የቆሎ (የልጆች) ገና

ዛሬ ዋዜማ ነው። — የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓል ዋዜማ። አንድ ጊዜ ተኝተን ስንነሳ ደግሞ ገና ይሆናል።… ዋዜማው እኛ ቤት (እኛ ሰፈር) “የቆሎ ገና” ወይም “የልጆች ገና” ተብሎ ይታወቃል። ቆሎ በየቤቱ ስለሚበላ ‘የቆሎ ገና’ …. ልጆች ካለከልካይ ስለሚጫወቱና ስለሚቦርቁ ደግሞ በተለዋጭ ‘የልጆች ገና’ ይባላል። እነሆ ቆሎው ቀራርቦ እየተበላ ነው። ሲሆን ጠላም ይቀርባል። እኔም ይህን ፅሁፍ ስፅፍ እጆቼን በየመሀሉ የኮምፕዩተሩን ቁልፎች ከመጫን የማሳርፈው ጠረጴዛው ላይ ባለው የቆሎ ሳህን ነው። ….ገና ነዋ! የቆሎ ገና!

እንደልጅ የገና ጨዋታውን ተጫውቼ ዋዜማውን ‘የልጆች ገና’ በሚል ስያሜው ባላከብረው እንኳን ቤት የተዘጋጀውን (በእውቅ ተዘጋጅቶ የተገዛውን) ቆሎ እየቆረጠምኩኝ ‘የቆሎ ገና’ ብዬ አከብረዋለሁ። ሰፈር ያሉ (ባጋጣሚ በዋዜማው ገብቼ የማውቅባቸው) ቤቶችም ውስጥ በዋዜማው ሁሉም ተሰብስቦ ቆሎ ይበላል። በቆሎ ገናው ውጪ ስናመሽ ደግሞ የእኔ እናት ደስ አይላትም። ለምንም አይደለም…ቆሎውን እየቆረጠምን አብረናት እንድንጫወት ስለምትጓጓ እንጂ። እነሆ ቤት በጊዜ ሰፍረን ቆሎውን እንቆረጥመው ይዘናል…

እስከዛሬ ድረስ የቆሎ ገና ወይም የልጆች ገና በሁሉም ኢትዮጵያዊ ቤተሰብ ውስጥ የዋዜማው መጠሪያ ስያሜ ይመስለኝ ነበር። ቅድም ከወዳጆቼ ጋር ስለዋዜማው አከባበር ስንጫወት ግን እንዲያ እንዳልሆነ አወቅሁኝ። ውጪ እንድናመሽና ፐርቸስቸስ ብለን እንድናሳልፍ ሲጋብዙኝ ‘አይ… እናቴ በገና ዋዜማ ውጭ ብዙ ስናመሽ ይደብራታል። ቤት ሄደን ቆሎ እንበትን እንጂ…በቆሎ ገናው ቤት ተሰብስቦ ቆሎ መቆርጠም ነው…’ ምናምን ስላቸው በግርታ ‘የምን ቆሎ?’ ብለው ጠየቁኝ። ስለእኛ ቤት ዋዜማ አጫወትኳቸው። እንዲያ ያለውን ባህል ከዚህ ቀደም እንደማያውቁ ተረዳሁ።

ከዚያም ቤት ስገባ እናቴን ስለባህሉ አመጣት ጠየኳት…. “መቼም ሌላ ቦታም የራሱ አከባበር ይኖረው ይሆናል… የቆሎ ወይም የልጆች በዓል የሚባለው ግን በጉራጌዎች ነው….” በማለት ጀምራ እንዲህ …

(ለአቀራረብ ያመቸኝ ዘንድ ቃል በቃል ከማድረግ ይልቅ አንዳንዱን ወደራሴ አፃፃፍ አምጥቼዋለሁ።)

“…ልጆች ገና ሲደርስ የገና ጨዋታ (ሩር) ይጫወታሉ። ከተማ ውስጥ ቢቀርም ገጠር ግን አሁንም አለ። በዓሉ ከመድረሱ በፊት ህፃናት በቃጫ ኳስ ጠፍረው በቆልማማ እንጨት እየጠለዙ ይጫወታሉ። ኳሱ “ቁር” ይባላል። እንጨቱ ደግሞ – “ድቤ”። ሩር ብቻ አይደለም፤ ፈረስ ጉግስም አለ ሌላም ብዙ ዓይነት ጨዋታ…– “በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ” ይባላል። እውነትም ማንም አይቆጣቸውም። — በተለይ በዋዜማው።….

