ዛሬ አብረን ተጫወትን ነው የሚባለው፤ ቁጭ ብድግ ስንል… – ከኋላችን ያሉት ሲጮሁብን! — እኛም ከፊት ለፊትያሉት ላይ ጮኧን አፀፋችንን ስንመልስ፤ በሙከራዎች ሁሉ ስንተቃቀፍ፤ ስንጮህ፣ ስንጨርፍ… – መቼስ ከሞላ ጎደል ሁሉም ጋር እንዲሁ ነበር?!… ደግሞ ስታዲየሙ ውስጥ ያለው ሀበሻ ሲታይ አንዠት ሲበላ?! ለነገሩ እኛንስ በጭለማው ማን ለይቶ አይቶን እንጂ፥ ቀላል እናባባ ነበር?!
ብቻ ሁላችንም በየፊናችንና በየቋንቋችን….
“ያ አላህ ያ ረቢ፣
አትበለን እምቢ!”
(ሀሳቡን) እያልን በሆያ ሆዬ ስንኝ ቋጠሮ ስንማፀን…. ‘ማርያም… ማርያም…’ እያልን ስንቋጥር! ‘የማርያም ልጅ ሆይ እባክህን….’ እያልን ስንጣራ! ….ደግሞ ሁሉም ዝም ጭጭ ያሉን መስሎን ስንተክዝ!….. ብቻ ከየትም መጣ ከየት፣ ማንም ፈጨው ማንም በዚያች ቀውጢ ሰዓት ዱቄቱ ነበር የሚፈለገው። – ‘የትም ፍጪው ዱቄቱን አምቺው!”ም አይደል ተረታችን?!
ክብሩ ይስፋ! ቆይቶ ዱቄቱም ከተፍ አለልን። ደስም አለን። አያልቅ የለ 90 ደቂቃው አልቆም ይበልጥ ደስ አለን። ተመስገንም አልን!! እንደ እምቦሳ ቦረቅን። ፈነጠዝን። ዘለልን። እልልልልል…. ተመስገን!!
መሀል ላይማ ብንጣራ፣ ብንጮህ…. ጠብ የሚል ብናጣ ጊዜ…. ለጆሮ ጠብ የሚል ነገር ፍለጋ በሀሳባችን አስርት ዓመታትን ወደኋላ ተጉዘን ስነቃል ይዘን መጥተን ነበረ…
“ቀና ብዬ ባየው ሰማዩ ቀለለኝ፣
አላህንም ሰፈራ ወሰዱት መሰለኝ።”
….ይሉትን ስነቃል። የጨነቀው ያለውን። – ያልኖርንባቸውን፣ ያነበብናቸውን፣ የሰማናቸውን አስርት ዓመታት ተጉዘን…. – ምን ተስንኖን?!…. የጨነቀው እንዲሁ ነው። ከእግዜር ጋር ጠብ ደንቡ ነው። እርጉዝ ያገባል።
ግና ከምኔው ተገላብጦ፣ ከእረፍት መልስ ነገሩ ሁሉ ፉርሽ ሲሆንብን፣ ቡርቅርቅ ብለን…. ሌላ ስነቃል ፈልገን መዘዝን (ይህችን ስነቃል እንኳን መጀመሪያ ከወዳጃችን ነበር የሰማናት)
“ወረዳ ፈረመ፣
ቀበሌ ፈረመ፣
አላህ ካልፈረመ፣
ነገሩ ከረመ።”
በቀይ ወጣ፣ በአረንጓዴ ገባ፣ በቢጫ ተጠነቀቀ…. ትርጉም አጥተው ነገሩ ሁሉ በድል ሆነልን። አረንጓዴ ቢጫ ቀይም አሸበረቀች!! በግሌ ከማሸነፍም በላይ ብዬዋለሁ። አይደለም እንዴ? የምር እንዲህ ያለ የጨዋታ አቅም አለ ብዬ የት ጠርጥሬ? የት ጠብቄ? ቀላል አይደሉምሳ አያ?! እሰይ…. እንኳን ያልሆኑ። እንኳን የከበዱ። እንኳን ያከበዱን። እንኳን ያሰከሩን። እንኳን የሆነልን። አሃ! ፐርቸስቸስ ብለን አመሸናታ….- ‘እንኳንስ ዘንቦብሽ፣ እንዲሁም ጤዛ ነሽ’ ይሉም የል?!
