ዮሐንስ ረቡዕ ረቡዕ ጫት አይቅምም።
— ሀሙስ ሀሙስም….
— አርብ አርብም….
— ቅዳሜ ቅዳሜም…
— እሁድ እሁድም…
— ሰኞ ሰኞም…
— ማክሰኞ ማክሰኞም…!! ይህን ብለን ጨዋታችንን እንቀጥላለን. . .
* * *
ድሮ (ወግ ነው መቼስ ዮሐንስም ድሮ አለው!) ሲባል ይሰማ ነበር… አሁን ግን ተምታቶበት በደንብ አይለየውም። ወይም ያኔ ሲነግሩት በደንብ አልሰማቸውም ነበር። ወይ ደ’ሞ በደንብ አልነገሩትም. . . (ምናልባት ነጋሪዎቹ ቃሚ ከነበሩ፥ ለመቃም ሲጣደፉ፣. . . ሊፈርሹ ሲዋከቡ. . . ወይም ደግሞ አጣርተው ስለማያውቁት. . . ወሬውን አጥርተው አልነገሩትም። ወይ ደግሞ በምርቃና አዛብተውታል። ወይ ደግሞ. . . ) የራሳቸው ጉዳይ! ብቻ ግን እንዲህ ነበር ያሉት. . .
‘ያልቃመ ተጠቀመ፣
የቃመ ተለቀመ?!’
ወይም. . .
‘የቃመ ተጠቀመ፣
ያልቃመ ተለቀመ?!’
እነሆ ዮሐንስ አለመለቀሙን ግን እናውቃለን። ቢቅም ኖሮ ግን ማን ነው የሚለቅመው?… ማለቴ ማን ነበር የሚለቅመው? ዱካክ በወፍ አምሳል? (ስለ ዱካክማ መዓት ያውቃል።) የምሩን፥ ይህቺ ለቀማ ግን ፌክ ሳትሆን አትቀርም። ይልቅስ የሆነ ነገር ትዝ አለው. . .
* * *
መርካቶ . . . መሀል ከተማ. . . እዛ የማይሸጥ የለ መቼስ. . .! ከእለታት በአንዱ ቀን. . .
ከሚሸጡ እቃዎች፣ አልባሳት፣ ሸቀጦች፣. . . መሀል ጥቅሶች ነበሩ። የሚሸጡ ጥቅሶች። የድሀን ቤት ማስዋቢያ። ቀዳዳን ሸፍነው እግረ መንገዳቸውን የሚነበቡ። ከምሁር ተርታ የሚያስሰልፉ። በተስፋ የሚሞሉ። ከሀይማኖታዊ እስከ ፆታዊ. . . –ልክ እንደ facebook status update የሚመስሉ ጥቅሶች. . . ጥቅማቸው የሁለት እዮሽ ነው። የልብን ቀዳዳ ባይደፍኑም ማባበል። እንዲሁም የቤት ግድግዳ ቡድርስ መሸፈን። (ብርድ ለመከላከል? ለዐይን ለመሙላት?)
ከ “የሚረዳኝ የለምና ከእኔ አትራቅ” (መዝሙረ ዳዊት 22፥11) እስከ. . . “አድርገህልኛልና ለዘለዓለም አመሰግንሀለሁ።” (መዝሙረ ዳዊት 52:9) ከ “rose is rose, sky is blue,/….and I love you!” እስከ “ሮዝ አበባ ላይ ታምሜ ተኝቼ/….ምናምን ምናምን….” በቀለም (በማርከር) ያበዱ ጥቅሶች። እነሱን የሚያጅቡ ምስሎች ተለጥፎባቸው። ሁሉም ነገር በእጅ ነበር የሚሰራው….
