ተመስገን! መቼስ ዞረው አይገቡ የለ እኩለ ሌሊቱ አልፎ ቤት ገባሁ። እኛማ አብሮ መጫወት ልምዳችን አይደል? … ዛሬም አብረን ተጫወትን ነው የሚባለው መቼስ። ቁጭ ብድግ ስንል… እንደ ልማዳችን በየፊናና ቋንቋችን ስንቋጥር፣ ስንፀልይ….
“የአላህ ያረቢ፣
አትበለን እምቢ!”
እያልን በሆያ ሆዬ ስንኝ ቋጠሮ ስንማፀን…. ‘ማርያም… ማርያም…’ እያልን ስንቋጥር! ‘የማርያም ልጅ ሆይ እባክህን….’ እያልን ስንጣራ! ….ደግሞ ሁሉም ጭጭታቸው ፀንቶ…. ጎሉ እየሄደ ሲነከር – ስናዝን፣…. ሲደገም – ስንከፋ፣…. ሲሰለስ…. ጭው ብሎብን! ፍዝዝ ቅዝዝ ብለን ተስፋ መቁረጥ ላያችን ላይ ሲደፋ… ሰማዩ የተከለበሰብን ሲመስለን…
እንደልማዳችን አስርት ዓመታትን ወደኋላ ተጉዘን ስነቃል ይዘን መጥተን ነበረ…
“ቀና ብዬ ባየው ሰማዩ ቀለለኝ፣
አላህንም ሰፈራ ወሰዱት መሰለኝ።”
….ይሉትን ስነቃል። – ያልኖርንባቸውን፣ ያነበብናቸውን፣ የሰማናቸውን አስርት ዓመታት ተጉዘን…. – ምን ተስንኖን?! የጨነቀው እንዲሁ ነው። ግና ደግሞ በጩኧት ብቻ አይደለምና?!….
‘የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው!” ብለን ብንጮህም ዱቄቱን አየሁ የሚል ጠፋ። አልቀናንም ወይም አልቻልንም… እናም ቡርኪና ፋሶ አፍሳ ወስዳዋለች። ምናልባት እርሷ ከእኛ የተሻለ አስፈልጓት ሊሆን ይችላል። ወይ ደግሞ ከእኛ በበለጠ ተገብቷት ሽልማቷ ሆኖላት ይሆናል። ብቻ ግን አልቀናንም!! በዚያም የብዙው ሰው የገፅ የአየር ንብረት ተለዋወጠ። ፀባያችን ከመቅፅበት ከፍ ዝቅ አለ።
ቀላል በትምክህት ደንፍተን ነበር አያ?! ደግ አደረግን!…. መደንፋት እንደው ከመልካም ምኞት ነውና ምንም ጉዳት የለውም። ቅሉ ወሰኑን አልፎ እርግጠኝነትን ሲያጎናፅፍ፥ ላልሆነ ብስጭትና ሀዘን ይዳርጋል እንጂ። እኛ ብንቋጥርም። እኛ ብንደነፋም። በረኛቸው በቀይ ቢወጣም። ቢጫ ቢፃፍ። ምን ቢባል… አላህ ዛሬ የፈረመው ለእኛ አልነበረም። ለቡርኪናፋሶ ነው።
“ወረዳ ፈረመ፣
ቀበሌ ፈረመ፣
አላህ ካልፈረመ፣
ነገሩ ከረመ።” ብለንም አልነበር?!….
