መክሸፍ እንደ ታገል ሰይፉ

እንደ መግቢያ

በመጀመሪያ ይህንን ጨዋታ “መክሸፍ….” ብዬ ላለመሰየም ከራሴ ጋር ጥቂት ውይይት አደረግሁና በሁለት ምክንያቶች ‘ተውኩት እንደገና።’ (ሃሃሃ….) አንደኛው ታገል የደረሰበትን ሁኔታ “መክሸፍ” ከሚለው ቃል በተሻለ የሚገልፀው ሌላ ቃል መፈለግ ዝቅ ማለትን ሊጠይቅ ይችላልና፥ ‘በውረጅ እንውረድ’ ፈሊጥ ከወረደ ጋር አብሮ መውረዱን አልወደድኩትም።

ሌላው ደግሞ ትናንትና ወዳጅ Tamrat “መክሸፍ እንደሰው ልጅ” ብሎ በውብ ቀምሞ ያቀረባትን ፅሁፍ አንብቤ፥ (Btw, የታሜን ፅሁፍ ታነብቡት ዘንድ ጋብዤያችኋለሁ።) ….ምናልባት መክሸፍ የሚለው ቃል አንባቢን ስለሚገፋ (ሰሞኑን በመደጋገሙ ምክንያት)፣ ሌላ አዲስ ቃል ተጠቅሞ ቢሰይመው ሊሻል ይችል እንደነበር አስተያየቴን ስሰጠው… “ያው መክሸፍ መክሸፍ ሲል ሰው ሁሉ፣ እስኪ እንሞክረው ብለን ነው።” በማለት በጨዋታ መልክ መመለሱን አስታውሼ፥….

…ሰው ሁሉ ‘መክሸፍ መክሸፍ’ ካለ ዘንዳ፥ በእኔ እይታ፥ ክፉኛ ለከሸፈው ታገል ሰይፉ ብጠቀመው፣ ሁኔታውን ለመግለፅ ይበዛበት እንደው እንጂ አያንስበትም ብዬ ነው። በዚያም ላይ ለበጣም ክሽፍ ሰው/ነገር መክሸፍ የሚለውን ቃል አለመጠቀም መሸፈጥ ሆኖ ከህሊና ጋር ሊያስተዛዝብም ይችላል። ነገራችንን “መክሸፍ” ብዬ በፕሮፌሰር መስፍን አዲስ መፅሀፍ ርዕስ ከሰየምኩ አይቀር ደግሞ፥ ኋላ ደጋፊ/አስራጭ (አሰረፀ እንድንል) ሲያሻኝ ማጣቀሱ ይቀለኝ ዘንድ አስቀድሜ ከ’ርሳቸው መፅሀፍ ላይ የሚከተለውን መዝዤ አስቀምጣለሁ።

“አንድ ሰው በአደባባይ ሲናገርም ሆነ ፅሁፍ አሳትሞ ሲያሰራጭ ራሱን አጋልጧል፤ የተናገረው ወይም የፃፈው መቶ በመቶ  ያህል በራሱ ጉዳይ ላይ ብቻ ከሆነ፣ የመተቸት ወይም ሀሳብ የመስጠት ግዴታ የለብንም፤ ነገር ግን የተናገረው ወይም የፃፈው በአገርና በህዝብ ጉዳይ ላይ ከሆነ፣ የዚያ አገር ዜጋ ሁሉ በጉዳዩ ውስጥ የመሳተፍና ሀሳቡን በሙሉ ነፃነት የመሰጠት መብት አለው፤ አለዚያ በየጓዳችን በሀሜት ብቻ እየተዘላዘልን እውነትን አንጥሮ በአደባባይ የማውጣቱን ዘዴ ሳንማር ሌላ ሶስት ሺህ ዓመታት እንቀጥላለን።” ~ መስፍን ወልደማርያም (2005) ‘መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ’ ገፅ. 78 – 79.

አንዳንዴ፥ አንድ ጊዜ የከሸፈ ነገር ደግሞ ሲከሽፍ ይታያል። ደጋግሞ መክሸፍ – በአካሉ – ብርቅ ባይሆንም ደርሶ ሲመጣ ማስገረሙ ግን አይቀርም። (ልክ ከሙታን ተለይቶ ተነስቶ እንደገና ሞተ እንደማለት ሆኖ ይሰማና እንደ ጉድ ይገርማል…) ለእኔ የታገል ነገር እንደዚያ ነው የሆነው። — በርግጥ ታገል ከከሸፈ ቆይቷል (ምናልባትም ደጋግሞ)፤ እነሆ በየካቲት ወር 2005 “ቁም ነገር መፅሄት” ቅፅ 12 ቁ. 145 እትም በኩል ደግሞ እንደ አዲስ መክሸፉን ተመለክቼ ስለርሱ ሽምቅቅ አልኩኝ።

ታገል – ታገል! 