አቤት የጥቅሱ ገበያ: ከመጠቀሚያ. . . እስከ መጠባበቂያ. . . ጥቅስ ድረስ የተሟላለት። ከችግር ቀን ስሞታ (አቤቱታ) እስከ ምቾት ቀን የእፎይታ ድምፅ። የችግሩ — በችግር ቀን፣ የሚበላ ሲጠፋ፣ ወዳጅ ፊት ሲነሳ፣ ጎረቤት ደጁን ሲዘጋ፣ ፀሀይ በቤቱ ስትጠልቅ ይለጠፋል። (ወይ ደግሞ እንዲያ የሆነ ሰው ይገዛዋል። እንዲያ ነኝ ብሎ ያመነ። ራሱን የመዘነ ሰው – ደሀ ሰው. . . ) በቦታዋ ጥቅሷ ቦግ ትላለች። — ችጋር ወለድ ፀሎት፣ ልመና፣ ተስፋ፣ እምነት. . . ከዚያ ሁሉ በላይ ደሞ የቤትን ቀዳዳ የመድፈን ተልዕኮ የሰነቀ!
የእፎይታ ድምፃም ጥቅሱ፥ በተድላ ቀን ይወጣና ይለጠፋል። በአንፃራዊ ተድላ። በአንፃራዊ ጥጋብ. . . በአንፃራዊ ምቾት. . .ፀሀይ በቤቱ ብቅ ስትል። ኩራዞች ላምባ ሲሞሉ። ምድጃው እንጨት ሲነድበት። (ምናምን ውስጡ ያለው ድስት ሊጣድበት) ድስት ሲታጠብ. . . (ወይም እንዲያ ሆነልኝ ብሎ ያሰበ ይገዛዋል።) — ምስጋና፣ እፎይታ፣ እርካታ. . . ከዚያ ሁሉ በላይ ደግሞ ማንቆላለጭ! ማናፋት! ማቅራራት! (ሰው እግር ጥሎት ቤት ዘው ሲል ጥቅሱ ዘው እንዲልበትና እንዲማረር።)
ገጣሚዎቻቸው የማይታወቁ ግጥሞች። ከ2 እስከ 4 መስመር የሚሆኑ ድርድር መስመሮች። ደሀው፣ ያልተማረው፣ ጎረምሳው. . . እንደሙላቱና እንደጉድለቱ የሚገዛቸው። ከገዙበት ስሜት ውጭ ሆነው (ትንሽ ሲሻሻሉ) ቢያነቧቸው በሳቅ ባያፈርሱ እንኳን በፈገግታ ሊያፈኩ የሚችሉ ጥቅሶች….ግጥሞች….– ከዚያ ባሻገር ግን ብርድ የሚከላከሉ። የቤት ቀዳዳን የሚደፍኑ። (የኑሮው ቢቀር)
ሻጩ (የነቃው ነጋዴ) ‘እልል በል ሀበሻ….’ እያለ ለተራበ ሀበሻ ይሸጣል። መንገደኛውን ለመማረክም ጮክ እያለ በተራ በተራ እያነሳ ያነባቸዋል። ሀበሻውም በልቡ ‘እልል’ እያለ ይከባል. . . ገበያውን! የጥቅሱን ጥብስ ገበያ!
አንደኛው እንዲህ ይነበባል. . .
“በጠፍጣፋ ድንጋይ ከተዘጋ በሩ፣
እናት አትገኝም፣ እንደ ወፍ ቢበሩ።”
ሞያዊ ትንታኔ አያሻውም። መልእክቱ ደርሷል። ድንጋይ…በር…ምናምን… ምንም እንደማይሰሩ፣ በሩ ተከፈተ ተዘጋ ምንም እንደማይረባው….. ገጣሚውም፣ ሻጩም ገዢውም ግጥም አርገው ያውቁታል። ግን ግድ የላቸውም። (ለነገሩ ማን ይመረምረውና ቀድሞ?) በቃ እናት ወርቅ ናት ነው መልእክቱ። ናት! ናት! ናት!
