የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፥ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማእከል፥ በ2001 ዓ/ም ያዘጋቸው የአማርኛ መዝገበ ቃላት “ሰከረ”ን በግስነት — ‘በአልኮል መጠጥ፣ በዕፅ…ምክንያት ስሜቱን የሚሰራውን መቆጣጠር አቃተው።’ ይልና፤… ከሰከረ ለቅፅልነት የረባውን “ሰካራም” —
1. አልኮል መጠጥ አዘውትሮ የሚጠጣ፥ ጠጪ።
2. አልኮል መጠጥ ጠጥቶ የሰከረ።’ ብሎ ይተረጉመዋል።
የእኛ ቤት (የእህቶቼ) መዝገበ ቃላት ደግሞ “ሰካራምን” ከስካር (ስ) ከረባ ቅፅልነት ባሻገር በቀለም ዓይነትነት ያስቀምጠዋል።… ቃሉን ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማሁት የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ ሳለሁ ነበር። [ትንሽና ትልቅነታቸው እርስበርሳቸው ሲተያዩ ሆኖ]… ትንሿ እህቴ ትልቋ እህቴን….
“እሙዬ ክሩን አቀብይኝ” አለቻት።
ትልቋ ቀልጠፍ ብላ ቀዩን ክር ብድግ ስታረገው …
ትንሿ: “አይ…ሰካራሙን አለቻት”… ሌላ ቀይራም አቀበለቻት። ደብለቅለቅ ያለ ቀለም ያለውን ቱባ ክር አንስታ አቀበለቻት። መግባባታቸው ገረመኝ። ልቤ ‘ጉድ’ አለ! (ብለን እናካብድ? ሃሃሃ…)
እነሆ ከዚያ በኋላ “ሰካራምን” በቀለም ዓይነትነት አወቅሁኝ። ሰካራም ማለት ብዙ ዓይነት ቀለማት በአንድነት ሲሰፍሩ (ካለመደባለቅ) የሚኖር መልክ መሆኑን ተማርኩኝ። ስሙን ከማወቄ (ከመማሬ) በፊት ሰካራሙ ክር ተቀምጦ ሳየው፣ በአቀላለሙ መልክና በቀለም አቀያየጡ ስርዓት እገረምና …‘ወይ ጉድ! እንዴት አቀለሙት?’ ብዬ ለራሴ እጠይቅ ነበር።… ከርሱ በፊት በስንቱ ተገርሜ ስጠይቅ እንዳልኖርኩ፤…. ከርሱ በኋላ በስንቱ ተደምሜ እንደማልጠይቅ፤… ላሊበላና ይምርሀነ ክርስቶስን አይኔ አይቼ የአድናቆት ጥግ ላይ እስክደርስ ድረስ…. (ውይ እርሱንም መፃፍ አለ ለካ?! :-/)
ከዚያ በኋላ በልጅ አእምሮዬ ሰካራም ሳይ ደስ ይለኝ ነበር። ክሩንም የሰከረውንም። እንደ ስምም እንደ ቅፅልም። (እንደ ስም – ቀለሙን፤ እንደ ቅፅል – ጠጥቶ ራሱን የሳተውን)። ከማንም በተሻለ ሰካራምን እንደተረዳሁ ይሰማኝና በልቤ እሸልል ነበር። የሰዉን ግድግዳ እየደበደበ (ሲያጠብቅ፣ ሲያላላ)፣ ያገኘውን እየጠለዘ፣ እየተሳደበ፣ እየተዘለፈ… ሲያልፍ፣ ህፃናቱ እየተከተሉትና ኮቱን እየጎተቱ : –
“ሰካራም ቤት አይሰራም፣
ቢሰራም ቶሎ አይገባም
ቢገባም ቶሎ አይተኛም
ቢተኛም ቶሎ አይነቃም…”
…ሲሉት እኔ በራሴ ሀሳብ እብሰለሰል ነበር። (ቃሉን በቀለምነት ካወቅሁ በኋላ ፀባዬ ተቀይሮ) ለእኩዮቼ ሰካራሙን ሰውዬ ከቀለሙ ጋር አነፃፅሬ እንዴት እንደማስረዳቸው አስብ ነበር። ሲሰክር ስለሚያየው የሚያምር ሰካራም ቀለም ዓይነት እንዴት እንደማስረዳቸው (ቢከራከሩኝ እንኳን ክሩን ከቤት አምጥቼ ማሳየት እንደምችል ሳይቀር እያሰብኩ) በልቤ አቀናብር ነበር። ቅንብሬን ሳልጨርስ ሰካራሙ ያልፍና ይረሳ ነበር። ሌላም ሰካራም ይመጣል… እርሱም እንደ አዲስ ሳቀናብር ያልፋል። ሌላም… ሌላም… ሌላ ቅንብርም… ሌላአአአ…
ሰካራም ቀለም እና ቅዳሜ
አሁን አሁን ግን ትንታኔውን ልብ አልለውም፡፡ እንዲያው
ከሰካራም ቀለም አመሰራረትና ትንታኔ፣ እንዲሁም ከልጅነት ትዝታዬ ይልቅ የቀለሙ ዓይነት ተዋህዶኝ የቀለም ዓይነት ለመጥራት እጠቀመዋለሁ፡፡ የሚያምር ቀለም። ሁሉም ነገር ያለው። ሁሉም የሞላለት። ምንም ያልጎደለው። ቅዳሜ ለእኔ እንዲያ ነች። ቅዳሜ መጥቶ ምን ጠፍቶ? ሁሉ ነገር ሙሉ ነው…. ቀይ ቢሉ፣ አረንጓዴ ቢሉ፣ ሀምራዊ ቢሉ፣ ሰማያዊ ቢሉ…. የቀለም ዓይነት። የመልክ ዓይነት። ድርድርድርድርድር….ጥቁርም ሳይቀር!…
ግን ጥቁሯን የምታሳየው ከስንት አንዴ ነው። ምናልባት በዓመት አንድ ጊዜ? – “እንደ ባቲ መንገድ?” ውሸት ምን ይሰራል?… የባቲ መንገድ የመጣልኝ አሁን ነው። ልክ አሁን። የጂጂ ሙዚቃ ዞሮ ተዟዙሮ “ባቲ”ዋ ጋር ሲደርስ… ባቲን ስትጫወት… ባቲን ስታንቆረቁር…. ወይ ግጥምጥሞሽ! ብለን ተደመምንና እንደምንም ሰካናት! ሃሃሃ…
“♩ ♬ ኧረ ባቲ ባቲ፣ ባቲ ከተማው
ከሚበላ በቀር የሚጣል የለው፤
እንደ ባቲ መንገድ፣ እንደ ወዲያኛው፣
በዓመት አንድ ቀን ነው፣ የምትገኘው፤ ♪
♫ ጨረቃ ባትወጣ፣ ደምቃ ባትታይ፣
አንተ ትበቃለህ፣ ለአገሬ ሰማይ፣
አንተ ትበቃለህ፣ ለአገሬ ሰማይ። ♫”
ስላጫወተከን እናስመሰግናለን !!