* እንዲህ ባሉ ቀናት…
እንዲህ ባሉ ቀናት ፖሊሶች ያሳዝኑኛል።…. ፌደራል ፖሊሶች። የሚገኝ ሳይኖር ልባቸውን መሬት ከህዝቡ ጋር ጥለው፥ በመኪና አርፋ ይዘው (ተንጠላጥለው) ከተማዋን እንዳበደ ዶሮ ይዞሯታል። በእግራቸው ዱላቸውን በወግ እያርመሰመሱ ይኳትናሉ። …መቼስ መጨፈር አይፈልጉም አይባልም። ቀላል ይፈልጋሉ? አየናቸው እኮ…. ባለፈው ማለፋችንን ያወቅን ጊዜ ዱላቸውን ትተው በስታዲዮም ዙሪያ ከእኛው ጋር ሲያረግዱም አልነበር?!
ብቻ እንኳን ደስ አላቸው!!
* * እንዲህ ባሉ ቀናት…
እንዲህ ባሉ ቀናት የኤርታ ጋዘጤኞች ያሳዝኑኛል። በተለይ የቲቪው። ውይ… ዝም ብለው እኮ ነው የሚቀባጥሩት። እኩዮቻቸው ሲቦርቁ እነሱ የእነሱን ቡረቃ ፖሊቲሣይዝ ያደርጉታል። ያድርጉታ! – ቀረባቸው። ግን እንዲያው እንዲያ ሲባክኑና ሲካለቡ ሳይ አንዠቴን ይበሉታል። የሆድን ስፋትም ቁልጭ አድርገው ያሳዩኛል። ቀላል ሰፊ ነው አያ?!
ግን ምናለ እንዲህ ባሉ ቀናት ጣቢያውም ስራ ቢያቆም? ለእርሱም ክብር ነው። …መቼም ‘በለፈለፉ በአፍ ይጠፉ!’ ነውና ነገሩ ብዙ ባወሩ ቁጥር ብዙ ይገመታሉ። እነሱ ደግሞ እንዲህ ባሉ ቀናት ብዙ ያወሩ ዘንድ ግድ ነው። ሆድ ነዋ… እንጀራ…. – ድንቄም እቴ!
ብቻ እንኳን ደስ አላቸው!!
* * * እንዲህ ባሉ ቀናት…
እንዲህ ባሉ ቀናት ህዝቡ አንዠት ይበላል። በቋፍ እንዳለ ሁሉ ትንሽ ነው የሚበቃው። ከ__ እስከ__ ሳይል ወጥቶ፣ ከ__ እስከ__ ሳይል ቅርጥፍጥፍ አርጎ ነው የሚበላው። የምር… እምባ አማጭነቱ ያይልበታል። በቃ ሊለያዩት ያሰቡትን ሁሉ አንድ ሆኖ ያበሳጫቸዋል። አቅሉን ስቶ ይቦርቃል። ማንም ማንንም አቅፎ ይስማል። ጎዳናው ላይ ተጥለቅልቆ ጎርፍ ይሰራል።
— የሰው ጎርፍ! የነፃነት ጎርፍ! የፍቅር ጎርፍ! የጉጉት ጎርፍ! የናፍቆት ጎርፍ! የምኞት ጎርፍ! የትልቅነት ተስፋ ጎርፍ! የአገር ስስት ጎርፍ! አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ጎርፍ… ልጅ አዋቂ፣ ሴት ወንድ፣ ሙስሊም ክርስቲያን፣…ምንም ሳይመራረጥ ሰውነትና ኢትዮጵያዊነት በቅተውት እርስበርሱ ይንቆላለጫል።
ኧረ እሰይ ሆነለት። እንኳን ደስ አለው!!
* * * * እንዲህ ባሉ ቀናት….
እንዲህ ባሉ ቀናት ግራ ገብቶኝ እንከላወሳለሁ። የምይዝ የምጨብጠው ነው የሚጠፋኝ። ውይ….ግራ ሲሉኝ – ቀኝ! ቀኝ ሲሉኝ – ግራ!… በቅጡ አልሰማም። በቅጡም አላወራም። እንዲህ ደስ ሲለኝ ከጣሪያ በላይ እጮሃለሁ። ወይ ደግሞ ከመሬት በታች ዝም እላለሁ። ኧም ጭጭ!… ኧረ ምኔም አይታወቅ። ሆኖም ግን አገላለፄ ይለያይ እንጂ ደስታ የእኔው ነች። የሰዉን ሁኔታ ሳይ ደግሞ እንባዬ ቅርርር ይላል። ችሎ ባይወርድም ቅርር ይላል… እንደ ስስ… እንደ ሆደ ቡቡ…. – ነኝ እንዴ? የራሴ ጉዳይ! ዛሬ ግን ችሎ ፈሰሰ… – ግን መነፅራም መሆኔ በጀኝ አያ!
ኧረ እንኳን የሆነልኝ። እንኳን ደስ ያለኝ!!
* * * * * እንዲህ ባሉ ቀናት. . .
