አንድ አፍታ፡ – ነገረ ቆሎ. . .

ህይወት ቆሎ ናት… ስንዴ ቆሎ ¬ ገብስ ቆሎ -¬ በሽንብራ የተደባለቀች ቆሎ -¬… ጎኗ ሱፍ ቁጭ ቁጭ ብሎ የሚያጅባት ቆሎ…. ሱፍ ለብሰው የሚከኳት ቆሎ… ¬ ሰነፍ ቆሎ፣ ጎበዝ ቆሎ… ¬_ ‘ፓ ቆሎ!’ እያሉ…. እየሰፈሩ የሚቸረችሯት…. የሚቆረጥሟት! የሚቀጯት! እየቆነጠሩ የሚቀጨቅጯት —

— ቀጭ ቀምቧ…. ቀምቧ ቀጭ…. ቀጭ ቀምቧ….

…..ቆሎ በአፉ ሞልቶ ቆንጆ ሴት ማለም – ለፈለገ – ቀላል ነው። ወይ ማስቲካዋን፣ ወይ ሂል ጫማዋን አርጋ…. በሊሾው ወለል ላይ፥ ቀጭ ቀንቧ ስትል በሀሳቡ እየሳለ – – – ሂል ቶፕስ – ዳሌዋን ማለም ይችላል። ¬ ‘የ – ኔ – ቆ – ን – ጆ– ’! ግን ከቻለበት ነው።…. ከፈለገ።…. ታዲያ እንዲያም ቢሆን ህልም አይታለፍም፤ የማይጨበጥ የማይዳሰስ ህልም…. – ህልም እልም!

ህይወትም እንዲህ ናት! እየቆረጠሟት የፈለጉትን ዓይነት ህልም መከለም ነው። ያው የስሜት ጉዳይ ነው! የፍላጎት ዓይነት።…. ጉልት እየተቸረቸሩ ቤተመንግስት ንጉስ ፊት የሚቀርቡ ቆሎ እንደሆኑ መመኘት…. ፆም የማደርን ያህል ቀላል ነው፤…..ዓለም ላይ ቁጭ ብለው፥ለመጠጥ ቤት እየተቸበቸቡ፥…. ከዳቤ ጋር የሚቀርብ የገዳም ቆሎነትን መመኘት ይቻላል፤… የለቅሶ ቤት ቆሎ ሳሉም የሰርግ ቤት ኮክቴል አጃቢነትን መቋመጥ መብት ነው። ግን ማሰብ ብቻ!

ኳስ ሜዳ ዙሪያ ቢቸበቸቡስ ቀላል ነው እንዴ? …. “እስኪ ከሽንብራው! ….ከሱፉ ጨምሪ እንጂ። …..ኤዲያ አንቺ ልጅ እጅሽ አ ይደለም የቆላው።…. ይሄማ ቤት አልተቆላም! የገበያ ነው።…” ቢባልለት!….. የገበያው ዱር ይቆላ ይመስል። የገበያ ሲሆን እግር ይቆላው ይመስል። ….ዝም ብለው ሲቀናጡ! አቅም ማሳየት! — የመግዛት አቅም። የመክፈል አቅም። — ገንዘብ የመክፈል?! ሁለት ቦታ የመክፈል?! ….የማዘዝ አባዜ። የመተቸት ፍቅር። የእልቅና ታናሹ….

እንዲህ ሲሆን ግን ህይወት ቆሎዋም ደስ ይላታል። ሰርክ በመታመስ ላይ እንዳለ አካሏን ታገላብጣለች። ዳሌዋን ሸሽጋ ሽንጧን ታተራምሳለች።…..የህይወት ሂልቶፕስ የት እንደሆነ ችለው ሲወጡ ብቻ ነው የሚታየው።…. ባላዩዋት ቁጥር ደግሞ ስታሳሳ! ሂልቶፕሷን እያቁለጨለጨች ኗሪዋን ማሴሰን ነው። እየተማረሩባት ብዙ የምታስመኝ። አልቆረጠም ብላ ጥርስ እየፈተነች ብዙ የምትፈለግ። ጥርስ ገብታ እያመመች የምትናፈቅ። ለዝዛም፣ ፈዝዛም፣ አደንዝዛም፣ አስተክዛም….

