ጂጂ “GIGI” የሚለውን 3ኛ አልበሟን በልዩ አዘጋጅታ፥ በደግነት ካበረከተችልን ጊዜ አንስቶ …ሁሌም ማለት ይቻላል… ለአድዋ ድል በዓል እለት ከእንቅልፌ የምነቃው በእርሷ ሙዚቃ ነው። ኧረ እንደውም በሰማኋት ቁጥር እንዳዲስ አድዋን አድዋን ታሸትተኛለች። ከልቤ ላይ የሆኑ ነገሮችን እየነቀለች በቦታው ላይ ሌሎች ነገሮችን ስትተክል አያታለሁ። አልከለክላትም። ደስ ይለኛል። እንዲያውም “ካህንዬ”ን ልሸልማት ይዳዳኛል። ምን ላርግ? ‘ልብን የሚመረምርና ከአንጀት ዘልቆ የሚገባ፥ ቃል ካንደበቷ እንደውሃ፣ እንደጅረት ሲፈስ’ሳይ?! እንድትል: –
♪♫ቃል ካንደበቱ እንደውሀ፣ ይፈሳል እንደ ጅረት፣
ልብን የሚመረምር፣ ዘልቆ የሚገባ ካንጀት ♪♫
ቀላል ከፍ ታረገኛለች አሃ?! ያየሁ… የነበርኩ… ታስመስለኝና በእጥቅ ኩራት ትሞላኛለች። “በደስታ፣ በፍቅር፣ በክብር፣ በድል” (በዜማ) ታራምደኛለች — ራሴው ባቀናሁት የሀሳብ ጎዳና ላይ፣ በመስመር…! በቀደምት ጀግኖች በተሰመረ ጠንካራ መስመር። የደምና የአጥንት መስመር። አስታውሳለሁ፥ አምናም “አድዋ” እየዘፈንኩ ነበር የነቃሁት። እንደነቃሁም ‘ የሆነ የሆነ ነገር ተጫውቼ ነበር። በከፊል እንዲህ ይቀነጨባል: –
ዛሬ ከእንቅልፌ የነቃሁት ይህንን ሙዚቃ እያንጎራጎርኩ እና የአድዋ ጦርነት እንዴት እንደ ነበረ በዐይነ ህሊናዬ ለመሳል እየሞከርኩ ነበረ። የተሰማኝም ስሜት የተለየ ዓይነት ሆኖ ፍፁም የሚያም ነበር። ልብን የሚሰብር አስቀያሚ ስሜት። ዓመት በመጣ ቁጥር ቀኑን ከመዘከር ውጪ፥ ስለኛ ነፍሳቸውን እንደከፈሉልን ቀርቶ እንዳልከፈሉልን አድርገን እንኳን መክፈል አልቻልንም። አውቀን በድፍረት ሳናውቅ በስህተት፣ ስለኛ የፈሰሰውን ደማቸውን ችላ ብለነዋል። ጥለን የምንሄደውን ሀብት ለማካበት ስንሽቆጠቆጥ፥ ዛሬም በወኔ ቢስነት አለን። ዛሬም የራሳችንን ክብር አሳልፈን ሰጥተናል። ትናንት አንድ ወዳጃችን ተገርሞ ያደረሰን ወሬ፥ ከነውሮቻችን ባህር ውስጥ በማንኪያ ሲጨለፍ ነው። እንዲህ ነበር. . .
“ሸገር ኤፍ ኤም ላይ የእሳት እና ድንገተኛ አደጋዎች ኤጀንሲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ እየተናገሩ ነው። የሚያወሩት በአዲስ አበባ ለግንባታ ሲባል በየቦታው በተቆፈሩ ጉድጓዶች ምክንያት ስለሚያደርሰው አደጋ ነበር። እናም ባለፈው ዓመት ብቻ 10 ሰዎች ጉድጓዶች ውስጥ ወድቀው መሞታቸውን ገለጹ። ለጥቀውም “በጣም የሚያሳዝነው”አሉ “በጣም የሚያሳዝነው የውጭ ዜጎችም በዚህ ምክንያት መሞታቸው ነው። ይህ ደግሞ ለገጽታችን….”