እንዲህ ባሉ ቀናት የፌስቡክ ወዳጆችን ማየት ደስ ይላል። (ያው በወል ከህዝቡ ቢደመሩም)… በፅሁፍ ሲታዩ ደስ ይላል። ሲነበቡ ያምራል። ዜማው ሁሉ አንድ ነው። ወሬው ሁሉ ተቀራራቢ ነው። ጉዳዩ ሁሉ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ላይ ያጠነጥናል። ከዚህ ቀደም በሀሳብ ከእኛ አይገጥሙም የምንላቸው እንኳን እንዲህ ባሉ ቀናት ልክክ ነው የሚሉት። የእኛኑ ሙዚቃ ይሞዝቃሉ። እኛም የእነርሱን ሙዚቃ እንሞዝቃለን። – ሲገርም! ለምን? ምናምን… ብለን በማጣራት አንደክምም። አንድም አይደለን?!
ኧረ እንኳን ሆነልን። እንኳን ደስ አለን!!
* * * * * * እንዲህ ባሉቀናት. . .
እንዲህ ባሉ ቀናት እናቴን ማየት ደስ ይለኛል። እርሷን ዝም ብሎ ማዳመጥ። የሆነ የሆነ ነገር እያወሩ ብዙ ማስወራት። ውይ! ስታውቅበት!…. እናቴ አልተማረችም። ‘ዐይኔ አይሰጠኝም’ ብላ ሞክራ ትተወዋለች እንጂ በስሱ ማንበብ ትችላለች። (ለምሳሌ “አዲስ ነገር” ጋዜጣ ታነሳና “አዲስ ነገር” የሚለውን ካነበበች በቃ!! …ስትፅፍ ከስሟ አትዘልም። ‘ዐይኔ የት ያያል?’ ትላለች። …ግን እርሱንም ‘እድሜ ለመንግስቱ ኃ/ማርያም እያለች ነው።’ በመንግስቱ ጊዜ መሰረተ ትምህርት ተምራ ነበር። ደግሞ ጎበዝ ሆና ትሸለም ነበር።
ያም ሆነ ይህ ግን ‘ተማርን’ የሚሉ ጎረቤቶቻችንን አለቅልቃ ትበልጣቸዋለች። (ወይም ለእኔ እንዲያ ይታየኛል።) እናቴ ስለሆነች አይደለም። በሀቅ ነው የምናገረው። የእኔ ሁለት ዲግሪዎችንም ችላ አፈር የምታበላቸው እናቴ ብቻ ነች። በፊቷ ያሸነፍኳት ልምሰል እንጂ ከእርሷ ጋር ማውራት ስጀምር ልቤ በቂጡ ቂብ ይላል። አይችልበትም።
እንደ እኔ መፅሀፍ አታጥቅስም። (ምናልባት ምዕራፍ ቁጥሩን ትታ መፅሀፍ ቅዱስን?!…እርሱንም ቢሆን የእምነት አባቶቿ ካስተማሯት አስታውሳ።) መጣጥፍ አታውቅም። ጋዜጣ የለ! መፅሄት የለ!…. ግን ‘መቼስ ካንተ አላውቅም… አልተማርኩም’ እያለች ልክ ልኬን ትነግረኛለች። ደስ ይለኛል። ከዚያ በላይ ደግሞ ስለምታሳምነኝና በአመክንዮ ስለምታምን በጣም ደስ ይለኛል። ስታምንም አታስቸግርም። ራሷን ከጊዜውና ከዘመኑ ጋር ማስተካከል ማንም አይችላትም። የማታውቀው ነገር ዛሬ ቢነገራት፣ ከዛሬ በኋላ ትተገብረዋለች… – ብቻ ትመንበት!
ገፍታ አለመማሯ ቢቆጫትም አትጠላውም። እንዲያውም ታመሰግንበታለች።…. በዚህ ረገድ ከ10 ዓመት በፊት ያለችኝን አልረሳውም። ሳጥኗን ከፍታ መሰረተ ት/ት ስትማር የተሸለመችውን የምስክር ወረቀት አውጥታ አየችውና በቁጭት “አዪ… ባላቋርጠው ይሄኔኮ እጨርስ ነበር።” አለችኝ።…. ወዲያው ደግሞ “ለነገሩ እንኳን አልተማርኩ። ደግሞ ልጅ አታብዙ የሚል ትምህርት ተምሬ አልወልዳችሁም ነበር ይሆናል።” ብላ አጣጥፋው ወደቦታው ወረወረችው።
እኛ ነን ማመስገኛዎቿ። እኛ ኮምፑተር ወይም መፅሀፍ ገልጠን ጓደኞቿ ቡና ሊጠጡ ሲመጡ ድምፃቸውን ዝግ እንዲያረጉ ቀስ ብላ ተጠቁማቸዋለች።… ‘የእኔን ስራ ነው የሚሰሩት…መጦሪያዬን…’ ትላቸዋለ። [ሲጀመር እኛ ቤት ካለን ጠይቃን ነው ቡናም የምታፈላው] … (ከመስመር ወጥቼ ቀባጠርኩ አይደል?)
