ግን ምን ያጣድፈናል?

አንዳንዴ ነፍሴ ሽማግሌ ነገር ትሆንብኛለች። በዚህም ራሴን እታዘበውና ብቻዬን እስቃለሁ። በቀላሉ ሊማርከው ይችላል፣. . . አጓጉቶት ይመርጠዋል. . . ተብሎ የሚታሰብ ነገር ልክ ደጃፌ ሲደርስ ራሱን በዜሮ ያባዛል — አንዳንድ ጊዜ በልማድ (tradition). . . — አንዳንዴ ደግሞ እንዲያው በደመነፍስ (instintct)። ጎጂ ያልሆነ ልማድ ካለምንም አሳማኝ ነገር ሊቀየር ሲል (ወይም ሲቀየር) ይደብረኛል፤. . . ደመነፍሴን ደግሞ ህይወቴ ላይ እንዲወስንልኝ ፊትና እድል ባልሰጠውም በደንብ አምነዋለሁ። ችላ ስለውም በሙሉ ልቤ አይደለም።

ዘመናዊ እውቀትና የኑሮ ወከባ፣ እንዲሁም ትእቢትና ትምክህት ባይጋርዱንብ ኖሮ ደመነፍስ የሚነግረን ብዙ ነገር እንዳለ አስባለሁ። አንዳንዴም ደመነፍሳችን ጮሆብን. . . ሳንሰማው ቀርተን፣ የጠረጠርነው (ግን ደግሞ ችላ ያልነው) ነገር ሲደርስ — ‘ውይ! ታውቆኝ ነበረ. . . ፊቴ ላይ ነበር. . . እያሰብኩት. . .’ ምናምን ብለን የፀፀት ሀረጋትን እንደረድራለን። የራሳችንን ማሰላሰልና ማወቅ በማይጠይቁ ነገሮች ላይ ግን ደመነፍስን ማዳመጥ ሊያተርፍ የሚችል ነገር ይመስለኛል። በርግጥ የሚያከስርበት ጊዜ ሊኖርም ይችላል። – ማን አይቶት፥ ማን እቅጩን ያውቃል?

በአዲስ መስመር ወደ ጥድፊያው ስንመለስ ደግሞ . . . ቦታ ቀይሮ ፈታ ለማለት ረዥም መንገድ 801589መሄድ በጣም ያስደስተኛል። የጉዞ ጣጣዬን ቶሎ ጨርሼ፣ ካሰብኩበት ቦታ በጊዜ መድረሱንና እንዳሰብኩት መዝናናቱን ባልጠላውም፣ የመንገዱ መርዘምና መጎተት ብዙም አያስጠላኝም። ወይ ደግሞ ለምጄው ተስማምቶኛል። እንደውም ደስ ይለኛል። እንደ ጥሩ ትርፍ. . . ከመኪና መንቀራፈፍ ጋር በተያያዘ መንገድ ላይ የማንበብ ልምድ አዳብሬያለሁ። ብዙ ጊዜም መሄዴን ሳላውቀው ነው የምደርሰው።

በፍፁም ትኩረት፣ ርጋታና አለመሰልቸት ውስጥ ሆኜ ካነበብኩባቸው ቦታዎች መካከል የክ/አገር አውቶቢሶች ዋናዎቹ ናቸው። የምሄደው በአዲስ መንገድ ከሆነ ደግሞ በመስኮት በክል ግራ ቀኙን እያየሁ ተፈጥሮን አደንቃለሁ። በሀሳብ እነጉዳለሁ። ምናምን ምናምን . . . ካለምርጫና ካለማቋረጥ ማንበብ መቻሉ ቀድሞም ለነበረኝ የጉዞ ፍቅር ተጨማሪ ቅመም ሆኖልኛል። ስለሆነም ረጅም መንገድ ስጓዝ እንደ ሚኒባስ ያሉ ፈጣን የሚባሉ የትራንስፖርት አማራጮችን ለመጠቀም አላስብም።

አያዝናኑኝም። መፅሀፍት አያስገልጡኝም። ፊት ለፊቱን እንጂ ግራ ቀኙን በመስኮት እንዳይminibus-accident1 እድል አይሰጡኝም። ነፍሴን ካለአግባብ ያዋክቧታል። በጭንቀትና በስጋት ወጥረው ካለ ቅጥ ያርገበግቧታል። ያንገበግቧታል። መጨረሻዋ ለማይታወቅ እርሷ. . . መጨረሻዋን ለቅፅበት ያሳይዋታል። በፈጣሪ ስልጣን ገብተው፥ ወስደው ይመልሷታል። ካለልቧ ዥዋዥዌ ያጫውቷታል። ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ የብዙ ነፍሳት መጨረሻ በሚኒባስ ሲወሰን ተመልክቻለሁ። ‘ኧከሌ/ኧከሊት. . .’ ብዬ በስምና በግብር በቅርብ የማውቃቸው ሰዎች በሚኒባስ ተሰናብተዋል። ቅዳሜ ለመገናኘት ቀጠሮ የነበረኝ ሰው በዋዜማው አርብ በሚኒባስ ተፈፅሞ በጣም አዝኜ አውቃለሁ። በየቦታውም ብዙ ዓይነት ታሪክ አለ። ብዙ ሰው እንደወጣ መንገድ ላይ ቀርቷል። ቶሎ ለመድረስ ሲጣደፍ በአጣዳፊው ተሰናብቷል። – በሚኒባስ!