….እነሆ ነገራችን ከረመና ለሌላ የቤት ስራ አቀብሎን ሄደ። ከቤት ስራው መሀል ግን የእኛን ሚና የዘነጋነው ይመስላል። ‘ባርሴሎና’ ምናምን ብለው ቡድናችንን ሲያንቆላጵሱት ጊዜ ላለፉት 31 ዓመታት ሰው ሲራመድ ቁጭ ማለታችንን ረስተነዋል። በመዳህ መስመር ውስጥ እንኳን ሳንውል ከአፍሪካም አፍሪካ የቆዳ ቀለምና ምናምን እያማረጥንና እየተከፋፈልን ስንደግፍ መኖራችንን ዘንግተነዋል።
ወደድንም ጠላንም ‘ወፌ ቆመች’ በመባል ላይ ያለ ቡድን መሆኑን ግን ሁላችንም ማወቅ ያለብን ጉዳይ ይመስለኛል። ቆሞ መሄድ እንዲህ የአንድ ሌሊት ክስተት አይደለም። ልጅ መቆም (መዳህ) ጀምሮ ‘ወፌ ቆመች’ ሲባል እንኳን ብዙ ጊዜ ወድቆ ይነሳል። አንዴ ደፋ አንዴ ቀና ሲል እናቱ (ቤተሰቦቹ) በብስጭት ተስፋ ቆርጠው ወይም ደግሞ በመሰልቸት ችላ ብለው ቢተውት ልጁ አረንጓዴያም እግረ ስንኩል ነው የሚሆነው። ዘለዓለሙን የሰው ልጅ ቆሞ እየሄደ ሲጫወት በጉልበቶቹ እጥፍጥፍ ብሎ በራፍ ላይ ተቀምጦ ተመልካች ነው የሚሆነው።
ቡድናችንንም ከዚያ በተለየ ማሰብ ያለብን አይመስለኝም። ገና ወፌ ቆመች እየተባሉ ነውና አብረን እንበላቸው። ድክመታቸውን አብረን እንድከምና እናግዛቸው። ‘Rome wasn’t built in a day’ ይለናል Sam cook…… ስለዚህ የቡድን ግንባታው ላይ እንረባረብ። መሰረቱ ላይ ነንና መሰረቱ ያምር ዘንድ አብረን ብንበረታ በእውነት ነገ ትልቅና ጠንካራ ቤት ይሰራ ይሆናል። በቤቱም እኛ እንደልብ ተንሰራፍተን ብዙ እንኖርበት ዘንድ ቢዘገይ እንኳን ለመጪው ትውልድ ኩራት ነው። (ትናንት ተገንብቶልን ቢሆን ኖሮ ዛሬ መሰረት ማውጣት ላይ አንደክም እንደነበር ልብ ይሏል።)
ውድድሩን በጥሩና ደረጃውን በጠበቀ ብቃት የጀመሩትን ልጆቻችንን….
“ወፌ ቆመች
አልደከመች”
…እያልን ከጎንና ከጎን፣ ከትከሻና ትከሻ እንደግፋቸው። ድጋፋችንን ሲያዩ በሂደት ይበረታሉና!!
* እንዲህ ባሉ ቀናት…
ፖሊሶች አያሳዝኑኝም። እንኳን አላግባብ በስሱም እንኳን የሚቦርቅ ደጋፊ የለምና ምንም የሚጠብቁት የላቸውም። በመሆኑም ከየትም ወደየትም አይርመሰመሱም። ዝም ብለው ጥግ ጥጉን ይዘው ይቆዝማሉ። ስራ መፍታታቸው ደስ የሚላቸው አይመስለኝም። ያው እነሱ መሮጥ፣ ማሯሯጥ አይደልም ስራቸው? የራሳቸው ጉዳይ…. ግን አያሳዝኑኝም።
