እኛና ኢትዮ ቴሌኮም

መቼም እኛና ኢትዮ ቴሌኮም ‘ምንና ምንድን ነን?’ ብሎ መጠየቅ አላዋቂ ያስብለናልና እሱን አናነሳም። ግን የግድ ‘ምንና ምን ናቹ?’ ብሎ በቀን 40 ጊዜ ከድርጅቱ እንደሚደርሱን የፅሁፍ መልእክቶች ችክ ብሎ የሚጠይቀን ቢመጣ ግን….
‘እኛና ETC ምንና ምንድን ነን፣
ጣውንጥ፣ ባላጋራ፣ የእንጀራ ዘመድ ነን’…..ምናምን ብለን እንመልሳለን። (ሆሆሆ….የገጣሚ ፈቃድን (poetic license) መጠቀም ይሏል እንዲህ ነው። ግን የእንጀራ ዘመድ የሚባል ነገር አለ እንዴ? ሆሆሆ…. ደግሞ ታች ድረስ ወርዶ በመከፋፈል ወንጀል መዝገብ እንዳንከሰስ ይቅርብን። — ስራ መፍታት ከሳሽና ተከሳሹን ያበዛዋል ብዬ እኮ ነው። ሃሃሃ….)

መቼም እንዲሁ ቤት ይምታልን ብለን እንጂ፣ በሁለተኛው ስንኝ ውስጥ በክፋትና ተንኮላቸው የሚታወቁ/የተለመዱ/በልማድ የተለዩ ወይም ደግሞ ክፋትና ተንኮልን አጉልተው የሚገልፁ ቃላትን ሁሉ ማጨቅም ነገሩን አይገልፀውም። ‘ምነው የለመድነውንና የረሳን የመሰልነውን ነገር ትቆሰቁሰው ዘንድ ምን አነሳሳህ? ያውም በምሽቱ?’ ምናምን ብሎ የሚጠይቅ ወዳጅም አይጠፋም። መቼም የእኛ ሰው ለመልስ ሳይጨነቅ መጠየቁን ተክኖታል…. ብዙ መልስ የሌላቸውን ጥያቄዎች ይጠይቃል…

ለጥያቄዎች መልስ ይሁን ብሎ ቃላት ቢሰትር፥ እዳው ኮብል ስቶን ነው የሚሆንበትና አያስበውም። (‘እዳው ገብስ የሚሉት አማርኛ ከገብስ መወደድና ከጌቶች ቆጣ ቆጣ ማለት ጋር ተያይዞ ተወዷል’ የሚል ወሬ ሰምተን እኮ ነው። ግን ምናለ ወጣቶቹ በጥቃቅንና በአነስተኛ ተደራጅተው ጆሮአችንን አሸዋ ቢገርፉልንና ከድካም ቢታደጉን? የምሬን እኮ ነው….) የእኛ ነገር!…አሁን ማን ጠርቶን እንዘባርቃለን?…. እርሱን ትተን የተነሳንበትን እንጫወት እስኪ። ነገሩ እንዲህ ነው…..

ዛሬ ካርድ የ15 ብር የሞባይል ካርድ ገዝቼ፥ አንድ ወዳጅ ጋ ስልክ ደውዬ (2 ደቂቃ ከ 24 seconds) እና e-mail አይቼ (ከ2 ደቂቃ ያነሰ) ወጣሁኝ። ከዚያም አገር ሰላም ብዬ፥ አንድ ወዳጄ የላከልኝን የፅሁፍ መልእክት ለመመለስ፥ አቀናብሬ ‘sent’ ብለው….. “Your account balance is insufficient for SMS Service. Please recharge first, dial 909 to recharge your account.” የሚል መልእክት ባናት ባናቱ 3 ጊዜ መጣልኝ። (ባለፈው 27text ልከውልኝ ስለነበር ’27 ጊዜ መጣልን’ ልንል አልንና ‘ተውነው እንደገና’ ሃሃሃ…)

ሶስትም ግን ብዙ ነው። አንዱ ይበቃ ነበር። ምናልባት ግን አንገብግበው ካርድ ማስገዛት አስበውም ሊሆን ይችላል። (የእኛና የነሱ የልጅ የጅል ጨዋታ አንዱ አካል…..ተነቃቅተናል….;) [ቀደምት አበወ ወ እመው፥ ‘በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ’ እንዲሉ ብስጭቱ ተደማምሮ ደሜን ከፍ አያረገውም?! (ሃሃሃ… ‘ሲሉ ሰምቼ፣ ከኮልፌ መጣሁ በሩን ዘግቼ!’ ሄሄሄ…..)] ከዚያም ቀሪ ሂሳቤን ለማወቅ 804 ደውዬ ሳነብ 0.11 ሳንቲም ብቻ ነው ያለኝ። ነገሩ ግራ አጋባኝ። አስደነገጠኝ። (ኦ…ማንበብ የማይችሉ ዓይኖች ምንኛ የታደሉ ናቸው? ምናምን ብዬም ጠይቄያለሁ….ሃሃሃ…ጋዜጣ ማንበብ ስለቻልን አይደል ከጌቶች ጋር ሌባና ፖሊስ የምንጫወተው?… እነሆ አዲስ ታይምስንም አቀለጧት!)

