የእኛ ሰው በጎዳና…

ጊዜው እንዴት ይሮጣል?…የዛሬ ዓመት ልክ በዚህ ሰዓት በመጠነኛ አደጋ የተነሳ ሆስፒታል ነበርኩኝ። እንዲህ ነበር….
 
በእለቱ The Good Ethiopian (ደጉ ኢትዮጵያዊ) የተባለ ቡድን ህይወቷን በአሳዛኝ ሁኔታ በቤይሩት ላጣችው ወ/ሮ ዓለም ደቻሳ ልጆች የሚሆን ገቢ ማሰባሰቢያ የስነፅሁፍና የሙዚቃ ፕሮግራም የሚካሄድበት ነበር። ፕሮግራሙ የታሰበውና የተዘጋጀው እዚሁ በፌስቡክ በምንተዋወቅ አስር የምንጠጋ ሰዎች ነበር።… በመጀመሪያ የዓለምን ሞት ተከትሎ (በቤሩት የኢትዮጵያ ቆንፅላ ፅ/ቤቱ በር ላይ ተጎትታ በመኪና መወሰዷን በማሰብ)የነበረው ሀዘንና ቁጭት ብዙ ሰው ዘንድ ነበር። ብዙ ተባለ። ብዙ ተገጠመ። ብዙ ስድ ፅሁፍ ተከተበ። ሁሉም ኡኡ አለ….
 
እርሱም ሳይበቃ Good Ethiopian (ደጉ ኢትዮጵያዊ)የተባለው ቡድን “ሁልጊዜ ከምናዝን የበኩላችንን እናድርግ” በሚል ዋና ዓላማ እዚሁ ፌስቡክ ላይ ተቋቋመ። የፌስቡክ ቡድኑ መስራቾች፥ በተመሳሳይ ጉዳዮች በመግባባት እናወራለን ብለው ያሰቧቸውን ሰዎች መጀመሪያ በinbox መልዕክት፣… ከዚያም በስልክ፣…ከዚያም በሌላ ስልክ… ስለጉዳዩ በዝርዝር አጫውተው/ጀንጅነው…. የሆነ ቅዳሜ ላይ በአካል ተገናኝተን ቡና እንድንጠጣ ሆነ።
 
የተወሰንነው (እኔን የወሰወሰኝን ጨምሮ) ከዚያ በፊትም እየተገናኘን ቡና በመጠጣት የተለያዩ ሀሳቦች ላይ እንወያይ ስለነበረ፣ በበኩሌ የቡና ቀጠሮው እንደተለመደው ለወዳጅነት መስሎኝ ነበረ። እንደተገናኘን ግን (ቀድሞ አጀንዳ ተይዞ ኖሮ) እዚያው ቡና ላይ አንዱ ሲነሳ አንዱ ሲጣል ተቆይቶ…. “ለምን የግሩፑን ሥራ…. በአጭር ጊዜ ውስጥ ለዓለም ደቻሳ ገቢ በማሰባሰብ ስራችንን አንጀምርም?” ምናምን የሚል ሀሳብ ቀረበ…
 
‘ይሁን! አይሁን!’ በሚል ትንሽ ተሟገትን። እኔ ጊዜውንም ከግምት በማስገባት፣ እርስበርስም በጥልቀት ስለማንተዋወቅም ጭምር… መግባባትና እርስበርስ ያለንን ጉልበትና ነገሮችን የመሸከም አቅም ቀድሞ መተዋወቅ ይሻላል በሚል፥ እንደዚያ ያለ የአጭር ጊዜ ፕሮግራም መታሰቡን አጥብቀው ከሚቃወሙ ሰዎች አንዱ ነበርኩኝ። ለብዙዎች ግን ሁሉም ነገር ቀላል ይመስል ነበር። በብዙኀን አባላት ዘንድ ከፍተኛ ጉጉትና የመለወጥ ስሜት (ambition) ነበር, thought I couldn’t be so. Honestly, what I can’t be at all is, ambitious!!!
 