** እንዲህ ባሉ ቀናት…
እንዲህ ባሉ ቀናት የኤርታ ጋዜጠኞች አያሳዝኑኝም። የቲቢውም ሆነ የሬድዮው ያው ናቸው። ድንገት ሲነቁ – ‘እንዲህ መሆን ነበረበት አልነበረበትም ብለው ሂስ ቢሰነዝሩ ነው።’ እንደልማዳቸው ሲፈዙ ደግሞ – ‘ሽንፈቱ ልማቱን እንደማያደናቅፍ አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለፁ።’ ‘ቡርኪናፋሶ 4 ጎል ማስቆጠሯ የፀረ ልማት ሀይሎች እጅ እንዳለበት ኢዜአ ዘግቧል’… ምናምን ቢሉ ነው። ወይ ደግሞ ምንም እንዳልተፈጠረ ሁሉ ወደ ሰርክ ጥዝጠዛቸው (propaganda) ያመራሉ። ያም ሆነ ይህ ግን አያሳዝኑኝም።
*** እንዲህ ባሉ ቀናት…
እንዲህ ባሉ ቀናት ህዝቡ አንዠት አይበላም። ይልቅስ ቆሽት ያቃጥላል። ያበሳጫል። የስሜታዊነቱ ልክ ጉልጉል ብሎ ባንዴ ይዘረገፋል። ለምቦጩም አብሮ ይዘረገፋል። ለምቦጭ ባይኖረው እንኳን ሞጌው ከበፊቱ በላይ ይሞግጋል። አጎብዳጅ መስሎ ይታያል። (ወይም ቀድሞም አጎብዳጅና ወረተኛ ነበረ።)…. ከብርቱው ጋር መሰለፍ ነው ህልሙ።
እናም ብርቱ ያለው ሲሰንፍበት ያዝናል። አንገቱን ይደፋል። አልፎም ተርፎም ይሳደባል፣ ትናንት ያከበረውን ያንኳስሳል። ድካሙን ሊደክምለት ቀርቶ ‘አይዞህ ወንድሜን’ ሊለው አይችልም። ሊለያዩት ለሚያስቡት ፊት ይሰጣቸዋል። ሁሉም በየስራ መስኩ ሰርክ ስኬታማና አንደኛ የሆነ ይመስል ብሔራዊ ተወካዮች ላይ ለመዘባበትና ብቃታቸውን ለማብጠልጠል ህዝቡ አንደኛ ነው።
[ክፍል ውስጥ 1ኛ ከሚወጣ ሰቃይ ተማሪ፣ መጨረሻ እስከሚወጣ ተስፋቢስ ተማሪ ድረስ፤ መስሪያ ቤት ውስጥ ከሚመሰገንና ከሚሸለም ጎበዝ ሰራተኛ፣ አልማጭና ስራው ላይ ቸልተኛ እስከሆነ ሰራተኛ ድረስ…. ሁሉም ብሔራዊ ተወካዮችን ማብጠልጠል ላይ ይበረታል። ነገሩን ለመረዳትና በእነሱ ቦታ ሆኖ ለማሰብ ጊዜ የለውም።] ለምን ይህ ሆነ? አልልም… ግን ይገርመኛል።
**** እንዲህ ባሉ ቀናት….
እንዲህ ባሉ ቀናት ግራ ገብቶኝ እንከላወሳለሁ። የምይዝ የምጨብጠው ነው የሚጠፋኝ። ….ግራ ሲሉኝ – ቀኝ! ቀኝ ሲሉኝ – ግራ!… በቅጡ አልሰማም። በቅጡም አላወራም። በብዙ ምክንያቶች ሆዴ ይንቦጫቦጫል። ሰው ማየት ያስጠላኛል። እንባዬ ቅርር ይላል። በሆነው በአንዱ (በሽንፈታችን) አጮልቄ ብዙ ነገር ነው የማየው። ዛሬም በህዝቡ ውስጥ ብዙ ነገር ነው ያየሁት። በተጫዋቾቹም ውስጥ ብዙ ነገር። በተጫዋቾቹ ውስጥ ደግሞ ራሴን አያለሁ።