ሂሳቡ እንዴት እንዲህ ይወርዳል? ብዬ መልስ የሌለው ጥያቄዬን ጠየቅኩኝ። ወዲያው ግን እንደ መረጋጋት አድርጎኝ፤ የእነርሱንና የእኔን ሌላኛውን የልጅ፣ የጅል ያላዋቂ ጨዋታ አስታውሼ….ከዚህ በፊት ኢንተርኔት ስጠቀም አላግባብ የተቆረጠብኝ ሳንቲም መልሶ መጥቶልኝ ያውቃልና ካርድ ሳልሞላ ጠበቅኩት። (መቼም ነገሩ ቢያሳፍርም እንዲህ ተማምኖ መመላለሱም ተመስገን ነው። ….ግን ምናለ በማይነጥፈው የፅሁፍ ጭቅጭቃቸው እንዲህ ሲያጠፉ ‘ይቅርታ’ ምናምን የምትል ነገር አክለው ቢልኩልን ኖሮ? ወይ ደግሞ መቀጫ 1ነፃ SMS….ሃሃሃ…

ትናንትናማ ሲላብን አመሸ አይደል? Recharge &Get Free local Airtime/SMS!
– 100Br get 15Min,
– 50Br get 10Min,
– 25Br get 3Min,
– 15Br get 5SMS
From Feb.5 – Mar.5, 2013/Tir 28 – Yek.26, 2005. ቂቂቂ….
ወይ ኢትዮ ቴሌ፣… :-/

ቆይቼ ድጋሚ 804 ደውዬ የቀረኝን ሂሳብ አየሁት። ተረጋጋሁ…..ከፍ ብሏል….(አስራ ምናምን….ቦታው ይመስላል።) ግን ብዙ ጥያቄዎች መረጋጋቴን ተከትለው መጡ። እንግዲህ በመጨረሻው ዘመን መረጋጋትም በሽታ ነው….ብዙ መልስ የሌላቸውን ጥያቄዎች ያስከትላልና…..። በቀን ስንት ጊዜ አንዱን መልእክት እየደጋገሙ በመላክ የሚያሰለቹን ለምንድን ነው? አሃ….እርሱን ስናነብ ደክመን መፅሀፍ ምናምን እንዳናነብ ነው? …ሃሃሃሃ…..

[መጀመሪያ ሰሞን ‘ደንቆሮው ህዝቤ በ5 ዙር ምናምን ካልነገሩት አይገባውም ብለው ለእኛ አስበው ነው።’ ምናምን ብለን ለመፅናናት እንሞክር ነበረ።…..አሁን ሳስበው ግን የፅሁፍ መልእክቶቹን operate የሚያደርግ ህፃን ልጅ ሳይኖር አይቀርም። ያው ያንዱ ልጅ እየተጫወተ እንዲያገለግል….በሁለት ድንጋይ…ሄሄሄ… ምናምን ብለን ልንቀውጠው አልንና ‘ተውነው እንደገና።’ ለካስ በዚህ ረገድ ትልቅ መሻሻል አሳይተዋል።]

ደግሞ ቀሪ ሂሳብ ከ2ብር ሲያንስ “ያሎት ቀሪ ሂሳብ አነስተኛ ነው። እባክዎትን ተጨማሪ ካርድ ገዝተው ይጠቀሙ።” የሚለውን ደግ ማስፈራሪያ ለምን ይሆን የተዉት? (መቼም እዚህ አገር ደግ አይበረክትም….እንግዲህ እርሱም ድሮ ከቀሩት እሴቶች ተርታ መመደቡ ነው…. ልንል አልንና፣ ይሄንንም ‘ተውነው እንደገና’ አሁንማ አሻሽለውት ለፍተላ አልተመቸንም። ሃሃሃ… )

በፈለጉት ሰዓት ሳንቲም እየቆረጡ ቆይተው የሚልኩልን ለምንድን ነው? (ካርድ ማሻሻጫም ሊሆን ይችላል….ሃሃሃ….) ደግሞ ሳይልኩልን ቢቀሩስ? ያወጡትን ታሪፍ በአግባቡ ተጠቅመው እንደሚቆርጡብን በምን እናውቃለን? (መቼም አንድ በደወሉ ቁጥር ቀሪ ሂሳብን ማየት በመኪና ዘመን በአህያ እንደመሄድ ነው….ደግሞስ አግባብ ባይሆንስ ማን ይጠየቃል? ማን ይከሰሳል? ለማን ይከሰሳል?)

እኛና ኢትዮ ቴሌ እንዴት ነው የምንተማመነው? አንድ እነሱ ብቻ የቴሌኮም አገልግሎት በሚሰጡበት አገር ውስጥ ‘ሲም ካርድ በርካሽ ግዙ’ ምናምን ሲሉ አይደብራቸውም?…ልንል አልናና ይሄንንም ‘ተውነው እንደገና።’ ይሄ የፅሁፍ መቅረቱንም ልብ ይሏል። ደግሞስ ነጋዴውን ላንድ ዓይነት እቃ አንድ ዓይነት ንግድ ፈቃድ ምናምን ብለው ህግ ከጣፉለት በኋላ በጎን ቀፎ መሸጣቸውን ምን አመጣው? ….ብዙ ጥያቄዎች…..

ይህ በእንዲህ እንዳለም ልንል አልንና ‘ተውነው እንደገና’ ያልናቸውን ነጥቦች ስናስብ ከዚህ በፊት በየstatus updateኡ “ኡኡ…” የማለታችን ውጤት ሊሆን እንደሚችልም ተሰማንና የልብ ልብ ተሰማን። 🙂 አያይዘንም፥ ሲደብራቸው ሊሰሙን ይችላሉና መጮሃችንንም አናቋርጥም ስንል ለራሳችን ቃል ገባን። ህህህህ….

እኔ የምለው የአርማ ለውጡን ግን ምነው አዘገዩት? ወይስ እንዳያዳግም አድርገው ለመቀየር ነው? እንዲያ ከሆነ፥ በጄ!!