ዘረኝነት ይብቃን!!

531477_162269207264151_1264232561_nከየትኛውም ወገን፣ በየትኛውም ቦታ ለመወለድ ማንም የራሱን አስተዋፅኦ አላደረገም፤ ምንም ነገርም አላዋጣም። እንኳን ብሔሩን (ዘሩን) ማንም ወላጆቹንም መርጦ አልተወለደም። ሌላው ቀርቶ ለ’ሰውነት’ም የታሰበው እርሱ መርጦና ፈቅዶ አይደለም።…እርስ በርስ በመበላለጥና በመናናቅ ስሜት ውስጥም ባዶ ትምክህት እንጂ ማንም ሌላ ምንም መሰረት የለውም። ስለሆነም…

እርስ በርስ በዘር መጦዛጦዝ፣ እንዲሁም ንግግርን ሁሉ በዘር በመመንዘርና በመዘርዘር እርስ በርስ መናቆርና ማናቆር እጅግ በጣም ኋላ ቀርነት ነው። እናም ይቅር። አእምሮአችንን እናፅዳ። ሌላው ሌላው ነገር ከቁጥጥራችን ውጭ ሆኖ መወራረሱ ቢከብደን፥ ቢያንስ ከዘረኝነት የፀዳች ኢትዮጵያን ለልጆቻችን እናቆይላቸው ዘንድ ቅንነት ካለን በቂ ነው።

“በአያቴ በር በኩል ማን እንዳለፈ አላውቅምና ዘሬን አትጠይቁኝ” (ሀሳቡን ነው እንጂ ቃል በቃል አላስታወስኩትም) ~ ሰለሞን ደሬሳ

Photo source: internet

ሰርግና ምላሽ

‘ቀልቀሎ – ስልቻ፣ ስልቻ – ቀልቀሎ’ ይሉት ነገር ደርሶ፣
‘ተደጋገፉ’ አሉ፣ ጎን ለጎን ቆሙ፤ — ክብረት ተደርምሶ፤
ኩራት ተሽቀንጥሮ፣… ሰውነት ተንቆ፣… እርም ተበጣጥሶ፤
ለልብ ቅብብል፣ ለሀሳብ ፍጥምጥም፣ – ውል ፊርማ ታድሶ፣
ወኔ ተጠርምሶ፣… ብር – አጥር ፈራርሶ፣… ህግ ተገርስሶ፤

— የእኒ’ያ ባላንጣዎች!

ይሁና!!

/ዮሐንስ ሞላ/

ዛምቢያ -ሉሳካ

መሳፍንት ባዘዘው
ብዙ ኢትዮያውያን ወገኖቻችን ሁለት አስርታት አመቶች ውስጥ፣ ሰርተው የመለወጥን ተስፋ ሰንቀው፣ ወደ ማንዴላዋ ደቡብ አፍሪካ ተመዋል። አሁንም ቢሆን መትመሙ ቀጥሏል። መቼ እንደሚያቆም አንድዬ ብቻ ነው የሚያውቀው። ከኢትዮጵያ ኬንያ ታንዛኒያ ሞዛንቢክ ደቡብ አፍሪካ አንዱ መንገድ ነው። ይህ መስመር ብዙዎቹን ወስዷል። ከሆነ ግዜ በኋላ ግን ታንዛኒያን ማለፍ እየከበደ መጣ። ስደተኞች እንደሚሉት ደቡብ አፍሪካ ታንዛንያን “እባክሽ ኢትዬጵያዊያንን እዛው መልሽልኝ! ውለታሽን አረሳም! ” ስላለቻት ነው።

ለዚህም ይመስላል የኔሬሬዋ ታንዛንያ አታልፏትም! አለች። ፖሊስ ከህዝቡ ጋር ተባበረ፣ ኢትዬጵያዊ ካያችሁ ጠቁሙ ጉርሻ አለው። እየተባለ በኪሲዋሊ ቋንቋ በየሚዲያው ተለፈፈ። “በውኑ ነብር ዥንጉርጉርነቱን ኢትዮጵያዊ መልኩን ሊለውጥ ይችላልን? ” እንዲል ቃሉ፣ ወገኔ ታንዛኒያ ላይ “እሩቅ አሳቢ ቅርብ አዳሪ ” ሆነ። ታንዛንያ እየያዘች ዲፖርት ብታደርግ መልካም፣ ህገ ወጥ ስደተኞችን የመቅጫ ህግ ስላላት፣ ወደ አሰቃቂ እስር ቤቶቿ ትወረውራቸው ጀመር ።

