ሽልንጌን…

ዛሬ በስካይ ባስ ሄጄ እንዴት ብርቅ ሆኖብኛል መሰላችሁ? ሃሃሃ….
ይልቅ ላጫውታችሁማ…

….መኪናውን ለማግኘት 7:30 መስቀል አደባባይ ድረስ ተብዬ ነበር። ከዚያም በልማድ እስከ መስቀል አደባባይ የሚፈጅብኝን ሰዓት አስልቼ ከቤት ወጣሁኝ። ያው እንደተለመደው የታክሲ ችግር ነበር። (እኔም ጊዜውን ሳሰላ ይሄንንም ከግምት አስገብቻለሁ።) ታክሲዎቹ እየሞሉ መጥተው እንደሚጭን ይቆማሉ፤ ግር ብለን ስንገባ አባብለው ያስወርዱንና ይሄዳሉ። በሚገርም ሁኔታ የሚመጡት ሁሉ ይደጋግሙታል። ምክንያቱ ከፊት ለፊት የተገተረው ትራፊክ ነበር። በዚያ በጠራራ ፀሀይ አድፍጦ ይጠብቃል። ያለፈ ያገደመውን ሁሉ እያስቆመ ወይ ይቀጣል፣ ወይ ይፈልጣል። — ስራው ያውጣው!

…6:55… 7:00… 7:05… 7:10… 7:15… እያለ ሰዓቱ እፍ ብሎ አንድም ሰው ሳይጫን 7:20 ደረሰ። ከዚያም መኪናው ጥሎኝ ቢሄድ የምጉላላውን አሰብኩና ትንሿን ታክሲ አናገርኩኝ። በስንት ሙግት በሀምሳ ብር ተስማምተን ጭኖኝ ነጎደ። ደግነቱ መንገዱ ክፍት ስለነበር እያዋከብኩት 7:40 ላይ ቦታው ደረስን። አደባባዩ ላይ የቆመ መኪና ሳጣ መጀመሪያ ጥሎኝ እንደሄደኝ አስቤ ነበር። ከዚያ ግን ረጋ ብዬ ሳጤነው 7:30 ተደርሶ መንቀሳቀሻው 8:00 ሰዓት መሆኑ ትውስ አለኝና ረጋ ብዬ ከተኮለኮሉት ተሳፋሪዎች አንዱን ጠየቅሁት። መኪናው መምጣቱንና ነዳጅ ልቅዳ ብሎ መሄዱን ነገረኝ።

በሸቅሁኝ። ሽልንጌ አንጀቴን በላችው።

ባቡር….ድሬዳዋ….ትርንጎ….ተሳፋሪ….ፋጡማ….ቅርጫት….ሽልንግ…. ጩኧት…. —- ሽልንጌን… ሽልንጌን….ሽልንጌን….

ልቤ በፋጡማ ለዛ ጮኧች። ቆሽቴ ነደደ። መልስ ላላገኝ ጠየቅሁኝ…ቅሉ ራሴኑ እንጂ ማንን ልጠይቅ?… እስኪ አሁን ሰላም ገብቻለሁና እናንተን ልጠይቅ…

ግን የምር በቂ ታክሲ ሳያቀርቡ ታክሲን ትርፍ ጭነሀል ብሎ መቅጣት ምን ይባላል?? ታክሲ “ትርፍ ጭነሀል” ተብሎ በሚቀጣበት አገር በነቀንዶ (ሀይገር)፣ እና በሎንችናዎች፣ (ኧረ በአንበሳ አውቶብስ ጭምር) ከትርፍ ሞልቶ ፈስሶ ከፖርቶመጋሊያው ላይ ለመጫን ጥቂት የቀረው ሰው መጫን የሚፈቀደው ለምንድን ነው??

ያም ሆነ ይህ ግን በስካይ ባስ ፍስስ ብዬ ስሄድ ሁሉም ተረሳኝ። የአውቶብሱ ምቾት ጉዞ ላይ መሆኔንም ጭምር አስረሳኝና ተረጋጋሁ። ድጋሚ አካብዳለሁ! — በስካይ ባስ መጓዝና በአውሮፕላን መጓዝ የሚለያዩት በአውሮፕላን መስኮት የሚታየው ደመና ሲሆን በስካይ ባስ ግን አይታይም። (ከፍጥነት ልዩነታቸው ባሻገር) በትንሽ ተጨማሪ ክፍያ ክብርንና ደህንነትን ጠብቆ መሄድም አለሳ? ጉዞዬ ከስካይ ባስ ፕሮግራም ጋር አልጣጣም ብሎ በስካይ ባስ ላልሄድኩባቸው እያዘንኩ ስካይ ባስ አገልግሎቱን አስፍቶ የሚጓዝባቸውን ቀናት ያበዛ ዘንድ ወይ ደግሞ እንደሱ ያሉ ነጋዴዎች ይበዙልን ዘንድ እመኛለሁ።

ቺርስ!!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s