የእኔ አለማመን የእርሱን ኢ-ማመን (አለማመን) ልክነት ለማረጋገጥ አይረዳውምና፥ ማንም እምነቴን በመደማመጥና በመግባባት ባልሆነ… በከንቱ ንግግር ሊፈትን፣ እንዲሁም በርካሽ ዘለፋ ሊያንቋሽሽ ቢደክም፥ አምናለሁና — እርሱ ለእኔ ከጠላት ወገን ነው። በማምነው ስለሚቀና፣ ወይ ደግሞ እኔ ካለኝ እምነት ዘንድ የቀረ ልብ ስላለውም የሚንጨረጨር ይመስለኛል፤… እንዲያ ከሆነም በመንጨርጨሩ ልክ የእምነቴን የማንጨርጨር ጉልበት አብረን እንረዳዋለንና ያስቀኛል።
ቢችልስ (ቢያውቅስ) የማያውቀውን (ቀድሞ የጣለውን) የእኔን እምነት ከማንቋሸሽና ከማጣጣል ይልቅ፣ የራሱን ኢ-አማኒነት ጥንካሬና ያሉትን እሴቶች በራሳቸው በማቆምያስደምመኝ ነበር። ሆኖም ግን ከርሱ ውጭ ላሉ ሰዎች ስሜትና የልብ መሻት ስለማክበርም ባይጨነቅ፥ ለሰው ልጆች ቅንጣት ታህል ርህራሄ እንደሌለው ነው የሚሰማኝ። አለማድመጥና ‘እኔን ብቻ ስሙኝ’ ባይነትስ ልጅነት (ካልሆነ ጅልነት)፤ ወይ ደግሞ የአሳዳጊዎች በደል ነውና በጊዜ ይገራ ይሆናል።
ደርሶ በነፃነት ወይም በስልጣኔ ስም ዘሎ መሳደብና መዘርጠጥ ግን ከዚያ በላቀ፣ የደም ውርስ ባህርይ ነውና ራስን ለማሸነፍ ከመወሰን ፈቃድ ውጭ ምንም አረዳውም። ማንም እንዲያ ሲያደርግም ለፍጥረታት ሁሉ በፀናች ምድር ላይ ከራሱ ጋር ብቻ መንጎማለል እንደሚፈልግ ነው የሚታየኝ።
በ‘አዛኝ ቅቤ አንጓች’ አቀራረብም ሆነ፥ ራስን አላግባብ በመካብ ትምክህት፥ እምነቴን ለመሸርሸር …(ላይችል በከንቱ)… በሚያደርገው ትግል ወቅት፥ ሰብአዊ መብቴን የመጋፋት አምባገነንነቱ፣ ምርጫና ነፃነቴን የማፈን ጭቆናው፣ ክብሬን የመንካት ድፍረቱና፣ ተስፋዬን የመንጠቅ ጉጉቱ ብላሽ የሆኑበት ጊዜ፥ በራሱ ፊት ክብሩን ያስገፍፋልና ያኔ እርሱን ነው አለማየት።
“ንዳል…
ነኝ እንዳልል፣
የት ቆሜ መሆኔን አየሁ” ~ ሰለሞን ደሬሳ (ዘበትልፊቱ)
P.S. ስለእምነት እንጂ ስለሀይማኖት አላወራሁም።