ፊልሞቻችን የገሀዱ ዓለም ኑሯችን ማሟያዎች (complemnts)?

Tragedy life vs Comedy records imagesCAU3G9AK

የምንኖረው ሌላ የሚሰራልን ፊልም ሌላ።…. ገሀዱ ዓለም ሌላ የሬድዮና የቴሌቪዥኑ ዓለም ሌላ።…. ፎቶው ሌላ የምሩ ገፅ ሌላ። ወሬው ፀአዳ፣ ኑሮው ማድያታም።… በዚህ አላግባብ አንጀት በሚበላ (tragedy) ኑሮአችን ላይ ማረፊያ እንዲሆኑን የሚሰሩልን አስቂኝ (comedy) ፊልሞች ብዛት ያሳቅቃል። የቴሌቪዥን ድራማውም እንደዛው ነው።

ከቀልድ ነፃ በሆነ የድራማ ዘውግ ላይም …ለድራማው ምልአት ምንም ጥቅም ሳይኖራቸው… እንዲያስቅ ብቻ ብቅ ብለው የሚጠፉ ገፀ ባህርያት ይኖራሉ። ቶክ ሾው ተብዬዎቹም በብዛት ማሳቅ ላይ ነው የሚያጠነጥኑት። ሙዚቃውም ቢሆን(በአብዛኛው)…ጠነከረ፣ ጆሮ ገባ ሲባል… ያው መከረኛ የፆታዊ ፍቅርን (romance) ዘውግ ሳይለቅ ደርሶ ተመላሽ ነው። …ከጊዜ ወዲህ ደግሞ ለወረት – አባይና ራዕይም ተጨምረውበት ይፈራረቃሉ።

ግን ምንድን ነው? በተለይ የፊልሞቻችን ነገር? በርግጥ ማሳሳቅ ክፋት የለውም። ክፋት የለውም ሳይሆን አግባብም ነው። ሆኖም ግን እያሳሳቁ ማረሳሳት እዳው ከባድ ነው። ጥቅምና ጉዳቱን ሳያሰላ…መቼቱ ዛሬ/እዚሁ ይሆንና ለማንም አይበጅም፤ ስንት ጉዳይ በሞላበት አገር ውስጥ ነገር ዓለሙ የሚወጥነው እንዴት እንደሚያስቅ ሲሆን ላስተዋለው ያሳቅቃል።

መደበኛ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ቧልት ይበዛቸዋል። የበዓል ዝግጅቶች ደግሞ ከመደበኛውም ይብሳሉ። እንደምሳሌ: ባለፈው የአባይ ግድብን 2ኛ ዓመት ፅንሰት ለማክበር የተደረገውና በኢቲቪ የተላለፈው ፕሮግራም ለንቁ አሸማቃቂ ነበር።… ሲሆን ሲሆን ብዙ ሳይንሳዊ ጥናቶችና የምርምር ፅሁፎች ቀርበው ሰፊ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ ቢሰራ ጥቅሙ የሁለት እዮሽ በነበረ። ግን ከማዘናጋት ጎን ለጎን ግቡ ማሳቅ ነውና እንዲያ አልሆነም። ይህን በተመለከተ ዓለማየሁ ገላጋይ በልዕልና (ቁጥር5 መጋቢት 2005)ጋዜጣ ላይ…

….ሲምፖዝየም፣ ኮንፍራንስ….ቢሆን እያንዳንዱን እሳቤ ተንትኖና ተርጉሞ ያልተፈለገ ውጤት የሚያመጣው ብዙ ነው። ስለዚህ እንቁላል በማንኪያ ይዞ መሮጥ፣ ገመድ መጓተትና የፌዝ እግር ኳስ መጋጠም የማይተረጎም፣ አስር ጊዜ ቢወቅጡት ያው እንቦጭ የሆነ ድርጊያ ነው። በዓል ይደምቃል፤ መንግሥት ከስጋት ይድናል። የጥንቶቹ መኳንንቶች የደብተራው ቅኔ ሽሙጥም ሊኖርበት ስለሚችል ሲደግሱ እንዲህ ይሉ ነበር አሉ፤ “ከሺህ ደብተራ የአንድ ቄስ ዳንኪራ” በዚህ ዘመንም የተቀዳው ይሄ አባባል ነው። በዚህ ምሁር ከመቆላመጥ፣ የአንድ አርቲስት እንቁላል ይዞ መሮጥ።….