ዛሬ በወዳጆች የinbox ጥቆማ ታገል ከቁም ነገር መፅሄት ጋር በነበረው ቆይታው፥ በአላዋቂነት ሊያሽሟጥጥብን ሞከረ መባሉን ሰማሁና አመሻሹ ላይ መፅሄቱን ፈላልጌ አነበብኩት። ሆኖም ግን ነገሮችን የሚመለከትበት መንገዱ ቀላልነት እንጂ ማሽሟጠጡ አልታየኝም። ማንም ገላውን ለመሸፈን በማይበቃ ቁራጭ ድርቶ ሊሸፋፈን ሲሞክር ራሱን ያጋልጣል። ‘ራሴን ሸፈንኩ’ ሲል – እግሩ፤ ‘እግሬን’ ሲል ደግሞ – ራሱ እየተገላለጠበት አበሳውን ያያል። ስህተት ለማረም ሌላ ስህተት ይሰራል።

እኔ ታገልን የተመለከትኩት እንደዚያ ነው። አንዱን ሲሸፍን አንዱ ሲራቆትበት ተመለከትኩትምና አንጀቴን በላው። እግዚአብሄር ምስክሬ ነው ከሚያሳዝነኝ በላይ አሳዘነኝ። ከምሳሳለት በላይ ሳሳሁለት። ግን ምን ያደርጋል? …እግረ መንገዱን ዘጭ አለብኝ። በፊት በየዋህነት (innocence) አድርጎትም ሊሆን ይችላል ያልኳቸውን ስህተቶቹን ሁሉ በቀይ አሰማመረባቸውና ተፈጠፈጠባቸው። የአፈጣፈጡ ሁኔታም “ጠላቴን ስመርቅ” የሚለው የቀድሞ ግጥሙን አስታወሰኝ፤…

“በሀብት ከፍ ከፍ፣
በስልጣን ከፍ ከፍ፣
ከዚያ የወደቅህ ‘ለት፥
አጥንትህ እንዳይተርፍ።”

[ግጥሙን ቃል በቃል በሙሉ ባለማስታወሴ ይቅርታ እጠይቃለሁ።]

ምስኪን!… የቱ ጠላቱ መርቆት ይሆን እንዲህ የባሰበት? መቼስ ሰው እንዲህ ሲሆን “ራሱን አጠፋ” ይባላል። ሆኖም ግን ራስ የማጥፋት ድርጊት ቸል ከተባለ፥ የልብ ልብ ሰጥቶ ‘በአጥፍቶ ጠፊነት መርህ’ ሌሎች  የዋሃን (ወይ ደግሞ ደቀ መዛሙርት) ይዞ ሊያጠፋ ይችላልና ስለርሱ ሳይሆን ስለነርሱ በስሱ በማሰብ ስል ይህንን መፃፉ አግባብ እንደሆነ ተሰምቶኛል። እናም “እግዜር ይሁነው” እያልኩ ወደ ገደለው እገባለሁ።

ቃለ መጠይቁ “በሲዲ የሚቀርብልን ነገር ግጥም አይደለም።” የሚል የፌስቡክ አስተያየት መኖሩን ጠቅሶ፥ የታገልን ሀሳብ በመጠየቅ ነው የሚጀምረው። እርሱም ለዚህ መልስ ሲሰጥ፣ በሲዲው ሽፋን ላይ – ግጥም ሳይሆኑ ለማዝናናት የቀረቡ መሆናቸውን መግለፁን በማስታወስ “…የተመለካታችሁኝ በኦርጂናል ሲዲ አይደለም። እባካችሁ ቅጂ ይብቃችሁ።…ነው የምላቸው።” በማለት በእርግጠኛነትና በግልፍተኝነት ነው።

በመሰረቱ ሰው እንደተረዳው (ወይም ግራ እንደገባው) መጠን አስተያየቱን ሲሰጥ ‘ከኦርጂናል ሰማህ ከቅጂ’ ብሎ ከመሞገት በፊት… አስተያየት ሰጪው ግር የተሰኘበትን ነገር አቅም በፈቀደ ካጠሩ በኋላ፣ ቀጥሎ የኦርጂናል ግዙ ምክሩን መለገስ የተሻለ ነው። ምናልባትም እንደተናጋሪው ትህትናና አዋቂነት፣ መልሱ “ኦርጅናል ግዙ” የሚለውን መልዕክትም አብሮ ያስተላልፍና ‘በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ’ ሊሆንም ይችል ነበር።

ሌዋታን?!

(ሌዋታን ታገል ከዚህ በፊት መንግስትን ያብጠለጠለበት (እንዲያ የነበብኩበት) የልብወለድ ስራው ርዕስ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡)

ከዚህ ቀጥለው የቀረቡለት 3 ተከታታይ ጥያቄዎች የሚያጠነጥኑት ደግሞ በ”በሚመጣው ሰንበት” መፅሀፉ ውስጥ ባካተተው ምስጋናና በሰጣቸው መታሰቢያዎች ዙሪያ ነው። ይህንንም ሲመልስ “….መቼም አባትየው ለአገሩ ጊዘውን መስጠቱን ደጋፊውም ተቃዋሚውም የማይክደው ነገር ነው። አከራካሪው ጉዳይ ለአገሩ በሰጠው ጊዜ ምን ያህል ጠቀማት፣ ጎዳት የሚለው ይመስለኛል። እኔ እዚህ ውስጥ አልገባሁም።….” ይልና…. እንደተድበሰበሰ ትቶት ከ’ሁለት ያጣ ጎመን’ ላለመሆን ይዳክራል። ምክንያቱም ይፈራል። –  ወይ ህዝቡን ወይ መንግስትን ይፈራል። …ነገሩን መመለስ ቀጥሎም “የኔ ጉዳይ ልጆቹ ናቸው፣ ልጆቹ ደግሞ የፖለቲካ ምልክት የለባቸውም።” ይለናል በእርግጠኝነትና በልዩ ቅርበት። (በእርግጠኝነትና በልዩ  ቅርበት ስል: እርግጠኛ ለመሆን ቅርበት ያስፈልጋል ብዬ ነው። የቅርበቱ ልዩ መሆን የሚስተዋለው ደግሞ ልጆቹን “ጉዳዬ” ማለት ሲጀምር ነው።)

