ነበር….ነበር…ነበር…. ብዙ ነገር ነበር…. በጣም ብዙ ነገር!!….ወድቆ ባይሰበር!!….
እንስራ የሴት ወገብ ጌታ ነበር፣…ጀርባዋ ላይ ጉብ ብሎ የሚያደምቃት፣ የሚያደቃት፣ የሚያሞቃት፣ የሚጨቁናት፣ የሚያደክማት፣ የሚያዝላት፣ ነፃነቷን የሚቀማት፣ ተመልካች ጉብል የሚጠራላት፣….. – ጌታ!!… ያው ወድቆ ባይሰበር ነበር!!….
የሌሎቹም ሸክላዎች ታሪክ እንደዚያው ነው። የሸክላ ድስት፣ የጀበና፣ የአበባ ጌጥ፣ የስኒ፣ የምናምን የምናምን…. ሸክሎቹ እስኪሰበሩ ድረስ የሆነ ነገር ነበሩ። ሲሰበሩ ግን ያው ሰባላ ሸክላ ናቸው። — ገል! ገላቸው ሲደቅ ደግሞ ሸክላ አፈር ይሆናሉ። እንደ አዲስ ሊቦኩና ለሌላ ተሰባሪ ነገር ተሹመው እስኪጠፈጠፉ ድረስ!
ሰውነትም እንዲያ ነው፡፡ እስኪሰበር ድረስ ብዙ ነገር ነበር!! ….ነው!! …ይሆናል!! የሰውነት ባህርዩም ከዚያ አያልፍም። …ከባህርያቱ መካከል ደግሞ ሀዘንና ደስታ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ተፈራራቂዎች ናቸው። አንዱ ሲመጣ፣ አንዱ… አንዱ ሲሄድ፣ ሌላው… እያሉ ተካ ተካ ይጫወታሉ። ሱዚ ይጫወታሉ። በሕይወት ገመድ ዙረት ላይ ገመድ ይዘላሉ።
ገመዱን እኛው ነን የምንዘውርላቸው። – ጠበልተኞቻቸው! የገመዷ ኗሪዎች!! እስከጊዜው ድረስ…. — አንዱ የአንዱን ቦታ ወስዶ “ነበር” እስኪያሰኘው ድረስ፡፡ አንዱ ቦታውን ተቀምቶ “ነበር” እስኪባል በተራው፡፡ እንዲህ ናቸው እነሱ! እንዲህ ነን እኛ! እንዲህ ናት ህይወት!! — ላንዱ ጩቤ፣ ላንዱ ቂቤ!!
ትናንት አሸንፈን ነበር?!… አዎ ነበር! ነበር… ባይሰበር!! ሄሄሄ…. ኧረ ጨዋታ ነው፣ እንጂ መች ወደቅን? ለእኔ ከማሸነፍም በላይ ሆኖልኝ ነበር። በዚያ ላይ ብቃታቸው! ኧረ ውሸት ምን ይሰራል?… ማለፋችንን ያወቅን እለት ከተሰማኝም ብዙ የሚልቅ ስሜት ነበር። ነበር ነበር ነበር….
የምር ግን ደስታን ማሳጠር ቀላል ነው። እንዲህ ነበር፣ እንዲያ ነበር…. ቢሆን ኖሮ፣ ባይሆን ኖሮ… ኖሮ ኖሮ ኖሮ…. የሚለውን ካሰብነው ምንም የሚያስደስተን ነገር ስለማይኖር በብስጭት ተጠቅልለን እንተኛ ነበር፡፡ የእናንተን አላውቅም….እኔ ግን በሆነ ከምለው ነገር ይልቅ የሆነው በልጦብኛል።
ሌላም ጊዜ እንዲሁ ነኝ። ብስጭትን መንከባከብ አልወድም። ድብታና ድብርትን እሹሩሩ ማለት ያሰለቸኛል። በቃ ዝም ብሎ ያልሆነውን ትቶ የሆነውን መቁጠር ነው። ከሆነው ነገር ላይ የሚሆን ነገር ፈላልጎ መልቀም ነው። በርግጥ የትናንቱ ከዚያም በላይ ነበር! ደስ የሚል!!
ደስታውና ስሜታችንን ሳንሰስት መግለፃችን ለቡድናችን ብርታት እንደሚሆነው እንዲሁም ሀላፊነት እንደሚጥልበት ሳስብ ደግሞ ይበልጥ ደስስስስ… ይለኛል። ሀላፊነት የሚያስፈራ ቢመስልም ደርሶ ሲጨበት ብቃትም ነው። ውበትም ነው። ህብረትንም ያጠነክራል።… ብዙ ነዎችንም ያመጣልናል!!
ፓ… 80 ምናምን ሚሊዮን ጉጉት፣ 80 ምናምን ሚሊዮን ጭንቀት፣ 80 ምናምን ሚሊዮን ጣእር፣ 80 ምናምን ሚሊዮን ጥሪ፣ 80 ምናምን ሚሊዮን ዋይታ፣ 80 ምናምን ሚሊዮን ጩኸት፣ 80 ምናምን ሚሊዮን ስጋት፣ 80 ምናምን ሚሊዮን ተስፋ፣ 80 ምናምን ሚሊዮን ጥቀርሻ፣ 80 ምናምን ሚሊዮን ቁጭታ፣ 80 ምናምን ሚሊዮን ብድግታ፣ 80 ምናምን ሚሊዮን ድብታ፣ 80 ሚሊዮን ፍቅር፣ 80 ሚልዮን ብርታት፣….
ለ11 ሰው አደራ (ቆይቶም በ10) ተሰጥቶ… 11 ሰው ትከሻ ላይ ተጥሎ… 11 ሰው ወገብ ላይ ተዱሎ… 11 ሰው እግር ላይ ተጥሎ… ፤ በፋራም ባራዳም ሲሰምር! በጥረትም በጥበብም ሲሳካ! በአንድ መቀነት ሲቋጠር! በአንድ መስፈሪያ ሲሰፈር!….
— በአረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ!!!!!
ፓ!…. ቀላል ያምራል?!
አቦ… የማርያም ልጅ ይሁነና!!
ግን እንዴት ያል ፍቅር ነው? እንዴትስ ሊተነትኑትና ሊዘከዝኩት ይችሏል?!… ዝም ብለው ይኖሩታል እንጂ!!