‹‹ምከረኝ… ምከረኝ… ምከረኛ!!…››

እድሜአችን ከፍ ካለ ጊዜ አንስቶ አዘውትሮ ‹‹ምከረኝ›› የሚል አብሮ አደግ ጓደኛ ነበረኝ፡፡ ‹‹ምከረኝ›› የሚለው እኔን ብቻ አይደለም፡፡ …ማንንም ያገኘውንና ‹ከእኔ ይሻላል› ብሎ ያሰበውን ሁሉ ‹‹እኔ እኮ አልረባም፤ እንዲህ ሆንኩ… እንዲያ… እስኪ ምከረኝ፡፡›› ምናምን ብሎ ዐይኖቹን በክብር እያቁለጨለጨ ይማፀናል፡፡ መቼስ ትናንት አፈር ያቧነኑት፣ ጭቃ የቧኩት አብሮ አደግ አፍ አውጥቶ ‹‹ምከረኝ›› ብሎ ምን አንዠት ዝም ያስብልና?! — ለአቅመ-ምክር በቃም አልበቃም ‹ይሆናል› ያሉትን የቆጥ የባጥ አውርተው ይሸኙታል እንጂ፡፡

ታዲያ ነገም ሲያገኝዎት ‹ምከረኝ› ከነገ ወዲያም ‹ምከረኝ› ከሆነ ያሰለቻል፡፡…በተከታታይና በሁሉም ነገር ላይ ‹ምከረኝ› መባልዎ፣ የትናንቱ (ምክር ያሉት) ‹ድንጋይ ላይ ውሀ እንደማፍሰስ› ድካም ብቻ እንደሆነ ይሰማዎትና ይደብርዎታል፡፡ ካመረሩ የሆነ ሙድ እየተያዘብዎት እንደሆነ ሊሰማዎትም ይችላል፡፡ ነገሩ ስር እየሰደደ ሲሄድ ደግሞ….የቀድሞው ወዳጅነት ጨክነው ምክር ፈላጊውን ይንቁት ዘንድ ባያስችልዎም፣ ይርቁት ዘንድ ግን ይገደዳሉ፡፡

አብሮ አደጌ እንዲህ ነበር፡፡ — ዛሬም ‹ምከረኝ› ነገም ‹ምከረኝ›… ከነገ ወዲያም ‹ምከረኝ›…. ከነገ ወዲያ ወዲያም ‹ምከረኝ›…. (ግን አልራቅሁም፡፡ አልናቅኩትምም፡፡…. እንዲያው እንጀራ አራራቀን እነጂ፡፡) ይህን ያስታወሰኝ ትናንት ምሳ ሰዓት ላይ ቢሮ አካባቢ የገጠመኝ ነገር ነው፡፡…

አብረን የምንሰራ (ከእኔ ጋር ተመሳሳይ የስራ ማዕረግ ያለው) ሰው ነው፡፡… እድሜው ከእኔ ብዙም አይርቅም፡፡… ቄንጡን በጥሶ ለመዘነጥ ይታገላል፡፡ (ወይ ጀማሪ ነው፡፡ ወይ ደግሞ የማየደክም ጉልበት አለው፡፡)… ከእኔ ጋር ጥሩ ሰላምታ ለመሰጣጠት የሚበቃ ቅርርብ አለን፡፡…. ልክ ምሳዬን በልቼ ስጨርስ መጥቶ እኔ ያለሁበት ጠረጴዛ ላይ ተቀመጠ፤….

በእኔ ቤት ወሬ ማሳመሬ….፤ ‹‹ኬፍ!….ስትቦጭቀኝ ነበር እንዴ…ስጨርስ መጣህ….›› አልኩት፤

እሱ፡ ‹‹ኸረ….እኔ የምለው፣ ወጣቱ ሁሉ ቦጫቂ ነው እንዴ፤ አልቻልኳቸውም!…. ኪሴ ፍራንክ ኖሮኝ ደግሞ ጠይቀውኝ እምቢ ማለት አይሆንልኝም፡፡ አላስወጣ አላስገባ አሉኝ፡፡ አቦ ይደብራላ፡፡ ሰፈር ልቀይር ይሆን….. እስኪ በናትህ ምከረኝ፡፡››

እኔ፡ (ነገሩን ከምኔው ሀሜት/ወደ ልመና ማዞሩ እየገረመኝ) ‹‹….ለምን ዝም ብለህ ትፈለጣለህ ታዲያ፡፡ ካንተ የሚለምነው እኮ ካንተ የተለየ ፍላጎትና አኗኗር የለውም፡፡ ልዩነቱ የሱን ፍላጎት አንተ ማሟላትህ ነው፡፡ በዚያ ላይ አጉል አስለምደህ እነርሱንም ማስነፍ ነው፡፡ የምትፈለጥለት ስታጣ ሊፈልጥህም ይችላል…..›› (ትልቅ ትልቅ ሆኜ ሳከብድ….ሃሃሃ)….

