የሽንት ቤት ፅሁፎች (graffiti)

እንደ መግቢያ

ጨዋታን ጨዋታም አይደል የሚያነሳና የሚጥለው…. እናም ትናንትና መክሸፍ እንደ ታገል ሰይፉ ብለን ወሬያችንን ካቀናበርንና ካጋጋልን በኋላ፣ ብዙ ወዳጆች ሽንትንትኑ ታገል “እንዴት ፌስቡክን የሽንት ቤት ግድግዳ ይለዋል?” ብለው ክፉኛ መንገብገባቸውን ተረዳሁ፡፡ (በነገራችን ላይ እድሜ ለታገል ይሁንና በትናንትናው እለት “ሽንትንትን” የምትል ቃል ለምንወዳት አማርኛችን ያበረከትንበት ሁኔታ ነው ያለው። ሃሃሃ…)

ከዚያ በኋላ፣ የወዳጆቼ መንገብገብ ከነበረብኝ መንገብገብ ጋር ተዳምሮና ስሜቴን አልቆት በእህህ ስቆዝም፤ እንዲሁም ወዳጅ Abe Tokichaw በጉዳዩ ላይ ያጫወተንን አነበብኩና ስለ ሽንት ቤት ፅሁፎች ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ስለ ግድግዳ ላይ ፅሁፎች ማሰብ ጀመርኩኝ። አስቤም አልቀረሁ፣ ጎለጎልኩኝ፡፡ ጎልጉዬም አልቀረሁ የመሰጡኝን ነገሮች አጠር መጠን አድርጌ ለእናነት ተንገብጋቢ ወዳጆቼ ላካፍላችሁ ወደድኩ፡፡ (ለገብጋባ አላልኩም፡፡ ሃሃሃ…)

ትርጉም (በስለሺ! ሃሃሃ….)

የግድግዳ ላይ ፅሁፍ ጥበብ በእንግሊዘኛው  graffiti ይባላል፡፡ ቃሉ ሲወርድ ሲዋረድ መጥቶ በዋናነት የግድግዳ ላይ ፅሁፎች ስያሜ ሆኖ የቀረ ይምሰል እንጂ አፈጣጠሩና አገባቡ ግድግዳን በመቦርቦር የሚፃፉ ፅሁፎችን (ስዕሎችና ቅርፆችን ጭምሮ) ለመግለፅ የሚውል  ነው፡፡  የግራፊቲ ስርወ-መሰረትም “graffiato” የሚል የጣሊያንኛ ቃል ሲሆን፤ ትርጉሙም scratched ማለት ነው። — የተፋቀ፣ የተፋፋቀ እንደማለት፡፡

እነሆ የተፋቀ ከሚለው የጣሊያንኛ ቃል ግራፊቲ የሚል ቃል መጣና ግድግዳ ላይ በፍቀት ለሚሰሩ የጥበብ ስራዎች ስያሜነት ሲያገለግል ኖሮ ኖሮ፣ ….በሂደት ቃሉ የአግልግሎት አድማሱን በማስፋት (ሄሄሄ….)፣ አሁን ግድግዳ ላይ በፍቀት፣ በፅሁፍ ወይም በስፕሬይ የሚፃፉ ፅሁፎችን በሙሉ ለመግለፅ ይጠቅማል፡፡ – ግራፊቲ!  ይህን አገባቡን ሲያሰረግጥልንም የ oxford መዝገበ ቃላት…..

‹‹Graffiti is writing or drawings that have been scribbled, scratched, or sprayed illicitly on a wall or other surface in a public place. Stickers and other adhesives are not considered graffiti. ›› ብሎ ይተረጉመዋል፡፡ ለግራፊቲ ወጥ የአማርኛ ቃል ማግኘት ስላልቻልኩ ግራፊቲ እያልኩ በእንግዘሊዘኛ ስያሜው በመጠቀም እቀጥላለሁ፡፡