***** እንዲህ ባሉ ቀናት….
እንዲህ ባሉ ቀናት ተጫዋቾቹ (ብሔራዊ ተወካዮቹ) ያሳዝኑኛል። በጣም አንዠቴን ይበሉታል። ውጤቱን ማጣታቸው ከማንም በላይ አንደኛ የሽንፈቱም የወቀሳውም ገፈት ቀማሾች ናቸውና ከማንም በላይ እንደሚያዝኑ ሳስብ ሀዘኔ ይብስብኛል። ሰማንያ ሚልዮን ጉጉት፣ ተስፋ፣ ምኞት፣ ጥም፣… ተሸክመው ነው የሚንቀሳቀሱት። …የምንበላውን ነው የሚበሉት።
በሚጫንባቸው ሀላፊነት ልክ ምግብ እንኳን በቋሚነት እንደሚለወጥላቸው እንጃ። መዘጋጃውና መለማመጃውም ቢሆን እንዳቂሚቲም ቢሆን ምቹ አይደለም። በአንፃሩ ፖለቲካዊም ማህበረሰባዊውም ጫና እነርሱ ላይ ይበረታል። ዛሬ እንኳን ‘አንድ ጎል ሲገባ ማሊያውን ገልጠው ቲሸርት እንዲያሳዩ ታዘዋል’ መባሉን ሰምቼ ጉድ ብዬ ነበር።
ያም ሆኖ ሳለ ሀላፊነት መቀበላቸው በርግጥ ኩራት ቢሆን እንጂ ጉዳት የለውም። ግን እንዲህ ሽንፈት ሲመጣ ባይተዋርነታቸው ድቅን ይልብኝና ግብግብ ያረገኛል። ከሚመጣው ነገር ይልቅም ያለፈው ነገር ላይ እያጠነጠኑ “እንዲህ ቢሆን ኖሮ” እያሉ ሲበሳጩና ራሳቸውን በፀፀት ሲጎዱ ከሚመጣው ነገር ላይ ብዙ እንደሚያጎድሉ ሳስብ ደግሞ ይበልጥ አዝናለሁ።
እንደዚያ የሚያደርጉት ደግሞ አገራቸውን (ያው ከነኗሪው ነው) በጣም ስለሚወዱና ስለሚያከብሩ መሆኑ ይሰማኝና ይበልጥ ያሳዝነኛል። እኛ አገር አኗኗራችን ቅርብ ነው። በመሆኑም ስንወቃቀስ እንኳን የመጎሻሸም ያህል ህመሙና ስሜቱ ይሰማናል። እነሱም ያንን ይመስለኛል ይበልጥ ፈርተውት አቅማቸውን የሚጨቁንባቸው።… ብቻ ግን ያሳዝናሉ!!
****** እንዲህ ባሉ ቀናት. . .
እንዲህ ባሉ ቀናት ወደ
ወደ ማህበራዊ ድህረ ገፆች መምጣት ያስጠላኛል። ስሜታዊው ብዙ ነው። አግባብ ያልሆኑ ፀያፍ ስድቦችን አያለሁ። ለምሳሌ አሁን ወዲህ ብቅ እንዳልኩ ‘ብታምኑም ባታምኑም በቁም ሞተናል።’ አለ መንግስቱ ኃ/ማርያም… የሚል update ተመልክቼ ደበረኝ። እርግጠኛ ነኝ የለጠፈው ሰው የመንግስቱን ታሪክ አያውቅም። ቢያውቅ ኖሮ መንግስቱ ንፁሀንን ዝም ብሎ ሲገድል ይበልጥ መዋረዱን በቁም መሞቱን ያውቅ ነበርና ለጥቅስ እርሱን አይጠራም ነበር።
ዝቅ ስል፥ “ዘሪሁን ዘርህ ቡን አይበል፥ እጅ አለኝ ብለህ አገር ታቈርጣለህ…ጀማልም ያው ነህ ለአድዋ ሰማእታት የተዘፈነ ዘፈን እየሰማህ ነው እንዴ ደቡብ አፍሪቃ የገባሀው? ምንታረገው እርግጫ እየተጫወትክ አድገህ…” የሚል ሌላ update ተመልክቼ ሌላ አዘንኩ። (በመሰረቱ ማንም በዘሪሁን ቦታ ላይ ስላልነበረ የሚሰጠው ነገር ከአስተያየት ስለማይዘል ስድብ ሊቀላቀልበት አይገባም።) ነውር ያይልብናል። የሀዘን ድባብ ያጠላበታል። ቅሬታ። ዝምታ። የሆነ ውሀ የተርከፈከፈበት ነው የሚመስለው። ለያውም የጎርፍ ውሀ…
