Day: February 1, 2013
ቸር ቸሩን ያሰማን አቦ!!
** የሰፈሩ አሉባልታ…. (የዛሬ ዓመት ገደማ የሰማሁት)
ካሚላትና ደምሰው አገር ምድር፣ ወዳጅ ቤተሰብ የሚያውቃቸው የፍቅር ጓደኛሞች በነበሩበት ወቅት እሷ “ኧከሌ” ከሚባል ‘አፈቀርኩሽ’ ብሎ ይጨቀጭቃት ከነበረ ነጋዴ ሰው ጋር የሆነ ዓይነት ግንኙነት ጀመረች። …አሉ። ግንኙነቱ በገንዘብ (በሌላ ጥቅም) የተሳሰረ ነበረ።…አሉ። እርሷ ከሰውዬው ጋር ያንን ነገር ስታስብና ስትጀምር በወቅቱ ከሰውየው የምታገኘውን የገንዘብ ጥቅም በማሰብ ነበረ።…አሉ። ኧከሌውም ስለፍቅረኛዋ ደምሰው መኖርና በይፋ መዋደዳቸውን ያውቅ ነበርና በ“ባንዘልቅ እንኳን አብረን እንደር” ወግ ነበር የገባበት።…አሉ።
ከዚያ ግን አንዴ የሚፈልገውን ካደረገና የምትፈልገውን ካደረገላት በኋላ አመረረ። ፍቅር ያልቅ ይመስል “አስጨርሺኝ”… “አብረን ካልኖርን ሞቼ እገኛለሁ። ያዙኝ ልቀቁኝ።” አለ፤. . . አሉ። ካሚላት ደግሞ ከወዳጇ ከደምሰው ጋር ያላት ግንኙነት በወዳጅ ዘመድ ዘንድ የሚታወቅ ነበርና እርሱን የመካዱ ነገር ፍፁም ስላልተዋጠላትና ማህበራዊ ገፅታዋን እንዳያበላሽባት ስለፈራች ‘ኡኡ አሻፈረኝ’ አለች።…አሉ። ከዚያ ብሩን እንድትመልስለት ጠየቃትና እንደሌላት ነገረችው።…አሉ። እንዳሉት ከሆነ፥ በዚህ ብስጭት ነበር አፍቃሪው ሰዎች ቀጥሮ አሲድ ፊቷ ላይ እንዲደፋባት ያደረገው። [አሉባልታውን ጥቂት ገታ እናድርገውና የሆነውን ደግሞ እናውራ…]
** አሲዱ የተደፋባት ሰሞን ከሚዲያዎች የሰማሁት….
ከተደፋባት በኋላም ወሬው ጉድ ተብሎ ሲቀባበል ቆይቶ በሚዲያዎች ቀርባ ስትጠየቅ አሲዱን የደፋባት ፍቅረኛዋ ደምሰው መሆኑን መሰከረች። ቤተሰቦቿም መሰከሩ። ሁኔታዎችን እያቀናበሩና እየዘረዘሩ ተነተኑት።….በሌላው ወገን ደግሞ ደምሰውና ዘመዶቹ (በተለይ ምስኪን እናቱ) እላይ ታች እያሉ ተከራከሩ። “እግዚአብሔር ይፍረድ” ብለው ተሟገቱ። አለቀሱ። ኗሪውም ግራ ገብቶት ሀሳቡና ፍርዱ ለሁለት ተከፈለ። ምንም ጠብ ሳይልላቸው ደምሰው ላይ የሞት ፍርድ ተፈረደበት ተባለ።