ከግራፊቲ ታሪክ ላይ በማንኪያ…

ግራፊቲ ከክርስቶስ ልደት በፊት ጀምሮ በተለያዩ ቦታዎች የነበረ መሆኑ ይነገራል። በምሳሌነት ግብፅ ውስጥ የሚገኙ ጥንታዊ የግራፊቲ ስራዎች የሚጠቀሱ ሲሆን፤ ያኔ የእንስሳት አጥንቶችን በመጠቀም ሰዎች በፍቀት የተለያዩ ፅሁፎችንና ቅርፆችን በዋሻዎችና ገዳማት ግድግዳዎች ውስጥ ያኖሩ እንደነበረ ይነገራል፡፡ በነዚያ ወቅቶች ሰዎች በፍቀት የፍቅር ጥቅሶችን፣ ፖለተካዊ ይዘት ያላቸውን ፅሁፎች፣ እና የተለያዩ ሀሳቦችንና ፍልስፍናዎች ያሰፍሩ የነበረ ሲሆን፣… በአንፃሩ አሁን አሁን በብዛት በግራፊቲ የሚገለፁት ማህበራዊና ፖለቲካዊ ሀሳቦች ብቻ መሆናቸውን በዘርፉ የተመራመሩ ሰዎች ይናገራሉ፡፡

ግራፊቲ ቋንቋን በማስተላለፍና በማሳደግ ረገድ ያለው ሚናም ትልቅ ነበር፡፡ እንደ ምሳሌ፡ ከክርስቶስ ልደት በፊት 1ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ እስከ ከክርስቶስ ልደት በኋላ 4ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ እድሜ እንዳለው የሚነገርለት የሳፋይቲክ ቋንቋ ብቸኛ መገኛ ምንጩ በደቡብ ሴርያ፣  ምስራቅ ዮርዳኖስ እና ሰሜን ሳውዲ አራቢያ በረሀዎች በረሀ ውስጥ በሚገኙ የግራፊቲ ፅሁፎች ላይ መሆኑ ይነገራል፡፡

ግራፊቲ ዘመናዊ መልክ ይዞ ብቅ እንዳለ የሚነገረው ደግሞ በጥንታዊት ግሪክ ኤፈሰስ ከተማ ውስጥ ልብ ቅርጽ ላይ ያረፈ ዱካን ከቁጥሮች ጋር በቅንብር ማስቀመጥ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ነው፡፡ እነዚያ ግራፊቲዎች ሴተኛ አዳሪነት ህይወት (prostitution) ማስታወቂያዎች እንደነበሩ የአካባቢው አስጎብኚዎች እንደሚገልፁ የወሬ ማህደሮች ያትታሉ፡፡ እንዲህ እንዲያ እያለ ግራፊቲ የተለያዩ አገር ሰዎች፣ በተለያዩ ጊዜያት አሻራቸውን ያኖሩ ዘንድ በመጥቀም የራሱን አሻራ ያኖረ የጥበብ ዘርፍ ነው፡፡

ወፍ አይሞትም! (ጀግና አይሞትም እንዲሉ)

እንደ ምሳሌ፡ በአሜሪካ ኦሪገን ግዛት በአንድ ብሔራዊ መስህብ ቦታ፣ የመፈረሚያ ድንጋይ ነበረ፡፡ በ1970ዎቹ ደግሞ የፈረንሳይ ወታደሮች በግብፅ ዘመቻቸው ወቅት፣ ስማቸውን በዋሻዎች ውስጥ ያኖሩ ነበር፡፡ ከዚህ ባሻገር ግራፊቲ ከሂፕ ሆፕ ባህል ጋር የተቆራኝ እንደሆነም ይነገራል፡፡ ቢሆንም ግን ከሂፕ ሆፕ ባህል ውጭም በተለያዩ ቦታዎችና ጊዜያት ላይ በጉልህ የሚታዩና ብዙ ኗሪ የሚጠቀማቸው የግራፊቲ ስራዎች አሉ፡፡

በ2ኛው የአለም ጦርነት ወቅት እና ከዚያ በኋላ በነበሩ አስርት አመታት ውስጥ፣ “Kilroy was here” የተባለና ከዚያ ቀደም ብብዙ አሜሪካውያን ይባል የነበረ ግራፊቲ በዓለም ላይ በብዛት የተስፋፋና በጥቅም ላይ የዋለ እንደነበር ይነገራል፡፡ በቅፅል ስሙ ‹ወፍ› ይባል የነበረው አሜሪካዊው ሳክስፎኒስትና የጃዝ አቀናባሪ ከሞተ በኋላ በኒው ዮርክ አካባቢ ይፃፍ የነበረው ግራፊቲ ‹‹ወፍ አይሞትም/ይኖራል›› ትርጉም የነበረው ነው፡፡ (‹‹ሀበሾቹም ጀግና አይሞትም›› እንድንል፡፡ ሃሃሃ…..)

