ዙረታም ነች! — የለየላት…!! ኡመቴ ዙረታም!
[‘ኡመቴ ምንድን ነው?’ አሃ… በቃ የድሮ የመንደራችን ቃል ነበር። እንደ’ሷ ያለ የሚጠራበት ቃል።]
ሰው ኡምት ሲል፣ መላ ቅጡን ሲያጥ ‘ኡመቴ ነው’ ይባላል።…እናም ‘ኡመቴ ናት!’…
አገር ምድሩን ስትዞር ነው የምትውለው…
ልክ መሬት እንደምትዞር፣ አታርፍም!
ዝም ብላ ስትዞር… ዝም ብላ!
…… እያወራች ስትዞር… — ሰሚ ፍለጋ!
…… እያላወራች ስትዞር….– ወሬ ፍለጋ!
…… እየበላች ስትዞር… — ‘እንብላ’ ምትለው ፍለጋ!
…… እየራባት ስትዞር….– ምግብ ፍለጋ!
…… ሲበሉ ስታይ ስትዞር…–ቅልውጥና!
ስታሳዝን!
ደግነቱ እንደ’ሷ መዞር አይደለም፤….ከተማው አዙሪት የለውም።
— ሲራዳት! ሲረዳት! ሲያረዳት! ሲያርዳት! ለርሷ ቤቷ መመለስ መርዶዋ ነው…
… ዞራ ቤቷ ትመለሳለች። ሲቀናት! ሲያቃናት! አሃ… ማለት የሚያቃናት ስታገኝ! የሚያቀናናት! — ከኑሮዋ! ከራሷ! ከጎረቤቷ!…
ግን ሁሉም ነው የሚቀናባት…
ታድላ!
ሴቶቹ — ‘የባቷ ውበት ከመዞር የመጣ ነው።’ ብለው ይቀናሉ።
— ቀንተውም ይዞራሉ። – ተደብቀው! እንደሷ ለመሆን! አልሆነላቸውም እንጂ ቢሆን በባታቸው መታወቁ ላይቀር….
ወንዶቹ — በርሷ አይደለም! ስትዞር በሚለክፏት ወንዶች ይቀናሉ።
— ቀንተውም አይቀሩ! ያለፈች ያገደመችውን ይላከፋሉ! እንደውሻ… ያንንም… ይሄንንም… — ልክፍ፣ ልክፍ! ቀን ጥሏቸው ‘ክፍ’ እስኪባሉ ድረስ መላከፍ…
ፀጉራቸውን ለውጣው፣ እንደ ጭን ገረድ አብረዋት ቢዞሩ ደስ ባላቸው….
ግን ኦሆ…
— ማን ያስጠጋል? ማን ይጠጋል?
ሰዉን እንጀራ ነው የሚያዞረው። አመል አይደለም። የርሷንም ‘አመል ነው’ ይሉታል እንጂ አይደለም። — ታውቃለች! ይገምታሉ! – እንጀራ ነው….
— አዳሜን እንጀራ በቆመበት ጭውውውው…. አርጎ ይመልሰዋል።
— ሄዋኔንም! እንጀራ ያዞራታል… እንጀራ ያዞራቸዋል…
ታዲያ ለምን ይቀኑባታል?
ሴት ስለሆነች? ወንድ ስለሆኑ? እና ምን ይጠበስ?
ሁሉም ዘዋሪ ነው። ሂያጅ።
— ‘ ♫ አዙረኝ አታዙረኝ’ እያለ ሲዞር የሚውል።
ሲንቀዠቀዠ…. ሲቅበዘበዝ….የሚውል! — እንደ ባጃጅ!
ያው ባጃጅ ነው!
… ባዶውን ወጥቶ፣ ሰው ጭኖ ይመለሳል።
… ሰው ጭኖ ወጥቶ፣ ባዶውን ይመለሳል።
እሷም!
ዙረት…
ባጃጅ ግን ሰው ከመጫን ከማራገፍ ሌላም ጥቅም አለው። ሲዟዟር ለድድ አስጪዎች ገቢ ያመጣል። የገቢ ምንጫቸው ነው። በቃ እንትን ይጫወታሉ! — ሞላ… ጎደለ…
ቁማር!