ከዚህም በላይ ብዙ ብለናል። ከዚህም በላይ ብዙ ሰምተናል።… በርግጥ እንግዳን ማክበሩና መንከባከቡ ጥንትም የነበረ ባህልና ማህበራዊ እሴታችን ነው። ግን እርሱም ራስን በማዋረድ ወጪ ሲሆን ያስጠላል። ለተከባሪውም ቢሆን አስቀያሚ ሽንገላ ነው። ደግነቱ ቅሌታችን በአማርኛ ነው። ለራሳችን በሰራነው ቋንቋ። ዓለምን በቀደምንበት መግባቢያ። እንደ እኔ ግን….ዛሬም ወኔ ያስፈልገናል። ከአባቶቻችን ድል ወኔ መቅዳት ግድ ይለናል። ከአድዋ ድል መማር አለብን።
በአካሉ ጣሊያንን ባይሆንም ብዙ ማባረር ያለብን ጠላት አለ። ዛሬም የአድዋ መንፈስ ነፃነታችንንና በኩራት ቆሞ መሄዳችንን ትናፍቃለች። እርስ በእርስ መከባበራችንና መተባበራችንን ትወዳለች። መሪዎቻችንም፣ እኛ ተመሪዎቹም አድዋን መዘከር ብቻ ሳይሆን እንደ አገባቡ በሚመች መልኩ ልንኖረው ይገባናል። ባፈሰሱልን ደም ፊታችንን ታጥበን፣ ከጠፈረን የዱካክና የእንቅልፍ ስሜት መላቀቅ ግድ ይለናል። የጂጂን ሙዚቃም በእንደዚያ ዓይነት የአካልና የአእምሮ ሁኔታ ላይ ሆነን በጋራ ስናቀነቅነው ይበልጥ ይጣፍጣል። ….ይህ የእኔ ሀሳብና ምኞት ነው!
- በነገራችን ላይ: – ሰሞኑን የአባይን ግድብ በተመለከተ ሳውዲአራቢያ ለእነ ግብፅ ወግና፥ ኢትዮጵያ ላይ ስንትና ስንት ማሽሟጠጦች አድርጋ ሳያባራ/ሳይረሳ፣ ቁጭቱም ብስጭቱም ሳይለቀን… በመነጋው (ከትናንት በስትያ) ጠሚው ሃይለማርያም የሳውዲ ልኡካንን ጠብ እርግፍ ብለው አቅፈው እየሳሙ ማስተናገዳቸው አይረሳም። ያም ሳያንስ አብረው ሆነውም የአትክልት ዓይነቶችን እያዩ ሲምነሸነሹ ነበር። እንዲህ ሆነናል እኛ! አድዋ ተዘንግታለች!!
ዛሬም ከያኒዋ በአድዋ ዜማዋ ትጮሃለች: -…
“♪♫ የሰው ልጅ ክቡር
ሰው መሆንኧ ክቡር
ሰው ሞቷል – ሰው ሊያድን፣
— ሰውን ሲያከብር
በደግነት፣ በፍቅር፣ በክብር ተጠርቶ፣
በክብር ይሄዳል፥ ሰው ሊኖር — ሰው ሞቶ፤” ♪♫
. . . እያለች፣ የሰው ልጅን ክቡርነት አንስታ፥ የተከፈለለትን የሰው ህይወት ዋጋና የተከፈለበትን ምክንያት በውብ ትርክት እያወሳች ስታንቆረቁር ቀሰቀሰችኝ።… ለማንም አላጋጭ ፊት ላለመስጠት በቁጭት የምታስታውስም ይመስላል።
ለነገሩ እኔና ቅዳሜ ቀስቃሽ አናጣም። ብናጣ ብናጣ “ስብሰባ እንዳትቀሩ፣ ምርጫ ካርድ ውሰዱ፣ የኮብል ስቶን አዋጡ፣… ምናምን” ብሎ በቅስቀሳው የሚያበሳጨን ቀበሌ አናጣም። ተሰብስበን እንዲያገኙን ብለው ነው መሰል፥ እንደ ልብ ወዳጅ የእረፍት ቀን ጠብቀው ነው በራችንን የሚቆረቁሩት። የአደረ የኢቲቪ ወሬ አናጣም።…
በአዘቦቱ በመቀስቀሻ ደወል (alarm) ቀድመን የምንነቃባቸው ድምፆች ሁሉ ቅዳሜ ሲሆን ሊቀሰቅሱን ይበረታሉ። የመንደርተኛው ጫጫታ፣ የባለ ምስሩ “አለ ምስር ምስር ምስር….” ድምፅ፣ የዐይነ ስውሩ የኔ ቢጤ
“ዐይኔን ግንባር ያርገው ብላችሁ አትማሉ፣
ይቸግር የለም ወይ መሪን ማባበሉ?!”
