የብርሃን ልክፍት በቅርብ ቀን…

540095_359925470795159_1890655638_n

ለተሰጠው ሰው፥ የእርግዝናን ጊዜ በሰላም አልፎ ልጅ መውለድ ቀላል ነው። ማሳደግና፥ (በውጭም በውስጥም) አሳምሮ ከማህበረሰብ መደባለቁ ግን የበለጠ ያደክማል።….. በዚሁ መስመር ሄጄ፥ እንደራሴ ልምድና መረዳት ሳስበውም፥ የፃፉትን አሳምሮ፣ ደረጃውን እንዲጠብቅ ተጨንቆና ስለአርትኦቱ፥ በዘርፉ ካሉ 522056_359599874161052_1690501995_nባለሞያዎች ጋር ተማክሮ፥ ለንባብ ማሰናዳቱ…. በተለይ ከመጻፍ ጋር ሲነፃፀር የበለጠ ያደክማል።
እውነት ነው! ፅሁፎቹን ስፅፍ ከነበረኝ ይልቅ… መመጠን አለመመጠናቸውን ለመረዳት ስመረምር፣ ከወዳጆች ጋር ስማከርና፣ በመጽሐፍ እንዲሆኑ ሳዘጋጅ ብዙ ደክሜያለሁ፤…. ስፅፋቸው ከፈጀሁት ጊዜ በላይ፥ ስለ መጽሐፍሳስብና ለመጽሐፍ ሳሰናዳቸው ፈጅቼያለሁ። “ምነው ማሳተም ባልኖረ!” ያልኩበት ጊዜማ ብዛቱ!አሳትሞ ማጋራቱን ሽሽት “ኧረ ምነው መፃፍ ባልወደድኩ ኖሮ!” አለማለቴም አንድ ነገር ነው።…ቢሆንም ግን፥ ዘርፉንና አንባቢን ከማክበር የመጣ ነውና ሲጀመር እንዳልነበረው ሲታለፍ ደስ ይላል፡፡

የሆነው ሆኖ ግን…. በወዳጆች ግፊትና፣ ሥራዎቼ ‘ለዘርፉ አስተዋፅኦ ቢያደርጉ’ በሚል የራስ ፍላጎት፣ የተነሳ ይህን መፃፍ ለማዘጋጀት ከወሰንኩኝ (ከራሴ ጋር ከተስማማሁ) ከአንድ ዓመት በላይ ሆኖኝ ነበር።… ከዚያም፥ አንዱን ሳነሳ ስጥል፣ አንዱን ስሰርዝ ስደልዝ፣ ‘እንዲህ ይሁን እንዲያ’ ስል ዛሬ ላይ ደርሼ “በቅርብ ቀን” በማለት የሽፋን ምስሉን (cover) ቀብድ ለማስያዝ በቅቻለሁ።:-) በእውነት ትልቅ እፎይታ ነው። የበለጠው እፎይታ ደግሞ መጽሃፉ ሲመረቅ ልንገናኝ ከፊት እንደሚቆየኝ ይሰማኛል፡፡

እውነቱን ለመናገር፥ መጽሐፉን ለማሳተም ወስኜ ዝግጅቱን ስጀምረው…. 305819_636911149659711_790201671_n“ከእኔ ይውጣልኝና ልገላገል”፣ “ወዳጆቼን ላስደስትና ጥያቄያቸውን በትህትና ልመልስ” “መጽሐፍ ቢኖረኝስ?”… ምናምን ከሚል ተራ ስሜትና ሞቅታ ሳይሆን፣ ለስነጽሁፍ ዘርፍ ሊሰጠው የሚገባውን ክብርና ፍቅር ለመረዳት በመጣር ነበር። በዚያም መሰረት “ይመጥናሉ” ያልኳቸውን ሰብስቤ “ይሆናል” ባልኩት አቀራረብ “የብርሃን ልክፍት”ን አዘጋጅቻለሁ። በዚህ ላይ የሚኖሩትን አስተያየቶች በመጠቀምና፣ በንባብ በመታገዝ ወደፊት (እድሜ ከሰጠን) የተሻልኩ እንደምሆን ግን አውቃለሁ፡፡

…. ከህብረተሰብ ጋር ከማቀራረብ ባለፈ፥ ለብዙ የታፈኑ ድምጾች ልሳን በመሆን ያገለግላልና ኢነተርኔት መጠቀም ደስ ይላል። ብዙ ጊዜ ይፍጅ እንጂ፥ ፌስቡክን ቀርቦ አውቆ፥ ኗሪዎቹን ማስተዋልና እርስበርስ ተቀራርቦ በነፃ መማማር ደግሞ ይበልጥ ደስ ይላል። — ያው ከነድክመትና ጉዳቱ ጋር ማለት ነው። በጊዜ እየተሻሻሉና በአጠቃቀም ረገድ እየጎለመሱ ሲመጡ ደግሞ፥ ድካሙም ጉዳቱም አብሮ ይቀንሳል።

በጽሁፍና በመጽሐፍ ዝግጅት መንገዴ ላይ፣ በአንድም በሌላም መልኩ አስተዋፅኦ አድርጋችኋልና፣ በክፋታችሁም በደግነታችሁም አብራችሁኝ (ዙሪያዬ) ለነበራችሁ በሙሉ ምስጋናዬ ከልብ ነው። እንኳን አወቅኋችሁ! ….እንግዲህ “ይሁን” ስትሉ የ”በቀርብ ቀን“ ወሬውን በዙሪያችሁ ሁሉ አዳርሱት።

Spread the news…. Share!!

የእኛ ሰው በጎዳና…

ጊዜው እንዴት ይሮጣል?…የዛሬ ዓመት ልክ በዚህ ሰዓት በመጠነኛ አደጋ የተነሳ ሆስፒታል ነበርኩኝ። እንዲህ ነበር….
 
በእለቱ The Good Ethiopian (ደጉ ኢትዮጵያዊ) የተባለ ቡድን ህይወቷን በአሳዛኝ ሁኔታ በቤይሩት ላጣችው ወ/ሮ ዓለም ደቻሳ ልጆች የሚሆን ገቢ ማሰባሰቢያ የስነፅሁፍና የሙዚቃ ፕሮግራም የሚካሄድበት ነበር። ፕሮግራሙ የታሰበውና የተዘጋጀው እዚሁ በፌስቡክ በምንተዋወቅ አስር የምንጠጋ ሰዎች ነበር።… በመጀመሪያ የዓለምን ሞት ተከትሎ (በቤሩት የኢትዮጵያ ቆንፅላ ፅ/ቤቱ በር ላይ ተጎትታ በመኪና መወሰዷን በማሰብ)የነበረው ሀዘንና ቁጭት ብዙ ሰው ዘንድ ነበር። ብዙ ተባለ። ብዙ ተገጠመ። ብዙ ስድ ፅሁፍ ተከተበ። ሁሉም ኡኡ አለ….
 