ግራፊቲና ሊሾ (የሲሚንቶ ልስን)

በዓለም ላይ ግራፊቲ እንደ ተራ መታሰቢያ ማህተምነትም ያገለግላል፡፡ በጣም የተለመደው አይነትም ሰዎች አሻራቸውን በርጥብ ሲሚንቶ ላይ የሚያሳርፉበትና መታሰቢያቸውን የሚያኖሩበት መንገድ ነው፡፡ በልማድ እንዲህ ያለው ግራፊቲ የሚደረገው የህብረት ስራን (ትብብርን) ለማስታወስ፣ ወይም ደግሞ የሰውየውን በዚያ ቦታ ላይ ለመዘከር እንደሆን በዘርፉ ላይ ትኩረት ያደረጉ ሰዎች ያትታሉ፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ በአራችንም ከትንሽ የበረንዳ ሲሚንቶ (ሊሾ) ስራ አንስቶ እስከ ትልልቅ የግንባታ ስራዎቸ ሲደረጉ በቦታው ያሉ ሰዎች ስማቸውንና አመተ ምህረቶችን ሲፅፉ ማየት የተለመደ ነው፡፡ ከዚያም ባለፈ ሰዎች በጣም አጭር የህይወት ታሪካቸውንና፣ የሚወዱትን ሰው ስም በሲሚንቶ ላይ ሲያርፍ ማየት አዲስ አይደለም፡፡ (ስድብና ዘለፋውን ችላ ብለን)

ግራፊቲና ተሳዳቢነት

ከዚህ ባሻገር ግራፊቲ የሰዎችን ስብህና ለማንቋሸሽና ለማጣጣልም ሲያገለግል ይስተዋላል፡፡ በዋናነትም ዘረኝነትን ለማስፋፋትና የተወሰነ ግሩፕን ለማንቋሸሽ/ለማጣጣል የሚውሉ ግራፊቲዎች ይጠቀሳሉ፡፡ ሆኖም እንዲህ ያሉ ግራፊቲዎች በሚመለከታቸው አስተዳደሮች ስለሚነሱ (ወይም ደግሞ በተጠቂዎቹ መልሰው ስለሚፈቀፈቁ – ምናልባትም ሌላ ስድብ ሰፍሮባቸው!) በታሪክ ማጣቀሻነት ይውሉ ዘንድ ፀንተው አይቆዩም፡፡ ብዙ ጊዜና ብዙ ቦታ የዘረኝነት ግራፊቲዎች በኮድ እነድሚፃፉና፣ ለተራ ተመልካች ስድብ እንደማይመስሉ የሚነግረን ‹ሆንኩዊስት‹ የተባለ ተመራማሪ ነው፡፡ ወደ እኛ አገር ስንመጣ ደግሞ በተለይ የሽንት ቤት ፅሁፎች በዘረኝነት ዙሪያ ሲያጠነጥኑ መመልከት የተለመደ ነው፡፡

WTC 9/11 ሰማይ ጠቀስ ህንፃ ግራፊቲዎች 

ግራፊቲን በተመለከተ በቅርብ ከምናስታውሳቸው ውስጥ አስገራሚ ዜና የነበረው  በመንትዮቹdad3c7a4e6ef7e02270f6a706700ac3a ህንፃዎች ምትክ የሚገነባው WTC 9/11 ግንባታ ላይ ግራፊቲ መፈቀድ ነው፡፡ በብዙ ግንባታዎች ላይ ሰራተኞች ግራፊቲ እንዳያስቀምጡና እንዳይፈርሙ ይከለከሉ የነበረ ቢሆንም፣ በዚህኛው ሰማይ – ጠቀስ ህንፃ ግንባታ ላይ ግን ግራፊቲ ያሰፍሩ ዘንድ መፈቀዱ ብዙዎችን አስገርሞ አልፏል፡፡ ግንባታ ቦታው ላይ ከሰፈሩት ግራፊቲዎች መሀልም ….

“Freedom Forever. WTC 9/11”. “Change is from within” “God Bless the workers & inhabitants of this bldg.” ይጠቀሳሉ፡፡ በተጨማሪም “We remember. We rebuild. We come back stronger!” የሚለው ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ የግንባታ ቦታውን በጎበኙበት ወቅት ያሰፈሩት ግራፊቲ ነው፡፡ የጥቃቱ ሰለባ ቤተሰቦችም ስማቸውንና አስተያየታቸውን እንዲያሰፍሩ ተፈቅዶላቸዋል፡፡

ፀረ – ግራፊቲ (ፀረ – ሽብር እንዲሉ! ሃሃሃ….) 