ያሆ ያሆ…ለበሞ542224_590713924288943_733926906_n
እንዞሪቴ ለበሞ ገና ለበሞ
ለበሞ ብንብና
ነባቼም በጉማ
ለበሞ ለበሞ
ድየ መሸም ይገቦ፣
ያሆ ያሆ…ለበሞ
እንዞሪቴ ለበሞ ገና ለበሞ
የገና ያበቾ፣
ያምና የርጅ ወርዶ፣
ያሆ ያሆ…ለበሞ
እንዞሪቴ ለበሞ ገና ለበሞ
በርጅ ኧርጆ
ሳምር ትፍጆ
ያሆ ያሆ…ለበሞ
እንዞሪቴ ለበሞ ገና ለበሞ
የገና ግየቶ
አዠሁ በዝ ቤቶ
ያሆ ያሆ…ለበሞ
እንዞሪቴ ለበሞ ገና ለበሞ
በገና ጨዋታ
አይቆጡም ጌታ
ያሆ ያሆ…ለበሞ
እንዞሪቴ ለበሞ ገና ለበሞ”

ይጫወታሉ። ይጨፍራሉ። … ጨዋታና ጭፈራው ለአንድ ቀን ብቻ ቢሆንም ደስታው ልዩ ነው። ጨዋታውን የሚያበቁት በዋናው በዋዜማው ምሽት ነው። ጨዋታውን ሲያበቁ ደግሞ በአካባቢው ካልወለዱ (መሀን) ሴቶች ካንዷ በራፍ  ላይ ጥለውት ለዓመቱ ልጅ ትወልድ ዘንድ ተመኝተው ነው። የጭፈራው ግጥምም በደፈናው ሲተረጎምም እንዲያ ነው የሚለው።

እንግዲህ በዚያ ቀን ያልወለደች ሴት እርሷ ደጅ ላይ ይጣልላት ዘንድ ጓጉታ ትጠብቃለች። “እኔ ደጅ ጣሉልኝ” ብላ አፍ አውጥታ የምትጠይቅም ትኖራለች። ያው የልጅ ጉጉቷ ነው የሚያስጠይቃት። እነርሱ ግን ቆመው ተመካክረው ነው ካንዷ ደጅ የሚጥሉት። የተጣለላትም ሴት እንደ አቅሟ ትሳላለች።…

…ከዚያ አምና ድቤውን ወደጣሉበት ቤት ይሄዳሉ። እዚያ ቆሎና ጠላ ተዘጋጅቶ ይጠብቃቸዋል። ስለት ከሰመረ ደግሞ በመነጋው የስለቱን ድግስ እዚያው ቤት ተገኝተው ይበላሉ።… እምነታቸው ይገርመኛል ብዙ ጊዜ ግን እንጨቱ የተጣለበት ቤት ሴት በዓመቱ ትወልዳለች። ከየቤታቸውም አምጥተውም ይጨምሩበትና ቆሎ ሲበሉ ሲበትኑ ያድራሉ። ገና ስለሆነ ቢበትኑም ግፍ የለውም። ማንም አይቆጣም።… ዛሬ ግን አይበተንም። ኑሮው አይሰጥም።

ከዚያ በዚያ ቤት ውስጥ ያድሩና ሌሊት 10 ሰዓት ገደማ ተነስተው ወጥተው እሳት ያነዳሉ። እንጨት ካልተዘጋጀላቸው አጥር ገንጥለውም ቢሆን ማንደዳቸው አቀርም። እሳት አንድደው ሲጨፍሩ ይነጋል። በገና ጨዋታ አይቆጡም ቤታ  ስለሚባል ምንም ቢያደርጉ ማንም አይቆጣቸውም። ሲነጋ ቤት ቤታቸው ሄደው ገላቸውን ታጥበው ገንፎ ይበላሉ። ተመልሰው ደግሞ አምና የጣሉበት ቤት ይሰበሰባሉ። ብዙ ጊዜ ስለምትወልድ ደስታ ነው….

ዛሬ ዛሬ በልምድ ተላልፎ በዓሉ ተረሳ እንጂ ሁሉም ትርጉም አለው። ቆሎው እረኞቹ የጌታን መወለድ ሲሰሙ ይዘው ይጓዙ የነበረውን ስንቅ በማሰብ ነው። እሳቱም የሚነደው ብስራቱን የሰሙት በሌሊት ስለነበር ነቅተው በመጠበቅ እሳት ይዘው ወደ በረቱ መሄዳቸውን በማሰብ ነው። ስለቱም ከአምላክ መወለድ ጋር ላልወለደ መልካም ለመመኘት ነው።…”

መልካም የገና በዓል!!

(ማስታወሻ: ፎቶ ከወንድም ዘሪሁን ተስፋዬ ግድግዳ የተገኘ)

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s