ስፈልግ ደግሞ…“ታገል ማሽቃበጥ ካልሆነ በቀር አባት ሲሞት የመጀመሪያው ነው እንዴ? ስንቱ አገሩን ለመጠበቅ (በየትኛውም የፖለቲካ አጀንዳ ስር ሆኖ) ጊዜውን የሰጠ አባት “የኢትዮጵያ” የመባል ወግ እንኳን ቀርቶበት “የደርግ ወታደር” እየተባለ ልጆቹን በትኖ ሞቶ የለ? ስንቱ አገሩ ያበቀለችው እህል ናፍቆት ከረሀብ ብዛት አጣጥሮ ይሞት የለ? ስንቷ እናት ከምግብ ናፍቆት የተነሳ ህይወቷ አልፎ ልጆቿ ደረቅ ጡቷን ሲምጉ ተከትለው የለ? ስንቱስ ስንኩል አካሉን (እድሉን) ይዞ በስተርጅና ለልመና ተሰማርቶ የለ? ስንቱስ (ትክክል ባለው ፖለቲካዊ አጀንዳ) ጊዜውን ለአገሩ ሲሰጥ ልጆቹን በትኖ እስር ቤት ተጥሎ የለ? በግፍ ተሰቃይቶስ አልፎ የለ? ስንቱስ ልጆቹን አገር ቤት በትኖ፣ በሞያው ተሰድዶ በየሰው አገሩ ባክኖ ቀርቶ የለ …” እያልኩ መሞገት እችላለሁ። ግን አውቆ የተኛ’ እንዲሉ ቢፈልግ እንደማይጠፋው ስለማውቅ ድካም ብቻ ሊሆን ይችላል።

በርግጥ መፅሀፉን ለማን መታሰቢያ ማድረግ እንዳለበትና እንደሌለበት የሚያውቀው እርሱ ነው። ማንምም ጣልቃ ገብቶ ልንገርህ አላለውም። መፅሀፉን ገዝቶ ካነበበው በኋላ ግን ቅሬታውን ገለፀ፤… ታዲያ በውኑ ይሄ እርሱ እንዳለው “ጅልነት” ሊባል ይችላልን? ምኑስ ከድፍረት ይቆጠርና ነው እንዲህ ያለውን “ልኩን የማያውቅ ደፋር ብቻ መሆኑን ነው መልሼ የምነግረው” ማለቱ? እርሱ “ግጥም አይደሉም” ያላቸውን ግጥሞች ለማዝናናት በሚል ፈሊጥ አትሞ ሲሸጥ ማን ደፋር አለው? መፅሀፉ ላይ እንደፈለገ ምስጋናና መታሰቢያ አድርጎ በ27 ብር ግዙ ሲል ማን ደፋር አለው?

በስሜት ተነሳስቶ የፃፋቸውን ግጥሞች፣ በስሜቱ ተመርቶ አመስግኖና መታሰቢያ አድርጎ ሲያበቃ… ስለምን የአንባቢው ስሜት ማዳመጥ ጋር ሲደረስ ይቆጣል? …ወይስ የማፈን (የሰዎችን የመናገር ነፃነት የመገደብ) ውርስ ነው? ቢያውቅስ — ልክ እርሱ ለማንም ምንም ማድረግ እንደሚችል እንደሚያውቅ ሁሉ፣ ሌላውም እርሱ ያለውን ነገር ካለምንም ማብራሪያና ድጋፍ፣ ቁጣና ማበሻቀጥ መረዳትና መተንተን ይችላል። እዚህ ጋር ከላይ ያስቀመጥናትን የፕሮፌሰርን ሀሳብ መመልከት ነገሩን ያጠነክረዋል። ደግመን ስናነባት እንዲህ ትላለች….

“አንድ ሰው በአደባባይ ሲናገርም ሆነ ፅሁፍ አሳትሞ ሲያሰራጭ ራሱን አጋልጧል፤ የተናገረው ወይም የፃፈው መቶ በመቶ  ያህል በራሱ ጉዳይ ላይ ብቻ ከሆነ፣ የመተቸት ወይም ሀሳብ የመስጠት ግዴታ የለብንም፤ ነገር ግን የተናገረው ወይም የፃፈው በአገርና በህዝብ ጉዳይ ላይ ከሆነ፣ የዚያ አገር ዜጋ ሁሉ በጉዳዩ ውስጥ የመሳተፍና ሀሳቡን በሙሉ ነፃነት የመሰጠት መብት አለው፤ አለዚያ በየጓዳችን በሀሜት ብቻ እየተዘላዘልን እውነትን አንጥሮ በአደባባይ የማውጣቱን ዘዴ ሳንማር ሌላ ሶስት ሺህ ዓመታት እንቀጥላለን።” ~ መስፍን ወልደማርያም (2005) ‘መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ’ ገፅ. 78 – 79.

