የፆም ወቅት

የያዝነው ሳምንት ለኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ጫፍ ጫፉን ካርኒቫል ነበር። የካርኒቫል አመጣጥ (etymology) ካርን (carne)ና ቫሌ (vale) ከሚሉ የላቲን ቃላት ነው። ካርን ማለት ስጋ (flesh/meat) ማለት ሲሆን፤ (“ስጋ በሊታ” ለማለት “carnivorous” እንደምንል…) ቫሌ ማለት ደግሞ ‘ቻዎ ቻዎ’ (farewell) ማለት ነው። [ይለናል የኖርማን ሌዊስ Word Power Made Easy መፅሀፍ]

ስለሆነም ‘ካርኒቫል’ ስንል “ስጋ ሆይ ቻዎ ቻዎ” እንላለን። እንደ ደምበኛ ካርኒቫል በየጎዳናው ባንቀውጠውም በየቤቱና በየሆቴሉ በስጋ እንቀውጠዋለን። …’ስጋ ሆይ ቻዎ ቻዎ!!’ እያልን። ከሰኞ ጀምሮ ለክርስቲያኖች የፆም ወቅት በመሆኑ፥ ይህ ሳምንት ባይሰየምም ለብዙዎች ካርኒቫል ነው። – ለሚፆሙትም ለማይፆሙትም! …መቼም ልብ ካልነው በየቦታው የምንታዘበው ነገር ለጉድ ነው።

ዛሬም ካርኒቫሉ ቀጥሏል። ሆቴሎች ተጨናንቀዋል። ጥብስ… ቁርጥ… ቅቅል… ሌላም ሌላም የስጋ ዘሮች… እንደጉድ ይበላሉ። ያም ሆነ ይህ ግን በየትኛውም ጊዜ ጥብስ መብላት ባይችሉ ካልሲን ጥብስ ጥብስ ማሰኘት ይችላሉ/ይገደዳሉ። (ማጠቢያ ውሀ ከሌለ ቀላል ነው)…ቁርጥ መቁረጥ ካልቻሉ ተስፋ መቁረጥ ቀላል ነው። (ለዚያውም በብዙ አማራጭ ታጥረው)…ቅቅል መብላት ካልቻሉ በነገሮችና በአየር ንብረት ለውጡ ይቀቀላሉ። (ሳይወዱ በግድ) ሌላም…ሌላም… ያው ምርጫ ነው። ግዴታ ነው።

እላዩ ላይ ደግሞ ቢራ፣ ውስኪ፣ ቮድካ፣ ጠጅ፣ አረቄ…. ሌላም ሌላም…

ቻው ቻው ስጋ!!

እግረመንገዳችንን ግን ቢያንስ ለፆሙ (እረፍትም ይሆነናልና) “ቻው ቻው” ልንላቸው የሚገቡን ብዙ ነገሮች አሉን። ችሎ ማሰናበቱ ቢቀር እንኳን ለመርሳት መለማመዱ መልካም ነው። እናም እንፆማለን ስንል ከብዙ ነገሮች እንፁም። ከብዙ ነገሮች እንታቀብ።

ለማህበራዊ ኑሮም ሆነ ለግል ስብዕና ጠንቅ የሆኑ ባህርይዎቻችንን እንሽሽ። ከግል እምነታችን (ሀይማኖት) የተነሳ ወቅቱ የፆም ወቅት ያልሆነልንም ብንሆን ካሉብን መጥፎ ባህርያት በመፆም ረገድ ፆሙን እንቀላቀለው። ያው ስጋን መሰናበቱን በጋራ አድርገነው የለ?! — የግል ሀሳቤ ነው!

ለምትፆሙ – መልካም የፆም ወቅት!… ለምትኖሩ – መልካም ኑሮ!… ለምታኗኑሩና ለምታጅቡ – መልካም ማኗኗር!… ከታች ኑሮ እንደበረዶ ቀዝቅዞባችሁ፣ ከላይ ሙቀቱ አንገብግቧችሁ፤ በህይወት ድርቀትና በኑሮ ግለት ውስጥ ለምትኳትኑ የኔ ቢጤዎች – መልካም mixed – ቆላና ደጋ! እንዲሁም ምኑም ለማይሞቅ ለማይበርዳችሁ – መልካም ወይናደጋ!! ሃሃሃ…

ትፆማለህ?” ሲሉህ፤
ኑሮን እንደኖረ፥…
“ኑሮ ራሱ ፆም ነው።”
ብለህ ስትመልስ…
ግን አታፍርም?!

/ዮሐንስ ሞላ/

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s