ ቆም ይል ዘንድ ግድ ነው። ቢያንስ ይሄን እያነበበ እነዚያ ይናፍቁታል። – እነዚያንም ቢሆን በተፅህኖ እንደፃፋቸው ፀሀፊው ራሱ ደጋግሞ ቢናገርም. . .

በቲቪ የሚያቀርባቸውን ቪዲኦዎች ግን እንኳን ዛሬ በልጅ አእምሮዬ እንኳን አልወዳቸውም። ጭራሽ ያስቁኝ ነበር። የሆነ የልጅ የጅል ነገር ሆነውብኝ። – ለራሴ ልጅ ሳለሁ። ሃሃሃ… ዝም ብሎ ቤት መምቻውን ድርግም፥ ድርግም እያደረገ ሲሄድ ያስቀኛል። እንዲያውም ቤት ለመምታት ብቻ የሚለቅማቸውን ቃላቶቹ በልጅ ቀልቤ እንኳን ነቄ እልበት ነበር።
ታ ታ ታ ታ ታ
ጄኪቻን ሲማታ
አምስቱን በተርታ
በእርግጫ፣ በቴስታ. . . ዓይነት ነገሮች።

ብቻ ግን እንደ እኔ ሙዴን ሰብስቤ እይዘውና የሚመጣውን ሰንበት ያጣብቀኛል ብሎ ያሰበ ሰው “በሚመጣው ሰንበት” ግጥሞች ወዲያው ተገፍተው 68ኛው ገፅ ላይ መጠናቀቃቸውን ሲረዳ ብሩ ያንገበግበዋል። (ከቻለ በ”ነይ ነይ ሰናድሬ” ዜማ “27 ብሬ፣ 27 ብሬ. . .” እያለ ያንጎራጉርና ሌላ መሳቂያ ያበጃል። ‘እዬዬም ሲደላ ነው’ እንዲሉ በራሱ ድምፅ ይስቃል። ሃሃሃ. . . ) በ27 ብሩ ምን ምን ሊያደርግ ይችል እንደነበር ያስባል። የግጥሞቹን ማለቅ የሚያረዳውም 69ኛው ገፅ ላይ ያለ ቀይ መብራት ነው። – “የግርጌ ምስጋና” ይላል።

(ቀን ከህይወት ባይሰማ ኖሮ) ገና ርዕሱን ሲመለከተው በእንግዳነት ግር ይለዋል። ግርታውን ውጦ ነገሩን ምርመራ ይዘልቃል. . . ለአፍታ መንገብገቡን ወደ ጎን እየገፋ። እንጂማ የጠፋበት ቀሪ ገንዘብ (ከ27 ብሩ ላይ) እንዳለ ተሰምቶት እርሱን ፍለጋ ወደኋላ ገፅ ያስስ ነበር። የገጣሚ ነገር — ምናልባት በሰምና ወርቅ ምናምን ጠፍሮ አስቀምጦት እንደሆነ። ሄሄሄ. . .

ከዚያ ተገጣሚው ይጠይቃል. . .
1. የእግርጌ ማስታወሻ ለምን አስፈለገ?
2. ለምን በረከት ስምኦን፣ ካፒቴን ሰለሞን ግዛው፣ ሻለቃ ኃይሌ ገ/ሥላሴ፣ አዋድ መሐመድ (አዲካ)፣ ኢንጂነር ተክለብርሀን አንባዬ (ልክ እዚህ ጋር ሲደርስ ኢንጂነር ተክለብርሀን ‘የአባቴ ስም አምባዬ ነው። ስሜን አጥፍተሀል’ ምናምን ብለው የሚወቅሱት ይመስለውና ፈገግ ይላል። ሄሄሄ…)፣ እስክንድር አሰፋ ከበደ (ሞኖ 2000)? ማመስገንስ መብቱ ነው። ግን ለምን የግርጌ ማስታወሻ ምናምን ማለት አስፈለገ? እንዲያውም ሲሆን “ልዩ ምስጋና” ምናምን መስጠት ነበር እንጂ። ብሎ በራሱ ፊት ገጣሚውን ከተመስጋኞቹ ጋር ለማቧቀስ ያብሰለስላል። ሃሃሃ. . . አሁን ሆዳምነቱ ይበልጥ ይታየዋል። በእነዚህ ሰዎች ታግዞ ከነበረ ምናለ ዋጋውን ቀነስ ቢያደርገው ኖሮ? የሚል ሌላ ጥያቄ ያነሳል።