ታገል ቀጥሎም

“የአንድን ደራሲ መፅሀፍ ሲገመግም ጣልቃ ከማይገባባባቸው ጉዳዮች አንዱ የመታሰቢያ  ገፅ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የምስጋና ገፅ ነው። አንድ ደራሲ ለህሊናው ታማኝ ከሆነ የሚያመሰግነውን ሰው የሚመርጠው ሰውየው በሌሎች ኧይን የሚታይበትን ገፅታ ከግምት አስገብቶ መሆን የለበትም ይልቁንስ ሰውየው በእርሱና በስራው ላይ ካሳደረው በጎ ተፅእኖ አንፃር ነው።…”

ሲል ይሰብካል።

ሆኖም ግን የሳተው ነገር ማንም የምታመሰግነውን ሰው እኔ ልምረጥልህ አለማለቱን ነው። እድሉ ወይም ፍላጎቱ ሆኖ ግን ያመሰገናቸው ሰዎች በይፋ የሚታወቁ ስለሆኑ አስተያየት ተሰጠበት። በቃ! እርሱ ሲያመሰግንና መታሰቢያ ሲሰጥ እንዲህ ዓይነት አስተያየቶች  ሊሰጡት እንደሚችሉ ቀድሞ ካልጠረጠረ ጅሉ እርሱ እንዳለው አስተያየት ሰጪው ሳይሆን፣ ራሱ ነው። በዚያም ላይ ታገል ያመሰገነውና መታሰቢያ የሰጠው በህዝብ ጉዳይ ላይ ነው። (የተለየ ቅርበት አለኝ ቢልም እንኳን) በመሆኑም ፕ/ር ቁልጭ አድርገው እንዳስቀመጡት ‘የዚያ አገር ዜጋ ሁሉ በጉዳዩ  ውስጥ የመሳተፍና ሀሳቡን በሙሉ ነፃነት የመስጠት መብት አለው።’

እንደዚያ ካልሆነ ግን ፕ/ር ቀጥለው እንደገለፁት ‘በየጓዳችን በሀሜት ብቻ እየተዘላዘልን እውነትን አንጥሮ በአደባባይ የማውጣቱን ዘዴ ሳንማር…’ ሌላ ብዙ ጊዜያት ያልፋሉ። በመሆኑም ከጓዳ ወጥተው ስሜታቸውን በፌስቡክ የገለፁትን (የገለፅነውን) ሰዎች “ችግር ፈጣሪ” እና “ለፌስ ቡክ ክብር የሌላቸው” ብሎ እርሱ ሀሳቡን ለሚገልፅ ሰው ክብር እንደሌለው መግለፅ አልነበረበትም። ይልቅስ ፌስቡክ ላይ አስተያየት መሰጠቱ፥ ይህንን የመናገርና ሀሳቡን ቦርቀቅ አድርጎ የማስረዳትና ራሱን በተሻለ የመግለፅ እድሉን አመቻችቶለታልና በጥሩ ጎኑ ተመልክቶት ማመስገንና፣ ፌስቡክ የተጫወተለትን ሚና ማድነቅ ይቀለው ነበር። ቅሉ ‘ከምን የዋለች ጊደር…’ ነው።

በክሽፈቱ ሲቀጥል…

“ደሀን የማመሰግንበት ምንም  ምክንያት አልነበረም። ከሀብታሙም ቢሆን እኔን ሳይሆን ኪነጥበቡን ለማገዝ የጣሩት ተመርጠው  ተመስግነዋል። በነገርሽ ላይ አሁን አሁን ግብፅ ስለአባይ አስር ሺህ ዘፈኖች አሏት። የእኛ ግን ሀምሳ አይሞሉም  እያሉ የሚተክዙሰዎች መነሳት ጀምረዋል። የግብፅ መንግስት የኪነጥበብ ሰዎችን ህይወት በተለያየ ሁናቴ ይንከባከባል። ለምሳሌ አንድ ደራሲ ቤቱን ዘግቶ መፃፍ ቢፈልግ የዓመት ደመወዙን ሰጥተው ይሸኙታል። ስራ ከሌለውም ድርሰቱን ቁጭ ብሎ የሚጨርስበትን በቂ ገንዘብ ይሰጠዋል ብቻ በቂ ችሎታ ይኖው።”….

በማለት አንድም ለደሀው ያለውን ንቀት በግርድፉ ያሳያል፤ (ሰውን በገንዘቡና ድጋፍ በማድረግ አቅሙ በመለካት) እንዲሁም ኢትዮጵያን ከግብፅ ጋር በማነፃፀር ለእድሜውም ለፆታውም የማይመጥን* ነገር ያወራል። በውስጥ ታዋቂነትም “እንዲህ ተንከባከቡኝ” ብሎ ይማፀናል። ወይ ደግሞ “እንዲህ ነው የተንከባከቡኝ” ሲል ያስረግጣል። እኛንም እኮ ይህ ፍላጎቱን መረዳታችን ነው “ጥበብ ሸረሞጠች” ያስባለን። ስለአባይ መፃፍ ካለበት ግብፅ 1000 ስላላት አይደለም። መፃፍ ካለበት ካለምንም ሁኔታ ይፃፋል እንጂ ማነፃፀሩ የትንሽ ነው።

