የሬድዮና የቴሌቪዥን ጋዜጠኞች የሰሞንኛ ቃላቶች ትርምስ ህመም

የጀመራቸው ሰሞን “እግዚአብሔር ይማር!” እያልን ባልሰማ፣ ባላየ ነበር የምናልፈው። አሁን አሁን ግን በሽታው ከሬድዮና ከቲቢ አልፎ ህትመት ሚዲያዎች ላይ መንሰራፋቱ ሲታየን ጊዜ ወደ እኛም እንዳይመጣ በመስጋት ኧረ ኡኡኡኡ…. አልን። ለነገሩ እዚህ አካባቢም መታየት ከጀመሩ ሰነባበቱ። የኢቲቢና የኢ-ሬ ጋዜጠኞች “ህዳሴ…. ህዳሴ…. ህዳሴ…. “ እያሉ ቢያደነቁሩን ጊዜ፣ በልጅ ኮልታፋ አንደበታችን….

“ለሞኝ ለቅሶ ቅዳሴ፣
ለስንፍናቸው ውዳሴ፣
የተፈጠረ አዲስ ቃል…
— ህዳሴ!”

…. ብለን ነገሩን ወረፍ ለማድረግ ሞክረን ነበር። ያኔ ባይሰሙንም “ትራንስፎርሜሽን” እንዲሁም “አባይ ይገደባል…” “ቦንድ ይሸጣል” ምናምን ይሏቸው ሀረጋት መጥተው ለአፍታ ፋታ ሰጡን። ቅሉ ጠሚው ሲሞቱ ለቅሶ ለመድረስ ይሁን ለምን እንጃ ከያሉበት ተኮለኮሉ። ተጎለጎሉ። ‘የህዳሴው እትትትት….. የህዳሴው ናናናና….. የህዳሴው መሀንዲስ… የህዳሴው ዶ/ር… የህዳሴው ገበሬ…. ህዳሴውን ለማስቀጠል… ፒርርርር….’ ምናምን ይባልልን ያዘ። ልክፍቱ ዛሬም ቀጥሏል….

መቼስ ማልጎደኒ ብለን “ያለበት ሁኔታ ነው ያለው” የሚለውን ሀረግ ከደማችን የደባለቅንበት ሁኔታ ነው ያለው። ሃሃሃ…. ሌላው ደግሞ ተግዳሮት የሚለው ቃል ነው። ተግዳሮት… ተግዳሮት…. ተግዳሮት… — በተለይ የመንግስት ጋዜጦች፣ ጦማሮች፣ ሬድዮኖችና ቲቢው (አንድ ለእናቱ ሞኖፖላይዝድ….) የሚያቀነቅኑት ሰሞንኛ የቃል ዜማ ነው። መጀመሪያ ሰሞን በልማድ በፈረንጅ አፍ የምንጠቀማቸውን ቃላት ተመጣጣኝ የአማርኛ ቃላት በመተካት ጥረቱ ‘ተግዳሮት’ የምትለውን ቃል ጎልጉሎ አምጥቶ በወጉና በቦታው እየተጠቀመ ያላመደን የነበረው አዲስ ነገር ጋዜጣ ነበር። ከነጣዕሙና ከነውበቱ…. (በእኔ ማስታወስ)

ከዚያ አዲስ ነገርነት ተግዳሮት በማለት መስሏቸው ይሁን ባልታሰበ ወረርሽኝ ሁሉም ያቀነቅኑት ያዙ። መጀመሪያ የቀድሞው ጠሚ እንደተጠቀሟት ነው የማስታውሰው… ከዚያ ሌሎች ሚንስትሮች…. ከዚያ የክልል ሀላፊዎች… ከዚያ የአውራጃ የበላዮች…. ከዚያ የክ/ከተማ ሹሞች… ከዚያ የወረዳ ባለስልጣኖች… ከዚያ የቀበሌ… ከዚያ የመንግስትን የስብሰባ አበል የበሉ ግለሰቦች…. ከዚያ ሞዴል ገበሬዎች…ከዚያ… ማቆሚያ የለውም። በተዋረድ ለሁሉም ይደረሳል። በተለይ ቲቢና ሬድዮው አደነቆሩን በሚባል መጠን ይጠቀሙታል…

