የብርሃን ልክፍትን ስንመርቀው! …በነፃነት ተስፋዬ

xhfanበነፃነት ተስፋዬ
(netsatesfa@gmail.com)

“ዕንቁ” መጽሔት፣ ቅፅ 6 ቁጥር 92፥ ግንቦት 2005 ዓ/ም

ለራስ ሳይሆን ለሌላ ሰው ብርሃን ለመሆን መነሳት ትልቅ የሕይወት ውሳኔን ይሻል። ዕድሜ ልክን እንደ ጃማ ለሕዝብ አዳም ወ ሔዋን ብርሃን እየሰጡ እስከ መጨረሻዋ ጭላንጭል መትጋት፣ ከዚያም ቀልጦ መቅረትን። ይህን መታደል የሚያገኙትና የሚፈፅሙት ደግሞ ጥቂት ናቸው። ብርሃን ለመሆንም እኮ መታደግ ያስፈልጋል። ለሌላው ብርሃን ለመስጠት ሲሉ መጣር፣ መጋር፣ መፈተን፣ መከራን መቀበል ሁሉ አለ። አንዱ እንደ ሻማ ብርሃን ሰጥቶ ቀልጦ ሲያልቅ፣ ወይም እንደ አምፖል ሲቃጠል፣ በምትኩ ሌላ ሻማ ወይም አምፖል የሚሆን ሰው እየተተካ እዚህ ደርሰናል።

እኛ ደግሞ ብርሃን ሆነው መንገዳችንን ያመለከቱንን፣ ጨለማውን ያበሩልን እና ሕይወታችንን ያደመቁልንን ትጉህ ሰዎች ማሰብ፣ ማድነቅ፣ ማመሰገንና ማክበር አለብን። ልብ ያላቸው መቼና የት ቦታ ሆነው ብርሃን እንደለገሱን እንኳን የማናውቃቸው ስንት ሻማዎቻችን ነበሩ፤ አሉ።

ዮሐንስ ሞላ ታዲያ ብርሃን የሰጡንና እየሰጡን ያሉትን ከልቡ ጥፏቸው ኖሮ “የብርሃን ልክፍት ያለባቸው ናቸው።” አለና የግጥም መድብሉን “የብርሃን ልክፍት” ብሎ ሰየመው። ምክንያቱንም የመጽሐፉ የጀርባ ሽፋን ላይ እንዲህ በማለት ገልፆታል።

ለሌሎች ብርሃን የመሆን ፀጋ ተችሯቸው፤… ብርሃን በመሆን ምግባር ተለክፈው፤… ወይ ደግሞ እንዲሁ ጥሎባቸው፤… ለሰው ልጆች ጥቂት ብርሃን ለመስጠት በብዙ የመከራ እሳት ውስጥ አልፈዋል። በየቦታው የሚቃጠሉም አሉ። — ምናልባት ያሰቡትን ብርሃን በመሆንና ባለመሆን መሀል ግብራቸው በውል ሳይለይ በከንቱ!

ሌሎች ደግሞ ብርሃንን በማየትና በመፈለግ ተለክፈው፣ በመከራ ውስጥ ሳሉ እንኳን ‘የብርሃን ያለ…’ ብለው ዋትተው ስለ ብርሃን ብዙ ደክመዋል። በየጊዜውና በየሁኔታው የሚማስኑም አሉ።….– ምናልባት የፍለጋቸው ስምረት በሰዎች ተቃጥሎ የማብራትና የማለፍ ዋጋም ቢሆን ግድ ሳይሰጣቸው።…. — አንዳንዴ እየተሳካላቸው፤…. አንዳንዴ ደግሞ፥ እንዲሁ በከንቱ!

ልክፍት ነው! የብርሃን ልክፍት!

በመድብሉ ውስጥ በመጽሐፉ ርዕስ የተሰየመ ግጥም ባይኖርም በብርሃን የመለከፍ ጠረን ያላቸው ግጥሞች አሉበት። በተለይ ”የእኔ ፍቅር ላንቺ“ በሚል ርዕስ የቀረቡት ግጥሞች የዚህ ቃና አላቸው። ዮሐንስ የግጥም መጽሐፉን ባስመረቀበት ድግስ ላይ ግን “የብርሃን ልክፍት” የተሰኘውን መድብሉ ውስጥ ያልተካተተ ግጥሙን ለእድምተኞቹ አንብቧል።

ብርሃን ሆነው ላደመቁን ሁሉ ይህን ክብር መስጠት ያኮራል። አርአያነትም ነው። ለዛሬው ማንነታችን መሠረት የሆኑንን ያውም በወጣት ገጣሚ ከሥነ ጽሑፍ በረከት ጋር ማመስገን ቢያውቁም ባያውቁም የሕሊና ሜዳሊያ እንደመሸለም ይቆጠራል። ገለታ ይግባህ።

