አዋሳ ገብርኤሏ ደርሷል። — ቅዱስ ገብርኤሏ! — መልአከ ገብርኤሏ! – ነገ ነው። በልጅነት አፍ ደግሞ – ‘አንዴ ተኝተን ስንነሳ ገብርኤል ይሆናል።’ ቀጤማው፣ ዳቦው፣ ጠላው፣ ጠጁ….. – ፌሽታ!! — አንዴ ተኝተን ስንነሳ ሁሉም ይሆናል። (ልጅ እያለሁ ‘አንዴ ተኝተን ስንነሳ….’ ‘ሁለቴ ተኝተን ስንነሳ…. እንዲህ ይሆናል!….. እንዲህ ቀን ይመጣል።’ ምናምን ስንል ዛሬ ናፕ የምንለውን ዓይነት ቆራጣ እንቅልፍ ተኝቶ መነሳትና ቀኑን ጎትቶ ማምጣት ያምረኝ ነበር። የማልፈልገውን ቀን ለማራቅ ደግሞ (ለምሳሌ ትምህርት የሚጀመርበትን ቀን) ብዙ በማምሸት (ባለመተኛት) ቀኑን መግፋት ያምረኝ ነበር። — አይ ልጅነት!)
ገብርኤሏ ሲደርስ ከተማው ብቻ ሳይሆን የሰዉ ስሜትም ድብልቅልቅ ይላል። የልቡ ሁኔታም ድብልቅልቅ ይላል። [በልባቸውም ቢሆን]…. አማኙ – ይሸልላል!…. ሌላ አማኙ – ይቀናል! ….. ፈታ ያለው ኢ-አማኒ በፌስቲቫሉ ይደመማል! – የልቡ ዳሌ በደቡብ ስልት ይደንሳል!… ወግ አጥባቂው ኢ-አማኒ ደግሞ ይበሳጫል! – የርሱን ማወቅ (በራሱ የተረጋገጠውን፣ ባነበባቸው መፅሀፍት የፀደቀውን ማወቅ) እየተነተነ ለህዝቡ አዛኝ ይመስላል (ወይም ያዝናል)!… – ያም ሆነ ይህ ዓመት በዓል ነው – የሽለላ! የቅናት! የድማሜ! የብስጭት ዓመት በዓል! – ሁሉንም እንኳን አደረሰው!!
እመት አዋሳም ከዓመት በዓሎቿ አንዱ ደርሶባት ወገቧን አስራ ሽር ጉድ ትላለች። ሰው ተቀብላ ታሳርፍና ሌላ መምጣት አለመምጣቱን ለማየት ከአንገቷ ቀለስ በማለት ዓይኖቿን በጥቁር ውሀ በኩል ወርወር ታደርጋለች። (ሻሸመኔ ባለውለታዋ ነች።… የወዲያኛዎቹን ከየአቅጣቻው አሰባስባ ታሳልጥላታለች። ታስተናብርላታለች። ታስተላልፍላታለች።) ደግሞ ታያለች… መለስ ብላ በቱላ፣ በቦርቻ በኩል ወደ ይርጋለም – ዲላ — ይርጋ ጨፌ — ሀገረ ማርያም —- ያቤሎ —– (ጲጲጲጲ…) ተምዘግዝጋም፣ እንዴትም አባቷ ብላ ቢሆን ሞያሌ ድረስ መብቷ ነው… – ልብ ካለች፥ ለገብርኤሏ የሚሸክፍ እንግዳ አታጣም።
አመት በዓሏ ሲደርስ እንዲህ ነች።… መለስ ቀለስ ነው ስራዋ። እንግዶቿን ትቀበላለች። — ዳኤ ቡሹ! – አኒ ኬራ!! መኪኖቹ ምዕመኑን ሞልተው ከተለያየ ቦታ እያመጡ መናህሪያዋ ላይ ያራግፉላታል። ቤተስኪያኑ በራፍም ያራግፉላታል። መኪኖቹ ደርሰው ማራገፊያቸው እንደቆሙ…. ቤንዚን ጠብ እንዳለበት እሳት ቦግ ያለ የመራገፍ ትርምስ ይታያል። — ምዕመናን ከመኪኖቹ ሲወጡ…. ቀን በሌዎች፣ ተራ አስከባሪዎች፣ ሌቦች (ያው ግርግር ለሌባ ያመች የለ?) ወደ መኪኖቹ ሲሮጡ እኩል ይሆናል። — እቃ ለመያዝ….. እቃ ለማስያዝ…. — ትርምስ!
ቦግ ያለው የሰው ትርምስ (እንደ እሳት ያለው) ወዲያው ክስም ይላል። (የሰው ቤንዚን ሲደፋበት መልሶ ቦግ እስኪል ድረስ) … ደርሰው ሲበተኑ። ምዕመናኑ ወደ ማረፊያቸው…. ቀን ሰራተኞቹ ወደ ጥጋጥጋቸው…. — ፀሀይዋን ሽሽት! ውይ ፀሀይ…. ለነገሩ ለማያውቃት ጥቁር እንግዳ እንጂ ለኗሪዎቿ ብርቅ አይደለችም። ስትጠፋ ነው ብርቅ። — ‘ኡኡቴ…. ማን ሊሞት ይሆን?’ ይባልላታል። ማን ሲሞት ፀሀይ ጠልቆ እንደሚያውቅ… — ራሳቸው ኡኡቴ!
እንግዲህ ነገ ነው ቀኑ። ከየቦታው የተሰበሰቡት ምዕመናን ነጠላቸውን አንጠላፍተው ከተማው አስፓልት ላይ ከቤተክርስቲያኑ ወደ ሀይቅ — ወደ እርሻ ጣቢያ መንገድ — ወደ ማውንቴይን —- ወደ ሰፈረ ሰላም (አቶቴ) (አላሙራ) —- ወደ ቅያሶቹ —- ወደ…. ይሰመራሉ። ልክ መንገዱ ላይ የተደፋ እርጎ ሊመስሉ (በታላቁ Adam Reta ልጅ፣ የግራጫ ቃጭሉ መዝገቡ አገላለፅ)። ከቤተስኪያኑ የተደፋ እርጎ ግን አይመስልም።… መሀል ላይ፣ ከቤተስኪያኑ ፊት ለፊት የቆመው የሀውልት ደንቃራ ያደናቅፈዋል….