ብቻ ግን ረጅም መንገድ በሚኒባስ መጓዝ አልፈልግም። አልጓዝም። ከሚኒባስ ውጭ አማራጭ መጓጓዣ በማይገኝበት ቦታ ካልሆነ በቀር አማራጭም አላደርገውም። ይልቁንስ በጣም ትልቁን አውቶብስ ነው የምመርጠው። ጉዞው በህብረት ከሌሎች ወዳጆች ጋር በሚሆንበት ጊዜ ወይ ደግሞ ስለአካሄዴ ተናግሬ ሚኒባስ እንድጠቀም ሲያግባቡኝ አልሰማቸውም። እሞግታቸዋለሁ። ሲስማሙ – አብረን እየተጫወትን በትልቋ እንሄዳለን። ላይ ወርጄ ታች ወጥቼ በሀሳቤ አልስማማ ሲሉኝ ደግሞ እነሱም – በፈጣኗ፤ እኔም – በተምዘግዛጊዋ እንለያያለን። – ሰላም ከደረስን ለመገናኘት ተቀጣጥረን።

የምቀርበው ሰው መንገድ እንደሚሄድ ሳውቅም፥ የወጪ ስንቄ – ‘በናትህ/ሽ በሚኒባስ ethiopian-busrides09እንዳትሄድ/ጂ’ የምትል የጭንቀት ሀረግ ናት። ብዙዎች ይገርማቸዋል። ‘ነፍስህን አንተ ተብቀሃት አይሆንም። በትልቅ መኪናም ሄደህ አደጋ ካለ አይቀርልህም። ከቀንህ አታልፍም’ ምናምን ምናምን. . .። አይገባኝም። የእኔ ሃሳብ አደጋ ማስቀረት ሳይሆን አለመሳቀቅ ነው። ሞትማ ምናባቱ! በጉርሻ ትንታም ሲቀራርብ አይተን እናውቃለን። ቀኑ በተመደበበት ህይወት ነው የምመላለሰው ብዬ ግን አላስብም።

ረጅም ርቀት በሚኒባስ በተጓዝኩባቸው አምስት በማይሞሉ ጊዜያት ውስጥ ሳስታውሰው (አንዳንዴም በጉዞው መሀል) እስቅበት ዘንድ ራሴን የታዘብኩበት ነገር አለ። መኪናው ፍጥነቱን ሲጨምር መንፈሳዊነቴ ይጨምራል። አላግባብ ፀሎተኛ እሆናለሁ። ነጠላ ማንጠላፋትና የፀሎት መዝገብ መግለጥ ያምረኛል። (ያልያዝኩትን) የማውቀውን ፀሎት ሁሉ እደረድራለሁ። በተማፅኖ እቀባጥራለሁ። “የጭንቀት ቀን ሳይመጣ በጉብዝና ወራት ፈጣሪህን አስብ።” (መፅሀፈ መክብብ 12፥1) የምትለዋ ትምህርት ነገርም ይበልጥ ይገለጥልኛል። በዚያም እስቃለሁ። በሰቀቀን። – እያነቡ እስክስታ!

ከዚህ በፊት ‘ሰላም መጣችሁ እንጂ ቶሎ መጣችሁ የሚለን የለምና ቀስ ብለን እንንዳ።’ የምትል የረሳኋትን ምንጭ ጠቅሶ የፃፋት መልእክት አንድ ወዳጄ ፅፏት አንብቤ ልቤ ሰርፃ ነበር። እናም ዛሬ ልደግማት ወደድኩ። — ‘ሰላም መጣችሁ እንጂ ቶሎ መጣችሁ የሚለን የለ’! ምን ያጣድፈናል? ታላቅ ወንድሜ ደግሞ ‘በአላስፈላጊ ጥድፊያ ውስጥ ሆነንና ቶሎ ለመድረስ ፍጥነት ጨምረን ተጉዘን የምናተርፋቸው ጊዜያት ተመዝግበው ቢደመሩ በዓመት አንድ ቀንም አይሞሉም። በዓመት አንድ ቀን ላላተርፍ አልሯሯጥም።’ ይላል።

ገበያን የሚያሰፋው የተጠቃሚ ፍላጎት ሁኔታ ነውና ተረጋግተን ሄደን በሰላም ለመግባት (ለመድረስ) በመፈለግ አደጋን እንቀንስ። ለፍላጎታችን የሚሆነውን መኪና መምረጥ ስንጀምር መጓጓዣዎቹ ፍላጎታችንን ለማርካትና ገበያ ለማግኘት በምንፈልገው መስመር ይገቡልናል። ‘እንደወጣ ቀረ’ ከመባል ያድነን።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s