የመጨረሻው ኑዛዜ

አድናን አሊ
e-mail: adnan2000free@yahoo.com

አሞራዎቹ ከበውናል። ነብሳችን ሳትወጣ ስጋችንን በጫጭቀው ሊበሉ አሰፍስፈዋል። ጉልበቶቻችን በጠኔ ዝለዋል፤ በረሃብ ደክመናል። ያረፈብንን ዝንብ እንኳ ‘እሽ’ ለማለት እጃችንን ማወናጨፍ አቅቶናል። ደክመናል። መንገዶቻችን ሁሉ ወደ አዘቅት ወስደውናል። አሁንስ የትኛው ተስፋ ቀረን? . . . . . . . . በአሞራዎቹ ከመሰልቀጥ በቀር።

እንዲህ ይሆናል ብለን እንዳንናገር አፋችን በሴራ ተተብትቦ ልሳን አልባ ሆነን ኖረናል። ከዝምታችን ብዛት አፋችን ላይ ሸረሪት ድሯን አድርታብናለች። በዚህች እንኳ የሞት ሽረት ትንቅንቅ ውስጥ ልሳናችን ተለጉሟል።
“ማን ያውጋ? . . . የነበረ
ማን ያርዳ? . . . የቀበረ” . . . ነበር ድሮ። የነበርነውም አላወራን፤ የቀበርነውም አላረዳን . . . . . ታዲያ ምን ይበጀን ይሆን? . . . . . ሞት በቀር። ‘በሞት አፋፍ ብሆን እንኳ ስለእውነት እመሰክራለሁ’ ያለው አንደበታችን ዛሬ ምን ዋጠው? ሳንናዘዝ አሞራዎቹ ሊቦጫጭቁን እኮ ነው። ለንሰሃ ጊዜ በሌለን ሰዓት . . . . . . ምነው ሐጥያታችን በኑዛዜ ቢቀልልን?

ማነህ? . . . . . . . . ፀሐፊ!
እስኪ ብዕርና ብራና ይዘህ የያንዳንዳችንን ጓዳ ጎድጓዳ እውነት ከትበህ አስቀረው። በአሞራዎቹ ከመበላታችን በፊት ኑዛዜያችንን አኑረው። በሞት አፋፍ ላይ ሆነው እውነት ይደብቃሉ ብለህ አትስጋ። ለመኖር ነው ሰው አድርባይ ውሸታም የሚሆነው።

አሁን ግን ደክመናል። በጠኔ፣ በረሃብ ደቀናል። እኛ የምንበላው ሳይኖረን የሰማይ አሞራዎች በኛ ስጋ ሊጠግቡ ነው። ይህ ነው እንግዲህ የሕይወት ሚዛን! Survival of the fittest!

ዓለም እኛን ከመመገብ ይልቅ የሰማይ አሞራዎቹን እና ጥንብአንሳዎቹን ለመመገብ መርጧል። “This Is Natural Selection!” እኛ አቅም አጥተናል። አቅም ያለው የኛን ስጋ ይበላል።

የወረወርናቸው ቀስቶች መልሰው እኛኑ ይወጉናል። የደማችን ዥረት ሆዳቸውን አሳብጧል፤ ልጆቻቸው እንደ ቅልብ ጫንቃቸው ወፍሯል። ይህ የዚች ዓለም ሚዛን ነው!

አሁን ደከመን የመጨረሻው እስትንፋሳችንን እየጠበቅን ነው። አሞራዎቹ ወደ መሬት ማዘቅዘቅ ጀምረዋል። ከቀይ መስቀል እርዳታ ቀድመው ይደርሱልናል።

አንተ ፀሐፊ!
ወረቀቶችህ በሌሉ የፍቅር ቃላት ውዳሴ እና በቅንዝረኞች ፈንጠዝያ ከሚሞሉ . . . ና . . . የኛን የሰቆቃ ኑዛዜያችንን ፃፍበት። ና! . . . አሞራዎቹ ስጋችንን እየቦጨቁ ሲሄዱ በካሜራህ ቅረጸን። የውዳቂ መጽሔትህ የፊት ሽፋን ባይሆን . . . ገጽ ማሟያ ወሬ ይሆንሃል። ሞዴሎቻችን በተጥለቀለቁበት የፊት ሽፋን ገጽ ጀርባ የኛን የጠኔ ክርፋት አትምበት።

እንዲህ ሆነው ነው የሞቱት ብለህ ዘግበን። አርሰው፣ ዘርተው፣ አጭደው መብላት አቅቷቸው በረሃብ ሞቱ ብለህ ዘግበን። አንተን ለሚሰሙ ጥራዝ ነጠቅ ሊቆች።

ካሜራዎች እያንዳንዷን ቅጽበት ያንሱ፤ እንዳንዷውን ቅጽበት ይቅረጹ።

አሁንስ ምን ቀረን? . . . ከገማው ስጋችን፤ ከከረፋው ማንነታችን በቀር። እንደ እባብ አፈር ልሶ መነሳት አልተማርን። የሌለንን ዛሬ ከየት እናምጣ?

