ላሊበላ ሁለት ጊዜ ሄጃለሁ። መጀመሪያ የሄድኩት በ2001 ዓ/ም ነበር። ቀጥሎ ደግሞ በ2003 ዓ/ም…. በ2004ም ላሊበላና ዙሪያው በዐይኔ ሲዞሩ ነበር፤ ሆኖም ግን ነገሮች ከአቅም በላይ ሆነውብኝ ሳንተያይ ተሸዋወድን። ይህ ዓመት ከማለቁ በፊት ብሄድም ደስ ይለኛል። በሚቀጥለው ዓመትም። ከዚያም… ከዚያም…. ኧረ ከዚያም…. ከኧኧኧኧ…ዚያም! ኧረ ከዚዚዚዚ….ያም!
እንደውም የላሊበላ ነገር ውል ሲለኝ እንደማልችልበት ልቤ የሚያውቀውን – “እዚያም በገደምኩ” ያሰኘኛል፤…ግን እርሱ ለተጠሩት ነው። ለእኔ ግን ደርሶ መመልከቱም እንደ መጠራት ሆኖልኝ አንዴ ያየሁት ዓለም ስሙ በተነሳ ቁጥር ያስፈነጥዘኛል። ከዚህ ቀደም ላሊበላን አይቶት የሚያውቅ ቢኖር ነገሬ ከጫፍ ጫፍ ይገባዋል። ከጫፍ ጫፍ
አይቶት የማያውቅ ደግሞ ‘አቦ ምን ያካብዳል?’ ዓይነት ስሜት ውስጥ ቢገባ አይፈረድበትም። – አላየማ! ….ደርሼ እጄን አፌ ላይ ጭኜ፣ ‘ኦ ማይ ጋድ! ኦ ኦ ኦ… ኦ ማይ ጋድ!’ ብዬ እንደ ድንጋይ ክልትው ብዬ እስክቀር ድረስ፥ እኔም እንደዚያ ነበር የምለው። – ‘አቦ ምን ያካብዳሉ?!’… አሁን ግን አይቻለሁና፥ እላለሁ…. እመክራለሁ…. እዘክራለሁ….
ሀይማኖቱ — ኦርቶዶክስ፣ ካቶሊክ፣ ጴንጤ፣ ሙስሊም፣ ጣኦት አምላኪ፣ ጠንቋይ ቀላቢ፣ ኢ-አማኒ፣ ግራ-ገብ…. ሌላም የፈለገውን ሆኖ፣ መረዳቱ የፈቀደለትን እምነት የሚከተል ማንም (በተለይ ኢትዮጵያዊ) በህይወት እያለ፣… በላሊበላ ለመደነቅና ቦታው ደርሶ አይቶ ‘በዐይኔ ዓለም አየሁ’ ለማለት፥ ማህበረሰባዊ ጤና ያለው (socially healthy) ቢሆን በቂ ነው። ምናልባት ጤነኛነቱ ላይ የአገር ፍቅር ስሜት ቢጨምርበትና ባንድራው ትዝ ቢለው ደግሞ ደስታው እጥፍ ድርብ ይሆንለታል፡፡ — እንደ እኔ ነው!
የመጨረሻውን ትንፋሽ ከመተንፈሱ በፊት… ዓለምን ከመሰናበቱና ወደ መጨረሻ ቦታው የመሄጃ ትኬቱን ከመቁረጡ በፊት…. ልቡ እንደምንም ቆርጦ፣…‘አልበላም አልጠጣም’ ብሎ ሳንቲም ቀርቅሮ፥ (ኧረ ሰርቆም ቢሆን) …ትኬት ቆርጦ በእድሜው ላሊበላን ቢያየው አይቆጭም። ስንት ነገር ለሚሆንላት፣ ከሰውነት ተራ ወጥቶ ስለርሷ ነፍሱን ለሚበድልላት ስጋውም ትልቅ ውለታ ነው። ከዚያ ወዲያ ምናልባት ላሊበላን በተመለከተ ሊቆጨው የሚችል ነገር ቢኖር ‘ወይኔ ላሊበላን ድጋሚ ሳላየው ሞትኩ’ ምናምን የሚል ቢሆን ነው። — ይሄም እንደ እኔ ነው!