ብዙ ሰው ለሚያምነውና ለሚያውቀው ነገር ማረጋገጫ ደስ ይለዋል። ምናልባት ለዚያ ይሆናል ግብይቱ—ማረጋገጫ መፈለግና፣ ማረጋገጫ መስጠት። ይሄም ማረጋገጫ ነው።…. ግን ደግሞ ንግድ! በምስኪን ኗሪ ስስ ጎን የታለመ ትርፍ! –ከዚያ ሁሉ በላይ ለሰሪውስራ!! ‘ስራ ለሰሪው፣ እሾ ላጣሪው!’ ለተሰሪው ደግሞ የግድግዳን ሽንቁር መድፈኛ ወሽመጥ! ግድግዳን ማሳመሪያ ቀለም!
ሌላው እንዲህ ይቀጥላል. . .
“አንድ ፍየል ነበር እንደ እኔ የከፋው፣
የሆዴን ብነግረው፣ ያ’ፉን ቅጠል ተፋው።”
ፍየሉ ይቅም ነበር? ፍየሉ ይሰማል? እርሱ ሞኝ ነው ለፍየል የሆዱን የሚነግረው? ምናምን ምናምን….ብዙ መጠየቅ ይቻላል። ግን ማንም አይጠይቅም። ዋናው መልእክቱ ነው። — ‘በሆዴ ብዙ አለ….ፍቶኛል’ ነው መልእክቱ!
ይቀጥላል. . .
“ሁለት ውሾች አሉኝ የማሳድጋቸው፣
ሰምቶ መቻልና ችሎ ማለፍ ናቸው።”
እዚህም መልእክቱ ደርሷል። ስለችሎ ማለፍና ስለሰምቶ መቻል (ህብተረሰባዊ ምርጥ ባህርያት) ይሰብካሉ።. . . ሌላም ብዙ ብዙ. . .
ከእነርሱ መሀልም ስለጫት የሚያወራው እንዲህ ይላል. . .
“የዓለም ሳይንቲስቶች በእውቀት የመጠቁ፣
ሁሉም ይቅማሉ እየተደበቁ።”
ይህኔ ጉድ ፈላ። ሲያዩት (በልጅ ወይም ባልበሰለ አእምሮ) ብስለቱ ይማርካል (ወይም በሳል ይመስላል)። ፍልስፍናው ይጠልቅለትና አንድ ብሯን መዠረጥ አርጎ መግዛት ነው (ያው ለተገለጠለት)። ግን ከዚያስ? አሃ….መልእክቱስ? ‘ቃሙ ችግር የለውም?!’ ‘እንኳን እናንተና የዓለም ሳይንቲስቶችም ይቅማሉ?!….ጫት ጀት ያደርጋል?!’…. ምናምን ምናምን….
መቼስ የእኛ ሰው ለሚያደርገው እያንዳንዱ ነገር ደጋፊና አረጋጋጭ አካል ሲያገኝ ደስ ይለዋል። ድጋፉ በግጥም ተገልፆ በወረቀት ሲሰፍርማ በቃ! ዮሐንስ ጥቅሱን (ግጥሙን) or whatever ባየበት ቅፅበት መደቡ ላይ አንድ ኮፒ ብቻ ነበረ። ኪሱ ውስጥ ደግሞ አንድ ብር። አናፍቶ ገዛሁት። ተከራክሮ። (ክርክሩ ለደንቡ ነው….ለገዥና ሻጭ ደንብ….)
ያኔ ጥቅሱን የገዛው ማርኮት አልነበረም። የዋህ ቃሚ (ከሰው ተደብቆ እየቃመ ለማቆም የሚታገል) አግኝቶት ሀሳቡን እንዳይለውጥ አሰቦ እንጂ።….የ6ኛ ክፍል ተማሪ ነበር… ፓ! ጀትነቱ!…. ቅሞ ነበር እንዴ? ሆሆሆ…..የምር ግን እንዲህ ዓይነት ተቆርቋሪነት ያስቀናል። እነሆ ዛሬ በ6ኛ ክፍሉ ዮሐንስ ቀና…. (ይሄ ነገር ለራሱም አስቆታል) የምር ግን 6ኛ ክፍሉ ናፍቆታል….ትናንት 6ኛ ክፍል ሲደርሱ የተለውን የሚወደውን ጓደኛውን ከ16 ዓመታት በኋላ በድምፅ ሲያወራው ባሰበት….
