ኮብል ስቶን ስትለክፈኝ….

የውድ እህቴ፥ ውድ ባለቤት ቀስቅሶኝ ነገሬን በ‘ነበር’ ባያስቀርብኝ ኖሮ… ዛሬ ጠዋት አርፍዶ መነሳት ነበር እቅዴ። ከእንቅልፌ ሲቀሰቅሰኝ፥ ከሞት የመንቃት ያህል ከብዶኝ ነበረ። ሆኖምለዛሬ…ቀጠሮ የያዝንለት ጉዳይ እንዳለን ሳስታውስ፥ ሳላንገራግር ከመነሳት ውጭ ሌላ አማራጭ አልነበረኝምና ተነሳሁ።… ተነስቼም ከቤት ወጣሁ።…. እስካሁንም ከተማውን ሳስስ አለሁ።

ዛሬ ጠዋት…

ፊቴን ታጥቤ ከቁርስ በፊት ከቤት ወጥተን ወደ ጉዳያችን ቢሮ አመራን። ሆኖም ግን ጉዳያችን ያለበት ቢሮ ቦታው አልነበረም፡፡…. ማለቴ ባለቢሮዋ ቢሮዋ ውስጥ አልነበረችም። ከብስጭት በፊት ድንገት አርፍዳ እንደሆነ ብለን  ጎረቤት ቢሮ ጠየቅን።  “ዛሬ አልመጣችም…. ሰኞ ትመለሱ ተባልን፡፡” (በትህትና እና በቀጭኑ) ከትናንት ወዲያም ለዚሁ ጉዳይ ወደ ቢሮዋ ሄጄ አልነበረችምና ሰኞ መመለሷም አጠራጠረን። በመሆኑም ለጎረቤቱ ባለቢሮ ነገሩን አስረድተን ስለሁኔታው ለማጣራትምንም… ምንም አያውቅም፡፡ እሱ እቴ!  ጭራሽ…”ከትናንት በስቲያ እኮ ቢሮው ክፍት ነበር። አልመጣችሁም።” ብሎ ሸመጠ፡፡

ያን በካደበት ሁኔታ ላይም እሱን ማመኑ ከባድ ነበርና እኔ ቆይቼ ልመለስ ተስማምተን ከእህቴ ባል ጋር ተለያየን —
የእህቴ ባል ወደ ስራ….
እኔ ወደ ቤት…
“ወደ ቤት…
ወደ ማድቤት…
አንድ እንጀራ ለጎረቤት…”

ወደ ቤት የተመለስኩት ቁርስ ለመብላት ነበር፡፡ ከዚያ በልቶ ለመመለስ፡፡ ከዚያ በኋላ፥ ሲሄዱ…. ሲሄዱ… ሲሄዱ… እንዲሉ፥ እኔም ስሄድ… ስሄድ… ስሄድ… ለኮብልስቶን ስራ በየቅያሱ ወደተቆፋፈሬው ሰፈሬ ተቃረብኩኝ። ስሄድ ያልታወቀኝን ያህል ስመለስ ቀፈፈኝ። በየቅያሱ ያልተቆፈረ መንገድ ለማግኘት እንደነዳጅ (ወይ ማዕድን) ፈላጌ መቆፈር ያሰኝ ነበርና ከተቆፈሩት በአንዱ ገባሁ። መቼስ ማልጎደኔ?!…
“አልበር እንዳሞራ፣ ሰው አርጎ ፈጥሮኛል፣
አንተን ባጣሁ ጊዜ ግራ ይገባኛል፡፡” ሃሃሃ….

ይሄንን ዜማ በጠዋቱ የመዘዝነው ከቁርስ በኋላ ለምናገኛት ቡና ማንቆላጰሻ ነበር። ውይቡንዬ…ቡኒ…ቡና…ቡን…፤ ድብርታችንን ሁሉ ቡን ለማድረግ፣ ሳንጨርሰው የወጣነውን እንቅልፍ ቦታው ላይ ለመበየድ፣ እንዲሁም ቀናችንን ለማንቃትና ለማቃናት…. ቡና ጥሩ መላ! ብለን ነው። ቡና የመጠጣቱ ሀሳብ ነበር መንገዴን ያስቀየረኝ: ከወደ ቤት –> ሰፈር ወዳለ ሆቴል —> ከዚያ ፊትለፊቱ ወዳለ ቡናቤት —-> ከዚያ….