“ሂልቶፕሴን ያያችሁ?
– አላየንም….
ኗሪዎች እባካችሁ…”

ህይወት ቆሎ…. እንደ ዱቤ ቆሎ…. በዱቤ የሚኖሯት…. በዱቤ ገዝተው በዱቤ የሚበሏት…. የተኮናተሯት ዓይነት! በብዙ ጨው ተለውሳ ውሀ የምታስጠማ። ከዚያ ብዙ የምታስጠጣ። መጠጥ የምታሻሽጥ። የምታሳክር። ….ህይወት ቆሎ። ጨው የበዛባት ቆሎ።…..“ማን ነሽ… ትንሽ አፌ ላይ አንቀዋልዬው የምመልስልሽ ቆሎ ካለሽ አውሺኝ። እንግዳ መጣብን የእኛው ቆሎ እስኪቆላ ድረስ….” የሚባልላት።

“ምነው እቴ? አይሟሟ!….ምነው ሰሰተች?…. ይዋጥባት ይመስል።…..” ተብሎ የሚገበዙባት….. እርሷን እየቆረጠሙ፣ “ባዶ ቤት በክረምት”ን የሚያንጎራጉሩባት። እየፈጯት በትዝታ ነጉደው መንገዱን የሚፈጩባት። ይገርማል! ….ከቆሎ ጋር ሆነው “ባዶ ቤት” ይባልባታል።….. ቆሎ ይዘው ቆሎ መመኘት ቅንጦት ነው። ሙቅ እንደማላመጥ ያለ ቅንጦት፤…አሻሮ ይዞ ከቆሎ መጠጋት ግን ከዚያም ይብሳል። — ሰገብጋባ ቅንጦት!

…. ያሻው ደግሞ ኑሮውን ሊደጉምባት በእንቅብ ሞልቶ የሚቸረችራት ቆሎ። -ህይወት፤

ስንዴ ቆሎ፣….
አጃ ቆሎ፣….. ቆሎ ቆሎ
ያቺን ትተህ ይችን ቶሎ!

ተብሎ በልጅ ኩልትፍትፍ አንደበት የሚዜምላት!

ጎረምሳ በእንካ ሰላምታ የሚረታባት! ረትቶ “እንካ ቆሎ” የሚባልበት….የሚሸለምበት… – የቆሎ ሽልማት! ደስ ሲል!!

“እንካ ሰላምታ
– በምንታ
በቆሎ…
– ምናለ በቆሎ?
ነይ ልቃምሽ ቶሎ”

…. እርሱ ጠይቆ፣ ልቃምሽ ብሏት ማን ቆሎ ችላ ልትቀር? ትሸለመዋለች! በሽልማት መልክ ላላማጯ ትበረከታለች!!

…. ጠጅ ቤት፣ መንገድ ዳር፣ መጠጥ ቤት፣….የምትንከራተት። — ቆርጣሚ ፍለጋ። ገዢ ፍለጋ። አሳዳሪ ፍለጋ። – አሳዳሪ ሆድ። ቆርጣሚ ጥርስ።…….. ቆርጣሚዎቿም ይፈልጓታል። ያለችበት መጥተው ይገዟታል። ዓይናቸውን እያንቀዋለሉ…. እያንከባለሉ…. እርሷን ቆርጥመው “ጠማኝ” ሊሉ። ሰበበኞች…. ጠማኝ ብለው ጋኑን ሊገለብጡ። ሲጠጡ ደግሞ ይናፍቋታል። ታጫውታለች። ታስቆዝማለች። እያሉ……..ከዚያም ፍለጋ መውጣት….

ዓይኗ ቆሎ፣ ጥርሷ ቆሎ፣ የወለዱ እንደሆን፣
ታመጣለች አማች ብረት መዝጊያ የሚሆን…

ይሉላታል በዜማ! ለእነሱ ኤልያስ ተባባል ኮልታፋ ነው። ኮልታፋ ስለሆነ… “ቆሎ” ለማለት ነው “ኮሎ” ያለው። በቃ — ካሉ አሉ ነው። – ህይወት ገብሷ አስክራቸዋለቻ!