ፀረ ግራፊቲ ቅብ ደግሞ ሰዎች በማጥፋት አባዜ የህዝብና የግለሰቦችን ንብረቶች እንዳያበላሹ ለማድረግ የሚጠቅም ዘዴ ሆኖ ብበዙ ቦታዎች ላይ የሚተገበር ነው፡፡ በዓለም ላይ በፀረ ግራፊቲ ዘመቻ ወቅትም ብዙ ቢሊዮን ዶላሮች ወጪ እንደሚሆኑ የ‹አንድሬው ቱርሌይ› ዘገባ ያትታል፡፡

ግራፊቲ በኢትዮጵያ (በተለይ የሽንት ቤት ፅሁፎች)

በኢትዮጵያ የግራፊቲ ጥበብ ከመች ጀምሮ እንደመጣ ባይታወቅም ጥንታዊነቱ ግን አይጠረጠርም፡፡ ለዚህም የአክሱም አካባቢን የድንጋይ ላይ ፅሁፎች መጥቀስና፣ ቢያንስ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የመጣ እንደነበር መገመት ይቻላል፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን ግራፊቲ በተለያየ ጊዜ ለተለያየ አላማ ያገለግላል፡፡ የትኛውንም የመፃፊያ ሰሌዳ ግድግዳ ብንለው፣ በርሱ ላይ የተፃፈ ነገር ሁሉ ግራፊቲ ነው ማለት ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የሰው ልጆችን ግድግዳ (የቆመ ነገርን ለመግለፅ ብቻ) አድርገን ብናስባቸው፣ ንቅሳት እንደ ጥሩ የግራፊቲ ምሳሌ ሊጠቀስ ይችላል፡፡ (ሃሃሃ…)

ንቅሳት (ታቱ) እንዲህ በዘመናዊ መልክ ከመስፋፋቱ በፊት በአገራችን ሰዎች የሚወዷቸውን ሰዎች ስም፣ ምስሎች እጃቸው ላይ ያሳርፉ ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪ፣ ከላይ እንደ ተገለፀው፣ በአገራችን ብበዛት የሚስተዋለው የሲሚንቶ ላይ ግራፊቲ ነው፡፡ ሊሾ ሲሰራ፣ በቦታው ያለ ሰው፣ በትኩሱ የሆነ ነገር ያትማል፡፡ ቢከለከል እንኳን ብዙ ጊዜ ተደብቆ (በጨለማ መጥቶ) ሲያደርገው ይስተዋላል፡፡ አሁን አሁን እየተለመደ የመጣው ደግሞ የሰርግ ስርዓት ላይ የፊርማ ግራፊቲ ነው፡፡

በተጨማሪም በጥሩም በመጥፎም ጎኑ የሚነሳው የሽንት ቤት ግራፊቲ ሌላውና ዋነኛው ነው፡፡ (የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል እንዲሉ፡፡ ሃሃሃ….) ሌላው ደግሞ የትምህርት ቤት ግድገዳዎችን ለግራፊቲ መጠቀም ነው፡፡ ዴክሶችን መፈቅፈቅም የተለመደ ነው፡፡ በዚህ ሁሉ ሂደት ግን ከሰል፣ ቾክና፣ ሹል ብረቶችና ቀለም የሚተፉ በዕሮች ዋነኛ መገልገያ መሳሪያዎች መሆናቸው ይታወቃል፡፡

ለምን ሽንት ቤት?

 ከሞላ ጎደል እንደምንረዳው የግራፊቲ ጥበብ ሀሳብን የመግለፅና መልእክትን የማስተላለፍ ፍላጎት ውጤት ነው፡፡ ሰዎች ሀሳባቸውን እንዳይሰጡ በሚጨቆኑባቸው ቦታዎች ደግሞ የግራፊቲ አጠቃቀም በድብቅ፣ ንብረቶችን በማበላሸትና ህሊናቸውን በመጨፍለቅ ዋጋም ቢሆን ሲተገበር ይስተዋላል፡፡ በርግጥ ከላይ እንደጠቀስነው ግራፊቲ በተለያዩ ቦታዎች  የራሱ የሆን የአጠቃቀም ታሪክ ያለው ቢሆንም ወደ እኛ አገር መጥተን ስንመጣ ግን አብላጫው ታሪኩ ህዝባዊ ግድግዳዎችን በማበላሸት መተግበሩ ነው፡፡