ሀሳቤን እንዲያ ብቀይርም መንገዱ ግን ያው በየመውጫ መግቢያው እንደተቆፋፈረ ነው። አማራጭ ባጣ፥ ከተቆፈሩት ካንዱ ወጥቼ ወደተቆፈሩት ወዳንዱ ዘለቅሁኝ፡፡ ከወዲያኛው የመንገዱ ጫፍ ሰዎች ቆመው ያየሉ፡ ወጣቶች… እናቶች… አባቶች… የትምህርት ቀን ስለሆነ ለአቅመ ት/ት መማር የደረሱ ህፃናትና ወጣቶች ሲቀሩ ከሁሉም አይነት ሰው ተኮልኩላል።

መጀመሪያ ጠብ ተፈጥሮ መስሎኝ…. የተፈነቃቀሉትን ድንጋዮች እያሰብኩም ‘ሜዳውም ያው ፈረሱም ያው!’… በለው! ብዬ በልቤ ሳጋግል ነበር፡፡ ከዚያ ግን ከግርግሩ ጎን የቆመ የጭነት መኪና ላይ ድንጋዮች እየተጫኑ እንደሆነ ሲገባኝ፥ ከመሀላቸው አንድ ቻይናዊ የመንገድ ሰራተኛ እንዳለ ጠረጠርኩኝ፡፡ መቼስ የእኛ ሰው ቻይኖች ሲሰሩ ማየት ይወዳል፡፡ እንዲያውም ትክ ያለው አስተያየታቸው፣ የቻይኖቹ አይኖች ጠባቦች ስለሆኑ ስለነሱ ሊያዩላቸው ነው የሚመስለው፡፡

እዚህና እዚያ እየረገጥኩኝ፥ መንገዱን አጋምሼ ስቃረብ… ድንጋይ ሰራተኞቹ ቻይኖች እንዳልሆኑ አየሁ። በዚህ ሁኔታው… ቁፋሮው እኛ በር ጋ ሲደርስ ታታሪዋ እናቴ ስራ ፈትታ ቆማ እንደማታያቸው እርግጠኛ መሆን እንደማይቻል አስቤ ፈገግ አልኩኝ፡፡  ፈገግግግ! — እናቴ ወሬ ስትከልም ታይቶኝ… ኧረ ጨዋታ እንጂ እሷስ ወሬ ጠላቷ ነው።…ብቻ ግን ድንጋዩ ሸክሙን ለመመልከት ከብበው ከቆሙት ምስኪን እናቶች ሁኔታ ውስጥ እናቴን ተመለከትኳት። ቤት ስሄድ ደግሞ ምናልባት የእናቴ ሁኔታ ውስጥ እነሱን እመለከታቸው ይሆናል።

ከመንገዶቹ ግራና ቀኝ ያሉት ቤቶች አብዛኞቹ እድሳት ላይ ነው የሚመስሉት፡፡ በተለይ ፊትለፊታቸው ከሚሰራላቸው የኮብልስቶን ሀሳብ ጋር ሲነፃፀር መድከማቸው ይጎላል። …ልዩነቱ ሱፍ በላስቲክ ጫማ እንደማድረግ ነው የሚሆነው፡፡ አዳሽ ያስፈልገዋል፡፡ ነዋሪው ቤቱን እንዳያድስ የሚፈርስ ሰፈር ስለሆነ በሚል ሰበብ ቀበሌው የእድሳት ፈቃድ የማይሰጥበት ጊዜ እነደነበር ትዝይለኛል፡፡….ለዚህም ይሆናል ያዘመሙ አጥሮች ይበዛሉ፡፡

‘አጥሮቹ እንደጠ/ሚው ጥርስ ፍንጭት ይበዛቸዋል’ ልል አልኩና ‘ተውኩት እንደገና’…- ለካስ እኔም ጥርሰ ፍንጭት ነኝ፡፡ ሃሃሃ…. – “ለጥርሰ ፍንጭት ሰው ምስጢር አትንገረው” ይልሃል አማርኛው ደግሞ! — ሳያውቅ! ሂሂሂ…. የምር ግን አጥሮቹ የሳዝናሉ፡፡ የሚንሾካሾኩ ይመስል እንደሾካካ አንዱ ወዳንዱ ሹክክ ብለው ነው የቆሙት፡፡ በዚያ ላይ የስር ጠባቂ ድንጋዮቻቸው ተፈልቅቀው ተወስዶባቸው… — በለው! ‘በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ’…– ልቤ አሁንም ያጋግላል፡፡

እንዲህ እንዲያ እያልኩ….
“ድናጋይ ለድንጋይ ዘለለች ጦጣ
እኔ አልለቅም ነፍሴ ብትወጣ…”

