‘ወፌ ቆመች’ እንባባል

ባለፈው ከቡርኪናፋሶ ጋር ገጥመን የተሸነፍን እለት እናቴ ስታፅናናኝ “ዝም ብሎ ሲሳካማ ሰነፍና ጉረኛ ያደርጋል።” ብላኝ ነበር። ያኔ በ’ከየትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው’ ስሜት ውስጥ የነበርኩ ቢሆንም፣ ቆይቼ ዛሬ ሳስበው እውነቷን ነው። ከብዙ እድልና ጥረት በኋላ የነገሮች አለመሳካት ለትልቅ የቤት ስራ ትቶ ሲያልፍ ደግሞ ቀጣዩ ስኬት ይበልጥ የሚያኮራና የሚያስመካ ይሆን ዘንድ እድል የሚሰጥም ነው። – ልብ አብሮ እስካለ! አሸማቃቂውስ የቤት ስራውን ለመስራት ስንሰንፍና ስንለግም ነው።

ቻይኖች እኛ አገር መጥተው እንዲህ እንዳሸን ሳይፈሉ በፊት (ሃሃሃ…) ‘አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር ርቀት በ1 እርምጃ ይጀመራል’ የሚል ምሳሌያዊ ንግግር ነበራቸው። መቼስ እኛ በቻይና ምርት መገልገል ብርቃችን አይደለምና ዛሬም እንዋሳቸው። — ‘አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር ርቀት በ1 እርምጃ ይጀመራል።’ እነሆ እርምጃችን ተጀመረና ‘ወፌ ቆመች’ እንባባል ያዝን። ዋጥነውም አነቀንም፥ ላለፉት 31 ዓመታት በቅምጥ ነበርን።

ያለፉትን 31 ዓመታት ችላ በማለትና የሚመጡትን 31 ዓመታት በማሰብ፥ ከመወቃቀሱና ከመመካከሩ ጎን ለጎን ጥንካሬ ያልናቸውን ማውሳቱና ስለጥንካሬው ሁሉ ማመስገኑ… አንድም ብርታት ይሰጣል። ሌላም ደግሞ ተስፋ መቁረጥን በማስቀረት ጠንካራ እሴቶችን (ጎኖችን) አጥብቆ ለመያዝ ይረዳል። ማንም በሰራው ስራ ቢጣጣልና በሀሳቡ ቢናቅ ግን ራሱን ከመጥላት ይጀምርና ልግመኝነትን ያጎለብታል። በቀልና ጥላቻንም ገንዘቡ ያደርጋል። – ‘ሆድን በጎመን ቢደልሉት ጉልበት በዳገት ይለግማል’ ይባላልና… ጠንካራ ጎኖችን ማውሳቱም በማሻሻል/በመለወጥ/በመገንባት ላይ ያተኮረ ቢሆን መልካም ነው።

ኢንሻ አላህ! – ከኖርነው የምንኖረው ይበልጣል። በዚያም ላይ አሁን ያለንን ጥሩ ጥሩ ነገር አጠንክረንና ‘አልችልም። ደካማ ነኝ። ይሄ ነው የሚገባኝ። ይሄ ነው ምሴ።’ ምናምን ማለትንና በህብረት ተጋግዞ መስራት መጥላትን አሽቀንጥረን ጥለን፣ በቅንነት ከበረታን ለውጥና ትልቅነት (ቢያንስ እርካታና እፎይታ) ህልም ሆነው አይቀሩብንም። ለተተኪው ትውልድ (ለልጆቻችን)ም የተሻለ ነገር ማስረከብ እንችላለን። የተሻለን ነገር የመረካከቡ ወግ እስኪሞላልን ድረስም፥ ቢያንስ ወኔ መቀዳዳትና የእልኧኝነት (በቀናው) ስሜት ዱላን መቀባበል ትርፉ ብዙ ነው የሚሆነው።

ይሄ የእኔ ሀሳብ ነው። አሁን እኔን የመሰለኝ ነው። ምንም እንኳን መነሻዬ የዛሬው የኳስ ሁኔታ ቢሆንም፣ ያልኩት ሁሉ ለብሔራዊ ቡድናችን ብቻ እንዲሆን ሳይሆን፣ እንዲያው በጅምላው ሳስበው የመሰለኝን ነው የተየብኩት። ምናልባት የመሰለኝ ከመሰለዎት በዘርፍዎ እና በቤትዎ ይለማመዱት። ያደርጉትም ከነበረ አጠንክረው ይግፉበት። ‘አይ እኔን የሚመስለኝ እንዲህ ሳይሆን እንዲያ ነው’ ሲሉ ደግሞ ያካፍሉኝና የተሻለውን ያስቀዱኝ።

— ይላል ዮሐንስ ሞላ ሲያካብድ! ሃሃሃ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s