እኛም አለን ሙዚቃ፣
__ስሜት የሚያነቃ!
በገናችን — ♫ ♬♩ ♪ ♫ ♬
መሰንቆአችን — ♩ ♪ ♫ ♬ ♬
ክራራችን — ♩ ♪ ♫ ♬ ♫
ዋሽንታችን — ♩ ♫ ♬♩ ♫ ♬
እምቢልታችን — ♩ ♪ ♬♩ ♪ ♬…
የኢትዮጵያ ሬድዮ እንዲህ ሳይበላሽ በፊት፣ የባህል ሙዚቃዎች ምሽት መግቢያ የነበረው ሙዚቃ የተስፋዬ ለማ ስራ ነበር። እንዲህ ብሎ ስለሙዚቃዎቻችን በሙዚቃ ያወራው ተስፋዬ፥ በተለይ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ በማስተዋወቅ ረገድ ከተለያዩ የአገሪቱ ቦታዎችና ብሔሮች የተውጣጡ ከ30 በላይ አባላት በነበሩት “ኦርኬስትራ ኢትዮጵያ” ዳይሬክተርነት (3ኛው ዳይሬክተር በመሆን) የተጫወተው ሚና ጉልህ ነበር።
በጎ ፈቃደኛ በመሆን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ (በቀድሞ ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ዩኒቨርስቲ) እንግሊዘኛ ትምህርት ያስተምር የነበርውን ጀማሪ ሙዚቀኛ፥ አሜሪካዊው ቻርለስ ሳተንን ወደ ኦርኬስትራው በመደባለቅ ከኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ጋር አስተዋውቆት፤…. በኋላም ከቻርለስ ጋር በመተባበር የኦርኬስትራ ኢትዮጵያ በአሜሪካ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃዎችን ይዞ “ብሉ ናይል ግሩፕ” በሚል ስም፥ ከ20 በላይ የአሜሪካ ከተሞች ዞሮ ያቀርብ ዘንድ ተስፋዬ የመሪነትና የአስተባባሪነት ስራ ሰርቷል።
በኋላም ኦርኬስትራ ኢትዮጵያ 2ሙሉ ስራዎችን አስቀርፆ አበርክቷል። (የአንደኛውን ባላውቅም አንደኛው በኢትዮፒክስ ቁጥር 23 ላይ ያለው መሆኑን ቀን ፋና ኤፍ ኤም የጣዕም ልኬት ላይ አድምጫለሁ።) ከዚህ በተጨማሪም ጋሽ ተስፋዬ ብዙ ሙዚቃዎችን ለብዙ ሙዚቀኞች ሰርቶ ሰጥቷል። ከብዙ በጥቂቱ፣ ጥላሁን ገሰሰ፣ ነዋይ ደበበ፣ ፀሀዬ ዮሐንስ፣ ኤልያስ ተባባል፣ ኤፍሬም ታምሩ፣ ይጠቀሳሉ። (እንዲያውም ፀሀዬና ነዋይን ችሎታቸውን ተገንዝቦ በራስ ቴአትር የሙዚቃ ባንድ እንዲታቀፉና ዘርፉን በይፋ እንዲቀላቀሉ ብዙው ጥረት የርሱ እንደነበር የጣዕም ልኬት ፕሮግራም ላይ ተዘግቧል። በዚህ ባለሞያን ፈልጎ ከሙዚቃው ጋር በማገናኘት ግብሩም በሚያውቁት ዘንድ ዘወትር ይመሰገናል።)
ጋሽ ተስፋዬ፥ በተለይ በድራማዊ ሙዚቃ ስራዎቹ የሚታወቅ ሲሆን፤ ብዙም ትኩረት የማይሰጣቸው ማህበራዊ ጉዳዮችንም በሙዚቃ በመስራት ረገድ ሚናው ትልቅ ነበር። እንደምሳሌ ለፀሀይ እንዳለ የሰራላትን “የህፃኑ ልጅ ለቅሶ” እና ለጥላሁን የሰራለትን “አንዳንድ ነገሮች”ና “አጉል ነው” ማንሳት ይቻላል፤ ከሙዚቃዊ ድራማዎቹ ደግሞ “ማሚቴና ከበደ” እና “ለቅዳሜ አጥቢያ” መጠቀስ ይችላሉ። ከዚህ ባሻገር ዛሬም ድረስ በተማሪዎች የምረቃ ባህል ላይ የምንጠቀምበትን የ“እንኳን ደስ አላችሁ” ህብረ-ዝማሬ ሰርቶ አበርክቷል።
እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ1980ዎቹ ተስፋዬ ወደ አሜሪካ በስደት ሄዶ፣ ቆይቶ የኢትዮጵያን ሙዚቃ፣ ባህል፣ እና ጥበብ ከአሜሪካዎቹ ጋር ለማቆራኘት በማሰብ፥ የኢትዮ-አሜሪካን የባህል ማዕከል፣ የናይል ኢትዮጵያ ጥምረትና ተስፋ ሙዚየምን መስርቷል። በመካከል በገጠመው የጤና እክል ምክንያት እንቅስቃሴዎቹን እስኪገታ ድረስም ቀድሞ ኦርኬስትራ ኢትዮጵያ ሳለ ከሚተዋወቁ ሰዎች መሀል አራቱ – ተስፋዬ፣ ቻርልስ ሳተን፣ ጌታመሳይ እና መላኩ ገላው – ድጋሚ አሜሪካ ላይ ተገናኝተው በጋሽ ተስፋዬ ዳይሬክተርነት “ዞሮ ገጠም” (reunion) የሚል መጠሪያ ያለው የኢትዮጵያ የባህላዊ ሙዚቃዎች ስብስብ አልበም አስቀረፁ። አልበሙን “ዞሮ ገጠም” (reunion) በማለት የሰየሙትም፥ ዞረው መገናኘታቸውን ለመዘከር የነበረ ሲሆን፣ ከአልበሙ የተገኘው ገቢ በሙሉም ለ Institute of Ethiopian Studies (ለኢትዮጵያ ጥናቶች ተቋም) እንቅስቃሴዎች መርጃ አበርክተዋል።
ጋሽ ተስፋዬ ለማ በ2000 ዓ/ም Ethiopian Yellow Pages የተባለ ድርጅት ያዘጋጀውን ኢትዮጵያ ሚሊንየም የክብር ሽልማት ተሸላሚ እንደነበረም ይታወቃል። ከዚህ አስተዋፅኦው ባሻገር ጋሽ ተስፋዬ በኤትኖሙሲኮሎጂስትነት ደረጃ፥ የሙዚቃንና የዳንስን ህብረተሰባዊና ባህላዊ ባህርዮቻቸውን ሲያጠና ነበር። ኋላም ላይ ከቅርብ ወዳጁ ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ ሙዚቃ ላይ የሚያጠነጥን መፅሀፍ ፅፎ አበርክቷል። በነበረበት የጤና ቀውስ ምክንያት ለረዥም ጊዜ በህክምና ሲረዳ ቆይቶ በትናንትናው እለት (ጥር 24/2005 ዓ/ም) ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።
የሚችልና ስለ ጋሽ ተስፋዬ ለማ አስተዋፅኦዎች በሰፊው ለማወቅ ያደረበት ቢኖር ከዚህ በፊት ከመዓዛ ብሩ ጋር በስልክ ያደረጉትን ቃለ መጠይቅ ነገ ምሽት ጨዋታ ፕሮግራም ላይ (ሲደገም) አልያም ከሸገር ኤፍ.ኤም. ማህደር ውስጥ አውርዶ ያዳምጥ ዘንድ እጋብዛለሁ።
ከተስፋዬ ግጥምና ዜማ ስራዎች ውስጥ የኤልያስ ተባባል “ማማዬ” እነሆ ተቀንጭቦ…
ኦሆሆሆሆ….
ከረጅም ማማ ላይ ጥንቅሽ የበላ ሰው፣
ከጎድጓዳ ስፍራ፣ ጠይም የሳመ ሰው፣
እንኳን ሽማግሌ፣ ዳኛም አይመልሰው፣ (2x)
ደጅ ጠናሁ፣ ደጅ ጠናሁ ከእንግዲህ ታከተኝ፣
የሆዷን ጠይቆ ማን ባሰናበተኝ?!
ማማዬ ማማዬ፣ ኧረ ነይ ማማዬ፣
ማማዬ ማማዬ፣ ሸጋ ልጅ ማማዬ፣
ማማዬ ማማዬ፣ ቆንጆ ልጅ ማማዬ፣
ዐይነ ኩሎ (?)፣ ሽንጠ ሎጋ የወለዱ እንደሆን፣
መልካም ፀባይ ያላት የወለዱ እንደሆን፣
እውቀት የምትሻ፣ የወለዱ እንደሆን፣
ታመጣለች አማች ብረት መዝጊያ ‘ሚሆን።
ማማዬ ማማዬ፣ ኧረ ነይ ማማዬ፣
ማማዬ ማማዬ፣ ሸጋ ልጅ ማማዬ፣
ማማዬ ማማዬ፣ ቆንጆ ልጅ ማማዬ
ነፍስ ይማር!!