እርሱም ሳይበቃ Good Ethiopian (ደጉ ኢትዮጵያዊ)የተባለው ቡድን “ሁልጊዜ ከምናዝን የበኩላችንን እናድርግ” በሚል ዋና ዓላማ እዚሁ ፌስቡክ ላይ ተቋቋመ። የፌስቡክ ቡድኑ መስራቾች፥ በተመሳሳይ ጉዳዮች በመግባባት እናወራለን ብለው ያሰቧቸውን ሰዎች መጀመሪያ በinbox መልዕክት፣… ከዚያም በስልክ፣…ከዚያም በሌላ ስልክ… ስለጉዳዩ በዝርዝር አጫውተው/ጀንጅነው…. የሆነ ቅዳሜ ላይ በአካል ተገናኝተን ቡና እንድንጠጣ ሆነ።
 
የተወሰንነው (እኔን የወሰወሰኝን ጨምሮ) ከዚያ በፊትም እየተገናኘን ቡና በመጠጣት የተለያዩ ሀሳቦች ላይ እንወያይ ስለነበረ፣ በበኩሌ የቡና ቀጠሮው እንደተለመደው ለወዳጅነት መስሎኝ ነበረ። እንደተገናኘን ግን (ቀድሞ አጀንዳ ተይዞ ኖሮ) እዚያው ቡና ላይ አንዱ ሲነሳ አንዱ ሲጣል ተቆይቶ…. “ለምን የግሩፑን ሥራ…. በአጭር ጊዜ ውስጥ ለዓለም ደቻሳ ገቢ በማሰባሰብ ስራችንን አንጀምርም?” ምናምን የሚል ሀሳብ ቀረበ…
 
‘ይሁን! አይሁን!’ በሚል ትንሽ ተሟገትን። እኔ ጊዜውንም ከግምት በማስገባት፣ እርስበርስም በጥልቀት ስለማንተዋወቅም ጭምር… መግባባትና እርስበርስ ያለንን ጉልበትና ነገሮችን የመሸከም አቅም ቀድሞ መተዋወቅ ይሻላል በሚል፥ እንደዚያ ያለ የአጭር ጊዜ ፕሮግራም መታሰቡን አጥብቀው ከሚቃወሙ ሰዎች አንዱ ነበርኩኝ። ለብዙዎች ግን ሁሉም ነገር ቀላል ይመስል ነበር። በብዙኀን አባላት ዘንድ ከፍተኛ ጉጉትና የመለወጥ ስሜት (ambition) ነበር, thought I couldn’t be so. Honestly, what I can’t be at all is, ambitious!!!
 
የበለጠው ስሜት መራንና እንቅስቃሴዎችን ለመጀመር ንዑስ ኮሚቴዎችን አዋቅረን ስራ ተከፋፍለን ተለያየን። አንተ ይህን አድርግ! አንቺ ይህን…. ተብሎ ሲደለደል እኔም በእለቱ ፕሮግራሙ ላይ የሚቀርቡ ስራዎችን በተመለከተ የቤት ስራ ወሰድኩኝ። ከዚያም ገጣሚዎችን፣ መድረክ መሪ፣ የሙዚቃ ባለሞያ…. የማናገርና ለፕሮግራሙ የማግባባት ስራው በዋናነት የእኔ ሀላፊነት ነበር።
 
በግሌ እንቅስቃሴዬ ጥሩ ሆኖ ቀርቤ ከጠየቅኋቸው ሰዎች በቀፋፊ መልስ ከመለሰኝ (ያሳፈረኝ መስሎት ካፈርሁበት) አንድ ግለሰብ በቀር ሁሉም ከአንድ አንድ ነገሩን ተስማምተውበት ነበር። እንደዚያ ሆኖ…. ስንጨቃጨቅ፣ ስንነታረክ፣ ስንስማማ፣ እንዲህ ይሁን፥ እንዲያ ስንል… ታልፎ የፕሮግራሙ ቀን ደረሰ።
 
ያን ቀን ከእንቅልፌ ማልጄ ነበር የተነሳሁት። ለፕሮግራሙ መሳካት መፈፀም የነበሩብኝ ብዙ ስራዎች ነበሩ። የጽሁፍ ስራ የሚያቀርቡት ገጣሚዎች ጋር መደወልና ማስታወስ፣ የተወሰኑት ጋርም በአካል መገናኘት፣ ባንክ መሄድና ከውጭ ካሉ ደጋጎች የተላኩ ብሮችን ማውጣት፣ ቲኬት ለመሸጥ ወዳጆች ጋር መሄድ፣ በዱቤ የሸጥኳቸውን ብሮች ለማምጣት…. ከዚያ በኋላ ደግሞ ቀን 7 ሰዓት ላይ ሁላችንም እንገናኝ ተብሎ ነበርና ወዳጆቼ ጋር ላለመጉደል። ሁሉ ነገር ትናንት እንደነበር ሁሉ አይረሳኝም። (በአጠቃላይ ነገሩ ላይ ወደፊት…የማጫውታችሁ ነገር ይኖረኝ ይኖር ይሆናል።)
 
….በሥራ ብዛት የተነሳ ቁርሴን ሳልበላ ነበር የወጣሁት። በፋሲካ በዓል ማግስት (ሀሙስ) ከቤት ቁርስ ሳይበሉ መውጣት ብዙም ባይለመድም (ለራስም ለቤተሰብም ደስ ባይልም) ወጣሁ። — አንድም ስራዎቹን ለመፈፀም ጊዜ ስለምቆጥብ፣ ሌላም ስራ እያለብኝ ብጎርስም ምግብ ስለማይወርድልኝ አንደኛዬን ጨራርሼ…ብዬ ነበር። ቁርስ አለመብላቴ አይደለም የሚገርመው…. ምሳም አልበላሁም።
 
አመሻሹ ላይ በዝግጅት ጉድለት ምክንያት sound system ስላልተስተካከለ ሙኒት እና ዮርግ ሸበሌ ፓርክ ውስጥ ቁጭ ብለው ስለነበር ከእነርሱ ጋር ቁጭ ብዬ መጫወት ጀመርን። በሙኒት ግፊት አንድ ሚሪንዳ ጠጣሁ። ከዚያም ሜሮን ጌትነትን ለማግኘት ሸበሌ ቴራሱ ላይ ወጣሁ። የሚበላ አዝዛ ስለነበር፥ በብዙ ጭቅጭቅ ሶስት ጉርሻ አጎረሰችኝ። ቁርስም፣ ምሳም እራቴም ሆነ። — አንድ ለቁርስ፣ አንድ ለምሳ፣ አንድ ለራት በሉት!
 