ቀጥሎም ሊሆኑ ስለሚችሉ እንቆቅልሾች ያስባል. . .
1. መፅሀፉ ህዳር 11/2005 ይላል። ሆኖም ግን በተባለው ቀን መፅሀፉ ገበያ ላይ አልዋለም። ለምን የተለየ 1 ቀን ተጠቀሰ?

2. ቀን ሰምቶት አፍሯልና የምስጋናዎቹን ይዘት ችላ ቢለውም እንኳን. . . የግርጌ ምስጋና የተደረገላቸው ሰዎች በእውነትም የአብዛኞቹ ግጥሞች መፃፊያ ምክንያቶች ከነበሩ ስለምን የራስጌ ምስጋና አልተበረከተላቸውም? ከዚያም ለራሱ ለመመለስ ይሞክራል። – በግምት። ምናልባት ‘ከሁለት ያጣ ጎመን’ ሆኖ በአንባቢው እጠላለሁ። ብሎ ፈርቶ. . . ወይም አንባቢውን ከመግቢያው ላለመግፋት መጨረሻ ላይ ተቀምጦ መውጫ ይሁነው። ብሎ እንደሆነ ግራ በገባው መንፈስ ይገምታል። ወዲያው ነገሩ ያበሳጭቶት ያሳዝነውና፣ ባዶ ሆዱ ይታየውና ተመስጋኞቹ ‘ምናባህ ቆርጦህ እግርጌ ወስደህ አስቀመጥከን?’ ብለው በተጣሉት ብሎ ይመኛል። ሃሃሃ. . .

3. ከፊት ለፊት መታሰቢያ የተደረገላቸው ልጆች የቀድሞው ጠ/ሚው (አልሞቱም የምትሉ ውሸት ነው። ሞተዋል። ይልቅስ አፈሩን ገለባ ያርግላቸው በሉ። ይላል በልቡ። ሄሄሄ) ልጆች መሆናቸውን ይረዳና ይጠይቃል። እናታቸው ለምን አልተጠቀሱም? የአባታቸው ስምስ? ሆነ ተብሎ አንባቢን ላለማስደበር (ላለመግፋት) የተደረገ ነው? ከዚያ ደግሞ መላ ምቱን ይቀጥላል። ለብ ማለቱና አድር ባይ ላለመባል መፍራቱ ፍጥጥ ብሎ ይታየዋል።በዚያም ይበልጥ ይናደዳል። ባዶ ክፍል ውስጥ መፅሀፉን በሀይል ወርውሮ “ሆዳም” ብሎ ይሳደባል። ሆዳም ሰው እንደማይሰማ ዘንግቶት። 😉

4. የግጥሞቹ ይዘቶች ጋር ሲገባ ደግሞ ግጥሞቹ የተበረከቱት ለተለያዩ ሰዎች ነው። ለተለያዩ ማለት ስማቸው እንደ መብራት – በራስጌ እንደ ጫማም – በእግርጌ ከተቀመጡት ውጪ ላሉ ሰዎች። ይዘታቸውም ቢሆን በከፊል አቋም የያዙ እንዳልሆኑ ይረዳል። ከዚያም ነገር ማጋጋል ይፈልግና ይላሉ – እንዴት? ‘ሽልማት ምናምን’ እያለ ሲሸልል ከርሞ አንዳንድ ግጥም እንኳን አይፅፍላቸውም? በዚያውም እኮ ገፁ ይበዛለት ነበር። በዚያውም ይበልጥ ይወደድ ነበር። በዚያው ሆዱ ይዳጉስ ነበር። ሃሃሃ. . .