[*ሴቶች ሆይ: “ለፆታው የማይመጥን” ስል ብዙ ወንዶች (በምናውቀውና በምንስማማበት መልኩ) ከሌላ ጋር መነፃፀር እንደሚደብረን ለመግለፅ ነው እንጂ ለሌላ አይደለም።… ምናልባት አታውቁ እንደሆነ ከጉዳዬ ወጣ ብዬ አንድ ምስጢር ሹክ ስላችሁ ‘ብዙ ወንዶች ከሴቶች ጋር ያላቸውን ግንኙነት ከሚያቋርጡባቸው አንኳር ምክንያቶች አንዱ በሴት ጓደኛቸው ከሌላ ወንድ ጋር መነፃፀር (compare መደረግ) መሆኑን የእኔ ጥናት ያሳያል። ሃሃሃ… የምር ግን ብዙ ወንድ “ኧከሌ ስላደረገ አድርግልኝ” ሲባል ደስ አይለውም።]

ታገልን በአካል ሳውቀው…

ታገልን ለመጀመሪያ ያወቅሁት እንዴት እንደነበረ ማስታወሱ “ደሀን የማመሰግንበት ምክንያት አልነበረም።” ማለቱን ኢ-ልክነት (የ “ኢ”ን አፍራሽነት ልብ ይሏል።) ለማሳየት ይረዳናልና ላጫውታችሁ። (ኢ-ልክነቱ በእኔ እይታ እንጂ አሁንም ቢሆን የምርጫው የርሱነት እንደተከበረ ነው።) ከእለታት በአንዱ እሁድ ነበረ። ቄራ መብራት ሀይል የሚገኝ ኢስት-ዌስት የተባለ አዳራሽ፣ የቤተሰብ ሰርግ ስለነበረብን ሁላችንም ተበታተንን፤ በብተናው መሰረትም እኔና የእህቴ ጓደኛ አብረን ለመሄድ ከሜክሲኮ ታክሲ ተጋፍተን ያዝንና ጉዞው ተጀመረ።

ትንሽ ተጉዘን መሀል መንገድ ላይ ታክሲው የጎደለበትን ሰው ለመሙላት ሲቆም ከሚጋፉት ሰዎች መሀል አንዱ ታገል ነበር። ተሳፋሪው እርሱ መሆኑ እንደተስተዋለ፥ ከውስጥም ከውጭም ትኩረት ሳበ። ‘ታገል ታገል…’ እያለ ሰዉ ሁሉ ስሙን ማንሾካሾክ ጀመረ። ከውጭ ያሉትም ግፊያቸውን ረገብ አደረጉት። ከውስጥ ያሉትም በማክበር ቦታ ለማስፋት ብድግ፣ ብድግ… ጠጋ፣ ጠጋ አሉለት። ‘ና እኔ ጋ፣ ና እኔ ጋ’ በሚል ማባበያ ዓይነት። — ታገል ነዋ!

እርሱም የትኩረት ማዕከል መሆኑ እንዳልተመቸው እያስታወቀበት እጅ ነስቶ ለመግባት ሲል ቀድመው የገቡት ታክሲውን ሞልተውታል። ረዳቱም “ሞልቷል” ለማለት አፍሮ ፀጉሩን ሲደባብስ፣ ፊት ያሉ ተሳፋሪዎችም በአንድ ጎን ከርሱም ጋር ተሳፍሮ  ለመቆየት፣ በሌላው እርሱን አክብሮ (እንዲሁም እርስ በርሱ ተከባብሮ) ቦታውን ለመልቀቅም በማሰብ “እኔ ልውረድ እኔ…” በማለት ሲገባበዙ…. ነገሩ ያልገባው ሾፌር ተበሳጭቶ “እናትህ እንዲህ ትሁን!  ዝጋውና እንሂድ አቦ…” (ዓይነት) ብሎ ዞር ሲል፣ ፊት ለፊት ታገል ነው። እርሱም በተራው ጋባዥ ሆኖ “እንዴ ለርሱማ ቢፈልግ ልቀጣ ጫነው” ብሎ ታገል ተጭኖ፣ በትህትና አመስግኖና በክብር እጅ ነስቶ ጉዞው ቀጠለ።

[ስፅፈው ረዥም ይምሰል እንጂ ሁሉም ነገር የአፍታ ክስተት ሆኖ አሰልቺ አልነበረም። ይህ ሁሉ ሲሆንም ታገል ፍፁም ሌሎቹን በማክበር….. አለመፈለጉን በትህትና በመግለፅ ሲታገል ነበር። ታገል – ሲታገል…. ሃሃሃ…] ታዲያ ይሄ ደሀ፣ በችርቻሮ ባይሆን እንኳን በጅምላው መመስገን ያንስበታል? (በችርቻሮውማ… ‘ሰማይን የሚያህል ብራና ተፍቆ፣ አባይን የሚያህል ቀለም ተበጥብጦ’ም አይዘለቀም።) እንግዲህ ይህ እኔ ከአንዳ’ንድ የገጠመኝ ነገር ነው። ይህ ቢቀር እንኳን ከያኒው ለስንት ፅሁፎቹ መነሻ ሀሳብ ከድሀ ህይወት አላገኘም? ፅፎ ሲያሳትምስ አብላጫው ገዝቶ አንባቢው ደሀው መሆኑን አላወቀም? (ሀብታም እንደው ብር ቢኖረው፣ ወይ ልብ ወይ ጊዜ የለውም ብለን ኮምፓችንን እናንጫጫው እንዴ? ሄሄሄ….)