ሰዓቱ ደርሶ ከነድክመቱ ጥሩ የሚባል ፕሮግራም አሳልፈን ቤት ቤታችን ተበተንን። እኔ ሰፈር ስደርስ 3 ሰዓት ገደማ ነበር። ቤት ለመድረስ የአንድ የ15 ደቂቃ መንገድ ሲቀረኝ የቤተሰብ ስልክ ተደወለልኝና አንስቼ ማውራት ጀመርኩኝ። አስፓልት ላይ ነው። ሰውና መኪና ለጉድ በሚመላለስበት አስፓልት። ትንሽ እንደሄድኩ…. ከኋላዬ የጎረምሳ እጅ ስልኩን ለመንጠቅ ያዘኝ። ስልኩን አጥብቄ ይዤው ኖሮ፣ ወይ ደግሞ እርሱ አጠንክሮ መንጠቅ ስላልቻለ… እንደነጠቀኝ አልወሰደውም ነበር። እኔም ዞርኩ።
 
እንደዞርኩ ግን ፊቴ ላይ ያረፈው የጎረምሳው ጩቤ ነበር። ከዓይኔ ከፍ ብሎ መሀል ላይ ወግቶኝ ስልኩን አስለቀቀኝ። አልሮጠም። ቀብረር ብሎ እየተሳደበ ሄደ። ከተቃራኒው የአስፓልቱ ጎን ላይ ጓደኞቹ እየጠበቁት ኖሮ ተቀላቀላቸው። በእጃቸው የያዙትን ገጀራ ሳይ ደነግጬ ዝም አልኩኝ።ማለፍም አለ። እርሱ ቢቀር ደግሞ ኪሴ ውስጥ የነበረ ጠቀም ያለ ብር (7 ሺህ የሚጠጋ) የነሱ ሲሳይ ሊሆንም ይችላል።
 
እናም ዝም! ደም እየወረደ ፀባይ ማሳመር!…በርግጥ መንገዱ ጭር አላለም ነበር። ብዙ ሰው ወደላይ ወደታች ይመላለስ ነበር። ልክ እኔን ሲወጋኝና እየተሳደበ ሲሄድ ደግሞ ቆመው ማየትም ጀመሩ። ወሬ ማየት ተክኖት የለ ህዝቤ?! ሲያዩኝ ይበልጥ በሸቅሁኝ። ብዙ ነገር አብራርቼ እንዲረዱኝ ተማፀንኩ፥ ወፍ የለም!
 
ደሜ እየተንዠቀዠቀ ብጮህ ብጣራ ወይ የሚለኝ አጣሁ። ከሶፍት አቅም የሚሰጠኝ አጣሁ። “አይዞህ” ማለትም ብርቅ ሆነ። መነፅሬ ወድቃ እንኳን እርሷን ፈልጎ የሚያቀብለኝ አጣሁ… (i need to wear a glass, to get my lost glass. Hehehe…) ዓይኔም በደም ተሸፍኖ ስለነበር መነፅሬን በዳበሳ አገኘሁት። – ለዓይን አምላክ አለው እንዲሉ አልተሰበረችም ነበር። እርሷን ይዤ ለእርዳታ ተጣራሁ። እንደሞኝ ለመንኩ! እንደሞኝ ሶፍት ለመንኩ! እንደ ልጅ “አይዞህ” መባል አማረኝ! እንደ ተራ ትኩረት ማግኘት ፈለግሁ! ….አሁንም ወፍ የለም!
 
ጥላዬን ፈራሁት።….ሚሰማኝ አልነበረም። ደሜ እየተንዠቀዠቀ ስልክ ወደማገኝበት ሱቅ ሄድኩኝ። ቅርብ ያሉ ሱቆች “አናስደውልም” አሉኝ። “ኧረ በራስህም ቢሆን” ብል ወይ ፍንክች! ይገርማል!…. “ምን ሆነህ ነው?” የሚልም የለ! ….ከዚያ በላቀ ግን፥ አገልግሎትን በመከልከል ወንጀልን መንከባከብ። ወንጀለኞችን መተባበር። በጣም አስጠላኝ። ….መጀመሪያ ህልም መሰለኝ። ደሙን ሳይ ስዳስስ፣ ሲቀዘቅዘኝ፣ ቁስሉ ሲሰማኝ…. ህልም እንዳልሆነ አወቅሁኝ። ኢትዮጵያዊነቴ አስጠላኝ። ሰውነቴ ደበረኝ። ናቅሁት። አማርኛ መናገር ቀፈፈኝ! “የሰው ያለህ” ብዬ የተጣራሁበት ድምፅ አንድ ሰው እንኳን ካላቀረበልኝ ምን ሊሰራልኝ? የምር ሽክክ አለኝ!
 
እዚያ — ዓለም ደቻሳ የተባለች ምስኪን፥ ቆንፅላው ፅ/ቤት በር ላይ ስትጎተት ዝም አሉ። እዚህ — ዮሐንስ ሞላ የተባለ ምስኪን ወጣት ለዓለም ደቻሳ ገቢ እሰበስብ ብሎ ባመሸበት፥ በራቸው ላይ (ያውም ዋና የመኪና መንገድ ላይ) ሲወጋና ሲቀማ ዝም አሉ። –እሳት ካየው ምን ለየው? እንዲሉ ሁለቱም ያው ናቸው።
 
ለራሳቸው ፈርተው ነው ይባልና ልጆቹን ለመያዝ መሞከር ይቅር… ግን ሶፍትና ውሀ መስጠት ምንም አይጎዳም ነበር። ድብልቅልቅ ባለ ስሜት ውስጥ ሆኜ፣ ማንንም እንዳልጠይቅ ተስፋ ቆርጬ ስሄድ፣ አንድ መልከመልካም ወጣት ሰው ምን ሆኜ እንደሆነ ጠየቀኝ። ነገርኩት። ሁሉንም ነገርኩት። ባለሱቆች ስልክ እምቢ እንዳሉኝም ነገርኩት። ሁኔታዬን አይቶ በጣም አዘነ።
 
….ከማዘኑ ብዛት ሳያስተውል ደሜን በእጁ ነክቶ አጠበኝ። ብከለክለውም አሻፈረኝ አለ…. “ባልረዳህ ፀፀቱ ይገለኝ የለ? አታስብ ወንድሜ!” አለኝ። እንደልጅ ጉንጬን እያሻሸ አባበለኝ። ስልኩን ሰጥቶኝ ወንድሜ ጋር አስደወለኝ። አንዠቴን በላው። መቼስ እግዜር ደግ ነው።… በአንዱ ልባችን ሲሰበር ባንዱ ይጠግናል። አሁን ደግሞ ከዚያም ወንድሜ ወዲያው ደርሶ ሆስፒታል ሄደን ተሰፋ።
 
— ታሪክን የኋሊት?! እንዲህም አይደል?
እግዚአብሔር ሌላ እድል ሰጥቶኝ “የዛሬ ዓመት” እያልሁ ታሪክ እዘክር ዘንድ እዚህ አድርሶኛልና ክብሩ ይስፋ።
 
Moral of the memo:
 
ይሄ በየመንገዱ ቅሚያና ውጊያ በጣም አሳሳቢ ነገር ሆኗል። እኔ ከማውቃቸው የቅርብ ወዳጆቼ ውስጥ ብቻ ከእኔ በኋላ የተከሰቱ 5 ወይም 6 አደጋዎችን አውቃለሁ። ምናልባት በኮብልስቶን ከተደራጁት ጋር በቅሚያና ዝርፊያ የተደራጁም ይኖሩ ይሆን? ለማንኛውም ግን ራስን መጠበቅና መጠንቀቅ መልካም ነው። ሰዎችንም እንኳን እርዳታ ጠይቀው፥ መደናበራቸውን አይተን የምንረዳ ያድርገን።
 
Viva Jo! 😉

ፊልሞቻችን የገሀዱ ዓለም ኑሯችን ማሟያዎች (complemnts)?