የበለጠው ስሜት መራንና እንቅስቃሴዎችን ለመጀመር ንዑስ ኮሚቴዎችን አዋቅረን ስራ ተከፋፍለን ተለያየን። አንተ ይህን አድርግ! አንቺ ይህን…. ተብሎ ሲደለደል እኔም በእለቱ ፕሮግራሙ ላይ የሚቀርቡ ስራዎችን በተመለከተ የቤት ስራ ወሰድኩኝ። ከዚያም ገጣሚዎችን፣ መድረክ መሪ፣ የሙዚቃ ባለሞያ…. የማናገርና ለፕሮግራሙ የማግባባት ስራው በዋናነት የእኔ ሀላፊነት ነበር።
 
በግሌ እንቅስቃሴዬ ጥሩ ሆኖ ቀርቤ ከጠየቅኋቸው ሰዎች በቀፋፊ መልስ ከመለሰኝ (ያሳፈረኝ መስሎት ካፈርሁበት) አንድ ግለሰብ በቀር ሁሉም ከአንድ አንድ ነገሩን ተስማምተውበት ነበር። እንደዚያ ሆኖ…. ስንጨቃጨቅ፣ ስንነታረክ፣ ስንስማማ፣ እንዲህ ይሁን፥ እንዲያ ስንል… ታልፎ የፕሮግራሙ ቀን ደረሰ።
 
ያን ቀን ከእንቅልፌ ማልጄ ነበር የተነሳሁት። ለፕሮግራሙ መሳካት መፈፀም የነበሩብኝ ብዙ ስራዎች ነበሩ። የጽሁፍ ስራ የሚያቀርቡት ገጣሚዎች ጋር መደወልና ማስታወስ፣ የተወሰኑት ጋርም በአካል መገናኘት፣ ባንክ መሄድና ከውጭ ካሉ ደጋጎች የተላኩ ብሮችን ማውጣት፣ ቲኬት ለመሸጥ ወዳጆች ጋር መሄድ፣ በዱቤ የሸጥኳቸውን ብሮች ለማምጣት…. ከዚያ በኋላ ደግሞ ቀን 7 ሰዓት ላይ ሁላችንም እንገናኝ ተብሎ ነበርና ወዳጆቼ ጋር ላለመጉደል። ሁሉ ነገር ትናንት እንደነበር ሁሉ አይረሳኝም። (በአጠቃላይ ነገሩ ላይ ወደፊት…የማጫውታችሁ ነገር ይኖረኝ ይኖር ይሆናል።)
 
….በሥራ ብዛት የተነሳ ቁርሴን ሳልበላ ነበር የወጣሁት። በፋሲካ በዓል ማግስት (ሀሙስ) ከቤት ቁርስ ሳይበሉ መውጣት ብዙም ባይለመድም (ለራስም ለቤተሰብም ደስ ባይልም) ወጣሁ። — አንድም ስራዎቹን ለመፈፀም ጊዜ ስለምቆጥብ፣ ሌላም ስራ እያለብኝ ብጎርስም ምግብ ስለማይወርድልኝ አንደኛዬን ጨራርሼ…ብዬ ነበር። ቁርስ አለመብላቴ አይደለም የሚገርመው…. ምሳም አልበላሁም።
 
አመሻሹ ላይ በዝግጅት ጉድለት ምክንያት sound system ስላልተስተካከለ ሙኒት እና ዮርግ ሸበሌ ፓርክ ውስጥ ቁጭ ብለው ስለነበር ከእነርሱ ጋር ቁጭ ብዬ መጫወት ጀመርን። በሙኒት ግፊት አንድ ሚሪንዳ ጠጣሁ። ከዚያም ሜሮን ጌትነትን ለማግኘት ሸበሌ ቴራሱ ላይ ወጣሁ። የሚበላ አዝዛ ስለነበር፥ በብዙ ጭቅጭቅ ሶስት ጉርሻ አጎረሰችኝ። ቁርስም፣ ምሳም እራቴም ሆነ። — አንድ ለቁርስ፣ አንድ ለምሳ፣ አንድ ለራት በሉት!
 