‘ፍየል ወዲህ…’

አቶ ታገል ከሌላ አገራት ጋር የጀመረውን ንፅፅር በመቀጠል….

“አብደላ እዝራ እንዳጫወተኝ ደግሞ የመን ውስጥ አንድ ገጣሚ ከተነሳ የአገሩ ሀብታሞች በሙሉ ተጠራርተው ለኑሮው የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ ያጎርፉለታል። ይንከባከቡታል። እኛ አገር ደግሞ ይኧውልሽ በስንት ዘመን አንዴ ኪነጥበብን የሚንከባከቡ ጥቂት ግለሰቦች ብቅ ሲሉ ለምን ተመሰገኑ ብለን እንተቻለን። ደስ አንልም?”

ብሎ  ለማሽሟጠጥ ይሞክራል። ተንጋሎ በማሽሟጠጥ ለአናቱ እያስተረፈ። ….አሁን ይሄን እንተንትነው ቢባል ጉንጭ ከማልፋት ያለፈ ፋይዳ ይኖረዋል?…. ሌላ ሌላውን ትተን ግን ከሰሞኑ የተዘጉብንን መፅሄቶችና ጋዜጦች ማንሳት የኪነጥበብ እንክብካቤውን አቅጣጫ ፍንትው አድርጎ ያሳያል።

የፌስቡክ ማህበረሰብን ሲተች ደግሞ …..

“ከዚህ የተነሳ ሰው ሲሞገስ ለምን እንላለን ነገር ግን ዳገቱ የቁልቁለቱን ያክል ነው የሚባል ተረት አለ። ምናልባት በየፌስቡኩና በየሚዲያው ታላላቅ የአገር ባለውለታዎች የሚናገሩትን በማያውቁና የማያውቁትን በሚናገሩ ምላሶች ዝቅ ዝቅ መደረጋቸው ከፍ ከፍ እንዳረጋቸው ያነሳሳኝ ይመስለኛል።… ስለዚህ ጀግኖችን ለማንሸራተት ያበጁት ቁልቁለት ካልሰቀጠጣቸው የቁልቁለቱን  ያክል ብድግ ያለውም ዳገት ሊረብሻቸው አይገባም።  ምክንያቱም የኔን ዳገት የፈጠረው የእነሱ ቁልቁለት ነው።”…

….በማለት ስለማያውቀው (ወይም አይቶት ስላልገባው) ነገር ይዘባርቃል። — ለዚያውም በ“ይመስለኛል”። ዳገቱን ያወራልናል። ዳገቴ ካለው ቦታ ሆኖም ፌስቡክ ተጠቃሚዎችን ወደማያውቀው ቁልቁለት እያቆለቆለ ለመዘርጠጥ ይባዝናል። …እግረ መንገዱን (ከላይ ራሱ በጀመረበት መልኩ) ‘ልኩን የማያውቅ ደፋርነቱንና… ከማሞ ቂሎ የዘቀጠ ጅልነቱን’ ይነግረናል። ….“የጊዮርጊስን መገበሪያ የበላ ሳይጠይቁት ይቀባጥራል” እንዲሉ፥ ሳይጠየቅ። (ጥያቄው ‘….አንዳንድ ሀብታሞችን በጣም ታሞግሳቸዋለህ ብለው የሚተቹም አሉ።’ ይላል እንጂ የፌስቡክን ስም አለማንሳቱን ልብ ይሏል።)

በእውነት ለዚህ ከንቱ ንግግሩ ማብራሪያ  መስጠት ማሰቡ ትንሽ ወደ ታች መውረድ ሊፈልግ ይችላልና ለአፍላፊው ሀይማኖቴና አስተዳደጌ ስለማይፈቅዱልኝ አላደርገውም። ሆኖም ግን ቢያንስ ለማሞገስ ያነሳሳውን ነገር በ“ይመስለኛል” ማለፉ አሳፋሪ መሆኑን መጠቆም አግባብ ይመስለኛል። (እኔም ይመስለኛል። ሃሃሃ….) ደግሞ እንደ ሀይለኛ ነገሩን ሲቀጥል “በእርግጥ እኔም የጥበብ ሰው ከሆንኩ ሌሎች ምን ይሉኛል ሳልል የስሜቴን ጅረት ተከትዬ መፍሰስ አለብኝ።”…. ይላል። ታዲያ ስለምን አንባቢው “ታገል ምን ይለኛል” በሚል የስሜቱን ጅረት ተከትሎ እንዲፈስ በመጠየቅ፥ የተሰጡትን አስተያየቶች በማብራራት ፈንታ በተራ ፍልስፍና ያወግዛል?

ከተፎው ታገል! (ክትፎው አላልኩም) 

ከ“ምናውቃለሁ እንጃ” ግጥም ስር ያሰፈረውን ማብራሪያ በተመለከተም….

“መገምገም ካለብኝ ባቀረብኩት ስራ እንጂ ባቀረብኩት ስፍራ መሆን የለበትም። ለምሳሌ በእዛን እለት በሚሊኒየም አዳራሽ ያቀረብኩት ግጥም ተጀምሮ እስኪያልቅ የሚተርከው በአፄ ፋሲልና በአፄ ላሊበላ ዘመን ስለነበረችው ታላቋ ኢትዮጵያ ነው።”

በማለት ጀምሮ፥ በ ‘ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ’ ነገር፣ መልሶ ወደ ማነፃፀሩ ይሄዳል፤ እንዲህ በማለት. . . .