“ልማቱ ዲዲዲዲ….ተግዳሮት እንዳለው ተገለፀ።”
“አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ነነነነ….ተግዳሮት እንዳልገጠማቸው ገለፁ”
“ፓፓፓፓ……ተግዳሮት….”
“ቂሊው ቂሊው ቂሊው…. ተግዳሮቶቹን ዘርዝሮ አቀረበ…”
“ተግዳሮቶቹን ለማሻሻል….እንዲህ እንዲህ እንዲህ…. ”
“…መንገዱን በታሰበው ጊዜ ላለማጠናቀቅ የነበሩ ተግዳሮቶች….”
“የፊልሙ ኢንዱስትሪ ተግዳሮቶች…. ቋቋቋ….”
“ነዋሪዋ አይጦቹ የፈጠሩትን ተግዳሮት በማሻሻል ልማቱን ማስቀጠል እንደሚቻል ጠቆሙ።”
“ኮብል ስቶን ስራው በቶሎ ተሰርቶ አለማለቅ፣ ውሾች አካባቢያቸውን ከሌባና ከፀረ ሰላም ሀይሎች ለመጠበቅ እንዳይችሉ ከፍተኛ ተግዳሮት እንደሆነባቸው ተገለፀ” ጳራራራ…. ጴሬሬሬ…. – የምር ድንቁር አረጉን።

“አግባብ” “ሌጋሲ” “በወፍ በረር” እና “የአንበሳውን ድርሻ” ደግሞ ሌላ አዝግ ድግምግሞሾች ናቸው። ለመሀላ የተባሉ ይመስል በያንዳንዱ ዜናና ዝግጅት ላይ ይጠቀሳሉ። አግባብ የጠሚው ውርስ ነበረች። ጠሚው፣ ለሚንስትሮች፣ ለክልሎች፣ ላውራጃዎች…. እያስተላለፉ ዛሬ ያደረሷት። ከዚያ ደግሞ ማረፊያቸውን የሬድዮና የቲቢ ፓሮቶች ላይ ያደረጓት….። የምር ግን በነሱ አጠቃቀም “አግባብ” ማለት ምን ማለት እንደሆነ ዛሬም አይገባኝም።

“….ከዚህ አግባብ… ተተተተ…”
“….የልማት አግባብ…ነነነነ….”
“እእእእ….በዚህኛው አግባብ ልናየው እንችላለን።”
“ዲሪሪሪ…. በወፍ በረር እንቃኛለን….”
“…ባልደረባችን ኧከሌ በወፍ በረር እንደተመለከተው….ጡጡጡ…”
“ርርርር… ለስፖርቱ ዜና በወፍ በረር….”
“ቷቷቷቷ…በወፍ በረር ደርሰን ስንመለስ…”
“ብላ ብላ ብላ….የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል….”
“አንበሳ ግቢው አዲስ አበባ ካሉት የቱሪስት መስህቦች ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል። ”
“ለወጣቱ የስራ እድል በመፍጠር የአንበሳው ድርሻ የኮብል ስቶን ነው።”
“የቦንዱ ሽያጭ ለግድቡ ስኬት የአንበሳውን ድርሻ እንደሚወስድ አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለፁ።”

ሌሎችም ብዙ ቃላት እየተደጋገሙ እያዛጉን ያለበት ሁኔታ ነው ያለው። ሄሄሄ…. ይህንንም ሁኔታ እኔና እህቴ በወፍ በረር ያደረግነው ጨዋታ፣ ጉዳዩን በርዕስነት እናነሳው ዘንድ የአንበሻውን ድርሻ ይይዛል። ነገሩን ከዚህ አግባብ ስንመለከተው ራዕይውን ለማስቀጠልና የኢትዮጵያን ህዳሴ ለማረጋገጥ በሚደረገው እንቅስቃሴ ሁሉ ተግዳሮቶቹን ለማጥፋት እንደሚረባረብ ህብረተሰቡ የገለፀበት ሁኔታ ነው ያለው። ሄሄሄ….

…ኧረ ባካችሁ!! ….ኧረ ባካችሁ!! …ኧረ ባካችሁ!!

One thought on “የሬድዮና የቴሌቪዥን ጋዜጠኞች የሰሞንኛ ቃላቶች ትርምስ ህመም”

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s