Tragedy life vs Comedy records imagesCAU3G9AK

የምንኖረው ሌላ የሚሰራልን ፊልም ሌላ።…. ገሀዱ ዓለም ሌላ የሬድዮና የቴሌቪዥኑ ዓለም ሌላ።…. ፎቶው ሌላ የምሩ ገፅ ሌላ። ወሬው ፀአዳ፣ ኑሮው ማድያታም።… በዚህ አላግባብ አንጀት በሚበላ (tragedy) ኑሮአችን ላይ ማረፊያ እንዲሆኑን የሚሰሩልን አስቂኝ (comedy) ፊልሞች ብዛት ያሳቅቃል። የቴሌቪዥን ድራማውም እንደዛው ነው።

ከቀልድ ነፃ በሆነ የድራማ ዘውግ ላይም …ለድራማው ምልአት ምንም ጥቅም ሳይኖራቸው… እንዲያስቅ ብቻ ብቅ ብለው የሚጠፉ ገፀ ባህርያት ይኖራሉ። ቶክ ሾው ተብዬዎቹም በብዛት ማሳቅ ላይ ነው የሚያጠነጥኑት። ሙዚቃውም ቢሆን(በአብዛኛው)…ጠነከረ፣ ጆሮ ገባ ሲባል… ያው መከረኛ የፆታዊ ፍቅርን (romance) ዘውግ ሳይለቅ ደርሶ ተመላሽ ነው። …ከጊዜ ወዲህ ደግሞ ለወረት – አባይና ራዕይም ተጨምረውበት ይፈራረቃሉ።

ግን ምንድን ነው? በተለይ የፊልሞቻችን ነገር? በርግጥ ማሳሳቅ ክፋት የለውም። ክፋት የለውም ሳይሆን አግባብም ነው። ሆኖም ግን እያሳሳቁ ማረሳሳት እዳው ከባድ ነው። ጥቅምና ጉዳቱን ሳያሰላ…መቼቱ ዛሬ/እዚሁ ይሆንና ለማንም አይበጅም፤ ስንት ጉዳይ በሞላበት አገር ውስጥ ነገር ዓለሙ የሚወጥነው እንዴት እንደሚያስቅ ሲሆን ላስተዋለው ያሳቅቃል።

መደበኛ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ቧልት ይበዛቸዋል። የበዓል ዝግጅቶች ደግሞ ከመደበኛውም ይብሳሉ። እንደምሳሌ: ባለፈው የአባይ ግድብን 2ኛ ዓመት ፅንሰት ለማክበር የተደረገውና በኢቲቪ የተላለፈው ፕሮግራም ለንቁ አሸማቃቂ ነበር።… ሲሆን ሲሆን ብዙ ሳይንሳዊ ጥናቶችና የምርምር ፅሁፎች ቀርበው ሰፊ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ ቢሰራ ጥቅሙ የሁለት እዮሽ በነበረ። ግን ከማዘናጋት ጎን ለጎን ግቡ ማሳቅ ነውና እንዲያ አልሆነም። ይህን በተመለከተ ዓለማየሁ ገላጋይ በልዕልና (ቁጥር5 መጋቢት 2005)ጋዜጣ ላይ…

….ሲምፖዝየም፣ ኮንፍራንስ….ቢሆን እያንዳንዱን እሳቤ ተንትኖና ተርጉሞ ያልተፈለገ ውጤት የሚያመጣው ብዙ ነው። ስለዚህ እንቁላል በማንኪያ ይዞ መሮጥ፣ ገመድ መጓተትና የፌዝ እግር ኳስ መጋጠም የማይተረጎም፣ አስር ጊዜ ቢወቅጡት ያው እንቦጭ የሆነ ድርጊያ ነው። በዓል ይደምቃል፤ መንግሥት ከስጋት ይድናል። የጥንቶቹ መኳንንቶች የደብተራው ቅኔ ሽሙጥም ሊኖርበት ስለሚችል ሲደግሱ እንዲህ ይሉ ነበር አሉ፤ “ከሺህ ደብተራ የአንድ ቄስ ዳንኪራ” በዚህ ዘመንም የተቀዳው ይሄ አባባል ነው። በዚህ ምሁር ከመቆላመጥ፣ የአንድ አርቲስት እንቁላል ይዞ መሮጥ።….

ብሎ ነበር ነገሩ የታዘበው። በቃ እኛ አገር እንዲህ ነው። በቴሌቪዥንና በሲኒማ ማሳቅ፣ ማሳቅ፣ ማሳቅ….አሁንም ማሳቅ፤ ከዚያ ደግሞ በኑሮ ማሳቀቅ። laughing-menየተመልካቹ ፍላጎትም የለመደው ላይ ያጠነጥናል። ድራማ ፊልም ቢሰራ ያመዋል። ጠንከር ያለ ጉዳይ ተይዞ ቢዋዛለት ይሰለቸዋል። እንቅልፉ  ይመጣል። በመሆኑም ወደ ሲኒማ ቤቱ ዝር አይልም። የሲኒማ ቤቶችን ወረፋ ለማጨናነቅና የተመልካች ብዛት ሰንጠረዡን ለመቆጣጠር ፊልሙ ማሳቅ አለበት። ቁም ነገር፣ ጠንካራ ሀሳብ፣ ቆንጆ የድራማ ፅሁፍ፣ ገራሚ ዝግጅት፣ ጉድ ያስባለ ትወና… ካላሳቁ ምንም ቦታ የላቸውም።

ሰው የጎደለውን ነገር ፍለጋ ሲኒማ ቤት ነዋ የሚሄደው። ከለቅሶና ከብሶቱ ለማረፍ ሳቅ ያስፈልገዋል። ለያውም ከፈጠራ የፀዳ የጅል ማሳቅ። እንዲያ እንዲሆን ነውና የተለማመደው ትንሽ በሰል ያለ ኮሜዲ ሲሰራለት እንኳን ራሱን ያመዋል። ለመጀመሪያ ጊዜ ከንፈሯን እንደተሳመች ኮረዳ ጭው ጭር ይልበታል። ሰማይና ምድሩ ተደበላልቀውበት ስለቱርጁማን ግራ ቀኙን ያማትራል። ‘ምነው እግሬን በሰበረው’ ካላለም…

የደሀ ጉዳይ – የራሱ ጉዳይ!

አገራችን ላይ የደሀና የሀብታም ነዋሪው ቁጥር የትና የትነት በግልፅ እንደሚታወቀው …(ከፆም ከማደር — እስከ — ለሻይ ዱባይ እስከመሄድ ድረስ…) ቢሆንም… ፊልሞቻችን በብዛት የሚያጠነጥኑት የሀብታም ቤት ኑሮ ላይ ነው። ለሰፊው ደሀ ህዝብ የሀብታምን ኑሮ ከምናብ ባለፈ በፊልም ምስል ያሳዩታል። በፊልምም፣ በዘፈን ክሊፕ ቀረፃም ወቅት የሚታዩት ቤቶችና ሁኔታዎች የብዙሃኑን አኗኗር የሚያሳዩ ሳይሆኑ የሀብታሙን ቤት የሚተርኩ ናቸው። በስመ ገፅታ ግንባታና ዓይንን ምረካ ጥበብ ወዲያ ተሽቀንጥራለች። የደሀው ጉዳይ ወዲያ ተዘንግቷል።

ደሀ issue የሌለው ይመስል ቀረፃዎች ሁሉ ሀብታም ሀብታም ይሸታሉ።…. ስለሀብት ይወራል። ስለሚንቀሳቀሱ ሚሊዮን ብሮች ይተረካል። ሰፊውን ህዝብ በትንሿ የቲቪ ስክሪን ያንቆላልጩታል። ጥጋበኞች የሚሟዘዙበትን ፊልም ሆዱን እያከከ ተመልክቶ ካንገት በላይ ይዝናናል። ምን ያድርግ እንዲያ ነዋ የተበጀው። ‘ደሀ ኑሮውን በእውኑ ይኖረዋልና ምን ቀርፆ ማሳየት ያሻል?’ በሚል ፈሊጥ ይመስላል…. ‘የደሀ ጉዳይ – የራሱ ጉዳይ’ ተብሎ ተትቷል። እርሱም ተስማምቶት ነው መሰል በኑው የጎደለበትን በፊልም ይሞላውና ከነችግርና ጥያቄው ተጠቅልሎ ይተኛል።

ይህቺ ናት አገሬ!