“ከማውቀው ድረስ በሰለጠኑት አገሮች ሳይቀር ታላላቅ የመንግስት ክብረ በዓሎች ላይ ገጣሚያንን መጋበዝ የተለመደ ነው።…. መሪዎቻችን አገራቸውን አይወዱም ከማለት አንፃር ከሆነ አገሩን  ከማይወድ መሪ ፊት ቆሞ የአገር ፍቅርን ማዜም እራሱ ጀግንነት ነው። መሪዎቻችን አገራቸውን ይወዳሉ ከተባለም እዚያ ስፍራ በቀረበው ግጥም ኢተገቢ ነገር አልተፈፀመም ማለት ነው ብዬ ነገሩን ችላ አልኩት።”……

በማለት አሁንም ቢሆን ጥግ ለመምረጥ መፍራቱንና፣ መሀል ሰፋሪነቱን በማደናገር ይነግረናል።

“ተወደደ የሚሉም አሉ።” ተብሎ ሲጠየቅ… “27 ብር?” በማለት ይጠይቅና፣ ዝብዘባውን በከንቱ ምሳሌ አጅቦ ይቀጥላል…

“ከሆነ እንግዲህ ሻይ ቤት ገብተሽ አንድ ሳህን ሙሉ ፓስታ በስምንት ብር ትመገቢያለሽ እንበል። ሆቴል ገብተሽ ደግሞ ሲኒ ማስቀመጫ በምታክል ጣባ እፍኝ ክትፎ በሰማኒያ ብር ትመገቢያለሽ የክትፎውን ዋጋ ውድ ነው ካልሽ ርካሽ ነገር ታውቂያለሽ ማለት ነው። ይህ እውቀት ግን አንድ ጣባ ክትፎን ለመገምገም በቂ አይደለም። ምክንያቱም የሆቴሉ ባለቤት ሰማኒያ ብር ሲያስከፍልሽ የስጋውን፣ የቅቤውን፣ የቅመሙን፣ የመስተንግዶውን ወጪ እግምት አስገብቶ ነው። ስለዚህ ከሻይ ቤቱ ፓስታ ጋር አነፃፅሮ ተወደደ ማለት ትንሽ ይከብዳል። የቀረበልኝ ነገር ዋጋውን ይመጥነዋል ወይ ብሎ መጠየቅ ግን ይቻላል። የዚህን ጥያቄ ትክክለኛ ምላሽ የሚያገኙት ታዲያ ዳርዳሩን በሽፋኑ በመታሰቢያው በግርጌ ማስታወሻው በምስጋናውና በዋጋው ዙሪያ የሚባክኑት ሳይሆኑ ግጥሞቹን ገልጠው ማንበብና ማጣጣም የሚችሉ ብቻ ናቸው።”

በማለት የአንባቢው ርካሽ የማወቅ ችግር እንጂ የርሱ ውድ መሆን ያለመሆኑን በትምክህት ይነግረናል። የርሱን ክትፎነትና የሌሎቹን ፓስታነት በኩፈሳ ያወራል። — እንግዲህ የመጥፋትና የመክሸፍ (መልሶ መላልሶ) ጥግ ማለት ይሄ ነው። (ካልሆነ ግን በአክብሮት ስለማተሚያ ቤት ዋጋ ውድነት ማውራት ይበቃው ነበር።)

‘ሽንትንትኑ’ ታገል (ሽንት እንትን አላልኩም!)

(እንትንትን የሚል ቃል ከዚህ በፊት ሰምቼ አላውቅም፡፡ የታገል ነገርም ታይቶ እንዳልታወቀ ነገር መላ ቅጡ ቢጠፋብኝ፣ በፈቃዴ ተሰምቶ የማይታወቅ ቃል ፈጠርሁለት፡፡)

ጥያቄው ቀጥሎ…. “እስካሁን ድረስ በፌስቡክ ላይ ለወረዱብህ ውግዘቶች ይሄን  ሁሉ ምላሽ ይዘህ ድምፅህን ያጠፋኧው ለምንድን ነው?” ተብሎ ሲጠየቅ

“ከመፅሀፍ ቅዱስ የምወደውና የሚመራኝ አባባል አለ። “የባልቴቶችን ከሚመስል ወሬ ራቅ” ይላል። እኔ ድሮ የማውቀው የባልቴቶች ወሬ በረከቦት ዙሪያ እንደነበር ነው። አሁን ወጣት ባልቴቶችን የሚሰበሰቡት ረከቦት ፌስቡክ ሆነ። ስለዚህ ከዚያ አካባቢ  ወሬ /መልስ ባለመስጠት/ መራቅ ነበረብኝ።”