አሻጋሪዎች ሌላ መንገድ ቀየሱ ። ከናይሮቢ – ካምፓላ – ኪጋሊ – ቡጅንቡራ በባስ እያቆራረጡ ከተጓዙ በኋላ ከቡጁምቡራ እስከ ዛምቢያ ጠረፍ ድረስ ረዥሙን የታንጋኒካ ሃይቅ በጭነት መርከብ የቋርጡታል። ከዚያ በመኪና ወደ ዛምቢያ ዋና ከተማ ሉሳካ፣ ከሉሳካ እስከ ሞዛንቢክ ደቡባዊ ጫፍ በተቆራረጠ የመኪና ጉዞ፣ እዛ ከደረስክ በኋላ ትንሽ የእግር ጉዞ በአሻጋሪህ ፈትአውራሪነት በጨለማ ታደርግና የሽቦ አጥሮች ተቀደውለህ ሹልክ እያልክ ብለህ ወርቅ የምታፈሰውን፣ የማሪያ ሚከቢያን ደቡብ አፍሪካን ርግጥ!!

አነሳሴ ዛምቢያ ሉሳካ ላይ ፣ በአንድ ወቅት ሁለት ወር ከ 15 ቃናት ታስሮ የነበር ጓደኛዬ ያጫወተኝን መጥፎ ትዝታውን ላክፍልህ ነው። ፁሁፌ ዘልዛላ ቢጤ ቢሆንብህም ፣ ታገሰኝ!
ሉሳካ ፣ ትንሽ ናት። ትልቁን ጎዳናዋን “የሃይለስላሴ ጎዳና” ብላ ሰይማለች ። የተወሰወሰችብን ትመስላለች ፣ አዲስ አበባ ተብሎ የሚጠራም መንገድ አላት። ጓደኛዬ ቪዛው ባለቀ ፓስፖርት ሲዘዋወር ተያዘና ወደ እስር ቤት ተወረወረ።

እስር ቤታቸው፣ አራት ሜ በአራት ሜ ስፋት ባላቸው ትንንሽ ክፍሎች የተከፋፈሉ ናቸው። እያንዳንዳቸው ከመቶ በላይ የአዳም ዘርን አጭቀው ይዘዋል ። ለአየር ማስገቢያ አይቅርብን በማለት ይመስላል የአንዲት ጡብ ስፋት ታህል ቀዳዳ አለቻት ። ወደ ትንሿ ሲኦል ከመግባትህ በፊት አለባበስህ ቁምጣ ሱሪ ብቻ መሆን አለበት ። ቁምጣ ከሌለህ ሱሪህን ትቆምጣለህ ።

‘ሲሚንቶ ወለል ላይ ያለመንጣፍ እንዴት እጋደማለሁ?’ ብለህ እንዳታስብና ጓደኛዬ እንዳይስቅብህ!…መጋደም ብሎ ነገር የለም ። ቁጭ ብለህ ነው ምትተኛው። እግሮችህን ከፈት አድርገህ ቁጭ ትላለህ፣ በአንተ እግሮች ክፍተት ሌላው ቁጭ ይላል፣ በተመሳሳይ መስመር ሌላውም እንዲሁ ይደረደራል። አስበው… ደረትህ እና ጀርባው ፣ ሙርጡና እንትንህ ግጥም ይላሉ። በድቀድቅ ጨለማ ውስጥ እንዲህ ሁነህ “ትተኛለህ”…ፎርሙን ካዛነፍክ ቅጣት አለው።

ቤቷ ጄኔራል አላት። ጄኔራሉ ከመቶ መናምኑ እስረኛ ውስጥ ጉልበተኛው ነው። አቅሙ ካለህ ጄኔራሉን ገጥመህ አፈር ድሜ አብላው እና ንገስ! ጄኔራሉ 6 ፍራሾችን ደርድሮ ጧ ብሎ ይተኛል። የእርሱ ምክትል ቁጥር 1 ይባላል ፣ እርሱ ደግሞ 4 ፍራሾችን ደርድሮ የሚተኛ። ቁጥር 2 ሶስት፣ ቁጥር 3 ሁለት፣ ቁጥር 4 አንድ ፍራሽ ላይ ይተኛሉ። 3 ፖሊሶች አሉ ከሶስቱ አንዱ አለቃቸው፣ ብርድ ልብስ አንጥፎ ሲተኛ ፣ ቀሪዎቹ ሁለቱ ባዶ ወለል ላይ የብርድ ልብስ ቁራጭ ተንተርሰው ይተኛሉ።

የመጨረሻው የሥልጣን እርከን የፅዳት ሰራተኞች ናቸው። አራት ሲሆኑ ሰራቸው ጄኔራሉን መንከባከብ ነው ። ልብሱን ያጥባሉ፣ ዙፋኑን ያፀዳዳሉ… በአንድ ጎናቸው እግር እና እራስ እየሆኑ እንዲተኙ ተፈቅዶላቸዋል ። ምግብ በቀን አንዴ የተቀቀለ ቦሎቄ ከገንፎ ጋር ይሰጡሃል ። ከኋላህ ባለው የሰልፍ ግፊ ባላንስህን ስተህ ከጨላፊው ያጨላለፍ ምት ውጭ ሆነህ ምግብህ ቢደፋ አለቀልህ! ነገ በዚህ ስአት ተመሳሳይ ችግር እንዳይገጥምህ አምላክን ለምን… ለዛሬው ምራቅህን ዋጥ!