ከዚያ በፊት ስለላሊበላ በእውቅ እና በጥበብ የተቀናበረ የቪዲኦ ምስል ተመልክቶ፣ በአንደበተ ርቱዕና አፍ አስከፋች ተራኪ ተተርኮለት፣ ወይም ሌላ… ብቻ እንዴትም ተደርጎ ስለላሊበላ አስደናቂነት ተነግሮት ቢሆን፥ ልክ እዚያ ሲደርስ ነገሩ ሌላ ሆኖ ነው የሚጠብቀው። ቪዲኦውን – ይጠረጥረዋል! ፎቶውንም! መጀመሪያ የነገሩትን የተረኩለትንም ይታዘባቸዋል! – ብዙ አጉድለውበታላ። እየቆየ ሲሄድ ግን አይፈርድባቸውም። እርሱም የተመለከተውን ለማውራት እንዴት ጀምሮ እንዴት እንደሚጨርስ ግራ ሲገባው ይረዳቸዋል።
ፎቶ ሊያሳይ ያወጣና ፎቶው ከሚያስታውሰው ጋር ሲነፃፀር ይደበዝዝበታል፡፡ ሰውየው ነገር መጠፈር የሚቀናው ከሆነ ደግሞ…. “የፎቶ፣ የቪዲኦ እና የትረካ፥ ከንቱነትና ስንፍና ሊታዩ ከሚችልባቸው ቦታዎች አንዱ ላሊበላ ነው” ብሎ ቢደመድም አይፈረድበትም። “ይናገራል ፎቶ” ብለን ዞር ከማለታችን ለላሊበላ ሲሆን ፎቶ እንደማይናገር እንታዘባለን። ከዚያም እናሻሽለዋለን – “ፎቶ አንዳንዴ አይናገርም! ቪዲኦም!”
መጀመሪያ ስሄድ የ16 ቀን ጉዞ ነበር። መንገድ ላይ ያሉትን የጎብኚ መዳረሻ ቦታዎች አቅማችን እስከፈቀደ ድረስ እየበረበርን ነበር ያለፍነው። ጉብኝቱን ስናቅድ ላሊበላ መካተቱ ጉዞውን ሀይማኖታዊ ያደርገዋልና ይቅር ብለው አጥብቀው የተሟገቱ አንድ፣ሁለት፣ ሶስት… ወዳጆች ነበሩ። (ሁለቱ ፕሮቴስታንት ነበሩ። አንደኛው ደግሞ ሙስሊም።) ከዚያ ግን በሰው ብልጫ እና በብዙ ሙግትና ማስረዳት ተረቱና ላሊበላም ተካተተ። ከዚያ በፊት በምንደርስባቸውና በምናርፍባቸው በፊት ቦታውን ከመበርበር በፊት ማረፍ ነበር የሚቀድመው። ላሊበላ ስንደርስ ግን እንዲህ አልነበረም….
ማረፊያ ክፍል ይዘን እቃችንን ካስቀመጥን በኋላ መጀመሪያ ይቅር ብለው ሲከራከሩ የነበሩት ሶስቱ ሲቀሩ ሁላችንም ተያይዘን ወጣን። (ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ሶስቱም ያሳዝኑኛል) ሁላችንም በየፊናችን ስለ ላሊበላ ‘ቱቲ’ ሰምተን ነበርና ተጣድፈን ቦታውን በቅምሻ ለማየት ጓጓን። በቀጣዩ ቀን ለመጎብኘት የትኬትና የአስጎብኚ ከፍለን ካመቻቸን በኋላ ወደ ቤ/ክኑ ተጣድፈን ገባን። የሌላውን በርግጠኝነት ባላውቅም እኔ ጭው አለብኝ። ፍዝዝ… ጭው…
ውሸት ምን ይሰራል? በወቅቱ የተመለከትኩትና የሄድኩት ሁሉ ህልም ህልም ይመስለኝ ነበር። ለሁለተኛ ጊዜ እስክሄድ ድረስም በዚያው የህልም ስሜት ውስጥ ነበርኩኝ። ህልም ይመስለኝና ደስታዬ ወሰኑን ሲያጣ “ህልም – እልም” ብዬ ለራሴ መሳቂያ አበጃለሁ፡፡ በፎቶና በቪዲኦ ከተመለከትኩት በላይ ትልቅ (ሰፊ) መሆኑ የመጀመሪያው የአግራሞት ምንጭ ሆኖልኝ ነበር። ከዚያ ሌላ ደግሞ ላሊበላ ሲባል፣ ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት በቅፅሩ ውስጥ እንዳሉ በወሬ ብሰማም በቴሌቪዥን አዘውትሬ የማየው ቤተ ጊዮርጊስን ነበር። በሚገርም ሁኔታ ግን ሌሎች 10 አስደናቂ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናት ግቢው ውስጥ መኖራቸውን አወቅሁኝ።