ሰዓቱ ደርሶ ከነድክመቱ ጥሩ የሚባል ፕሮግራም አሳልፈን ቤት ቤታችን ተበተንን። እኔ ሰፈር ስደርስ 3 ሰዓት ገደማ ነበር። ቤት ለመድረስ የአንድ የ15 ደቂቃ መንገድ ሲቀረኝ የቤተሰብ ስልክ ተደወለልኝና አንስቼ ማውራት ጀመርኩኝ። አስፓልት ላይ ነው። ሰውና መኪና ለጉድ በሚመላለስበት አስፓልት። ትንሽ እንደሄድኩ…. ከኋላዬ የጎረምሳ እጅ ስልኩን ለመንጠቅ ያዘኝ። ስልኩን አጥብቄ ይዤው ኖሮ፣ ወይ ደግሞ እርሱ አጠንክሮ መንጠቅ ስላልቻለ… እንደነጠቀኝ አልወሰደውም ነበር። እኔም ዞርኩ።
 
እንደዞርኩ ግን ፊቴ ላይ ያረፈው የጎረምሳው ጩቤ ነበር። ከዓይኔ ከፍ ብሎ መሀል ላይ ወግቶኝ ስልኩን አስለቀቀኝ። አልሮጠም። ቀብረር ብሎ እየተሳደበ ሄደ። ከተቃራኒው የአስፓልቱ ጎን ላይ ጓደኞቹ እየጠበቁት ኖሮ ተቀላቀላቸው። በእጃቸው የያዙትን ገጀራ ሳይ ደነግጬ ዝም አልኩኝ።ማለፍም አለ። እርሱ ቢቀር ደግሞ ኪሴ ውስጥ የነበረ ጠቀም ያለ ብር (7 ሺህ የሚጠጋ) የነሱ ሲሳይ ሊሆንም ይችላል።
 
እናም ዝም! ደም እየወረደ ፀባይ ማሳመር!…በርግጥ መንገዱ ጭር አላለም ነበር። ብዙ ሰው ወደላይ ወደታች ይመላለስ ነበር። ልክ እኔን ሲወጋኝና እየተሳደበ ሲሄድ ደግሞ ቆመው ማየትም ጀመሩ። ወሬ ማየት ተክኖት የለ ህዝቤ?! ሲያዩኝ ይበልጥ በሸቅሁኝ። ብዙ ነገር አብራርቼ እንዲረዱኝ ተማፀንኩ፥ ወፍ የለም!
 
ደሜ እየተንዠቀዠቀ ብጮህ ብጣራ ወይ የሚለኝ አጣሁ። ከሶፍት አቅም የሚሰጠኝ አጣሁ። “አይዞህ” ማለትም ብርቅ ሆነ። መነፅሬ ወድቃ እንኳን እርሷን ፈልጎ የሚያቀብለኝ አጣሁ… (i need to wear a glass, to get my lost glass. Hehehe…) ዓይኔም በደም ተሸፍኖ ስለነበር መነፅሬን በዳበሳ አገኘሁት። – ለዓይን አምላክ አለው እንዲሉ አልተሰበረችም ነበር። እርሷን ይዤ ለእርዳታ ተጣራሁ። እንደሞኝ ለመንኩ! እንደሞኝ ሶፍት ለመንኩ! እንደ ልጅ “አይዞህ” መባል አማረኝ! እንደ ተራ ትኩረት ማግኘት ፈለግሁ! ….አሁንም ወፍ የለም!
 