አንዳንድ ትልልቆች “እሰይ! የታባቱ! እንዲህ ልኩን አስገብቶ መቀጣጫ ማድረግ ነው እንጂ።” ሲል ነገሩን አከባበዱት። ሌሎች ትልልቆች ደግሞ የነገሩን ጭምጭምታ አውቃለሁ በሚል (ወይም ሰምተው ኖሮ) “ምስኪን የእኔ ጌታ… ባላደረገበት ከሆነ ግን ያሳዝናል። ቸኩለው ባይፈፅሙ ምናለ? ኧረ የድሀ አምላክ…” ምናምን እያሉ ክፉኛ አዘኑ። ህፃናትም ከሁለተኞቹ ወገኖች አሉባልታውን ቃርመው ኖሮ በR-Kelly “burn it up” ዜማ ከጣሪያ በላይ እየጮሁ ተጫወቱ… — “ካሚላት… ባሏን ስትከዳው አሲድ ደፋባት” እያሉ። ትልልቆቹም ነገሩን እነሱ እንዳላመጡት ሁሉ መልሰው ተቆጧቸው። አፋፋቸውን አሏቸው። “ጡር ነው” በእንዲህ ያለ ነገር አይቀለድም ብለው ቆነጠጧቸው።
ሁሉም እርሱን እየተቀባበለ የፍርዱን ፍፃሜ ለመስማት ቸኮለ። መቼስ እኛ ነገር ጉዳይ የሚፈፀመው ተዘንቦ ተባርቆ ስለሆነ (እንዲህ ባለ ጊዜ ጥሩም ነው) ፍርዱ ወዲያው አልተፈፀመበትም። እርሱም ይግባኝ ጠይቆ በክርክር ፍርድቤቱ ፍርዱን አቀለለት። አቃቤ ህግ በተራው ይግባኝ ጠይቆ ፍርዱን አከበደበት። ….20 ዓመት።…. ከዚያ ደግሞ መልሶ እድሜ ልክ። – ለእናቱ ሁለቱም እኩል ነበር።
** አሉባልታውን እንቀጥል….
ሲኖሩ ሲኖሩ፣ ከለዕታት ባ’ንዱ ቀን ተደራቢው አፍቃሪ በገንዘብ ምክንያት ምስጢሩን ከሚያውቁ ወዳጆቹ ጋር ከፍተኛ ጠብ ውስጥ ገቡ።…አሉ። ከዚያ በኋላ ደካማ ጎኑን ጠብቀው ሲያጠቁት “እንደውም ይሄን የማታስተካክል ከሆነ ካሚላት ላይ አሲድ ያስደፋህባት አንተ መሆንህን ለፖሊስ እንናገራለን።” አሉት።… አሉ። እርሱም ደንብሮ ነገሩን በሰላም ፈቱት።….አሉ። ግና በአካባቢው ጆሮ ጠቢ ነበርና ነገሩን ሄዶ ለእናትየው ሹክ አላቸው።… አሉ። እናትየውም ለፖሊስ። የሰፈሩ ሰው ደግሞ በስማ በለው ላልሰማ። ወሬው ሰፈር ለሰፈር ሲቀባበል ደርሶን ጉድ አልን። ያኔ በሀዘኔታ በየፊናቸው ሲሟገቱለት የነበሩት የአሸናፊነት ስሜት ተሰማቸው። ጉድ አንድ ሰሞን ነውና ሳምንት ሳይሞላ ወሬው ተረሳ።
(እንግዲህ ከላይ ያለው ሁሉ “አሉ” ነው።)