ማስታወሻ

በደረቅ ትርጉሙ complement ማለት ማሟያ፣ ማረጋጊያ፣ ማጣጣሚያ፣ ማስማሚያ እንደማለት ነው። ብዙ ጊዜ የስነምጣኔ ሀብት(economics) ትንታኔ ላይ ያገለግላል። ለምሳሌ ወጥ የእንጀራ complemet ነው። ወጡ እስኪመጣለት እንጀራው እንደጎዶሎ ነው። ነዳጅ የመኪና complement  ነው። የcomplement ሸቀጦች (goods) ባህርይ እርስበርስ መፈላለጋቸው ነውና የአንዱ ዋጋ መዋዠቅ ሁኔታ ሌላኛውም ላይ በቀጥታ ተፅህኖ ያሳድራል።

የግድ ስለሚፈላለጉ (አንዱ ላንዱ ሙላት ስለሆነ) የአንዱ ዋጋ መጨመር የሌላውን ዋጋ መጨመር ይወስነዋል። ልክ እንደዚያው የአንዱ ዋጋ መቀነስ ደግሞ የሌላውን ዋጋ መቀነስ ይወስነዋል። በዚህ መሰረት ከሄድንና ፊልሞቻችንን የገአዱ ዓለም ኑሮ ማሟያዎች ካልናቸው የኑሮው መዝቀጥና አሳዛኝነት ሁኔታ…. የፊልሞቹን የማሳቅ አቅምና ሁኔታ በቀጥታ ይወስነዋል ማለት ነው። ይሄ ደግሞ ያለውንና የሚመጣውን ገግልፅ ያሳየናል።

— መሰለኝ!

የቅዱስ ያሬድ ታሪክ

ቅዱስ ያሬድ በ505 ዓ/ም በአክሱም ተወለደ። አባቱ አብዩድ ወይም ይስሐቅ እናቱም 524275_507752735929406_552060275_nክርስቲና ወይም ታውክልያ ይባሉ ነበር። የነርሱም ሀገራቸውና ርስታቸው አክሱም ነበር። ቅዱስ ያሬድ በተወለደ በ7 ዓመቱ አባቱ ስለሞተ እናቱ ክርስቲና የአክሱም ገበዝ ለነበረው ለአጎቱ ለጌዲዎን እንዲያሳድገውና እንዲያስተምረው አደራ ብላ ሰጠችው። ከጌዴዎንም ቤት 25 ዓመት እስኪሆነው እየተማረ አደገ። ከዚያም መፃህፍትን ማለት ብሉይንና አዲስን ተማረ። ከዚህም በኋላ መምህሩ (አጎቱ) ጌዴዎን ሲሞት እርሱ ተተክቶ የመጽሐፍ መምህር ሆነ። በዚህም ጊዜ በዲቁና ሚስት አግብቶ ልጆችን ወለደ። ቀጥሎም ቄስ ሆነ።

በእርሱም ዘመን 9ኙ ቅዱሳን ከውጭ አገር በችግር ምክንያት ተሰደው ስለመጡ፤ ይህም ማለት በቁስጥንጥንያ መንግሥት ዮስጥንያኖስ ዩስቲኒያኖስ በነገሠበት ከ527 ዓ/ም እስ ከ 565 ዓ/ም ድረስ በምሥራቅ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በአንድ ባሕርይና በሁለት ባሕርይ ወገኖች ውስጥ ብዙ ሁከትና ፍጅት ስለነበረ ከዚያ በመሸሽ የመጡ ካህናትና መነኮሳት ስለነበሩ ከእነርሱም አንዱ በአክሱም ከተማ አጠገብ የነበረው አባ ጰንጠሊዎን ስለነበር፤ ቅዱስ ያሬድ እየተመላለሰ የውጭውን አገር ቤት ክርስቲያን ባሕልና ሥርዓት ይጠይቀው ነበር ይባላል።

ከዚያም በኋላ ቅዱስ ያሬድ የውጭውን አገር ቤት ክርስቲያን ባሕልና ሥርዓት ለመጎብኘት ሁለት ጊዜ ተመላልሼ የሮምን ቤተ ክርስቲያን፤ 2ኛይቱን ሮም የተባለችውን የምሥራቅና የቁስጥንጥንያን ቤተ ክርስቲያን ጎበኘሁ’ ሲል በመዝሙሩ እርሱ ራሱ ገልፆልናል። (ወሪድዬ ብሔረ ሮሜ ለቤተ ክርስቲያን ርኢክዋ አእመርክዋ አፍቀርክዋ ከመ እኅትየ ሠናይ ሐለይኩ፤ እምድኅረ ጉንዱይ ዓመታት ወእምዝ እምድኅረ ኅዳጥ መዋዕል ካዕበ ርኢክዋ ወትትሐጸብ በፈለገ ጤግሮስ) እንደዚህ እያለ የውጭውን አገር ቤተ ክርስቲያን ሲያመሰግን ይገኛል።

ከሱ በፊት በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ደንበኛ የሆነ ቅኔና ዜማ ትምህርት ስለሌለ ደንበኛ የሆነ ቅኔና ዜማ ለማስገኘት ተዘጋጀ። የድርጅቱም መጀመሪያ ይህ ነበር። ሃሌ ሉያ ለአብ ሃሌ ሉያ ለወልድ ሃሌ ሉያ ወለመንፈስ ቅዱስ፤ ቀዳሚሃ ለጽዮን ሰማየ ሣረረ ወበዳግም አርአዮ ለሙሴ ዘከመ ይገብር ግብራ ለደብተራ ብሎ ከነበሩት ከብሉይና ከሐዲስ ሊቃውንት አንዱ እርሱ ስለ ነበርና ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንም ብዙ አሳብ ስለነበረው ከብሉይና ከሐዲስ፣ ከሊቃውንት መጻሕፍትም ከነአትናቴዎስ ከነቄርሎስ ከነዮሐንስ አፈወርቅ መጻሕፍት ለምስጋናና ለጸሎት የተስማሙትን ቃላት እየመረጠና እያቀና በአራቱ ክፍለ ዘመን፣ በመፀውና በሐጋይ በጸደይና በክረምት እንዲነገር አድርጎ ወስኖ አዘጋጀ።

