ከገጠር ወደ ከተማ የሚሰደዱ ስሞች…

ስም መጠሪያ ነው። – አንዱን ከአንዱ መለያ! አፍ ላይ ቀለለ፥ ከበደ፤… ጣፈጠ አልጣፈጠ፥ ያው መጠሪያ ነውና በስም አንቀልድም። ይህንንም የምጭረው የማንም ስም ላይ ለማሽሟጠጥ (ወይም እንዲያሽሟጥጡ በር ለመክፈት)፣ አንዱን ከአንዱ ለማለካካትና ለማበላለጥ… ወይም በሌላ የተለየ ምክንያት ሳይሆን፥ አሁን ስላለው ነባራዊ ሁኔታ በቀለለኝ መልኩ ለመጫወት በማሰብ ነው። ይህን ከገለፅሁ ዘንዳ ጨዋታዬን ልቀጥል…
*
*
*
ብዙ ጊዜና ብዙ ቦታ ለሰው ልጆች ስም ሲወጣ እንዲሁ ዝም ብሎ አይደለም። በሆነ ዓይነት ምክንያትና ፍላጎት እንጂ! በማውቀው ልክ (በብዛት ካስተዋልዃቸው መካከል) የስም አወጣጥ/አመጣጥ ምክንያቶችን ልከፋፍላቸው ብል፤… በጣም ውድ (ብርቅ) በሆነ ነገር መሰየም፤ ለምሳሌ: – አልማዝ፣ እንቁ፣ ወርቅነሽ፣ ብርቄ፣ ብርነሽ፣….፥ ለአፍና ለአጠራር በሚጣፍጥ ቃል መሰየም — ትርጉሙን አወቁትም አላወቁትም! (ይሄ በማደግ ላይ ያሉ ከተማዎች ውስጥ ይዘወተራል።)፤…

ልጅ የተወለደ ሰሞን በሚፈጠር ህብረተሰባዊ ክስተት መሰረት መሰየም፤ ለምሳሌ: – ደርጉ፣ ነፃነት፣ አብዮት፣ ህዳሴ፣ ግድቡ፣ አባይ፣ ድሌ፣ ፋሲካ፣ ገና፣….፥ በአንድ ገናና ወቅታዊ ጉዳይ ወይም ግለሰብ ስም መሰየም፥ ለምሳሌ: አብዮት፣ ሉሲ፣ ሚሊኒየም፣ ዚዳን፣ ኦባማ፣….፥ ምኞትን፣ ተስፋን ወይም ፍላጎትን ለማንፀባረቅ በማሰብ መሰየም፤ ለምሳሌ: – ተስፋዬ፣ ይልቃል፣ ስንሻው፣ አንሙት፣ ፍላጎት፣ ደምመላሽ፣ ማለፊያ፣ ሰላም፣ ይበልጣል፣….

ፅድቅና መንግስትን በማሰብ፤ ለምሳሌ: – ቸርነት፣ ምህረት፣ ፃድቁ….፥ ለማመስገን፤ ለምሳሌ: – ምስጋና፣ ስጦታ፣ ፀጋ፣ እድላዊት፣….፥ ልጁ እስከተወለደበት ጊዜ ድረስ የነበረን ተድላም ሆነ ውጣ ውረድ ጠቅለል አድርጎ ለማስቀመጥ በማሰብ፤ ለምሳሌ: – ሙሉቀን፣ ስንታየሁ፣ ብዙአየሁ፣ ምንታምር፣ ነጋ….፥ ከኑሮ ጋር የሚደረግን ግብግብና ሁኔታውን ለመግለፅ በመፈለግ፤ ለምሳሌ: – በርታ፣ ጠንክር፣ አንሙት፣….፥ ቅዱስ መፅሐፍትን በማጣቀስ፤….

በእዚያ አካባቢ በሚመጡ እንግዶች ስም መሰየም (ለምሳሌ: – እኔ በምሰራበት አካባቢ ዶክተር የሚባል ልጅ ነበረ። ገርሞኝ ምክንያቱን ስጠይቅ እርሱ በተወለደበት ጊዜ ዶ/ር ገዛኸኝ የሚባሉ ሰው እዚያ አካባቢ ስለነበሩ ነው። እዚህ ጋር ፈገግታ የሚያጭረው “ዶክተር” እንደማዕረግ ስም ሳይሆን እንደ መጀመሪያ (መጠሪያ) ስም መወሰዱ ነው።)፤…. ወይም ሌሎች ብዙ ምክንያቶችን ተንተርሶ ስም ይወጣል።
*
*
*
ዛሬ መጫወት ያማረኝ ግን በጣም ውድ (ብርቅ) በሆኑ ነገሮች ላይ ተመርኩዘው (በሌላ ምክንያት ሳይሆን፥ ብርቅነታቸው ተወድዶ ብቻ) ስለሚሰጡ ስያሜዎች ነው። እንደሚታወቀው ውድነትና ብርቅነት፥ ብዙ ጊዜ፥… በተዘዋዋሪ ከገቢና አቅርቦት ጋር ይያያዛል። ወርቅ ውድ የሚሆነው ወርቅ እንደልብ በሌለበት ነው። ብር ውድ የሚሆነው ብር እንደልብ በሌለበት ነው።… ወይም ደግሞ የቁሶቹ ተፈላጊነት ከፍተኛ በሆነበት ቦታና ሁኔታ ነው።

