ሰርግና ሙዚቃው

“ሙዚቃ እያሰሙ ገደል ይከቱታል።” የምባል ዓይነት ነኝ። ከየትኛውም ዓይነት ሙዚቃ ጋር መንፈሴን ልክክ አድርጌ ሌላውን ነገርና አካባቢዬን መርሳት እችላለሁ። ልክ የብርሃን ልክፍት መፅሐፍ ላይ ገፅ 60 ላይ በ“ፍቅሬ ሙዚቃዬ” እንዳልነው ዓይነት መሆኑ ነው….

“ሀገር ቢደባለቅ፣ ቢዘነብ ቢባረቅ፣
ቢተኮስ ቢደለቅ፣ ቢነጠፍ ቢወደቅ፣
ቢበተን ቢሰፋ፣ ቢወረቅ ቢጨረቅ፣
ቢከፈት ቢገለጥ፣ ቢቀበር ቢደበቅ፣
ቢታረስ ቢዘራ፣ ቢታጨድ ቢወቃ፣
ቢታዘል ቢታቀፍ፣ ቢጎሸም ቢደቃ፣
ውድሽ መች ልሰማ?!”

/ዮሐንስ ሞላ – የብርሃን ልክፍት ከገፅ 60 ላይ የተቀነጨበ/

በዚያም የተነሳ ይመስላል፥…. በስምና በመደብ ዓይነት መተንተኑን ባልካንም፥ ራሴን ደስ በሚያሰኘኝና ደረቴን በራሴ ፊት በሚያስገለብጠኝ (በሚያስናፋኝ) ልክ ሙዚቃ እንደምረዳም አምናለሁ። ሄሄሄ…. “ሁን” ተብዬ ተማክሬ ባውቅ ኖሮ “ሙዚቀኛ” ነበር የምለውና የምሆነው። በርግጠኝነት “ይህን በሆንኩ ኖሮ” ብዬ በማስብበት የትኛውም ቅፅበትም “ሙዚቀኛ በሆንኩ ኖሮ” ማለቴ ቀዳሚውን ስፍራ ይይዝብኛል።…

ቢቀዳ ቢደፋ፣ ቢታረድ ቢበላ፣
ቢበጠር ቢነጠር፣ ቢሰጣ ቢቆላ፣
ቢሰባበር ባላ፣ ቢፈራርስ ገላ፣
ሕዝባ’ዳም ቢሸበር፣ ቢታመስ ከተማ፣
ሺህ ቢወድቅ ቢገደል፤ ቢቆስል ቢደማ፤
ሀገር ቢበረበር፣ ቢወረር ባድማ፤
ውድሽ መች ልሰማ?!”

/ዮሐንስ ሞላ – ላይ ከተቀነጨበው የቀጠለ/

አሁንም ቢሆን እንደ ኃይለኛ ህልም ውስጥ ገብቼ ምናምን ሳስብ …ራሴን የሆነ ጊዜ ላይ፣ የሆነ ቦታ ላይ፣ የሆነ ዓይነት ሙዚቃ ራሴን ችዬ ስጫወት አየውና ሳቅ ያፍነኛል፤ ደግሞ ጊታር ነው የምጫወተው… የምጫወተው ለህዝብ ይሁን ለራሴ እንደሆነ ሳልለይ ግን ህልሙ እልቅ ይልና ብንን እላለሁ። ስለሙዚቃ ሌላ ጊዜ እንጫወታለን፥ ዛሬ ግን ወደ አሰብኩት “የሰርግ ሙዚቃ” ወሬ ላሽ ልበል።

የሰርግ ሙዚቃ

ሰርግ አልወድም። የሰርግ ሙዚቃ ስሰማ ግን በሆነ ርቀት ልክ ከፍ እላለሁ።13792785-wedding-picture-bride-and-groom-in-love የሆነ ነገር መጥቶ ውርር ያደርገኝና ልቤን ያሳክከኛል። ወደ ሆነ የማላውቀው ቦታ ይወስደኝና ይመልሰኛል። ከዚያ ስመለስ ደግሞ ወደ ሆነ በትንሹ የምፈራው ቦታ ያደርሰኛል። የምፈራው ስለማላውቀው ነው። አብሮኝ የሚጓዘውን ሰው ምንነትና ከየትነት መንገር ስለማልችል ነው። ግን ያው ሲለመድ ይረሳል። ሙዚቃውም እየበረታ ሲሄድ ነገር ዓለሙን ያዘነጋልና ፍርሃቱም እንግድነቱም ቅፅበታዊ ነው።