…በማለት አጉል አዋቂነቱን ይቀባጥራል።

‘ባልቴት’ ካላቸው መሀል በሌሎች አገራት ፌስቡክ ረከቦት ዙሪያ ተገናኝተው መንግስት መገልበጣቸውን አያውቀውም። ምክንያቱም ወይ ፌስቡክ አካውንት የለውም፤ ወይ ደግሞ እርሱ ዙሪያ ያሉት ባልቴቶች ብቻ ናቸው። አገራችን ውስጥም በፌስቡክ አማካኝነት ብዙ ዓይነት የማህበረሰብ ስራዎች መሰራታቸውን አያውቅም። ምክንያቱም ወይ ፌስቡክ የለውም። ወይ ደግሞ ፌስቡክ መጠቀም አይችልም። ደግሞም እርሱ እንዳለው ባልቴቶች ተሰብስበው እያወሩ ነው ቢባል እንኳን የመፅሀፉን ጥቅስ በግርድፉ ወስዶ እንደጋሻ በመጠቀም፣ ከመራቅ ይልቅ እንደተቆርቋሪ ዜጋ መርዳትና ማስረዳት ይችል ነበር። ግን ወይ ፌስቡክ አካውንት የለውም። ወይ ደግሞ ፌስቡክ መጠቀም አይችልም።

ከድንዛዜው ቢነቃ ግን ኢንተርኔት በውሀ አለመስራቱን (በተለይ እኛ አገር) በመገንዘብ፣ ፌስቡክ ላይ ያሉ ወጣቶች (በእርሱ መፅሀፍ ዙሪያ ለመወያየት ፍላጎት የሚኖራቸው) ቢያንስ ኢንተርኔት የመጠቀም ጥቂት እውቀትና፣ ለኢንተርኔት የመክፈል አቅም ያላቸው መሆኑን ገነዘብ ነበር። መፅሀፉንም ቢሆን ገዝተን አንብበን ማውገዛችን ይገባው ነበር። ቅሉ ቅልብልብ ነውና…. “….ከጠፋ ራስ ጋር አተካራ መግጠም  አልሻም።….” ምናምን ብሎ ቃለመጠይቅ አድራጊዋ ሳታሰናብተው ለመቋጨት ያመሰጋግናል።

ከዚያም እህት አልጋነሽ “እኔ መች ጨረስኩ?” ትለዋለች። እርሱም (የምንተእፍረቱን መሰለኝ) “ቀጥይ” ይላታል። ጠየቀችው…. “ከዚህ ሁሉ ውዥንብር አንፃር ፌስቡክ ጠቃሚነው ትላለህ?” (መቼስ ተጠይቆ “አላውቅም/ይለፈኝ” ማለት ነውር ነው) መለሰላት….

“ጠቃሚነቱ ምንም አያጠያይቅም ግን ይህን የሚወስነው አጠቃቀማችን ነው። እዚህ ላይ የማስታውሰውን ገጠመኝ ልንገርሽ…”

ይልና ስለፌስቡክ ጊዜ መግደያነት ራሱ የፈጠረውን እንጨት እንጨት የሚል ቀልድ በአንድ አዛውንት ስም ይነግረናል። (የአዛውንትን ቋንቋ ጠንቅቄ ስለማውቅ።… አዛውንቱ የተማሩና የነቁ ስለሆኑ ነው ብንል እንኳን፥ እርሳቸው ፌስቡክ ስለመክፈት ቢያስቡ እንጂ ጊዜ መግደያነቱ አይታያቸውም ነበር።) ይቀጥልናም…

“እንደኔ እንደኔ ፌስቡክ ላይ ችግር የሚፈጥሩት ለፌስቡክ ክብር የሌላቸውና ፋይዳውን በቅጡ ያልተገነዘቡ ወገኖች ናቸው። እነዚህ ወገኖች ድሮ ድሮ ስማቸውን ደብቀው በየሽንትቤቱ ግድግዳ ላይ ብዙ ዓይነት ሀሜቶችንና ነውሮችን ሲፅፉ የኖሩ ይመስለኛል። አሁን ደግሞ ፌስቡክን እንደ ሽታ አልባ የሽንት ቤት ግድግዳ ላይ እንደሚያደርጉት ዛሬም ስማቸውን ደብቀው ያሻቸውን ነውር ይፅፋሉ። ያም ሆኖ ፌስቡክ የሽንት ቤት ግድግዳ ሆኖ የቀረው በነዚህ ወገኖች ደካማ ግንዛቤ ብቻ እንጂ በአግባቡ በሚጠቀሙት ወገኖች አይደለም።”

በማለት በከንቱ ነውር በጅምላ ያወራል። (ደግሞም የርሱ መፅሀፍ ላይ አስተያየት መስጠት ትልቅ ችግር የሆነ ያህል።)

አሁን ለዚህ መልስ ይሰጣል? ቢሰጥስ “ሽንት”ን ገላጭ (adjective) አድርጎ ካልሆነ የሚመጥን ነገር ይገኝለት ይሆን?? ከሁሉም በላይ ግን የገደለኝ “ሽንት ቤት” ካለው ቦታ ድድ ማስጣቱ። ወይ ደግሞ ሽንት ቤት ካለው ቦታ የተለቀሙለትን ወሬዎች አምኖ ተቀብሎ ራሱን መጉዳቱ። ሃሃሃ….

ከዚህ በላይ ክሽፈት ግን ከወዴት ይገኛል?!

ማስታወሻ: ከዚህ በፊት በመፅሀፉ ላይ በግሌ የሰጠሁትን አስተያየት ማንበብ የሚፈልግ ቢኖር ይሄን በመጫን ማንበብ ይችላል፡፡

/ዮሐንስ ሞላ/