አሞራዎቹም የሳር ጎጆዋችን ክዳን ላይ አርፈዋል። እኛን ለመቦጨቅ አሰፍስፈዋል። ከመሬት ተንጋለን ሰማዩን እናማትራለን። እግዜር ከሰማይ ወርዶ እንዲያስጥለን እንማጸናለን። ተማጽኖዋችን በበረታ ቁጥር አሞራዎቹም ወደኛ ይቀርባሉ።

ማናችሁ? . . . እናንት ፀሓፊያን!!!
የሕብረተሰቡ ችግር የኛ ችግር ነው ትሉ አልነበር? በስራዎቻችን ሕብረተሰቡን እናንፀባርቃለን ትሉ አልነበር? . . . ምነው ታዲያ የኛ ችግር ችግራችሁ አልሆነም?

************************************

ተቀበል አዝማሪ
ተቀበል ግጥሜን
ና ወዲህ ጠጋ በል

. . . . . . . . ‘ካንበሳ መንጋጋ ስጋ የሚነጥቁ’

ብለህ አንጎራጉር
አንት አዝማሪ ዘምር
ጮክ አርገው ድምጽህን
ከጫፍ ጫፍ ይሰማ
ንጠቅ ከኔ ዜማ
ውሰድ የኔን ስንኝ
ድገመው እንደ ሞኝ

. . . . . . . . ‘ካንበሳ መንጋጋ ስጋ የሚነጥቁ’

ድገመው አንድ ጊዜ
ማሲንቆህ ሳይበቃ
የፈዘዘች ነፍሴ፣ ባንተ ጩኸት ትንቃ።

ተቀበለኝ ግጥም
እንደማር እንደጠጅ
እንደወይን የሚጥም
ተቀበለኝ ግጥም
አንጎራጉር ዜማ
አለም ሁሉ ይስማ

. . . . . . . . ‘ካንበሳ መንጋጋ ስጋ የነጠቁ’

ብለህ አሳምረው
አንተ ደሃ አዝማሪ፣ የምጮኽ ላንተው ነው።

‘ካንበሳ መንጋጋ ስጋ የነጠቁ
ከረሃብ ጋር ታግለው ተረተው ወደቁ
በአሞራዎቹ፣ በጥንብ አንሳዎቹ፣ ተበልተው አለቁ’

 

. . . . . . . . ‘ካንበሳ መንጋጋ ስጋ የሚነጥቁ’

ብለህ ዘምርልኝ
አንተ ቂል አንተ ሞኝ

* * *

ና አንተ ፀሐፊ. . .

አዝማሪው ከብዶታል
የኔን ስንኝ ማለት
እስኪ በብራናህ
ፃፈው የኔን ውድቀት

. . . . . . . . ‘ከተራሮቹ ጫፍ እስከ ሸለቆዎቹ
. . . . . . . . ምንም ማይበግረው፣ ጠንካራ ክንዶቹ
. . . . . . . . ዛሬ ከመንገድ ዳር
. . . . . . . . ወድቆ ይማፀናል
. . . . . . . . ወደ ሰማይ ያያል . . .’

ፃፈው የኔን ውድቀት
ሳትጨምር እብለት

አዝማሪው ደክሞታል
አዝማሪው ከብዶታል
አንተ ትጉህ ሰው ነህ
ፃፍልኝ እባክህ
እባክህ . . . እባክህ
ከመሞቴ በፊት
ክተብ ይሄን እውነት

****************************

አሁን አሞራዎቹም ወርደዋል። የሞት ሽረት ትግል ሊጀመር ነው። አሞራዎቹ ከኛ ስጋ የሚያገኙ መስሏቸዋል፤ ካገጠጡ አጥንቶቻችን በቀር። እስትንፋሳችን በቀጭኗ መውጫ ተወጥራለች። ቁስሎቻችን ላይ ዝንቦች ካረፉ ሰንብተዋል። እነሱን ለማባረር ክንዳችን ዝሏል።
አሁንስ ምን ቀረን? . . . ታፋችን ሲዘነጠል ከማየት በቀር። በመንቁራቸው የዓይኖቻችንን ብሌን ሲያፈርጡ ከምንሰማው የፃር ድምጽ በቀር።

ምነው ቶሎ ጀምረው በገላገሉን። የሞት መንገድ እንዲህ ይርቃል እንዴ? . . . ለምን ስቃያችንን ያራዝሙታል? . . . ለምን በድምፆቻቸው ያሸብሩናል?
ድምጽ!
ድምጽ!!
ድምጽ!!!
የአምቡላንስ ድምጽ!
ማነው ቀድሞ የሚደርስልን???

“ላነስተስልም! . . . ላነስተስልም! . . . ላነስተስልም!”

One thought on “የመጨረሻው ኑዛዜ”

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s