የካሉሻ ቧልያዋ ዛምቢያ እንዲህ ነች!

‹‹ምከረኝ… ምከረኝ… ምከረኛ!!…››

እድሜአችን ከፍ ካለ ጊዜ አንስቶ አዘውትሮ ‹‹ምከረኝ›› የሚል አብሮ አደግ ጓደኛ ነበረኝ፡፡ ‹‹ምከረኝ›› የሚለው እኔን ብቻ አይደለም፡፡ …ማንንም ያገኘውንና ‹ከእኔ ይሻላል› ብሎ ያሰበውን ሁሉ ‹‹እኔ እኮ አልረባም፤ እንዲህ ሆንኩ… እንዲያ… እስኪ ምከረኝ፡፡›› ምናምን ብሎ ዐይኖቹን በክብር እያቁለጨለጨ ይማፀናል፡፡ መቼስ ትናንት አፈር ያቧነኑት፣ ጭቃ የቧኩት አብሮ አደግ አፍ አውጥቶ ‹‹ምከረኝ›› ብሎ ምን አንዠት ዝም ያስብልና?! — ለአቅመ-ምክር በቃም አልበቃም ‹ይሆናል› ያሉትን የቆጥ የባጥ አውርተው ይሸኙታል እንጂ፡፡

ታዲያ ነገም ሲያገኝዎት ‹ምከረኝ› ከነገ ወዲያም ‹ምከረኝ› ከሆነ ያሰለቻል፡፡…በተከታታይና በሁሉም ነገር ላይ ‹ምከረኝ› መባልዎ፣ የትናንቱ (ምክር ያሉት) ‹ድንጋይ ላይ ውሀ እንደማፍሰስ› ድካም ብቻ እንደሆነ ይሰማዎትና ይደብርዎታል፡፡ ካመረሩ የሆነ ሙድ እየተያዘብዎት እንደሆነ ሊሰማዎትም ይችላል፡፡ ነገሩ ስር እየሰደደ ሲሄድ ደግሞ….የቀድሞው ወዳጅነት ጨክነው ምክር ፈላጊውን ይንቁት ዘንድ ባያስችልዎም፣ ይርቁት ዘንድ ግን ይገደዳሉ፡፡

አብሮ አደጌ እንዲህ ነበር፡፡ — ዛሬም ‹ምከረኝ› ነገም ‹ምከረኝ›… ከነገ ወዲያም ‹ምከረኝ›…. ከነገ ወዲያ ወዲያም ‹ምከረኝ›…. (ግን አልራቅሁም፡፡ አልናቅኩትምም፡፡…. እንዲያው እንጀራ አራራቀን እነጂ፡፡) ይህን ያስታወሰኝ ትናንት ምሳ ሰዓት ላይ ቢሮ አካባቢ የገጠመኝ ነገር ነው፡፡…

አብረን የምንሰራ (ከእኔ ጋር ተመሳሳይ የስራ ማዕረግ ያለው) ሰው ነው፡፡… እድሜው ከእኔ ብዙም አይርቅም፡፡… ቄንጡን በጥሶ ለመዘነጥ ይታገላል፡፡ (ወይ ጀማሪ ነው፡፡ ወይ ደግሞ የማየደክም ጉልበት አለው፡፡)… ከእኔ ጋር ጥሩ ሰላምታ ለመሰጣጠት የሚበቃ ቅርርብ አለን፡፡…. ልክ ምሳዬን በልቼ ስጨርስ መጥቶ እኔ ያለሁበት ጠረጴዛ ላይ ተቀመጠ፤….

በእኔ ቤት ወሬ ማሳመሬ….፤ ‹‹ኬፍ!….ስትቦጭቀኝ ነበር እንዴ…ስጨርስ መጣህ….›› አልኩት፤

እሱ፡ ‹‹ኸረ….እኔ የምለው፣ ወጣቱ ሁሉ ቦጫቂ ነው እንዴ፤ አልቻልኳቸውም!…. ኪሴ ፍራንክ ኖሮኝ ደግሞ ጠይቀውኝ እምቢ ማለት አይሆንልኝም፡፡ አላስወጣ አላስገባ አሉኝ፡፡ አቦ ይደብራላ፡፡ ሰፈር ልቀይር ይሆን….. እስኪ በናትህ ምከረኝ፡፡››

እኔ፡ (ነገሩን ከምኔው ሀሜት/ወደ ልመና ማዞሩ እየገረመኝ) ‹‹….ለምን ዝም ብለህ ትፈለጣለህ ታዲያ፡፡ ካንተ የሚለምነው እኮ ካንተ የተለየ ፍላጎትና አኗኗር የለውም፡፡ ልዩነቱ የሱን ፍላጎት አንተ ማሟላትህ ነው፡፡ በዚያ ላይ አጉል አስለምደህ እነርሱንም ማስነፍ ነው፡፡ የምትፈለጥለት ስታጣ ሊፈልጥህም ይችላል…..›› (ትልቅ ትልቅ ሆኜ ሳከብድ….ሃሃሃ)….