የመጽሐፉ (የድርሰቱ) ስም ድጓ ተባለ። ድጓ ማለትም በአክሱምና በአድዋ ቋንቋ (በትግርኛ) ደጉዓ ማለት መዝሙረ ኃዘን፥ የኃዘን ዜማ፥ ማለት ነው። – ሙሾ። የዜማውን ዓይነት በሦስት ክፍል ወስኖ ተናግሮታል። እነርሱም ግዕዝ፣ ዕዝል፣ ዓራራይ ይባላሉ። ግዕዝ ማለትም አንደኛ በመጀመሪያ የተገኘ ማለት ነው፤ ዕዝል ማለትም ሁለተኛ ሆኖ ከግዕዙ ጋር ተደርቦ፣ ተጨምሮ (ታዝሎ) የሚነገር ማለት ነው።  ዓራራይ ማለትም ሦስተኛ ተጨማሪ ሆኖ አራኅራኂ፣ ርኅራኄ/አሳዛኝ ልብን የሚመስጥና ደስ የሚያሰኝ ማለት ነው። ይህን ድርሰቱን ያዘጋጀበት ዘመን ከ540 ዓ/ም ሲሆን የመጨረሻ ልጁ አፄ ገብረ መስቀል መንግሥቱን ወረሰ።

አፄ ገብረ መስቀልና አባ አረጋዊ ቅዱስ ያሬድ እነዚህ ሦስቱ በአንድነት እንደነበሩ ታሪከ ነገሥቱና ገድለ አረጋዊ 10926_631987166817917_496445836_nይገልጽልናል። አቡነ አረጋዊ የደብረ ዳሞን ተራራ አቀማመጥ አይተው ደስ ስላላቸው፣ ንጉሡ  አፄ ገብረ መስቀል በዚሁ ተራራ ላይ እንዲኖሩበትና እንዲጸልዩበት ፈቀደላቸው። እርሳቸውም ይህንን ተራራ ከተረከቡ በኋላ በተራራው ላይ የጸሎት ቤት ስለሌለ ንጉሡ አፄ ገብረ መስቀልን አንድ ቤተ ክርስቲያን እንዲሠራላቸው ለመኑት። ንጉሡም ቤተክርስቲያን ልሠራ የምችልበትን ሥፍራ መርጠው ያመልክቱኝ ብሎ ነገራቸው አቡነ አረጋዊም ተነሥተው ዞረው ቦታውን መርጠው አሳዩት።

ከዚህ በኋላ ንጉሡ በአዋጅና በትዕዛዝ ድንጋዩና እንጨቱ እየተሰበሰበ በከብትና በሠረገላ እየተጋዘ ተሰበሰበና ከታች ወደ ተራራው ላይ ወጥቶ ተሠራና የቤተ ክርስቲያኑ ሥራ በሁለት ዓመት አለቀ። ባለቀም ጊዜ የቤተክርስቲያኑ ሥራ ተመልካቾችን አስደነቀ። ለዚሁም ቤተክርስቲያን ልዩ ልዩ የሆኑ አልባሳት፣ የብርና የወርቅ የተደጎሱና የተከፈፉ መጻሕፍትን አበረከቱ። ከማኅበረ በኩር የመጣውን የእመቤታችንን የቅድስት ድንግል ማርያምን ጽላት አግብተው አቡነ አረጋዊ ባርከውና ቀድሰው ንጉሡና ጳጳሱ ቆረቡ። ከዚያም አፄ ገብረ መስቀል በተራራው ላይና በግርጌ ላሉት ሠራዊት ግብር አብልተው ነዳያን ሁሉ ጠገቡ።

ከዚህ በኋላ ቅዱስ ያሬድ በአክሱም ሲያስተምር ሳለ በንጉሡ አፄ ገብረመስቀልና አቡነ አረጋዊ፥ ወደዚህ ተራራ መጥቶ ቤተ ክርስቲያኑን  እንዲጎበኝና እንዲዘምር ተጠርቶ ሲመጣ ከተራራው ሥር ሲደርስ የአቡነ አረጋዊን ደቀመዛሙርት ማትያስና ዮሴፍ የሚባሉትን ከወንዝ ዳር ዓሣ ሲያጠምዱ አግኝቶ ዳኅንኑ ዝስኩ አረጋዊ አቡክሙ (ይህ አረጋዊ አባታችሁ ደህና ነው?) ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም ደኅንነታቸውን ነገሩት። ከዚያም ቅዱስ ያሬድ ወደ ተራራው ላይ ወጥቶ ከአቡነ አረጋዊ ጋር በመንፈሳዊ አምኃ በፍቅር ተገናኙ ወደ ቤተክርስቲያኑም ሄዶ 3 ጊዜ ሰግዶ ከተሳለመ በኋላ የሕንጻውን ማማር በአድናቆት ተመልክቶ ከፍ ባለ የዜማ ድምፅ እያጉረመረመ እንዲህ ሲል ዘመረ።

‘ይሄውፅዋ መላዕክት እንተ በሰማያት ይሄውፅዋ መላዕክት እስመ ማኅደረ መለኮት ፆድክዋ ፆድክዋ ፆድክዋ ወርኢኩ ሥነ ሕንፄሃ ለቅድስት ቤተክርስቲያን ምሥአል ወምስጋድ ወምሥትስራየ ኃጢአት ይዕቲ ቅድስት ደብተራ።’ የሚለውን መዝሙር ከዘመረ በኋላ ስምንት ቀን ያህል ከአቡነ አረጋዊ ጋር ሰንብቶ ንጉሡ ወደ አለበት ወደ አኩሱም ተመልሶ ሲገባ አንቀጸ ብርሃን ተብሎ የተሰየመውን ድርሰትን ቅድስት ወብፅዕት ብሎ በዜማ ደረሰ። ከዚህ በኋላ ንጉሡ አፄ ገብረ መስቀልና አቡነ አረጋዊ ከቅዱስ ያሬድ ጋር አብረው ወደ ሌላ ጠቅላይ ግዛት ጉብኝት ሄዱ። ከዚያም በአንዱ ደሴት ላይ የቅዱስ ቂርቆስን ቤተ ክርስቲያን ሠርተው ተቀመጡ። በዚያም ቦታ ቅዱስ ያሬድ ሁለት ዓመት አስተማረ። እርሱ እራሱ ጻፈው የሚባል ድጓ ምልክት የሌለው ዛሬ በዚሁ ደሴት በጣና ቂርቆስ ይገኛል።

ከዚህም ደሴት ከጣና ቂርቆስ ተነሥተው ንጉሡና አቡነ አረጋዊ ቅዱስ ያሬድም ወደ ደጋው ወደ ጋይንት ወጡ። በዚያም አንድ 1ትልቅ ተራራ አግኝተው መውጫው ጠፍቶባቸው ሲጨነቁ አንድ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልዕክተኛ መጥቶ አቡነ አረጋዊን (ዙር አባ መንገለ ምሥራቅ) አባ መውጫውን በምሥራቅ በኩል ታገኘዋለህ ሲል አመለከታቸውና ሦስቱም ተያይዘው ወደ ተራራው ላይ ወጡ። በዚሁ ተራራ ላይ የእመቤታችንን ቤተ ክርስቲያን ሠሩ። የተራራውም ስም እስከ ዛሬ ድረስ ዙር አምባ ተብሎ ይጠራል።ቅዱስ ያሬድ በዚሁ ተራራ ላይ ሦስት ዓመት ዝማሬ መዋሥዕት የተባለውን መዝሙር አስተምሯል። ይህም ቦታ እስከ ዛሬ ድረስ የዝማሬና የመዋሥዕት ምስክር ቦታ ሆኖ ይኖራል።