ሰዎች በየሽንት ቤቱ፣  መጥፎ ሽታውን ተቋመውና ግድግዳውን እያበላሹት መሆኑን እያወቁም ጭምር የሚፅፉት ለምን እንደሆነ ጠይቀን መልሱን ብንፈልግ፤ ብዙ መድከም ሳያስፈልገን፣ በሰዎች ሀሳብን የመግለፅ ፍላጎት ላይ መታፈንና ይሉኝታ ተጨምረውበት መሆኑን በቀላሉ እንረዳለን፡፡ (ለመሳደብ የሚጠቀሙትን ሳንቆጥር፤ ሆኖም ግን ተሳዳቢዎቹ ቢሆኑም ጀርባቸው ቢጠና ስነልቦናዊም ሆነ ማህበረሰባዊ ትንታኔ ሊሰጠው የሚችል አመጣጥ ሊኖራቸው እንደሚችል እገምታለሁ፡፡) እዚህ ጋር መሳት የሌለብን አንድ ነጥብ ደግሞ ሀሳብን በመግለፅ ፍላጎት ውስጥ የመደመጥ ፍላጎትም መኖሩን ነው፤ እንዲያ ባይሆንና ይነበብልኝ ባይልማ ቤቱም ሊፅፈው ይችል ነበር፡፡

መጠየቅ ነውርና ለጥላቻ ዋዜማ በሆነበት ቦታና ጊዜ ወቅት ሰዎች ጥያቄያቸውን ተደብቀው ይጠይቃሉ፡፡ (በዚህ ረገድ ሀይማኖታዊ ጉዳዮች ላይ ለማውራት መተፋፈር፤ እንዲሁም ገዢ መንግስትን ለማውገዝ መፍራት በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡) የሰዎች አስተሳስብና እምነት በማይከበርበት ቦታ ላይ ሰዎች ተደብቀው ሀሳባቸውን የመግለፅ ፍላጎት ያዳብራሉ፡፡ የሚያምኑበትና ጠቃሚ የሚሉት ነገር ሲኖራቸው፣ እንደ አቅማቸው መጠን ተደብቀው ይሰብካሉ፡፡ ለዚህም መጠናቸው እንደልብ ባያንከላውስም፣ ለአገራችን ህዝባዊ ሽንት ቤቶች ዋነኛ የግራፊቲ መድረኮች ናቸው፡፡

ፌስቡክ የእኛ ግራፊቲ ማስፈሪያ ግድግዳ!!

ምንም እንኳን ፌስቡክ በአካሉ ግድግዳ ስላልሆን የግራፊቲን ትርጉም አገባብ ቢፃረርም፣ (እኛ ግን ታገል በቀደደው ገብተን) ፌስቡክ ዘርፈ ብዙ የሆነ የግራፊቲ ማስፈሪያ ግድግዳችን መሆኑ ግልፅ ነው፤ እንላለን፡፡ ከላይ እነደዘረዘርነው የተለያየ የግራፊቲ አጠቃቀም አይነት ፌስቡክ ላይም በአይነትና በጥራት ተሰባጥረው ይገኛሉ፡፡ (አንዳንዴ በድብቅ፣ ብዙ ጊዜ ደግሞ በትክክለኛ ስም፡፡) በተለይ በዚህ – ጋዜጦችና መፅሄቶች እንዲዘጉ በሚገደዱበት – ወቅት ሰዎችን በማስተንፈስና መረጃ በማቀባበል ዘንደ፤ እንዲሁም ህብረተሰባዊ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶችን ለማድረግ የፌስቡክ ሚና ትልቅ ነው፡፡ እናም እንላለን!! —

ፌስቡክ ሆይ ለዘላለም ኑሪ!!!

በክፉ ያየሽ – ዐይኑ ይጥፋ!!!!

/ዮሐንስ ሞላ/

2 thoughts on “የሽንት ቤት ፅሁፎች (graffiti)”

  1. Hi Yohanes, You are writing mini research articles! I’m surprised. By the way, you can even sell such an article to one of the magazines or newspapers. I haven’t had time to read the rest of your blog but as I roughly looked into it, it is really a great contribution! Berta!
    Eyob Getahun

  2. ኑርልን ወንድሜ … በፌስ ቡክ ላይ ያላቸዉ አሉታዊ ሃሳቦችን የሚያመክን ጥሩ ጽሁፍ ነዉና ወድጄልሃለሁ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s