እሱ፡ አዲስ ነገር እንደተገለጠለት ሰው ጭንቅላቱን ላይ ታች እየነቀነቀ አየር ወደውስጥ ስቦ (እንዴት ተገለጠልህ በሚል ግርምት)….. ‹‹እውነትህን ነው፤…. ብሩ ለራስም አይበቃም፡፡ ታውቃለህ…. ወሯ ሳታልቅ ብድር ነኝ…. ባንክ የለ ምን የለ፤ ኸረ እስኪ ምከረኝ በናትህ…. ብር እንዲበቃኝ ምን ላድርግ አንተ ቸገረኝ አትልም፡፡ እንደው ምን እያደረግክ ነው፡፡ ምከረኝ እስኪ….››

እኔ፡ (ሊመጣ ብቅ ያለውን ሳቄን እንደምንም ኮረኩሜ መለስኩትና….) ‹‹ሁሉም ጋር እኮ ያው ነው! መቼስ…፤ ካንተ ጋር ስለማንበዳደር ነው እንጂ እኔም በብድር ነው ወሩን የምገፋው››….

እሱ፡ (አሁን ብቻውን አለመሆኑ ደስ ብሎት ነው መሰል ዘና ብሎ ተስተካክሎ….) ‹‹ሚስት እንኳን ሳናገባ አረጀን እኮ፤ አሁን ላግባ ብትልስ፣ ምን ታረጋታለህ….››

እኔ፡ ከአፉ ቀልቤ….. ‹‹ያው ያገቡት ሚስቶቻቸውን የሚያደርጉትን ነዋ››

እርሱ፡ ….‹‹ማለት ምን ታበላታለህ ማለቴ ነው ኸረ….›› ብሎ አብራራ፡፡
(አትጨቅጭቀኝ አልለው ነገር የልብ ወዳጄ አይደለ…. ግን አንዴ ገብቼበታለሁና ምን አደርጋለሁ፤ ልምከር እንጂ…. )

እኔ፡ ‹‹….ለማግባት ልብህን ክፈት፤ እድልህ ከሆነ የምታበላዋንም ይሰጥህ ይሆናል…››

እርሱ… ‹‹እንደሱማ አሪፍ ነበር፡፡ ግን ጠበስክ እንዴ…. አንተ ግን አታገባም….››

እኔ፡ (አሁን አገኘሁት ብዬ ደስ እያለኝ….) ‹‹ምን ባክህ…. እስኪ እንዴት ልጥበስ ምከረኝ›› ›

እርሱ፡ ወሬዬን አስቀይሶ….. ‹‹የምር አሪፏን ባገኝ አገባ ነበር፡፡ ብንፈልግ በረሀብ እንሙትና ታሪካችን ይመር እንጂ…. ደግሞ ከእንደዛ ዓይነቷ ጋር ሆነህ ብትሞትስ ምን ጣጣ አለው፤ በናትህ እስኪ ምከረኝ…. ምን ላርግ እንድጠብስ…››
(ጥያቄውን በጥያቄ ይሏል እንዲህ ነው፡፡) ተናደድኩኝ፡፡

እኔ፡ (የምክር አገልግሎት መስጫ ቢሮ የከፈትኩ ያህል ከስራ ቆጥሬው….) ‹‹ዐይኖችህን ከፍተህ ፈልግ…. የመሰለችህን ቅረብ…. የተግባባሀትን አግባ…. ከዚያ እየተመካከራችሁ ኑሮ እንዳረጋችሁ መሆን ነው፡፡ ባይሞላልህ መከራ ይመክርሀል፡፡›› …..ብዬው፤ አያያዙ ካልፈቱት የማይፈታ ስለሆን…..በእርሱ የ‹ምከረኝ› ጋጋታ ምክንያት ትዝ ያለኝ አብሮ አደጌ ጋር ደወልኩኝ፡፡

ስልኩ ጠራ… ♫♫

‹‹ሃሎ….ሃሎ…. እንዴት ነህ ሰላም ነው….ተጠፋፋን አይደል….›› ምናምን ተባብለን….. ወዲያው….

አብሮ አደጌ፡ ‹‹ኸረ ምን ባክህ …እንዲህ ሆን፣ እንዲያ….እስኪ በናትህ እንገናኝና ምከረኝ፡፡›› ሲለኝ ስልኩን ሳልዘጋው ሳቅሁኝ፤ እርሱም ነገሩ ሳይገባው አብሮኝ ሳቀ…. (ስቄ ስጨርስ እንደማብራራለት እርግጠኛ ሆኖ….ቅድመ ሳቅ መሆኑ ነው….) የሆነ ቀልድ ነግሬው ተሳሳቅን፡፡

ስልኩ ተዘጋ!