ከጥቅሱ መደብ ጥቅሶች ይሄም ጥቅስ ትዝ አለው. . .
“ታምሜ ብተኛ፣ ቆሜ ባንቀላፋ፣
እንገናኛለን እኔ አልቆርጥም ተስፋ።”
***
አሁን ልቡ እየዘመረ ነው….በደማቋ ጨረቃ ውበት ልቡ ጠፍቷል…. ኧረ እንዲህም አድርጋው አታውቅ… ልጆቹ ሲዘምሩ በሀሳቡ ይሰማዋል። የርሱም ድምፅ ይሰማዋል….መዝሙራቸውን እየሰማ በየመሀሉ ይጠይቃል….
“ጨረቃ ድምቡል ቦቃ
አጤ ቤት ገባች አውቃ፣
/እሿ ደግሞ ሾካካ ነች። ንጉስ ቤት መግባት ትወዳለች። ማለቴ ንጉስ ልብ…:)/
አጤ ቤት ያሉ ሰዎች
ፈተጉ ፈታተጉ
/ገብሱን? አጃውን?/
በቁልፊት አስቀመጡ
/ለምን?….ከዚያስ?/
ቁልፊቷ ስትሰበር፣
/ውይ….ማን ሰብሯት ይሆን?/
በዋንጫ ገለበጡ፣
/ቢራውን?…አሃ! ሊጠጡ?/
አጃ ቆሎ፣ ስንዴ ቆሎ
/ውይ…. ስንዴ ቆሎ ይምጣብኝ። በሱፍ ያበደ ስንዴ ቆሎ። አቆላሉ…አበላሉ… ኧረ ማቅረቢያ እንቅቡስ ቢሆን?! መብላት ግን ደስ አይለኝም። ሲቆላ ሳይና ሰዎች ሲበሉ ሳይ ግን ሰው ይናፍቀኛል። በክረምት. . . ስንዴ ቆሎ. . . ከሰል ተቀጣጥሎ. . . ጋቢ ተለብሶ. . . ሲበላ. . . ሲቆረጠም. . . ሲሞቅ. . . ፓ!/
ያቺን ትተህ፣ ይህቺን ቶሎ!”
/ወይ ጉድ…የቷን ትቼ? የቷን ቶሎ?/
በላይ በላዩ ይጠይቃል። ልጅነቱ ናፍቆታል. . .
***
ቀጠለ. . .
በሀሳቡ መጡበት — ልጅነቱ. . . ጓደኞቹ. . . የሚቀናበት (ጠብቆም ላልቶም ቢነበብ ግድ የለውም) ዮሐንስ. . . ዘፋኙ. . .
“ኧረ ልጆች ልጆች እንጫወት በጣም፣
ከእንግዲህ ልጅነት ተመልሶ አይመጣም።”
/ከ6ኛ ክፍል በታች የነበሩ ጓደኞቹ/
“…………………………………………………..
……………………………………………………
……………………………………………………
……………………………………………………”
/የሚቀናበት ዮሐንስ/
“ላይታረስ ጉም (?)፣ ኑግ እንደ ሱፍ ላይነጣ፣
ተመልሶ ናፈቀኝ፣ ተመልሶ ላይመጣ…”
/ዘፋኙ/
ወደ ጨረቃዋ ተመለሰ. . . አይፈረድበትም ኧረ! በጣም ታምራለች. . .
አሁን አይጠይቅም. . . ዝም ብሎ ይዘምራል. . .
“…ጨረቃ ድምቡል ቦቃ
አጤ ቤት ገባች አውቃ፣
አጤ ቤት ያሉ ሰዎች
ፈተጉ ፈታተጉ
በቁልፊት አስቀመጡ
ቁልፊቷ ስትሰበር፣
በዋንጫ ገለበጡ፣
አጃ ቆሎ፣ ስንዴ ቆሎ
ያቺን ትተህ፣ ይህቺን ቶሎ!…”