እርሷም ትጫወታለች! የርሷ ቁማር ግን ከመንገዱ ጋር ነው… ከቀናት ደግሞ ካሳራፊዋ ጋር፤ ካሳፋሪዋ (ላልቶ)፤ ካሳፋሪዋ (ጠብቆ)… ዞራ ዞራ ሲደክማት! ዞራ ዞራ ስታገኘው!…
እስከዚያው ግን፥ ዝም ብሎ መዞር፣
መዟዟር፥
የሰው ናላ ማዞር፣
‘♫ mአዙረኝ አታዙረኝ….
… አሽከርክረህ፣ ከሱ ጣለኝ! ♬’
የዙረት ዜማ…!
ማይክ ይዞ ማዜም!
ካለማይቅ ማዜም!
ዜማ!
ዜማ… ዝሙት… ዘማዊ… ዘመናዊ…
… ‘♫ አዙረኝ አታዙረኝ….
… አሽከርክረህ፣ ከሱ ጣለኝ! ♬’
ግን እሱ ማን ነው?….አሃ! ማንም ነው። ማንም!
ለርሷ ሰው እኩል ነው። ዟሪ ማሳረፍ የሚችል መደብ ካለው ሰው እኩል ነው። ማለት ሲደክማት ደረቱን ተደግፋ ካረፈችበት ወንድ እኩል ነው።
እስክታርፍ ድረስ ካሳረፋት! አስክትደርስ ድረስ ካሳፈራት!
እኩልነት!
እርሷና እርሱ ግን ይበላለጣሉ….
— በመዞር ትበልጠዋለች!
— በማሳረፍ ይበልጣታል!
— በማሳፈር ትበልጠዋለች!
—- በመሳፈር ይበልጣታል!
አይ አይ… ያው ናቸው። — አይበላለጡም! — እኩል ናቸው!
— መዞሯን ፈልጋው ነው!
— መፈለጓ ቢፈልገው ነው!
— ማሳረፉ ብታርፍለት ነው!
— ማረፏ ቢያሳርፋት ነው!
— መሰፋፈራቸውም ቢሰፋፈሩ ነው!
እና?!
የመጀመሪያ ልጇን ስትዞር አርግዛው፣ ስትዞር ነበር የወለደችው…
…ከዚያ ግን ስትዞር ሞተባት። ‘ኧረ ሞት ያንሰዋል እሷ እየዞረች ማን ያጥባው?’ – ብለው ያሟት ነበር። – በሰፈሯ፤
ግን አይደለም!
የመጀመሪያ ልጇን ስትዞር አስረግዟት፣ ሲያዟዙር ነበር ያስወለዳት….
… ከዚያ ገደለባት። ‘እሱ እያዞረ ጡቷን እየተሻማት ልጁን ማን ያጥባው?’ – ብለው ያሙት ነበር። – በሰፈሩ፤
ሀሜተኞች!
ግን አሁንም እየዞረች ነው። ደግሞ ነፍሰ ጡር ነች።
እየዞረች አርግዛለች…
እየዞሩ…
ግን ንጉስ ይሁን ቄስ ማን ያውቃል? – ያቺ የቁርጥ ቀን መጥታ ትለይላታለች እንጂ። እስከዚያው ግን ትዞራለች… ይዞራሉ… — ‘አዙረኝ፣ አታዙረኝ’
— ሰው ስትጭን፣ ሰው ስታራግፍ!
— ወላጅ ስታድን፣ አዋላጅ ስታስስ!
— ሰው ሲጫናት፣ ሰው ሲራገፋት!
— ወላጅ ስታገኝ፣ ወላጅ ስትሸኝ!
— ስታሳፍር፣ ስታፍር!
ለምዳዋለች!
ጭው ብሎባት…. ጭው የምታደርግበትን ትፈልጋለች….
እጅና እጅ ተቆላልፈው….
‘♫ ♬አዙረኝ አታዙረኝ፣
አሽከርክረህ ከዚያ ጣለኝ!♫ ’
ከመደቡ… ከማስወለጃው… ከመውለጃው…. አሃ! እርጉዝ ናት! – ሁለት ነፍስ!
— ማርያም ትቅረባት! እስከዚያው ግን…
♫ ♬አያዙራት አያዙራት፣
ከመደቡ ያሳርፋት! ♫ ♬
/ዮሐንስ ሞላ/