ብቻ እንዲህ ባሉ ቀናት እርሷን ማየት ደስታን ይጨምራል። ዛሬ ግን ቤት አይደለሁምና አላየኋትም። ሆኖም ግን መገመት አይቸግረኝም። እንዲህ ያሉ ጨዋታዎችን ስናይ አብራን ትቀመጣለች። ሲጀመር ጀምሮ ተማፅኖዋ ብዙ ነው። “እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሁን።” ብላ ጀምራ ብዙ እያለች ትቆያለች። ማን ከማን እየተጫወተ እንደሆነ ብትጠየቅ ግድ የላትም። “ኢትዮጵያ አለች አይደል?” ትላለች። መልሱ “አዎ” ከሆነላት ሌላው ትርፍ ነው። “ቢሆንም ባይሆንም አገር ነው መቼስ” ትላለች…
አንድ አስር ደቂቃ እንደታየ ደግሞ ጭንቀቱ አላስችል ቢላት ብድግ ብላ ወደ መኝታዋ ለመሄድ ትነሳለች። “እግዚአብሔር ይሁናቸው። ጭንቀቱ ገደለኝ….ልተኛ። ካገቡ ግን ቀስቅሱኝ…” ብላ…። ግን ችላ አተታኛም። – እርሷም እኛም እናውቃለን። ከመግባቷ ሙከራዎችን ምናምን አይተን ድምፅ ካሰማን አያስችላትም… ድምፅ ባናሰማም አያስችላትም። መጀመሪያ መኝታዋ ሆና የአንዳችንን ስም ትጣራለች። ማንም አልሰማ ሲላት ደግሞ ከነፒጃማዋ ከመኝታዋ ብቅ ትላለች። የመጀመሪያ ጥያቄዋ “አገቡ?” የሚል ነው…
ከዚያ ደግሞ ዐይን ዐይናችንን ታይና መምከር ማፅናናት ትጀምራለች። “አይዟችሁ አባኤ…. ለነርሱ ካለው አይቀርም። አትበሳጩ።” ምናምን ብላ በተራ በተራ እያየችን ትደጋግመዋለች። – ሰማናትም አልሰማናትም! ለርሷ ጭንቀቱ የሁለት እዮሽ ነው። — አንድም ስለ ኢትዮጵያ፣ ሌላም ስለልጆቿ።…. ‘የወለደ አልፀደቀ’ እንድትል ራሷ።
ብቻ እንዲህ ወጣ ገባ ስትል እንቅልፏንም በቅጡ ሳታንቀላፋ ከእኛ ጋር ታመሻለች። ጨዋታው ሲያልቅ ደግሞ የእኛን ጨዋታ እንቀጥላለን። ዛሬ ግን ናፍቃኛለች። ክፉኛ!! ልደውልላትም ብሞክር ኔትዎርክ እምቢ አለኝ። ደስታዋ ግን አይጠረጠርም….
ኧረ እንኳን ሆነላት! እንኳን ደስ አላት የእኔ እናት!!
* * ኳሱ ፍቅሯ….
ታይቶኝ ከባህር ስትጠልቂ፣ ከምድር ከሰማይ ስትርቂ፣
ታይቶኝ ከነፋስ ስትረቅቂ፣ ከፀሀይ ጨረቃ ስትደምቂ፣
ሲጠጣ እንዳደረ ሰው ሲጨልጥ ውስኪ አረቂ. . .
ጢንቢራዬን የሚዞረው፣ ሰውነቴ የሚርደው፣
ኧረ በምን ነው ዓለሜ? በምን ያል የቀን ለከፋ፣
ስምሽ ሲነሳ ‘ሚያልበኝ፣ ነገር ዓለሜ ሚጠፋ?
በዐይኔ ዞሮ የሚያስቀኝ. . .
ንቅሳትሽ፣ ድምድማትሽ – አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ፣
ኩል፣ ቀለምሽ፣ ውቅራትሽ – አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ፣
ብር አምባርሽ፣ ድሪና አልቦሽ – አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ፣
ጥበብ ቀሚስ፣ ውስጥ ልብስሽ – አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ፣
የአንገት ልብስሽ፣ መቀነትሽ – አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ፣
ነጠላ ጋቢ፣ ኩታ ጃኖሽ – አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ፣
በዐይኔ ዞሮ የሚያስቀኝ. . .
ነበር ያልነው ጠዋት? አሁን ሌላ አንጨምርም። ይህንኑ እየደገምንና “አለ ገና” እያልን እንስቃለን…
እንኳን ሆነልን!! እንኳን ደስ አለን!!!