ስለ አሰራሩማ ምኑ ተወርቶ ምኑ ይተዋል? እንዲያው ታምር ነው። ካለምንም መሸራረፍ በቅርፅ መፈልፈላቸው፣ የመስኮቶችና የማዕዘናት እኩልነት፣ የውሀ ልኮች ልኬት፣ የግድግዳው መስተካከልና ልሙጥነት፣ የበሮች አሰራር፣ ስዕላቱ፣ በቅርፅና በደንብ የተሰሩት መተላለፊያዎች…. ምኑም ቢዘረዘርና ቢብራራ ነጋሪውንም ተነጋሪውንም አያረካም። ብቻ ጉድ እንዳልኩኝ አይቼው፣ ጉድ እያልኩኝ ተመለስኩኝ። ዛሬም ሳስበው ሌላ ነገር አልልም፡፡ — ጉድ ነው የምለው። “ሰው ነው የሰራው” “መንፈስ ቅዱስ” ብለው ለሚሟገቱ ሰዎች መልስ ለማቀናበር ሳልደክም ለራሴ ግልጋሎት የሚሆን መልስ ስላገኘሁ ደግሞ ይበልጥ ደስ ይለኛል። እንዲህ ነው….
በእኔ እምነት ሰው ይህን ሰራ ቢባል እንኳን ያስበውና ደፍሮ ይጀምረው ዘንድ ወይ እብድ (የአእምሮ ህሙም) መሆን አለበት፣ ወይ ደግሞ የተለየ መንፈስ ሊኖረው፣ ሊያመላክተው ይገባል። ሌላ ሌላውን ብተወው እንኳን የድንጋዩና የፈልፋዩ በአንድ ቦታ መከሰት እንዲያው ግጥምጥሞሽ ነው ማለት ይከብደኛል። በተለይ መፈልፈሉና መፈፀሙ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ መውሰዱን ሳስተውል፤ ያም ሆነ ይህ ግን ከሚታየው ነገር ርቄ በማይታየው ነገር እየተብሰለሰልኩ የማንንም ዋጋ (credit) የማሳጣት ሀሳቡም፣ መብቱም፣ አቅሙም የለኝም። ማንም ሰራው ለምንም ሰራው… ላሊበላ ለዐይኖቼ ታምር ነው።
እንግዲህ ከ900 ዓመታት በፊት እኒያን የመሳሰሉ ህንፃዎች ተፈልፍለው ባለበት ሁኔታ በአካባቢው ላይ ተመሳሳይ የኗሪዎች ቤት አለመኖሩን መመልከት ሌላ አግራሞት የሚያጭር ነገር ነው። (የሰው ሀሳብ ነው ብለን ለአፍታ ስናስብ) ሌላው ቀርቶ በአካባቢው ለመውቀጫና ለወፍጮ የሚፈለፍሉት ድንጋይ እንኳን ያን ያህል ሊስተካከልና ቀልብን ሊያማልል፣ ገና ሲታይ እንዲያስቅ ተደርጎ የተሰራ ነው የሚመስለው፡፡ በየመንገዱ የገበጣ ጉድጓዶችን ለመፈልፈል የተጀመሩ ድንጋዮችም አሉ። ታዲያ ግን የጉድጓዶቹ ቁጥር ከመደበኛው የገበጣ ጉድጓድ ቁጥር ሳይደርስ ወይ መሽቶባቸው ወይ ደግሞ ደክሟቸው ሳይጨርሷቸው ሄደዋል። በመነጋው አልተመለሱበትም…. ወይ ረስተውታል… ወይ ደግሞ ከብዷቸዋል።