ከዚህ በኋላ ቅዱስ ያሬድ ወደ አክሱም ተመልሶ ለሥጋ ወደሙ ጸሎት የሚያገለግሉትን 14ቱን ቅዳሴዎች በዜማ ተናገረ። ቅዳሴውን በዜማ የተናገረበት ቦታ መደባይታብር ይባላል። ይህም መደባይታብር የሚባለው ቦታ ለአክሱም ሰሜን ሆኖ ከአክሱም ግማሽ ቀን ያህል በእግር ያስኬዳል። ከዚያም ወደ ሰሜን ተራራዎች ወደ ጠለምት ሔዶ ምዕራፍ የተባለውን የዳዊትን መዝሙር ተናገረ። ከዚህ በኋላ ወደ ወገራና ወደ አገው እየዞረ ካስተማረ በኋላ ከሰሜን ተራራዎች ሥር ባሉት በአንዱ ገዳም ውስጥ በብሕትውና ከቆየ በኋላ በሰሜን ምሥራቅ ባለው ሸዋ ውስጥ በ571 ዓ/ም ግንቦት 11 ቀን አረፈና ተቀበረ።

ከዚህ በኋላ የእርሱ ደቀመዛሙርት ሳዊሮስና ሳንድሮስ በልዳዶስ የሚባሉት ከርሱ የተማሩትን የዜማ ባሕልና ሥርዓት በትግሬና በሰሜን አውራጃ እየተዘዋወሩ በየገዳማቱ ሁሉ ስለአስተማሩ የቅዱስ ያሬድ ድርሰት እስከ ዛሬ ድረስ ጸንቶ ይኖራል።

ምንጭ:“የቅዱስ ያሬድ ታሪክና የዜማው ምልክቶች” ግንቦት 15/ 1959 በትንሳኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት የታተመ መጽሐፍ

አንድ አፍታ፡ – ነገረ ቆሎ. . .

ህይወት ቆሎ ናት… ስንዴ ቆሎ ¬ ገብስ ቆሎ -¬ በሽንብራ የተደባለቀች ቆሎ -¬… ጎኗ ሱፍ ቁጭ ቁጭ ብሎ የሚያጅባት ቆሎ…. ሱፍ ለብሰው የሚከኳት ቆሎ… ¬ ሰነፍ ቆሎ፣ ጎበዝ ቆሎ… ¬_ ‘ፓ ቆሎ!’ እያሉ…. እየሰፈሩ የሚቸረችሯት…. የሚቆረጥሟት! የሚቀጯት! እየቆነጠሩ የሚቀጨቅጯት —

— ቀጭ ቀምቧ…. ቀምቧ ቀጭ…. ቀጭ ቀምቧ….

…..ቆሎ በአፉ ሞልቶ ቆንጆ ሴት ማለም – ለፈለገ – ቀላል ነው። ወይ ማስቲካዋን፣ ወይ ሂል ጫማዋን አርጋ…. በሊሾው ወለል ላይ፥ ቀጭ ቀንቧ ስትል በሀሳቡ እየሳለ – – – ሂል ቶፕስ – ዳሌዋን ማለም ይችላል። ¬ ‘የ – ኔ – ቆ – ን – ጆ– ’! ግን ከቻለበት ነው።…. ከፈለገ።…. ታዲያ እንዲያም ቢሆን ህልም አይታለፍም፤ የማይጨበጥ የማይዳሰስ ህልም…. – ህልም እልም!

ህይወትም እንዲህ ናት! እየቆረጠሟት የፈለጉትን ዓይነት ህልም መከለም ነው። ያው የስሜት ጉዳይ ነው! የፍላጎት ዓይነት።…. ጉልት እየተቸረቸሩ ቤተመንግስት ንጉስ ፊት የሚቀርቡ ቆሎ እንደሆኑ መመኘት…. ፆም የማደርን ያህል ቀላል ነው፤…..ዓለም ላይ ቁጭ ብለው፥ለመጠጥ ቤት እየተቸበቸቡ፥…. ከዳቤ ጋር የሚቀርብ የገዳም ቆሎነትን መመኘት ይቻላል፤… የለቅሶ ቤት ቆሎ ሳሉም የሰርግ ቤት ኮክቴል አጃቢነትን መቋመጥ መብት ነው። ግን ማሰብ ብቻ!

ኳስ ሜዳ ዙሪያ ቢቸበቸቡስ ቀላል ነው እንዴ? …. “እስኪ ከሽንብራው! ….ከሱፉ ጨምሪ እንጂ። …..ኤዲያ አንቺ ልጅ እጅሽ አ ይደለም የቆላው።…. ይሄማ ቤት አልተቆላም! የገበያ ነው።…” ቢባልለት!….. የገበያው ዱር ይቆላ ይመስል። የገበያ ሲሆን እግር ይቆላው ይመስል። ….ዝም ብለው ሲቀናጡ! አቅም ማሳየት! — የመግዛት አቅም። የመክፈል አቅም። — ገንዘብ የመክፈል?! ሁለት ቦታ የመክፈል?! ….የማዘዝ አባዜ። የመተቸት ፍቅር። የእልቅና ታናሹ….

እንዲህ ሲሆን ግን ህይወት ቆሎዋም ደስ ይላታል። ሰርክ በመታመስ ላይ እንዳለ አካሏን ታገላብጣለች። ዳሌዋን ሸሽጋ ሽንጧን ታተራምሳለች።…..የህይወት ሂልቶፕስ የት እንደሆነ ችለው ሲወጡ ብቻ ነው የሚታየው።…. ባላዩዋት ቁጥር ደግሞ ስታሳሳ! ሂልቶፕሷን እያቁለጨለጨች ኗሪዋን ማሴሰን ነው። እየተማረሩባት ብዙ የምታስመኝ። አልቆረጠም ብላ ጥርስ እየፈተነች ብዙ የምትፈለግ። ጥርስ ገብታ እያመመች የምትናፈቅ። ለዝዛም፣ ፈዝዛም፣ አደንዝዛም፣ አስተክዛም….

“ሂልቶፕሴን ያያችሁ?
– አላየንም….
ኗሪዎች እባካችሁ…”

ህይወት ቆሎ…. እንደ ዱቤ ቆሎ…. በዱቤ የሚኖሯት…. በዱቤ ገዝተው በዱቤ የሚበሏት…. የተኮናተሯት ዓይነት! በብዙ ጨው ተለውሳ ውሀ የምታስጠማ። ከዚያ ብዙ የምታስጠጣ። መጠጥ የምታሻሽጥ። የምታሳክር። ….ህይወት ቆሎ። ጨው የበዛባት ቆሎ።…..“ማን ነሽ… ትንሽ አፌ ላይ አንቀዋልዬው የምመልስልሽ ቆሎ ካለሽ አውሺኝ። እንግዳ መጣብን የእኛው ቆሎ እስኪቆላ ድረስ….” የሚባልላት።

“ምነው እቴ? አይሟሟ!….ምነው ሰሰተች?…. ይዋጥባት ይመስል።…..” ተብሎ የሚገበዙባት….. እርሷን እየቆረጠሙ፣ “ባዶ ቤት በክረምት”ን የሚያንጎራጉሩባት። እየፈጯት በትዝታ ነጉደው መንገዱን የሚፈጩባት። ይገርማል! ….ከቆሎ ጋር ሆነው “ባዶ ቤት” ይባልባታል።….. ቆሎ ይዘው ቆሎ መመኘት ቅንጦት ነው። ሙቅ እንደማላመጥ ያለ ቅንጦት፤…አሻሮ ይዞ ከቆሎ መጠጋት ግን ከዚያም ይብሳል። — ሰገብጋባ ቅንጦት!