…አሳዛኝ ወ ሸንቋጭ እንጉርጉሮ፣ የቀን በሌዎቹ “ቆሻሻ አውጡ” ተማፅኖ፣ (ከቆሻሻው ጋር እንጀራቸውን እያሰቡ) የባለ ሱቁ የለስላሳ ጠርሙስ ለቀማ፣ የቤተስኪያናቱ ደወል…
“ቀን በቀን ተፈጭቶ፣ ቀን በቀን ተቦክቶ፣ ቀዳሚት ስትመጣ፣
የሚሰማ እንጂ፣ ቀስቃሽ መች ቸገረ?፣ ‘ሚጋግር መች ታጣ?!”
/ዮሐንስ ሞላ/
ያልነውም በቅዳሜው ነው። የአዘቦት ቀናቱ ሲገፉልንና የእረፍት ቀናችን ሲመጣ ቀስቃሹ ብዙ ነው። ጋጋሪው፣ አቃጣዩ፣ ጠባሹ ብዙ ነው። ወይ ደግሞ በ“መቼስ ማልጎደኒ” ብሂል ችለን ኖረን… ኖረን… ኖረን… ቅዳሜ ሲደርስ ይሆናል የሚሰሙን?! ይበልጥ የሚቆጠቁጡን?! – ምናልባት?!
— እንደ እኔ ነው!
ድካሜን ይበልጥ የምረዳው ስራዬን ጨርሼ ሳርፍ ነው። የመታፈኔ/ዝም የማለቴ ልክም መናገር ስጀምር ይበልጥ ይታወቀኛል። ከንፈሮቼ እርስ በርስ እየተነካኩ እንደኩበት ሲንኮሻኮሹ ተጠባብቀው ዝም የማለታቸው ነገር ይታያል። ቅዳሜ ቀን …በፈቃዴ… አንፃራዊ ነፃ እሆናለሁ። እናም መታፈኔ ይበልጥ ይሰማኛል። በፍፁም ነፃነት፣ ኩራትና ክብር በመንቃቴ ስሜቴን ካለፉት ቀናት ጋር ሳነፃፅረው የመታፈኔ ልክ ይጎላል።
ብዙ ድምፆች ጆሮዬ ስር ተኮልኩለው መጥተው ይጮሁብኛል። ይቀሰቅሱኛል። የአብዛኞቹ መቀስቀስ ማስጠላት የለውም። ማንቃትና ቀኔን የማራዘም ስራ ነው የሚሰሩት። እንዳሳርፋቸው ነው የሚማፀኑኝ። (ላልችልበት)… እነሆ ዛሬም ነቅቻለሁ። ዛሬ ግን ድል፣ ኩራት፣ ክብር፣ ነው የቀሰቀሱኝ። አደዋችን ከቅዳሜያችን ጋር ገጥበው ድርብ በዓል ሆኖ፤ እያንቆላለጩኝ! ‘ብትነሳ ይሻልሃል። ቀንህን አታባክነው።’ ዓይነት። እንድትማፀን ጂጂ: –
♪♫ እምዬ እናት ዓለም እስኪ አንቂኝ ከእንቅልፌ፣
ቀኔን ሳላሳምር እንዳልቀር ሰንፌ፣
ቤቴን ሳላፀዳው እንዳልቀር ሰንፌ…♪♫
ወይ ጂጂ! በእውቅ የሙዚቃ አዋቂዎች ተቀምሞ ለ50 ሰከንዶች የሚንቆረቆረው መግቢያ የሙዚቃ ቅንብር እዚያው አድዋ ነው ወስዶ ጠብ የሚያደርገኝ። አልጋዬን ሳልለቅቅ ሩቅ ተጉዤ፣ ከድል አምባዬ… ከአድዋዬ… ከመመኪያዬ… ከማስፈራሪያዬ… እደርሳለሁ። ሾፌሩ – ሙዚቃ፣ ከሙዚቃም – የጂጂ ሲሆን ደግሞ ለእኔ መንገዱ ሌላ ነው። አልጋ ባልጋ ሆኖ ታሪክ ዘካሪ ሳይሆን፣ ታሪክ መስካሪ ያደርገኛል።
♪♪ የተሰጠኝ ህይወት ዛሬ በነፃነት፣
ሰው ተከፍሎበታል ከደምና ካአጥንት፣
ስንት ወገን ወደቀ በነፃነት ምድር
ትናገር አድዋ፣ ትናገር ትመስክር፣
ትናገር አድዋ፣ ትናገር አገሬ፤
እንዴት እንደቆምኩኝ ከፊታችሁ ዛሬ፤ ♪♪