“እውል ብሎ ከሰው፣ አድር ብሎ ከሰው
ነብር ጉሮሮውን፣ ፍየል ገብቶ ላሰው።”ይላል የአገሬ ሰው ሆድ አደሮችን ሲታዘብ። እንቆቅልሹ ይቀጥላል። – ሀበሾች ነና።

ታገል በመፅሀፉ ውስጥ “በጨለማ የሚያበራው ትል” በሚል ርዕስ ያቀረባትን ግጥም ላካፍላችሁና ነገሬን ልቅጭ። በረከትነቷ //ሳያውቁ ለተደነቁ….ሳይሰሩ ለተከበሩ….እና ባይባረኩ ለሚመለኩ የዋሆች….// ይላል። ሳያውቀው ያረገው እንደሆን እንጃ፤ እኔ ግን ጅምላ ጨራሽ ሆና አገኘኋትና ለራሱም ጭምር አበረከትኳት። – በሰፈሩት ቁና መሰፈር እንዲህ ነው። ሃሃሃ…. ወይ ደግሞ ተንጋለው ቢያጎኑት ተመልሶ ካናት። ሄሄሄ…

በሺህ ዓይኖች የተከበብክ፣ ተከናንበህ የፅልመት ማቅ
እንደ ጠቢብ የተነበብክ፣ እንደ ብርሃን መልከ ደማቅ
ዓይን ሁሉ ከርቀት ያየህ፣ በራስህ ድምቀት የታጠርክ

“ብርሃን ነኝ!” ብትል ዋሸክ፣ ብርሀንማ ብትሆን ቅሉ፣
ጨለማው ጥሎ በሸሸክ፣ ካለህበት ስፍራ ሁሉ…
አንተ ግን ፅልመት ነው ተስፋክ፣ በጨለማ እሚያበራ ትል
ንጋታችን እስኪያጠፋ፣ አፈር አይንካኝ የምትል….

ክብርህ እንዴት ተከበረ? ጥሩ ተብለክ ስመ – ጥሩ
“መንገድ ነው” ብሎ ለደፈረ፣ ጉድጓዶች እንደነበሩ
“ጉድጓድ ነው” ብሎም ለቀረ፣ መንገዶች እንደተሰሩ
ካልገለፅክለት ገስግሰህ፣ ምን ሊፈይድ ጉንድሽ ጮራህ
ካናታቸው በላይ ነግሰህ፣ ከፍ ብለህ ስለበራህ. . .

ተመሳጥረህ ከፅልመቱ፣ ብትንጎማለል በግርማ፣
ብትብለጨለጭ በከንቱ፣ ውጧቸው ድቅድቅ ጨለማ፣
ገደል ገብተው ለሚሞቱ፣ ካልደረስክላቸውማ
ቅንጣት ብርሃን ካልተረፈህ፣ ከቁም ዳፍንት የሚያጠራ
ዋጋም የለህ ላይን ገዝፈን ሽቅብ ብትከንፍ እንዳሞራ. . . .

በጠፍ ጀምበር በቀን እጦት፣ ገደሉን ፅልመት ሸፍኖ፣
ጋራውን ጨለማ ውጦት፣ ያንተ ድምቀት ብቻ ገኖ፣
ከጋራው በላይ ደንድነህ፣ “ጋራው እኔ ነኝ” የምትል፣
አንተ እንደሆን ኢምንት ነህ፣ ራስህን የምትፈትል፣
ፅልመታችን ያገነነህ፣ በጨለማ ሚያበራ ትል. . .

/ታገል ሠይፉ/

One thought on “የ “በሚመጣው ሰንበት” እንቆቅልሾች?!”

  1. Pingback: Luminomania…

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s