** በትናንትናው እለት ደግሞ የአዲስ አድማስ ጋዜጣን ዋቢ አድርጎ www.amharictube.com የተባለ ድህረገፅ እንዲህ ዘገበ….
“በካሚላት አህመዲን ላይ አሲድ ደፍቷል በመባል የተከሰሰው እና የዕድሜ ልክ እስራት የተፈረደበት ደምሰው ድርጊቱን እንዳልፈፀመና “የፈፀምነው እኛ ነን” ያሉ ወጣቶች ሰሞኑን ለፖሊስ ቃል መስጠታቸውን ምንጮች ጠቆሙ። ከዛሬ ስድስት ዓመት በፊት የፍቅር ጓደኛው በሆነችው ካሚላት ላይ የአሲድ ጥቃት ማድረሱ በሰው ምስክርና በማስረጃ ተረጋግጧል ተብሎ የተከሰሰው ደምሰው፣ ጉዳዩን እንዳልፈፀመ በመናገር ቢከራከርም በሰውና በሰነድ ማስረጃዎች ተረጋግጧል በማለት ፍ/ቤት በሞት እንዲቀጣ ወስኖ ነበር።
ተከሳሽ ይግባኝ ጠይቆ ቅጣቱ ወደ 20 ዓመት ዝቅ ብሎለት የነበረ ቢሆንም ዐቃቤ ሕግ እና የሕግ ባለሞያ ሴቶች ማኅበር ይግባኝ በማለት ተከሳሹ የዕድሜ ልክ እስራት እንዲቀጣ መወሰኑ ይታወቃል። ከስድስት ዓመታት በኋላ ሰሞኑን “ድርጊቱን እኛ ነን የፈፀምነው” ያሉ ግለሰቦች መገኘታቸውን የተከሳሹ ወላጅ እናት ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መጠቆማቸውን የሚናገሩት ምንጮች፤ የተባሉት ሦስት ወጣቶች ጫት ቤት ተቀምጠው የፈፀሙትን ድርጊት እያነሱ ሲያወሩ የሰሙ ሰዎች፣ ለተከሳሽ ቤተሰብ በመንገር ጉዳዩ ክትትል እንዲደረግበት ጥቆማ መስጠቱን ገልፀዋል።
የተባሉት ወጣቶችም ተይዘው በሰጡት ቃል፣ ድርጊቱን መፈፀማቸውን አምነው ቃላቸውን መስጠታቸውን እና ትላንት ደምሰው ከማረሚያ ቤት ወጥቶ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ቃሉን ሰጥቶ መመለሱን ምንጮቻችን ተናግረዋል። የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጉዳዩን እያጣራ በመሆኑ መረጃ ለመስጠት እንደማይችል ገልፆልናል።”
** Moral of the story – in line with the አሉባልታ and z facts! – in my opinion!
1. አትስረቅ። (ከ10ቱ ትዕዛዛት አንዱ)
2. አታመንዝር። (ከ10ቱ ትዕዛዛት አንዱ)
3. በሀሰት አትማል እንዲሁም አትመስክር።(ከ10ቱ ትዕዛዛት አንዱ)
4. የባልንጀራህን ቤት አትመኝ የባልንጀራህን ሚስት ሎሌውንም ገረዱንም በሬውንም አህያውንም ከባልንጀራህ ገንዘብ ሁሉ ማናቸውንም አትመኝ። (ከ10ቱ ትዕዛዛት አንዱ)
5. በነገሮች ሁሉ ችኩል አትሁን።
6. አትበቀል። ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ። (ከ10ቱ ትዕዛዛት አንዱ)
7. ፍርድህ ሁሉ በጥንቃቄ ይሁን።
8. አትግደል። (ከ10ቱ ትዕዛዛት አንዱ)
(በበኩሌ ባልሰሩት ወንጀል እንዲህ መንገላታት ከሞትም የሚከብድ ከባድ ቅጣት ነው። 6 ዓመት አይደለም 6 ቀን እስርቤት ውስጥ መቆየትን ምንም እንደማያካክሰው አውቃለሁ።
9. ምናልባት ማረሚያ ቤት ውስጥ ያሉ ታራሚዎች በሙሉ በሰሩት ወንጀል ላይሆን ይችላልና ነገሩ ይጣራ። ፍርድ ሲሰጥም በጥንቃቄ ይሁን።
10. አሁንም ነገሩ ቶሎ እልባት ያግኝና ነፁህው ሰው ይለቀቅ። ጥፋተኛውም ባለው ሀይልና አቅም ሳይሆን በሰራው ስራ ተመዝኖ ይቀጣ።
11. ‘እውነትና ንጋት እያደር ይጠራል።’
12. እግዚአብሔር እውነተኛ ዳኛ ነው።
13. ሌላም ሌላም….
ቸር ቸሩን ያሰማን አቦ!!