ብሎ ነበር ነገሩ የታዘበው። በቃ እኛ አገር እንዲህ ነው። በቴሌቪዥንና በሲኒማ ማሳቅ፣ ማሳቅ፣ ማሳቅ….አሁንም ማሳቅ፤ ከዚያ ደግሞ በኑሮ ማሳቀቅ። laughing-menየተመልካቹ ፍላጎትም የለመደው ላይ ያጠነጥናል። ድራማ ፊልም ቢሰራ ያመዋል። ጠንከር ያለ ጉዳይ ተይዞ ቢዋዛለት ይሰለቸዋል። እንቅልፉ  ይመጣል። በመሆኑም ወደ ሲኒማ ቤቱ ዝር አይልም። የሲኒማ ቤቶችን ወረፋ ለማጨናነቅና የተመልካች ብዛት ሰንጠረዡን ለመቆጣጠር ፊልሙ ማሳቅ አለበት። ቁም ነገር፣ ጠንካራ ሀሳብ፣ ቆንጆ የድራማ ፅሁፍ፣ ገራሚ ዝግጅት፣ ጉድ ያስባለ ትወና… ካላሳቁ ምንም ቦታ የላቸውም።

ሰው የጎደለውን ነገር ፍለጋ ሲኒማ ቤት ነዋ የሚሄደው። ከለቅሶና ከብሶቱ ለማረፍ ሳቅ ያስፈልገዋል። ለያውም ከፈጠራ የፀዳ የጅል ማሳቅ። እንዲያ እንዲሆን ነውና የተለማመደው ትንሽ በሰል ያለ ኮሜዲ ሲሰራለት እንኳን ራሱን ያመዋል። ለመጀመሪያ ጊዜ ከንፈሯን እንደተሳመች ኮረዳ ጭው ጭር ይልበታል። ሰማይና ምድሩ ተደበላልቀውበት ስለቱርጁማን ግራ ቀኙን ያማትራል። ‘ምነው እግሬን በሰበረው’ ካላለም…

የደሀ ጉዳይ – የራሱ ጉዳይ!

አገራችን ላይ የደሀና የሀብታም ነዋሪው ቁጥር የትና የትነት በግልፅ እንደሚታወቀው …(ከፆም ከማደር — እስከ — ለሻይ ዱባይ እስከመሄድ ድረስ…) ቢሆንም… ፊልሞቻችን በብዛት የሚያጠነጥኑት የሀብታም ቤት ኑሮ ላይ ነው። ለሰፊው ደሀ ህዝብ የሀብታምን ኑሮ ከምናብ ባለፈ በፊልም ምስል ያሳዩታል። በፊልምም፣ በዘፈን ክሊፕ ቀረፃም ወቅት የሚታዩት ቤቶችና ሁኔታዎች የብዙሃኑን አኗኗር የሚያሳዩ ሳይሆኑ የሀብታሙን ቤት የሚተርኩ ናቸው። በስመ ገፅታ ግንባታና ዓይንን ምረካ ጥበብ ወዲያ ተሽቀንጥራለች። የደሀው ጉዳይ ወዲያ ተዘንግቷል።

ደሀ issue የሌለው ይመስል ቀረፃዎች ሁሉ ሀብታም ሀብታም ይሸታሉ።…. ስለሀብት ይወራል። ስለሚንቀሳቀሱ ሚሊዮን ብሮች ይተረካል። ሰፊውን ህዝብ በትንሿ የቲቪ ስክሪን ያንቆላልጩታል። ጥጋበኞች የሚሟዘዙበትን ፊልም ሆዱን እያከከ ተመልክቶ ካንገት በላይ ይዝናናል። ምን ያድርግ እንዲያ ነዋ የተበጀው። ‘ደሀ ኑሮውን በእውኑ ይኖረዋልና ምን ቀርፆ ማሳየት ያሻል?’ በሚል ፈሊጥ ይመስላል…. ‘የደሀ ጉዳይ – የራሱ ጉዳይ’ ተብሎ ተትቷል። እርሱም ተስማምቶት ነው መሰል በኑው የጎደለበትን በፊልም ይሞላውና ከነችግርና ጥያቄው ተጠቅልሎ ይተኛል።

ይህቺ ናት አገሬ!

ማስታወሻ

በደረቅ ትርጉሙ complement ማለት ማሟያ፣ ማረጋጊያ፣ ማጣጣሚያ፣ ማስማሚያ እንደማለት ነው። ብዙ ጊዜ የስነምጣኔ ሀብት(economics) ትንታኔ ላይ ያገለግላል። ለምሳሌ ወጥ የእንጀራ complemet ነው። ወጡ እስኪመጣለት እንጀራው እንደጎዶሎ ነው። ነዳጅ የመኪና complement  ነው። የcomplement ሸቀጦች (goods) ባህርይ እርስበርስ መፈላለጋቸው ነውና የአንዱ ዋጋ መዋዠቅ ሁኔታ ሌላኛውም ላይ በቀጥታ ተፅህኖ ያሳድራል።

የግድ ስለሚፈላለጉ (አንዱ ላንዱ ሙላት ስለሆነ) የአንዱ ዋጋ መጨመር የሌላውን ዋጋ መጨመር ይወስነዋል። ልክ እንደዚያው የአንዱ ዋጋ መቀነስ ደግሞ የሌላውን ዋጋ መቀነስ ይወስነዋል። በዚህ መሰረት ከሄድንና ፊልሞቻችንን የገአዱ ዓለም ኑሮ ማሟያዎች ካልናቸው የኑሮው መዝቀጥና አሳዛኝነት ሁኔታ…. የፊልሞቹን የማሳቅ አቅምና ሁኔታ በቀጥታ ይወስነዋል ማለት ነው። ይሄ ደግሞ ያለውንና የሚመጣውን ገግልፅ ያሳየናል።

— መሰለኝ!