የሚለኝን የቡና አምሮቴን ላስታግስ ድንጋይ ለድንጋይ እየዘለልኩ ስተላለፍ….. ከፊትለፊቱ 60 ዓመት የሚገመቱ አዛውንት የቆሙበት በስርዓት ያልተቀመጠ ድንጋይ አይቼ እግሬን ጢብ አረግሁበት፡፡…. አዛውንቱን ለትንሽ ገፍቶ ሳታቸው፡፡ ጮሁ። ደነገጥኩኝ። ወዲያው ግን ምንም ስላልተጎዱ ደስ አለኝና ዝቅ ብዬ እግራቸውን እየዳበስኩ “ይቅር በሉኝ አባቴ!” አልኳቸው… አልሰሙኝም።… እሳቸው ይራገማሉ… ሰፈሩም ይራገማል… እንዳልሰማ ሆኜ ይቅርታዬን እያደጋገምክ ጎዘጎዝኩት። አልሰሙኝም ወይም አይፈልጉም ነበር። ብቻ በጣም አመረሩ…

እኔም ነገሩ ግራ ገብቶኝ “አባ እኔ እኮ አይደለሁም፣ ድንጋዩ አጉል ቆሞ ስለነበር ነው፡፡ ከተጎዱ ደግሞ ሀኪም ቤት እንሂድ፤ ግን ምንም አልሆኑምና ይቅርታዬን ተቀበሉ፡፡” …አልኳቸው፡፡ (በልባዊ ትህትና) አልሰሙኝ መሰል በቁጣው ቀጠሉ፡፡ እኔም በልቤ ተናደድኩ፡፡ ዝም ብዬ እንዳላልፍ ሰዉ ወሬ ቅርሚያ ከፊት ለፊቴ ተከምሯል፡፡ ግራ ገባኝ…

በቆምኩበት… ከጎረምሶቹ አንዱ፥ “ደግሞ ይናገራል እንዴ? መሰባበር ነበር…” ሲልና እርሱን ተከትለው እርግማኑን እንዳዲስ ሲቀባበሉት….ንዴቴን ከልቤ ወደ ምላሴ አመጣኋትና….

“እንደውም ምንም ይቅርታ አያስፈልገውም፡፡ እስካሁንም ይቅርታ ብዬ የለመንኩዎት በትህትና ነው፡፡….እንግዲህ እርሱን ካልወደዱ ደግ አደረግኩኝ!…. ድንጋይም በተፈጥሮው ሰባሪ ነው፣ እግርም ተሰባሪ ነው፡፡… እርስዎስ መጀመሪያ አይተው አይቆሙም፡፡ ተጎዳሁ ሲሉ አሳክሞታለሁ፡፡ ወንጀል ሰራ ሲሉ ይክሰሱኝ፡፡…ፓራራራ…. ታታታ…. ” ምናምን ምናምን አዘነብኩባቸው። እርግማኑ ቀጠለ… መንገዱም ተከፈተ….

ነገሩ በማበሳጨትና በማዝናናት መሀል ሰንጎኝ ስሄድ፣ የ9ኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ የገጠመኝ ነገር ትዝ አለኝ….

እንድ ግድንግድዬ ወጠምሻ ከሁለት (ወይም ከሶስት) መሰል ጎረምሶች ጋር እየተንከባለለ ይመጣል፡፡ እኔም ወሬ እየቃረምኩ ክጓደኞቼ ጋር ግራ ቀኝ እያየሁ ነበርና የምሄደውና…ከየት መጣ ሳይባል (ከየት ሄድኩ ሳይባል) ሆዱ ላይ ተቀረቀርኩኝ፡፡ እሱም እሳት ለብስ እሳት ጎርሶ፣ (ሁኔታው ከነመልኩ ዛሬም ትዝ ይለኛል)… እኔንም እንደሚጎርሰኝ ሁሉ ጠቅልሎ ይዞኝ…

“እያየህ አትሄድም?” አለኝ፡፡

….ሰደበኝ። ሲሳደብ ስላላስቻለኝ (ከመሰደብ መመታት ይቀለኛል)

“እኔ ባላይ አንተ አታይም?” አልኩት እኩል ተቆጥቼ….

ጓደኞቹ ሳቁበት…አዝኖ እንደለቀቀኝ ሁላ “አሳዛኝ” ብሎ የምንተፍረቱን ትቶኝ ሄደ።
(አማርኛ አተረፈችኝ። እነሆ ከዚያም በኋላ እንደ ነፍሴ መውደድ አረጋት ጀመርኩ ብዬ ላካብድ? ሃሃሃ…)

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s