ለሁለተኛ ጊዜ ስሄድ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአየር መበላሸት ምክንያት ጉዞው እየተስተጓጎለበት ካሰብነው ጊዜ በላይ ነበር የቆየነው። በግማሽ ልብ እንደተጉላላሁ ቢሰማኝም፣ በግማሽ ልብ ደስ እያለኝ ነበር፡፡ ላሊበላ እንደ አዲስ ሲታይ እንደ አዲስ ሰለሚናፍቅ አምሮት ለማውጣት ጥሩ አጋጣሚ ነበር የፈጠረልኝ፡፡ ምናልባት ለዚህም ይሆናል – የሁለተኛው ጉዞዬ ህልም አይመስለኝም። ሆኖም ግን ስሙን በሰማሁ ቁጥር ይናፍቀኛል፡፡ ያኔ አብሮኝ የተጓዘ እንግሊዛዊ ወዳጄ ስለተመለከተው ነገር ሲነግረኝ፣ – ‘ከዚህ በፊት ብዙ ቦታዎችን ተመልክቼ ተደንቄያለሁ ላሊበላን የሚያህል አስደናቂ ነገር ግን አላየሁም፡፡ ወደፊትም የማይ አይመስለኝም፡፡’
ከላሊበላ 42 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ የሚገኘው ደግሞ በዋሻ ውስጥ የተገነባው ይምርሀነ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ ዋሻው ለቤተ ክርስቲያኑ እንደ ክዳን ሆኖለታል፡፡ ወይ ደግሞ ዋሻው እንዳይወድቅ ህንፃው ደግፎት ይመስላል፡፡ ይምርሀነ ክርስቶስ ከላሊበላ በ90 ዓመታት ገደማ (ትክክለኛ ቁጥሩን አላስታውሰውም) የሚያረጅ ሲሆን በመፈልፈል ፈንታ የተገነባ ህንፃ መሆኑ ይበልጥ ያስገርማል፡፡ ግንባታ ከመሆኑ አንፃር በአካባቢው ተመሳሳይ ባይሆን እንኳን እንደ ነገሩ የተሞከሩ ግንባታዎች አይታዩም፡፡ እኔ ያየሁትን ተናገርኩኝ እንጂ፣ በላሊበላ ዙሪያ ይምርሀነ ክርስቶስ
ብቻ አይደለም ያለው፡፡ እንግዲህ የሞላለት ቦታው ደርሶ ልቡን በፈለገው ዜማና ስልት ማስዜም ነው፡፡ ምንም ሆነ ምን ግን የዜማው ይዘት
‘ዐይኔ ዓለም አይ እግሬ ደርሶ፣
የድንጋይ ወጋግራ የድንጋይ ምሰሶ፣’
ከሚል እንደማይዘል ይሰማኛል፡፡ ነገሬን ስቋጭም… ከላይ ካሰፈርኳቸው አንቀፆች አንዱን ደግሜ በማለት ነው…. ሀይማኖቱ — ኦርቶዶክስ፣ ካቶሊክ፣ ጴንጤ፣ ሙስሊም፣ ጣኦት አምላኪ፣ ጠንቋይ ቀላቢ፣ ኢ-አማኒ፣ ግራ-ገብ…. ሌላም የፈለገውን ሆኖ፣ መረዳቱ የፈቀደለትን እምነት የሚከተል ማንም፣ (በተለይ ኢትዮጵያዊ) በህይወት እያለ፣… በላሊበላ ለመደነቅና ቦታው ደርሶ አይቶ ‘በዐይኔ ዓለም አየሁ’ ለማለት፥ማህበረሰባዊ ጤና ያለው (socially healthy) ቢሆን በቂ ነው። ምናልባት ጤነኛነቱ ላይ የአገር ፍቅር ስሜት ቢጨምርበትና ባንድራው ትዝ ቢለው ደግሞ ደስታው እጥፍ ድርብ ይሆንለታል፡፡ — እንደ እኔ ነው!
ማስታወሻ፡ መጨረሻ ላይ በተከታታይ ያሉት አምስት ፎቶገራፎች ከኢንተርኔት የተገኙ ናቸው፡፡
መልካም የገና በዓል ለሚያከብሩት በሙሉ፡፡
Melkam ye gena beal lantem…. betam des yemil tsihuf nebere …. eskayew guaguchaleh le eskezaw gin agizehegnal…. degagime be manibebina fotowochun bemayet ezelkalehu.