ለ ኢትዮ ቴሌ
ጉዳዩ: – ይግባኝ!
የቅድመ ክፍያ ሂሳብ ሽያጭ ካርድ ዓይነት ከፕላስቲክነት ወደ ካርቶንነት መለወጡ ይታወቃል። ለውጡን ያስተዋልነው ሰሞን፥ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ባለሱቆቹን ስንጠይቅ ግምታቸውን “ከቻይና ነበር የሚመጣው፣ አሁን እዚህ መስራት ስለጀመሩ ነው።” ብለው ነገሩን። እኛም ከውጭ መምጣቱ አዲስ እውቀት፣ በአገር ልጅ መሰራቱ ደግሞ ብርቅ ሆኖብን ነበር ያሳለፍነው።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ግን አልፎ አልፎ ያስተዋልነው ችግር ቁጥሩን ለማየት ቅቡ ሲፋቅ ያታግልና ቁጥሩም አብሮ ይፋቃል። ከዚህ በፊት ቁጥሮቹን እየገመትንና እያገጣጠምን ይሰራልን ነበር። ዛሬ ግን የ50 ብር ካርድ ገዝቼ ስፍቀው ቁጥሩ አብሮ ተፍቆ ሂሳቤን ሳልሞላ የቀለጥኩበት ሁኔታ ነው ያለው። ቁጥሩን እያገጣጠምኩ ልሞክረው አስቤ የነበረ ቢሆንም፣ የልጅነት እድሜዬ በሙከራ እንዳያልቅ በመስጋት ትቼዋለሁ።
[በነገራችን ላይ ከ10 ብር ባንዴ ወደ 50 ብር የተመነደግሁት 10 ደቂቃ ቦነስ አገኝ ብዬ መሆኑና፤… በፊት ደግሞ ከ100 ብር ወደ 10 ብር ያቆለቆልሁት፥ ብከስርም የ10 ብር ካርድ ልክሰር ብዬ እንደነበር ይታወቅልኝ።…ብዬ ላካብድ እንዴ? ሄሄሄ…]
ይህንን ጉዳይ ላማክረው ባለሱቁ ጋር ስሄድ “ቴሌ የምታውቀው ሰው ካለ በቀለላሉ በሴርያል ቁጥሩ ያወጡታል። የምታውቀው ከሌለ ግን እሺ አይሉህም። በፊት ይነግሩ ነበር፣ አሁን ግን ጠያቂው ሲበዛ ተማረው አቆሙት።” አለኝ። እኔም በሆዴ “ለዚህም ዘመድ?” ብዬ… ነገሩን አጥብቄ ብጠይቀውና እርሱ ካርድ ሊገዛ ሲሄድ እንዲጠይቅልኝ ባግባባው፣ እርሱ ራሱ ለራሴና ለደንበኞቼ ስሞላ ከሰርኩ ያላቸውን ካርዶች አውጥቶ አሳየኝ።
ለምስኪኑ፣ ወር ጠብቆ ኗሪና የብድር ተዳዳሪው እኔ ዛሬ በኤኮን “chop my money” የማላልፈው ጠንከር ያለ ዱላችሁ ስላረፈብኝ በአደባባይ “ይግባኝ” ስል እጮሃለሁ።
ምርጫ አልባው የዘወትር ተቃጣይ ደንበኛችሁ ዮሐንስ ሞላ
(የማይነበብ ፊርማ)