ልጅ እያለሁ ከሰፈር ርቄ ወደ ማላውቀው ቦታ ከጠፋሁባቸው ምክንያቶች ከሌላ ሰፈር የሚመጣን የሰርግ ሙዚቃ ተከትሎ መሄድ— ይገኝበታል። ከአንዴም ሁለት ሶስት ጊዜ የሰርግ ሙዚቃ ተከትዬ ጠፍቼ አውቃለሁ። (ሙሾ ተከትዬም ጠፍቼ አውቃለሁ። እርሱን ሌላ ጊዜ እንጫወት ይሆናል።) ሰፈር ውስጥ ሰርግ ካለ ከጓደኞቼ ጋር ደጃፉ ላይ ነበር የማመሸውና ቤት ደስ አይላቸውም። ባይላቸውም ግን እየተቆጣሁም ቢሆን ሄጄ አመሻለሁ። ….ልቀላውጥ! ምግብ አይደለም… የሰርግ ሙዚቃ ልቀላውጥ!

ልቤ “ውድሽ መች ልሰማ?” ማለቱን ይቀጥላል!– በኩራት ከፍ ብሎ!

ሙዚቃውም ቀጥሏል…..

“ዲን ዲን ዲሪሪን
ዲን ዲን ዲሪሪን….
የወይን አበባዬ፣ የወይን፣
የወይን አበባዬ፣ የወይን፣
እኛም ወደናል ትሁን።”

አፅዳቂና ፈቃጅም አለ ማለት ነው። ግን ባይወዱ ኖሮስ….?! ውዷ መች ሊሰማ?!

“ሙሽሪት ባንድ አልጋ፣
ሙሽራው ባንድ አልጋ፣
መልአክ ይመስላሉ፥
ክንፉን የዘረጋ።….”

ከሙዚቃው ጋር ልቤ ቅልጥ ይልና፣ ሊቀየር ጋብ ሲል ልቤ ይጠይቃል። “ለምን በአንድ አልጋ በአንድ አልጋ ይሆናሉ? ሰርግ አይደል እንዴ? ክንፋቸውን የዘረጉ የሚመስለው አብረው ለመሆን ስላኮበኮቡ ነው? ለምን ጊዜ ይገድላሉ?….አብረው አይተኙምና ክንፉን የሰበሰበ መልአክ አይመስሉም?” ምናምን ምናምን…..

“አናስገባም ሰርገኛ፣
እደጅ ይተኛ….”

የሚለውን ሲሰማማ ልቤ በሳቅ ይፈርሳል። ማጨብጨቡን ትቶ ይበሳጫል። “ምን ያካብዳሉ?….ለምን ያስመስላሉ?“ ምናምን እያለ ብቻውን ይቆዝማል። ኧረ እንዲያውም ልጅ እያሁ “አናስገባም” የሚል ግጥም ፅፌ ነበር። (በኋላ ማስታወሻ ደብተሬን ፈልጌ እከልማትና፥ ብቻዬን እስቃለሁ።)

ሙዚቃው ቀጥሏል….

የሰርግ ሙዚቃ እውነተኛ ዳኛ ነገርም ይመስለኛል። “ማነሽ ባለተራ?” እያለ ሁሏንም እኩል ያንቆላጵሳል። ባለተራ የሆነችውን ሁሉ በውዳሴ ያቀላልጣል። ሚዜ አይቀረው፣ ቤተሰብ አይቀረው… ጎረቤትና ጓደኛ አይቀረው… አማረች አላማረች ጉዳዩ አይደለም። ወፍራም ብትሆንም ”ችብ አይሞላም ወገቧ“ ይባልላታል። እናቷ ፈትለው ባያውቁም ”እናቷ ፈታይ እንዝርት ሰባቂ“ ይባልላታል።…. ዓለሟ ነዋ!

“ዓለምሽ ዛሬ ነው ዛሬ፣
እቴ ሸንኮሬ….”

እያለ ማቀላለጥ ነው። እህ…. የራስ ዓለም ከሆነ ማን ምን ሊያገባው? ኧረ ማንም! የሰርግ ዘፈኖቹ ይውረዱ፣ እኛም ከአልጋችን እንውረድ። ዛሬ የሁለት ከባባድ ወዳጆች ሰርግ አለብኝ!
.
.
.

“ኦሆ… የቤተ ዘመዱ፥
ይታያል ጉዱ!
ኦሆ… ዘመድ ነን ያላችሁ፣
እስኪ እንያችሁ!
ኦሆ… ጓደኛን ያላችሁ፣
እስኪ እንያችሁ!

እስክስ… እስክስ…
እንዲህ… እንዲያ…
.
.
አይፈራም ጋሜ አይፈራም፣
ወገብሽ ልክ አይሰራም፤”

ሠናይ ቀዳሚት!

የብርሃን ልክፍትን ለመግዛት ከታች ይጫኑ።

Buy Now Button with Credit Cards