የልብን ፍላጎት ለማሟላት ወይም የሚወዱትንና የሚሳሱለትን ልጅ — “እንደዚያ ውድ ነገር የከበርክ/ሽ” ለማለት ስያሜው ሊወረስ ይችላል። በዚህ አካሄድ አስበነውም፥ የሆኑ ዓይነት ስሞች ከገጠር ወደ ከተማ ሊሰደዱ እንደሚችሉ መገመትና መጫወት እንችላለን። …. ከገጠር ተሰድደው መምጣት ብቻ ሳይሆን እንደ አዲስ የሚወለዱትንም መጠርጠር ይቻላል።
ለምሳሌ: – ድሮ መብራት ብርቅ በነበረበት ዘመን፥ የከተማው የመብራት መስፋፋት ወሬ ወደ ገጠሩ ሲዛመት፥… ልጅን በውዱ መብራት ስም “መብራቱ፣ መብራቴ፣ መብራት ነሽ፣ አበራሽ፣ ፋኖሴ፣ ማሾ….” እየተባለ ይሰየም ነበር።

አበው ወእመው፥ “መልከ ጥፉ በስም ይደግፉ” እንዲሉ በሁኔታዎች የጎደሉ ነገሮችን በስያሜ ይሞላሉ። በዚህ ረገድ ብዙ ነገሮችን ማንሳት ይቻላል።ራሱ “ከተማ” ብሎ ስም፥ ሰያሚዎቹ ለከተማ የሰጡትን ነገር ሊያሳየን ይችላል። ዛሬ ግን ከተማው ውስጥ በየጊዜው በሚታየው የመብራት መጥፋት ችግር ምክንያት እነ ”አበራሽ፣ መብራቴ፣ መብራት ነሽ፣ ፋኖሴ፣ ማሾ….” ከተማ ውስጥ ለሚወለዱ ልጆች …የነገሩን ብርቅ ድንቅነት በማድነቅ ብቻ ተወስኖ… መሰጠት ይጀምሩ ይሆናል። ከውኀ ጋር በተያያዘም እነ “ውሃ ወርቅ” ወደ ከተማ መጥተው ለሚወለዱ ልጆች ስያሜ ይሆናሉ።

የድሮ ባላባት መውዜርና ምንሽሩን ይወለውል እንደነበር፥ የዛሬ የከተማ እመቤትና ጌቶች ለውሃ መቅጃ እቃዎቻቸው የሚያሳዩት እንክብካቤ ሲታይ፥…. ምናልባት ወደፊት “ቧንቧዬ፣ ባልዲዬ፣ መቅጃዬ፣ ሃይላንዷ፣ ጀሪካን፣ ለገዳዲ፣….” እየተባለ እንዳስፈላጊነቱ ሌሎች ውድ ስሞች ከውድ ልጆች መወለድ ጋር ሊወለዱ እንደሚችሉ ያስጠረጥራል።

“ንፁህ” ም ከጠፋበት ይገኝና እንዳዲስ ያገለግል ይሆናል። እነ “ጥም ቆራጭ” የሚሉ ስሞችም ይወለዱ ይሆናል። ….ከስልክ አገልግሎት መስፋፋት ጋር የተሰጡ ስሞች መኖራቸውን ከዚህ ቀደም ሰምቼ ባላውቅም፣ ነገሩ አሁን ባለው ሁኔታ ከቀጠለ ግን “ኔትወርኬ” የሚል ስም በቅርቡ በሽ እንደሚሆን እንጠረጥራለን። 🙂

ያው ጨዋታ ነው! – ግን ብሶት ወለድ ጨዋታ!

በገጠርና በከተማ መካከል ግን ከመልክአ ምድራዊ አቀማመጥ ውጭ ምንም ልዩነት እንዳይኖር አገልግሎቶች በጥራትና በብዛት ይሟሉ ዘንድ እንማፀናለን!

እስኪ እናንተም ጨዋታውን ቀጥሉበት… አርብም አይደል?! 😉

መልካም የእረፍት ቀናት!

 

 

 

 

 

 

 

“የብርሃን ልክፍት”ን ለመግዛት (ለማዘዝ) ከታች ያለውን ይጫኑ።

Buy Now Button with Credit Cards