.
.
በእኔ ልምድና መረዳት፥… የራስን ስሜት በመንከባከብ ሰበብ፥ የጻፏቸውን ግጥሞች፥ የሆነ ዓይነት ደረጃ እንዲኖራቸው ተጨንቆና፣ ከሰዎች ጋር ተማክሮ፥ በመጽሐፍ መሰብሰቡ… በተለይ፥ ከመጻፉ ጋር ሲነፃፀር እጅግ አድካሚ ነው።
ምንም ሆኑ ምን፥ የገጣሚው እፎይታ ግጥሞቹን ሲጽፋቸውና ውስጡ የሚመላለሰውን ሐሳብ ችሎ ወረቀት ላይ አስፍሮ ሲገላገለው ነው። — መሰለኝ። ከዚያ በኋላ ደግሞ፥ የጻፋቸውን ግጥሞች ከማኅበረሰቡ ጋር ለመደባለቅ በማሰብ ሌላ መንገድ ይጀምርና፥ በጊዜ ሲዘልቀው ዳግም ‘እፎይ’ ይላል። አሁን ለእኔ እንደዚያ ሆኖልኛል።
እውነት ነው… ደረጃቸው ምንም ሆነ ምን፥ ግጥሞቹን ስጽፍ ከነበረኝ ድካም ይልቅ… በመጽሐፍ መልክ እንዲሰበሰቡ ለመወሰን ሳንገራግር፣‘ይሁኑ’ ያልኋቸውን ስመርጥ፣ መመጠን አለመመጠናቸውን ለመረዳት ስመረምር፣ ከወዳጆች ጋር ስማከርና፣ በመጽሐፍ እንዲሆኑ ሳዘጋጅ የበለጠውን ደክሜያለሁ።
ግጥሞቹን ስጽፋቸው ከፈጀሁት ጊዜም በላይ፥ ስለ መጽሐፍ ሳስብና ይህንን መጽሐፍ ሳዘጋጅ ፈጅቼያለሁ። “ምነው ማሳተም ባልኖረና ባልጀመርሁት!” ያልሁበት ጊዜማ ብዛቱ!… ከአድካሚነቱ አንጻርም መጽሐፍ የማሳተም ሐሳቡን ሽሽት “ኧረ ምነው መጻፍ ባልወደድሁ ኖሮ!” አለማለቴም አንድ ነገር ነው።… ያም ሆነ ይህ ግን፥ ሁሉም ዘርፉንና አንባቢን ከማክበር የመጣ ነውና፥ ሲጀመር እንዳልነበረው ሲታለፍ ደስ ይላል።
የሆነው ሆኖ… በወዳጆች ግፊትና፣ የግጥም ሥራዎቹ ‘ለዘርፉ አስተዋፅኦ ቢያደርጉ’ በሚል የራስ ፍላጎት የተነሳ ይህን መጽሐፍ ለማዘጋጀት ከወሰንሁኝ (ከራሴ ጋር ከተስማማሁኝ) ከአንድ ዓመት በላይ ሆኖኝ ነበር።ከዚያም፥ አንዱን ሳነሳ ስጥል፣ ስሰርዝ ስደልዝ፣ ስጨምር ስቀንስ፣ ‘እንደዚህ ይሁን እንደዚያ’ ስል፥… ዛሬ ላይ ደርሼ፥ “ይመጥናሉ” ያልኋቸውን ሰብስቤ “ይሆናል” ባልሁት አቀራረብ “የብርሃን ልክፍት”ን አዘጋጅቼአለሁ።
እውነቱን ለመናገር፥ መጽሐፉን ለማሳተም ወስኜ ዝግጅቱን ስጀምረው… “ከእኔ ይውጣልኝና ልገላገል”… “ዘወትር መጽሐፍ እንዳሳትም የሚገፋፉኝን ወዳጆቼን ላስደስትና ጥያቄያቸውን በትህትና ልመልስ”… “መጻፌ ካልቀረ፥ መጽሐፍ ቢኖረኝስ?”… ምናምን ከሚል ተራ ስሜትና ሞቅታ ሳይሆን፤ ለሥነ – ጽሁፍ ዘርፍ ሊሰጠው የሚገባውን ክብር ለመረዳትና ለመጠበቅ በመጣር ነበር።
ያም ሆነ ይህ ግን፥ ይህ የግጥም ስብስብ መጽሐፍ የመጀመሪያ ሙከራዬ እንደመሆኑ መጠን፥ በአንባቢዎች ገንቢ አስተያየት፤ እንዲሁም በተሻለ የንባብና የኑሮ ልምድ ቢታገዝ፥ ቀጣይ ሥራዬ የተሻለ እንደሚሆንና እንደሚዳብር አምናለሁ። ስለሆነም ግጥሞቹን አንብባችሁ ‘እንዲህ ቢሆን… እንዲያ ባይሆን…’ የምትሉት ማንኛውም አስተያየት ቢኖርና ብታደርሱኝ ለእኔም ለዘርፉም መልካም ነውና… አደራ።
ዮሐንስ ሞላ
2005 ዓ/ም
ለመግዛት (ለማዘዝ) ከታች ይጫኑ።
nice to see you having blog i hope you will benefit from this and i hope this blog will be top #100,000 with in 3 years. but if you consider writing in English
just keep it up