ወዲያው እናቴ አዘውትራ የምትለው ነገር ትዝ አለኝ፡፡ እንዲህ ነበር….

‹‹ብልህን ልምከረው – ምን ይስታል ብዬ
ሞኝን ልምክርው – ምን ይሰማል ብዬ…››

የእናቴን አባባል ይዤ…. የፍልስፍና አድማሴን አስፍቼ አብሮ አደጌንና የቢሮዬን ልጅ በሞኝና በብልህ ለደለድላቸው ማብሰልሰል ስጀምር፣ ‹‹ምከረኝ›› የምለው ሰው ማሰብ ጀመርኩኝ! ሃሃሃ….

አንድ አፍታ 2

ዙረታም ነች! — የለየላት…!! ኡመቴ ዙረታም!
[‘ኡመቴ ምንድን ነው?’ አሃ… በቃ የድሮ የመንደራችን ቃል ነበር። እንደ’ሷ ያለ የሚጠራበት ቃል።]
ሰው ኡምት ሲል፣ መላ ቅጡን ሲያጥ ‘ኡመቴ ነው’ ይባላል።…እናም ‘ኡመቴ ናት!’…
አገር ምድሩን ስትዞር ነው የምትውለው…
ልክ መሬት እንደምትዞር፣ አታርፍም!

ዝም ብላ ስትዞር… ዝም ብላ!
…… እያወራች ስትዞር… — ሰሚ ፍለጋ!
…… እያላወራች ስትዞር….– ወሬ ፍለጋ!
…… እየበላች ስትዞር… — ‘እንብላ’ ምትለው ፍለጋ!
…… እየራባት ስትዞር….– ምግብ ፍለጋ!
…… ሲበሉ ስታይ ስትዞር…–ቅልውጥና!

ስታሳዝን!

ደግነቱ እንደ’ሷ መዞር አይደለም፤….ከተማው አዙሪት የለውም።
— ሲራዳት! ሲረዳት! ሲያረዳት! ሲያርዳት! ለርሷ ቤቷ መመለስ መርዶዋ ነው…
… ዞራ ቤቷ ትመለሳለች። ሲቀናት! ሲያቃናት! አሃ… ማለት የሚያቃናት ስታገኝ! የሚያቀናናት! — ከኑሮዋ! ከራሷ! ከጎረቤቷ!…
ግን ሁሉም ነው የሚቀናባት…

ታድላ!

ሴቶቹ — ‘የባቷ ውበት ከመዞር የመጣ ነው።’ ብለው ይቀናሉ።
— ቀንተውም ይዞራሉ። – ተደብቀው! እንደሷ ለመሆን! አልሆነላቸውም እንጂ ቢሆን በባታቸው መታወቁ ላይቀር….
ወንዶቹ — በርሷ አይደለም! ስትዞር በሚለክፏት ወንዶች ይቀናሉ።
— ቀንተውም አይቀሩ! ያለፈች ያገደመችውን ይላከፋሉ! እንደውሻ… ያንንም… ይሄንንም… — ልክፍ፣ ልክፍ! ቀን ጥሏቸው ‘ክፍ’ እስኪባሉ ድረስ መላከፍ…
ፀጉራቸውን ለውጣው፣ እንደ ጭን ገረድ አብረዋት ቢዞሩ ደስ ባላቸው….
ግን ኦሆ…
— ማን ያስጠጋል? ማን ይጠጋል?

ሰዉን እንጀራ ነው የሚያዞረው። አመል አይደለም። የርሷንም ‘አመል ነው’ ይሉታል እንጂ አይደለም። — ታውቃለች! ይገምታሉ! – እንጀራ ነው….
— አዳሜን እንጀራ በቆመበት ጭውውውው…. አርጎ ይመልሰዋል።
— ሄዋኔንም! እንጀራ ያዞራታል… እንጀራ ያዞራቸዋል…
ታዲያ ለምን ይቀኑባታል?
ሴት ስለሆነች? ወንድ ስለሆኑ? እና ምን ይጠበስ?
ሁሉም ዘዋሪ ነው። ሂያጅ።
— ‘ ♫ አዙረኝ አታዙረኝ’ እያለ ሲዞር የሚውል።
ሲንቀዠቀዠ…. ሲቅበዘበዝ….የሚውል! — እንደ ባጃጅ!