እሱ፡ አዲስ ነገር እንደተገለጠለት ሰው ጭንቅላቱን ላይ ታች እየነቀነቀ አየር ወደውስጥ ስቦ (እንዴት ተገለጠልህ በሚል ግርምት)….. ‹‹እውነትህን ነው፤…. ብሩ ለራስም አይበቃም፡፡ ታውቃለህ…. ወሯ ሳታልቅ ብድር ነኝ…. ባንክ የለ ምን የለ፤ ኸረ እስኪ ምከረኝ በናትህ…. ብር እንዲበቃኝ ምን ላድርግ አንተ ቸገረኝ አትልም፡፡ እንደው ምን እያደረግክ ነው፡፡ ምከረኝ እስኪ….››

እኔ፡ (ሊመጣ ብቅ ያለውን ሳቄን እንደምንም ኮረኩሜ መለስኩትና….) ‹‹ሁሉም ጋር እኮ ያው ነው! መቼስ…፤ ካንተ ጋር ስለማንበዳደር ነው እንጂ እኔም በብድር ነው ወሩን የምገፋው››….

እሱ፡ (አሁን ብቻውን አለመሆኑ ደስ ብሎት ነው መሰል ዘና ብሎ ተስተካክሎ….) ‹‹ሚስት እንኳን ሳናገባ አረጀን እኮ፤ አሁን ላግባ ብትልስ፣ ምን ታረጋታለህ….››

እኔ፡ ከአፉ ቀልቤ….. ‹‹ያው ያገቡት ሚስቶቻቸውን የሚያደርጉትን ነዋ››

እርሱ፡ ….‹‹ማለት ምን ታበላታለህ ማለቴ ነው ኸረ….›› ብሎ አብራራ፡፡
(አትጨቅጭቀኝ አልለው ነገር የልብ ወዳጄ አይደለ…. ግን አንዴ ገብቼበታለሁና ምን አደርጋለሁ፤ ልምከር እንጂ…. )

እኔ፡ ‹‹….ለማግባት ልብህን ክፈት፤ እድልህ ከሆነ የምታበላዋንም ይሰጥህ ይሆናል…››

እርሱ… ‹‹እንደሱማ አሪፍ ነበር፡፡ ግን ጠበስክ እንዴ…. አንተ ግን አታገባም….››

እኔ፡ (አሁን አገኘሁት ብዬ ደስ እያለኝ….) ‹‹ምን ባክህ…. እስኪ እንዴት ልጥበስ ምከረኝ›› ›

እርሱ፡ ወሬዬን አስቀይሶ….. ‹‹የምር አሪፏን ባገኝ አገባ ነበር፡፡ ብንፈልግ በረሀብ እንሙትና ታሪካችን ይመር እንጂ…. ደግሞ ከእንደዛ ዓይነቷ ጋር ሆነህ ብትሞትስ ምን ጣጣ አለው፤ በናትህ እስኪ ምከረኝ…. ምን ላርግ እንድጠብስ…››
(ጥያቄውን በጥያቄ ይሏል እንዲህ ነው፡፡) ተናደድኩኝ፡፡

እኔ፡ (የምክር አገልግሎት መስጫ ቢሮ የከፈትኩ ያህል ከስራ ቆጥሬው….) ‹‹ዐይኖችህን ከፍተህ ፈልግ…. የመሰለችህን ቅረብ…. የተግባባሀትን አግባ…. ከዚያ እየተመካከራችሁ ኑሮ እንዳረጋችሁ መሆን ነው፡፡ ባይሞላልህ መከራ ይመክርሀል፡፡›› …..ብዬው፤ አያያዙ ካልፈቱት የማይፈታ ስለሆን…..በእርሱ የ‹ምከረኝ› ጋጋታ ምክንያት ትዝ ያለኝ አብሮ አደጌ ጋር ደወልኩኝ፡፡

ስልኩ ጠራ… ♫♫

‹‹ሃሎ….ሃሎ…. እንዴት ነህ ሰላም ነው….ተጠፋፋን አይደል….›› ምናምን ተባብለን….. ወዲያው….

አብሮ አደጌ፡ ‹‹ኸረ ምን ባክህ …እንዲህ ሆን፣ እንዲያ….እስኪ በናትህ እንገናኝና ምከረኝ፡፡›› ሲለኝ ስልኩን ሳልዘጋው ሳቅሁኝ፤ እርሱም ነገሩ ሳይገባው አብሮኝ ሳቀ…. (ስቄ ስጨርስ እንደማብራራለት እርግጠኛ ሆኖ….ቅድመ ሳቅ መሆኑ ነው….) የሆነ ቀልድ ነግሬው ተሳሳቅን፡፡

ስልኩ ተዘጋ!

ወዲያው እናቴ አዘውትራ የምትለው ነገር ትዝ አለኝ፡፡ እንዲህ ነበር….

‹‹ብልህን ልምከረው – ምን ይስታል ብዬ
ሞኝን ልምክርው – ምን ይሰማል ብዬ…››

የእናቴን አባባል ይዤ…. የፍልስፍና አድማሴን አስፍቼ አብሮ አደጌንና የቢሮዬን ልጅ በሞኝና በብልህ ለደለድላቸው ማብሰልሰል ስጀምር፣ ‹‹ምከረኝ›› የምለው ሰው ማሰብ ጀመርኩኝ! ሃሃሃ….

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s