ጥላዬን ፈራሁት።….ሚሰማኝ አልነበረም። ደሜ እየተንዠቀዠቀ ስልክ ወደማገኝበት ሱቅ ሄድኩኝ። ቅርብ ያሉ ሱቆች “አናስደውልም” አሉኝ። “ኧረ በራስህም ቢሆን” ብል ወይ ፍንክች! ይገርማል!…. “ምን ሆነህ ነው?” የሚልም የለ! ….ከዚያ በላቀ ግን፥ አገልግሎትን በመከልከል ወንጀልን መንከባከብ። ወንጀለኞችን መተባበር። በጣም አስጠላኝ። ….መጀመሪያ ህልም መሰለኝ። ደሙን ሳይ ስዳስስ፣ ሲቀዘቅዘኝ፣ ቁስሉ ሲሰማኝ…. ህልም እንዳልሆነ አወቅሁኝ። ኢትዮጵያዊነቴ አስጠላኝ። ሰውነቴ ደበረኝ። ናቅሁት። አማርኛ መናገር ቀፈፈኝ! “የሰው ያለህ” ብዬ የተጣራሁበት ድምፅ አንድ ሰው እንኳን ካላቀረበልኝ ምን ሊሰራልኝ? የምር ሽክክ አለኝ!
 
እዚያ — ዓለም ደቻሳ የተባለች ምስኪን፥ ቆንፅላው ፅ/ቤት በር ላይ ስትጎተት ዝም አሉ። እዚህ — ዮሐንስ ሞላ የተባለ ምስኪን ወጣት ለዓለም ደቻሳ ገቢ እሰበስብ ብሎ ባመሸበት፥ በራቸው ላይ (ያውም ዋና የመኪና መንገድ ላይ) ሲወጋና ሲቀማ ዝም አሉ። –እሳት ካየው ምን ለየው? እንዲሉ ሁለቱም ያው ናቸው።
 
ለራሳቸው ፈርተው ነው ይባልና ልጆቹን ለመያዝ መሞከር ይቅር… ግን ሶፍትና ውሀ መስጠት ምንም አይጎዳም ነበር። ድብልቅልቅ ባለ ስሜት ውስጥ ሆኜ፣ ማንንም እንዳልጠይቅ ተስፋ ቆርጬ ስሄድ፣ አንድ መልከመልካም ወጣት ሰው ምን ሆኜ እንደሆነ ጠየቀኝ። ነገርኩት። ሁሉንም ነገርኩት። ባለሱቆች ስልክ እምቢ እንዳሉኝም ነገርኩት። ሁኔታዬን አይቶ በጣም አዘነ።
 
….ከማዘኑ ብዛት ሳያስተውል ደሜን በእጁ ነክቶ አጠበኝ። ብከለክለውም አሻፈረኝ አለ…. “ባልረዳህ ፀፀቱ ይገለኝ የለ? አታስብ ወንድሜ!” አለኝ። እንደልጅ ጉንጬን እያሻሸ አባበለኝ። ስልኩን ሰጥቶኝ ወንድሜ ጋር አስደወለኝ። አንዠቴን በላው። መቼስ እግዜር ደግ ነው።… በአንዱ ልባችን ሲሰበር ባንዱ ይጠግናል። አሁን ደግሞ ከዚያም ወንድሜ ወዲያው ደርሶ ሆስፒታል ሄደን ተሰፋ።
 
— ታሪክን የኋሊት?! እንዲህም አይደል?
እግዚአብሔር ሌላ እድል ሰጥቶኝ “የዛሬ ዓመት” እያልሁ ታሪክ እዘክር ዘንድ እዚህ አድርሶኛልና ክብሩ ይስፋ።
 
Moral of the memo:
 
ይሄ በየመንገዱ ቅሚያና ውጊያ በጣም አሳሳቢ ነገር ሆኗል። እኔ ከማውቃቸው የቅርብ ወዳጆቼ ውስጥ ብቻ ከእኔ በኋላ የተከሰቱ 5 ወይም 6 አደጋዎችን አውቃለሁ። ምናልባት በኮብልስቶን ከተደራጁት ጋር በቅሚያና ዝርፊያ የተደራጁም ይኖሩ ይሆን? ለማንኛውም ግን ራስን መጠበቅና መጠንቀቅ መልካም ነው። ሰዎችንም እንኳን እርዳታ ጠይቀው፥ መደናበራቸውን አይተን የምንረዳ ያድርገን።
 
Viva Jo! 😉