ያው ባጃጅ ነው!
… ባዶውን ወጥቶ፣ ሰው ጭኖ ይመለሳል።
… ሰው ጭኖ ወጥቶ፣ ባዶውን ይመለሳል።
እሷም!
ዙረት…
ባጃጅ ግን ሰው ከመጫን ከማራገፍ ሌላም ጥቅም አለው። ሲዟዟር ለድድ አስጪዎች ገቢ ያመጣል። የገቢ ምንጫቸው ነው። በቃ እንትን ይጫወታሉ! — ሞላ… ጎደለ…
ቁማር!

እርሷም ትጫወታለች! የርሷ ቁማር ግን ከመንገዱ ጋር ነው… ከቀናት ደግሞ ካሳራፊዋ ጋር፤ ካሳፋሪዋ (ላልቶ)፤ ካሳፋሪዋ (ጠብቆ)… ዞራ ዞራ ሲደክማት! ዞራ ዞራ ስታገኘው!…
እስከዚያው ግን፥ ዝም ብሎ መዞር፣
መዟዟር፥
የሰው ናላ ማዞር፣
‘♫ mአዙረኝ አታዙረኝ….
… አሽከርክረህ፣ ከሱ ጣለኝ! ♬’
የዙረት ዜማ…!
ማይክ ይዞ ማዜም!
ካለማይቅ ማዜም!

ዜማ!

ዜማ… ዝሙት… ዘማዊ… ዘመናዊ…
… ‘♫ አዙረኝ አታዙረኝ….
… አሽከርክረህ፣ ከሱ ጣለኝ! ♬’
ግን እሱ ማን ነው?….አሃ! ማንም ነው። ማንም!
ለርሷ ሰው እኩል ነው። ዟሪ ማሳረፍ የሚችል መደብ ካለው ሰው እኩል ነው። ማለት ሲደክማት ደረቱን ተደግፋ ካረፈችበት ወንድ እኩል ነው።
እስክታርፍ ድረስ ካሳረፋት! አስክትደርስ ድረስ ካሳፈራት!

እኩልነት!

እርሷና እርሱ ግን ይበላለጣሉ….
— በመዞር ትበልጠዋለች!
— በማሳረፍ ይበልጣታል!
— በማሳፈር ትበልጠዋለች!
—- በመሳፈር ይበልጣታል!

አይ አይ… ያው ናቸው። — አይበላለጡም! — እኩል ናቸው!
— መዞሯን ፈልጋው ነው!
— መፈለጓ ቢፈልገው ነው!
— ማሳረፉ ብታርፍለት ነው!
— ማረፏ ቢያሳርፋት ነው!
— መሰፋፈራቸውም ቢሰፋፈሩ ነው!

እና?!

የመጀመሪያ ልጇን ስትዞር አርግዛው፣ ስትዞር ነበር የወለደችው…
…ከዚያ ግን ስትዞር ሞተባት። ‘ኧረ ሞት ያንሰዋል እሷ እየዞረች ማን ያጥባው?’ – ብለው ያሟት ነበር። – በሰፈሯ፤
ግን አይደለም!
የመጀመሪያ ልጇን ስትዞር አስረግዟት፣ ሲያዟዙር ነበር ያስወለዳት….
… ከዚያ ገደለባት። ‘እሱ እያዞረ ጡቷን እየተሻማት ልጁን ማን ያጥባው?’ – ብለው ያሙት ነበር። – በሰፈሩ፤

ሀሜተኞች!

ግን አሁንም እየዞረች ነው። ደግሞ ነፍሰ ጡር ነች።
እየዞረች አርግዛለች…
እየዞሩ…
ግን ንጉስ ይሁን ቄስ ማን ያውቃል? – ያቺ የቁርጥ ቀን መጥታ ትለይላታለች እንጂ። እስከዚያው ግን ትዞራለች… ይዞራሉ… — ‘አዙረኝ፣ አታዙረኝ’
— ሰው ስትጭን፣ ሰው ስታራግፍ!
— ወላጅ ስታድን፣ አዋላጅ ስታስስ!
— ሰው ሲጫናት፣ ሰው ሲራገፋት!
— ወላጅ ስታገኝ፣ ወላጅ ስትሸኝ!
— ስታሳፍር፣ ስታፍር!

ለምዳዋለች!

ጭው ብሎባት…. ጭው የምታደርግበትን ትፈልጋለች….
እጅና እጅ ተቆላልፈው….
‘♫ ♬አዙረኝ አታዙረኝ፣
አሽከርክረህ ከዚያ ጣለኝ!♫ ’
ከመደቡ… ከማስወለጃው… ከመውለጃው…. አሃ! እርጉዝ ናት! – ሁለት ነፍስ!

— ማርያም ትቅረባት! እስከዚያው ግን…

♫ ♬አያዙራት አያዙራት፣
ከመደቡ ያሳርፋት! ♫ ♬

/ዮሐንስ ሞላ/

አትሽሺኝ ውዴ!

“ሀብት አልቦ መናጢ፣ የነጣ የገረጣ፣
እንኳን የሚያበላኝ፣ የሚበላው ያጣ፣
… ነው!!”
ብለሽ አትሽሺኝ፣
አደራሽን ውዴ!!