…. ያሻው ደግሞ ኑሮውን ሊደጉምባት በእንቅብ ሞልቶ የሚቸረችራት ቆሎ። -ህይወት፤

ስንዴ ቆሎ፣….
አጃ ቆሎ፣….. ቆሎ ቆሎ
ያቺን ትተህ ይችን ቶሎ!

ተብሎ በልጅ ኩልትፍትፍ አንደበት የሚዜምላት!

ጎረምሳ በእንካ ሰላምታ የሚረታባት! ረትቶ “እንካ ቆሎ” የሚባልበት….የሚሸለምበት… – የቆሎ ሽልማት! ደስ ሲል!!

“እንካ ሰላምታ
– በምንታ
በቆሎ…
– ምናለ በቆሎ?
ነይ ልቃምሽ ቶሎ”

…. እርሱ ጠይቆ፣ ልቃምሽ ብሏት ማን ቆሎ ችላ ልትቀር? ትሸለመዋለች! በሽልማት መልክ ላላማጯ ትበረከታለች!!

…. ጠጅ ቤት፣ መንገድ ዳር፣ መጠጥ ቤት፣….የምትንከራተት። — ቆርጣሚ ፍለጋ። ገዢ ፍለጋ። አሳዳሪ ፍለጋ። – አሳዳሪ ሆድ። ቆርጣሚ ጥርስ።…….. ቆርጣሚዎቿም ይፈልጓታል። ያለችበት መጥተው ይገዟታል። ዓይናቸውን እያንቀዋለሉ…. እያንከባለሉ…. እርሷን ቆርጥመው “ጠማኝ” ሊሉ። ሰበበኞች…. ጠማኝ ብለው ጋኑን ሊገለብጡ። ሲጠጡ ደግሞ ይናፍቋታል። ታጫውታለች። ታስቆዝማለች። እያሉ……..ከዚያም ፍለጋ መውጣት….

ዓይኗ ቆሎ፣ ጥርሷ ቆሎ፣ የወለዱ እንደሆን፣
ታመጣለች አማች ብረት መዝጊያ የሚሆን…

ይሉላታል በዜማ! ለእነሱ ኤልያስ ተባባል ኮልታፋ ነው። ኮልታፋ ስለሆነ… “ቆሎ” ለማለት ነው “ኮሎ” ያለው። በቃ — ካሉ አሉ ነው። – ህይወት ገብሷ አስክራቸዋለቻ!

ህይወት ቆሎዋ ጢንቢራቸውን ታዞረዋለች!….ታባክናቸዋለች። ሲሻት ደግሞ ትቆላቸዋለች። እንደራሷ አድርጋ እርር…. እርሷን እንደቆላት ቁልት ታደርጋቸዋለች። በምድር ምጣድነት በኑሮ መቁያነት ታምሳቸዋለች። ታገላብጣቸዋለች። ቢያርሩም ለአመል ነው። በዪ አያጡም። ጨው ስታበዛባቸው ደግሞ ተከታይ ውሀ ይቀዳላቸዋል።… የማታ ማታ ግን የአፈር ሲሳይ ናቸው።…. እሳት እራት ወደ እሳት፣ የተቆሉት ወደ አፈር፣ ያልተቆሉት ወደ እሳት….

….ግብአተ መሬት….

ወይኔ ቆሎ…. ቆሎ ቆሎ.
አልሰማሁም ነበር አልሰማሁም ነበር፤
ለእኔ ያርገው ቆልዬ ለእኔ ያርገው።
ይሄ ጅብ መሬት ሊቆረጥምሽ….

.
.
“እምቢ…. እምቢ ለቆሎ…. እምቢ ለጥርሴ ጌታ….በወንፊት ሞልታ፣ በሰፌድ መጥታ፣….. አጫውታ አማሽታ….. እምቢ ቆሎ! ተይ አታድርጊኝ ከርታታ….”

ዥዋ – ዥዌ —
— ከሙሾ ወደ ቀረርቶ…. በቃ ህይወት ስትቆላ እንዲህ ነው!

እስከዚያው ድረስ፣ ግብአተመሬቷ እስኪፈፀም ግን ትሰፈራለች። ትኩስ ትኩሱን ያዞሯታል። በእንቅብ ሞልተው ይሰፍሯታል። ልጅ ያለው ልጁን አስይዞ…. የሌለው ራሱ ይዟት…. ይሰፍራታል። በየጠጅ ቤቱ። በየቡና ቤቱ…. ጉልበተኛ መጥቶ እስኪበትናት። የጠገበ መጥቶ እንቅቧን አንገጫግጮ እስከሚደፋት።…. ሰካራም በጥፊ እስኪወለውላት።

… ከተደፋች እንቅቡ ይቀራል። እንቅብ ካለ ቆሎ፣ ቆሎ ካለ እንቅብ ምንም ናቸው። እንቅብና ቆሎ ከሌሏት አዟሪዋስ ምን ትሰራለች? እነሱ ኖረው እርሷ ባትኖርስ?…. ከተደፋች መስፈሪያውም ተሽቀንጥሮ የጎማ ሲሳይ! ኦ መሰፈር ከንቱ። ኦ መስፈር ብላሽ።…. ሰዎች እንደመልቀም ሆነው፣ ከንፈር እየመጠጡ ክንብል ክንብል፣ ድፍት፣ ክብልል፣ ክብብ… ከዚያ ያሟታል። ፊት ለፊቷ።… ‘ኧረ ባክሽ ይሄን ልትሸጭው?!’ ብሩን እንደሚሰጥ እየተግደረደሩ…
.
.
.
ውይ ያቿት…. መጣች እንቅቡን ይዛ! ማነሽ ባለቆሎ…?! ውይ እብድ መጣላት! ስትዞርም እንቅቧን በካልቾ ሲልባትም እኩል ሆነ። ውይይ…

ዝ – ር – ግ – ፍ—-
—-እ – ር – ፍ!

ከመታፈሪያ፣ ከመሰፈሪያ እንቅቡ ወጥቶ እንግዳ አስፓልት ላይ….

ብ ¬
ት ¬ ን –
ት ¬ ን ¬ ት ¬ ን…
– ት ¬ ን ¬ ት ¬ ን -!

¬ – , ..
¬ _ – – =
ብ ¬ት ት ¬ ን ¬ ት ¬ ን — ሜዳ ላይ!!

ህይወት ቆሎ ¬__
¬ – , ..
¬ _ –
¬ _ – – =

/ዮሐንስ ሞላ/