…ያየ የነበረ ያህል ነው የምትነግረን። ደግሞ ወዲያው እኛንም ያየ የነበረ የምታስመስለን። ደግሞ የሚጠራጠር ቢኖር ምስክር ትጠራለች። ምስክር ስትጠራ ሰው (ጀግና) አይደለም። ጀግኖቹማ ተሰውተዋል።… አደዋን ነው። አገሯን ነው። ኢትዮጵያን ነው። “እንዴት ፊታችሁ ቆሜ በኩራት እንዳለሁ አድዋ ትንገራችሁ። ጠይቋት እስኪ… አገሬ ትዘክዝክላችሁ።” ትላቸዋለች።
♪♫ በኩራት፣ በክብር፣ በደስታ፣ በፍቅር፣
በድል እኖራለሁ ይኧው በቀን በቀን
ደሞ መከራውን ያን ሁሉ ሰቀቀን። ♪♫
…ስትል ደግሞ መከራና ሰቀቀኑን የተከፈለውን መስዋዕት ሁሉ ታወሳለች። የምታመሰግንም ይመስላል። ‘እኔ በየቀኑ ልኖር እነሱ በየቀኑ ሞቱ’ ዓይነት ጥልቅ ምስጋና። የአድዋ ድል ቀጣይነትንም ታስረግጣለች። የወዳደቁና መነሳት የሚገባቸው ነገሮች እንዳሉም ትጠቁማለች። ታመሰግናለች። እንዲህ ስትል: –
♪♫ አድዋ ዛሬ ናት አድዋ ትናንት፣
መቼ ተነሱና የወዳደቁት፣
ምስጋና ለእነሱ ለአድዋ ጀግኖች፣
ለዛሬ ነፃነት ላበቁኝ ወገኖች፣♪♫
የድሉን ወሰን የለሽነትና ለመላው ጥቁር በረከትነት ደግሞ እንዲህ ቅልብጭ አድርጋ ታስቀምጠዋለች። አፍሪካን በእማማ ኢትዮጵያ መቀነትነት ሸብባ በአንድ ትመቀንተዋለች። አሁን ምስክሯን ስታጠናቅር ሰፋ አድርጋው… አፍሪካንም ትጠራታለች። ‘ምን አሰፈራሽ? ተናገሪ እንጂ።’ እያለች ትወሰውሳታለች። ‘አንቺ ካላወራሽው ማን ያወራዋል? ሰው እኮ ከንቱ ነውና ይረሳዋል።’ መሆኑ ነው። ‘ዛሬ ግን ምን ሆነን ፈዝዘናል?’ የምትልም ይመስላል።
♪♫ የጥቁር ድል አምባ፣ አድዋ
አፍሪካ፣ እምዬ ኢትዮጵያ
ተናገሪ… የድል ታሪክሽን አውሪ። ♪♫
የዛሬ ዓመት “የታሪክ አልጋችን” ብዬ የፃፍኩትን ግጥም ልጎትተውና መልካም ቀን ተመኝቼ ጨዋታዬን ላብቃ።
ከታሪክ አልጋ ላይ፣ በምቾት አርፌ፣
የኋሊት ስጋልብ፣ በሀሳብ ተንሳፍፌ፣
በምኞት ቃዥቼ፣ በተስፋ አንኳርፌ፣
ሰርክ ስንጠራራ፣ ደክሜ፣ ሰንፌ፣
አለሁ — እንደተኛሁ…
…ገፅ ልገነባ፣ ገፅ እያበላሸሁ፤
ፍቀድ አባታ’ለም !
__ቀስቅሰኝ ከንቅልፌ፣ ገፅታዬን ገንባ፣
ወኔህን አስቀዳኝ !
__በደምህ ታጥቤ፣ ድል አ’ርጌ ልግባ።
/ዮሐንስ ሞላ/
ሙዚቃው ይቀጥላል…
…የአድዋ ድል ስሜትም!!
♪♫ የሰው ልጅ ክቡር
ሰው መሆንኧ ክቡር
ሰው ሞቷል – ሰው ሊያድን፣
— ሰውን ሲያከብር
በደግነት፣ በፍቅር፣ በክብር ተጠርቶ፣
በክብር ይሄዳል፥ ሰው ሊኖር — ሰው ሞቶ፤ ♪♫
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!
ማስታወሻ:
አንጋፋውና ውዱ ጋዜጠኛና ደራሲ ማሞ ውድነህ የዛሬ ዓመት በዚህ ቀን ነበር ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት። የካቲትና የአገር ባለውለታዎች ሞት ግን ምንድን ነው የሚያገናኛቸው? 😦
ነፍስ ይማር!!