ችጋር እስኪጠፋ፥ ከላዩ ተቀርፎ
የደሀ አዳሩ – ባይሞላ ችሎ አልፎ
በፍቅር ተቃቅፎ፣ ገላው ተቆላልፎ

ባይበላ ታርሶ፣
… አፍ ላፍ ተጎራርሶ፤
… ምራቅ ተደባብሶ፤
… ምላስ ተላልሶ፤
ነውና!

/ዮሐንስ ሞላ – 1995 ዓ/ም/

የፆም ወቅት

የያዝነው ሳምንት ለኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ጫፍ ጫፉን ካርኒቫል ነበር። የካርኒቫል አመጣጥ (etymology) ካርን (carne)ና ቫሌ (vale) ከሚሉ የላቲን ቃላት ነው። ካርን ማለት ስጋ (flesh/meat) ማለት ሲሆን፤ (“ስጋ በሊታ” ለማለት “carnivorous” እንደምንል…) ቫሌ ማለት ደግሞ ‘ቻዎ ቻዎ’ (farewell) ማለት ነው። [ይለናል የኖርማን ሌዊስ Word Power Made Easy መፅሀፍ]

ስለሆነም ‘ካርኒቫል’ ስንል “ስጋ ሆይ ቻዎ ቻዎ” እንላለን። እንደ ደምበኛ ካርኒቫል በየጎዳናው ባንቀውጠውም በየቤቱና በየሆቴሉ በስጋ እንቀውጠዋለን። …’ስጋ ሆይ ቻዎ ቻዎ!!’ እያልን። ከሰኞ ጀምሮ ለክርስቲያኖች የፆም ወቅት በመሆኑ፥ ይህ ሳምንት ባይሰየምም ለብዙዎች ካርኒቫል ነው። – ለሚፆሙትም ለማይፆሙትም! …መቼም ልብ ካልነው በየቦታው የምንታዘበው ነገር ለጉድ ነው።

ዛሬም ካርኒቫሉ ቀጥሏል። ሆቴሎች ተጨናንቀዋል። ጥብስ… ቁርጥ… ቅቅል… ሌላም ሌላም የስጋ ዘሮች… እንደጉድ ይበላሉ። ያም ሆነ ይህ ግን በየትኛውም ጊዜ ጥብስ መብላት ባይችሉ ካልሲን ጥብስ ጥብስ ማሰኘት ይችላሉ/ይገደዳሉ። (ማጠቢያ ውሀ ከሌለ ቀላል ነው)…ቁርጥ መቁረጥ ካልቻሉ ተስፋ መቁረጥ ቀላል ነው። (ለዚያውም በብዙ አማራጭ ታጥረው)…ቅቅል መብላት ካልቻሉ በነገሮችና በአየር ንብረት ለውጡ ይቀቀላሉ። (ሳይወዱ በግድ) ሌላም…ሌላም… ያው ምርጫ ነው። ግዴታ ነው።

እላዩ ላይ ደግሞ ቢራ፣ ውስኪ፣ ቮድካ፣ ጠጅ፣ አረቄ…. ሌላም ሌላም…

ቻው ቻው ስጋ!!

እግረመንገዳችንን ግን ቢያንስ ለፆሙ (እረፍትም ይሆነናልና) “ቻው ቻው” ልንላቸው የሚገቡን ብዙ ነገሮች አሉን። ችሎ ማሰናበቱ ቢቀር እንኳን ለመርሳት መለማመዱ መልካም ነው። እናም እንፆማለን ስንል ከብዙ ነገሮች እንፁም። ከብዙ ነገሮች እንታቀብ።

ለማህበራዊ ኑሮም ሆነ ለግል ስብዕና ጠንቅ የሆኑ ባህርይዎቻችንን እንሽሽ። ከግል እምነታችን (ሀይማኖት) የተነሳ ወቅቱ የፆም ወቅት ያልሆነልንም ብንሆን ካሉብን መጥፎ ባህርያት በመፆም ረገድ ፆሙን እንቀላቀለው። ያው ስጋን መሰናበቱን በጋራ አድርገነው የለ?! — የግል ሀሳቤ ነው!

ለምትፆሙ – መልካም የፆም ወቅት!… ለምትኖሩ – መልካም ኑሮ!… ለምታኗኑሩና ለምታጅቡ – መልካም ማኗኗር!… ከታች ኑሮ እንደበረዶ ቀዝቅዞባችሁ፣ ከላይ ሙቀቱ አንገብግቧችሁ፤ በህይወት ድርቀትና በኑሮ ግለት ውስጥ ለምትኳትኑ የኔ ቢጤዎች – መልካም mixed – ቆላና ደጋ! እንዲሁም ምኑም ለማይሞቅ ለማይበርዳችሁ – መልካም ወይናደጋ!! ሃሃሃ…

ትፆማለህ?” ሲሉህ፤
ኑሮን እንደኖረ፥…
“ኑሮ ራሱ ፆም ነው።”
ብለህ ስትመልስ…
ግን አታፍርም?!