******* እንዲህ ባሉቀናት. . .
እንዲህ ባሉ ቀናት እናቴን ማየት ደስ ይለኛልም አይለኝምም። ከሀዘን ብዛት ትደነግጣለች። በጣም ታዝናለች። አሁንም ሀዘኗ የሁለት እዮሽ ነው። — አንድም ኢትዮጵያ በመሸነፏ (እንደማናችንም)። ሁለትም እኛ ልጆቿ እንደሚደብረን ስለምትገነዘብ። ዛሬም በውድቅቱ ቤት ስገባ ድምፅ ሰምታ ከእንቅልፏ ነቅታ ጠርታኝ….
“እንዴት ሆኑ?… እኔ አንድ ሲገባባቸው ከዚያ በላይ እንዳልደነግጥ ብዬ እረፍት ላይ ተኛሁ” አለችኝ። የሆነውን ነገርኳት። ነቃ አለች። አዘነችም። ማዘኗን ያወቅሁት ከ “አዪዪዪ…” አባባሏ ድምፅ ነው። ወዲያው በተኛችበት ማፅናናቷን ቀጠለች። ….
“አይዞህ አባ! ምን ይደረጋል። ሁልጊዜ ፋሲካ የለም። እነዚያም እኮ እንዲህ ጓጉቶ የሚጠብቃቸው ሰው አያጡም።” ….ወዲያው መለስ ብላ “ግን አበቃላቸው?” አለችኝ። እንዳላበቃላቸው ነገርኳት “ተመስገን!… ታዲያ አንዳንዴ መሸነፍ እኮ ጥሩ ነው። ካለዚያ ጉረኛና ሰነፍ ያረጋል።” አለችኝ።…. (ይገርመናኛል! ሩጫ ስንሸነፍም እንዲህ ነች።)
*** ኳሱ ፍቅርሽ…
ታይቶኝ ከባህር ስትጠልቂ፣ ከምድር ከሰማይ ስትርቂ፣
ታይቶኝ ከነፋስ ስትረቅቂ፣ ከፀሀይ ጨረቃ ስትደምቂ፣
ሲጠጣ እንዳደረ ሰው ሲጨልጥ ውስኪ አረቂ. . .
ጢንቢራዬን የሚዞረው፣ ሰውነቴ የሚርደው፣
ኧረ በምን ነው ዓለሜ? በምን ያል የቀን ለከፋ፣
ስምሽ ሲነሳ ‘ሚያልበኝ፣ ነገር ዓለሜ ሚጠፋ?
በዐይኔ ዞሮ ያስቀኛል. . .
ንቅሳትሽ፣ ድምድማትሽ – አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ፣
ኩል፣ ቀለምሽ፣ ውቅራትሽ – አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ፣
ብር አምባርሽ፣ ድሪና አልቦሽ – አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ፣
ጥበብ ቀሚስ፣ ውስጥ ልብስሽ – አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ፣
የአንገት ልብስሽ፣ መቀነትሽ – አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ፣
ነጠላ ጋቢ፣ ኩታ ጃኖሽ – አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ፣
በዐይኔ ዞሮ ያስቀኛል. . .
/ዮሐንስ ሞላ/
ብለን ነበር ባለፈው። አሁንም ሌላ አንጨምርም። ይህንን እያቀነቀንን የቀን ትሻልን እንናፍቃለን።
መች ተነካና?
ይቀራል ገና!!
እያልን በቀሪውም አምላክ ይረዳን ዘንድ ጥበቡንም በተጫዋቾቻችን ላይ ያደርግ ዘንድ እንማፀናለን።
አሜን!!