ህይወት ቆሎዋ ጢንቢራቸውን ታዞረዋለች!….ታባክናቸዋለች። ሲሻት ደግሞ ትቆላቸዋለች። እንደራሷ አድርጋ እርር…. እርሷን እንደቆላት ቁልት ታደርጋቸዋለች። በምድር ምጣድነት በኑሮ መቁያነት ታምሳቸዋለች። ታገላብጣቸዋለች። ቢያርሩም ለአመል ነው። በዪ አያጡም። ጨው ስታበዛባቸው ደግሞ ተከታይ ውሀ ይቀዳላቸዋል።… የማታ ማታ ግን የአፈር ሲሳይ ናቸው።…. እሳት እራት ወደ እሳት፣ የተቆሉት ወደ አፈር፣ ያልተቆሉት ወደ እሳት….

….ግብአተ መሬት….

ወይኔ ቆሎ…. ቆሎ ቆሎ.
አልሰማሁም ነበር አልሰማሁም ነበር፤
ለእኔ ያርገው ቆልዬ ለእኔ ያርገው።
ይሄ ጅብ መሬት ሊቆረጥምሽ….

.
.
“እምቢ…. እምቢ ለቆሎ…. እምቢ ለጥርሴ ጌታ….በወንፊት ሞልታ፣ በሰፌድ መጥታ፣….. አጫውታ አማሽታ….. እምቢ ቆሎ! ተይ አታድርጊኝ ከርታታ….”

ዥዋ – ዥዌ —
— ከሙሾ ወደ ቀረርቶ…. በቃ ህይወት ስትቆላ እንዲህ ነው!

እስከዚያው ድረስ፣ ግብአተመሬቷ እስኪፈፀም ግን ትሰፈራለች። ትኩስ ትኩሱን ያዞሯታል። በእንቅብ ሞልተው ይሰፍሯታል። ልጅ ያለው ልጁን አስይዞ…. የሌለው ራሱ ይዟት…. ይሰፍራታል። በየጠጅ ቤቱ። በየቡና ቤቱ…. ጉልበተኛ መጥቶ እስኪበትናት። የጠገበ መጥቶ እንቅቧን አንገጫግጮ እስከሚደፋት።…. ሰካራም በጥፊ እስኪወለውላት።

… ከተደፋች እንቅቡ ይቀራል። እንቅብ ካለ ቆሎ፣ ቆሎ ካለ እንቅብ ምንም ናቸው። እንቅብና ቆሎ ከሌሏት አዟሪዋስ ምን ትሰራለች? እነሱ ኖረው እርሷ ባትኖርስ?…. ከተደፋች መስፈሪያውም ተሽቀንጥሮ የጎማ ሲሳይ! ኦ መሰፈር ከንቱ። ኦ መስፈር ብላሽ።…. ሰዎች እንደመልቀም ሆነው፣ ከንፈር እየመጠጡ ክንብል ክንብል፣ ድፍት፣ ክብልል፣ ክብብ… ከዚያ ያሟታል። ፊት ለፊቷ።… ‘ኧረ ባክሽ ይሄን ልትሸጭው?!’ ብሩን እንደሚሰጥ እየተግደረደሩ…
.
.
.
ውይ ያቿት…. መጣች እንቅቡን ይዛ! ማነሽ ባለቆሎ…?! ውይ እብድ መጣላት! ስትዞርም እንቅቧን በካልቾ ሲልባትም እኩል ሆነ። ውይይ…

ዝ – ር – ግ – ፍ—-
—-እ – ር – ፍ!

ከመታፈሪያ፣ ከመሰፈሪያ እንቅቡ ወጥቶ እንግዳ አስፓልት ላይ….

ብ ¬
ት ¬ ን –
ት ¬ ን ¬ ት ¬ ን…
– ት ¬ ን ¬ ት ¬ ን -!

¬ – , ..
¬ _ – – =
ብ ¬ት ት ¬ ን ¬ ት ¬ ን — ሜዳ ላይ!!

ህይወት ቆሎ ¬__
¬ – , ..
¬ _ –
¬ _ – – =

/ዮሐንስ ሞላ/

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s