/ዮሐንስ ሞላ/

የፆም ወቅት

የያዝነው ሳምንት ለኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ጫፍ ጫፉን ካርኒቫል ነበር። የካርኒቫል አመጣጥ (etymology) ካርን (carne)ና ቫሌ (vale) ከሚሉ የላቲን ቃላት ነው። ካርን ማለት ስጋ (flesh/meat) ማለት ሲሆን፤ (“ስጋ በሊታ” ለማለት “carnivorous” እንደምንል…) ቫሌ ማለት ደግሞ ‘ቻዎ ቻዎ’ (farewell) ማለት ነው። [ይለናል የኖርማን ሌዊስ Word Power Made Easy መፅሀፍ]

ስለሆነም ‘ካርኒቫል’ ስንል “ስጋ ሆይ ቻዎ ቻዎ” እንላለን። እንደ ደምበኛ ካርኒቫል በየጎዳናው ባንቀውጠውም በየቤቱና በየሆቴሉ በስጋ እንቀውጠዋለን። …’ስጋ ሆይ ቻዎ ቻዎ!!’ እያልን። ከሰኞ ጀምሮ ለክርስቲያኖች የፆም ወቅት በመሆኑ፥ ይህ ሳምንት ባይሰየምም ለብዙዎች ካርኒቫል ነው። – ለሚፆሙትም ለማይፆሙትም! …መቼም ልብ ካልነው በየቦታው የምንታዘበው ነገር ለጉድ ነው።

ዛሬም ካርኒቫሉ ቀጥሏል። ሆቴሎች ተጨናንቀዋል። ጥብስ… ቁርጥ… ቅቅል… ሌላም ሌላም የስጋ ዘሮች… እንደጉድ ይበላሉ። ያም ሆነ ይህ ግን በየትኛውም ጊዜ ጥብስ መብላት ባይችሉ ካልሲን ጥብስ ጥብስ ማሰኘት ይችላሉ/ይገደዳሉ። (ማጠቢያ ውሀ ከሌለ ቀላል ነው)…ቁርጥ መቁረጥ ካልቻሉ ተስፋ መቁረጥ ቀላል ነው። (ለዚያውም በብዙ አማራጭ ታጥረው)…ቅቅል መብላት ካልቻሉ በነገሮችና በአየር ንብረት ለውጡ ይቀቀላሉ። (ሳይወዱ በግድ) ሌላም…ሌላም… ያው ምርጫ ነው። ግዴታ ነው።

እላዩ ላይ ደግሞ ቢራ፣ ውስኪ፣ ቮድካ፣ ጠጅ፣ አረቄ…. ሌላም ሌላም…

ቻው ቻው ስጋ!!

እግረመንገዳችንን ግን ቢያንስ ለፆሙ (እረፍትም ይሆነናልና) “ቻው ቻው” ልንላቸው የሚገቡን ብዙ ነገሮች አሉን። ችሎ ማሰናበቱ ቢቀር እንኳን ለመርሳት መለማመዱ መልካም ነው። እናም እንፆማለን ስንል ከብዙ ነገሮች እንፁም። ከብዙ ነገሮች እንታቀብ።

ለማህበራዊ ኑሮም ሆነ ለግል ስብዕና ጠንቅ የሆኑ ባህርይዎቻችንን እንሽሽ። ከግል እምነታችን (ሀይማኖት) የተነሳ ወቅቱ የፆም ወቅት ያልሆነልንም ብንሆን ካሉብን መጥፎ ባህርያት በመፆም ረገድ ፆሙን እንቀላቀለው። ያው ስጋን መሰናበቱን በጋራ አድርገነው የለ?! — የግል ሀሳቤ ነው!

ለምትፆሙ – መልካም የፆም ወቅት!… ለምትኖሩ – መልካም ኑሮ!… ለምታኗኑሩና ለምታጅቡ – መልካም ማኗኗር!… ከታች ኑሮ እንደበረዶ ቀዝቅዞባችሁ፣ ከላይ ሙቀቱ አንገብግቧችሁ፤ በህይወት ድርቀትና በኑሮ ግለት ውስጥ ለምትኳትኑ የኔ ቢጤዎች – መልካም mixed – ቆላና ደጋ! እንዲሁም ምኑም ለማይሞቅ ለማይበርዳችሁ – መልካም ወይናደጋ!! ሃሃሃ…

ትፆማለህ?” ሲሉህ፤
ኑሮን እንደኖረ፥…
“ኑሮ ራሱ ፆም ነው።”
ብለህ ስትመልስ…
ግን አታፍርም?!

/ዮሐንስ ሞላ/