ዮሐንስ ሞላ ማኅበራዊ ሚዲያን በተለይ ደግሞ ፌስቡክን ለሥነ ጽሑፍ ገበታነት እየተጠቀመ ያለው ንቁ ትውልድ አባል ነው። “ጠይም በረንዳ” የተሰኘ የፌስቡክ ገጽና የራሱ ብሎግ አለው። የብዕሩን ጠንካራነት ያየሁት በነዚህ ገጾች ላይ በሚያቀርባቸው ወጎች፣ ምልከታዎች፣ ግጥሞችና በመሳሰሉት ጽሑፎች ነው።

ይህ የማሕበራዊ ሚዲያ መድረክ በርካታ ወጣት ጽሐፊዎችን ያፈራ ሐሳብን በነጻነት የመለዋወጥ መድረክ የፈጠረ፣ በቀላሉ ሊታተሙ ያልቻሉ ጽሑፎችን በራሳችን ቋንቋ ያገኘንበት ነው። መድረኩ ልክ እንደ ሥነ ጽሑፍ ክበባት ተስፋ ያላቸው ጸሐፊዎችን እየፈጠረ መሆኑን አፌን ሞልቼ እናገራለሁ። የመጻፍ አቅማቸውን የሚያዳብሩበትን የጥበብ መጋሪያ እንዲያቁሙ አድርቿቸዋልና።

በዓይነ ሥጋ ተያይተው የማያውቁ ግን በብዕሮቻቸው የሚተዋወቁ ወጣቶች በተለይ በፌስቡክ ላይ በሚፈጠሩ የጥበብ ገጾች ላይ እያደረጉት ያሉት ተሳትፎ የሚደነቅ ነው። “የብርሃን ልክፍት” በተመረቀበት ዕለት በጽሑፎችቻቸው ብቻ የሚተዋወቁ ባለገጾች ዐይን ለዐይን ተገናኝተው ተጠፋፍተው እንደተገናኙ ዘመዳሞች ሠላምታ ተለዋውጠዋል። ይህንኑ ስሜታቸውን በምረቃው ምሽትና ዋዜማ በየፌስቡክ ገጾቻቸው ላይ አዝንበውታል።

በምረቃ በዓሉ ላይና ከዚያም በኋላ ድርሰቶቻቸውን አሳትመው በቅርቡ የሚያስመርቁ እንዳሉ ሰምተናል። ዮሐንስ ብዕሩን አትብቶ  ይህን የግጥም መድብል ለአንባቢያን ሲያቀርብ ለአገራችንም ሥነጽሁፍ አንድ ተጨማሪ መጽሐፍ አበርክቷል ማለት ነው። በድርሰቱ ይዘትና አቀራረብ ላይ ግንቦት 8 ቀን 2005 ዓ.ም. በተካሄደው የምረቃ ሥነሥርዓት ላይ ደረጀ በላይነህ ጥሩ አስተያየት ሰጥቷል።

በበኩሌ፥ “የብርሃን ልክፍት” ጥሩ ግጥሞችን ይዟል እላለሁ። በውስጣቸው ጠንካራ ሀሳብ አለ። የደራሲው ጥብቅ ስሜት ይነበባል። አብዛኞቹ አገራዊ ጉዳይን የያዙ፣ የአገሬ ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ ናቸው። ረጃጅም ግጥሞቹ ርዕሰ ጉዳዩን በጥብቀት ይዳስሳሉ። በተለይም ጥሩ የቃላት አጠቃቀም አቅም አለው። የሚጠቀምባቸው ቃላት ቀላል፥ ግን እምቅ ሐሳብ የሚገልፁ  ናቸው። አዳዲስ ቃላትን ፈጥሮ መጠቀሙ፣ የግዕዝ ቃላትን እንደምስል መቁጠሪያ መገልገሉ፣ ድርጊት ገላጭ ቃላት በመደርደር ክዋኔን በቃላት ማሳየቱና የመሳሰሉት የአቋም ማሳያ ሆነው ሊጠቀሱ ይችላሉ። መንፈሳዊ ዕውቀቱ ለቀደም ጠቃሽ አጻጻፍ የግብአት ምንጭ ሆኗል።

ሥነ ቃላትን የግጥም አካላት ማድረጉ በታሪክ ላይ የተመሠረቱ ሁነቶች ላይ ተመርኩዞ ጉዳዩን ከአሁኑ ዘመን ሁነት ጋር እያነጻጸረ ማቅረቡ፣ የብዕር ጥንካሬውን ያመለክታል። “ከአያያዝ ይቀደዳል፣ ካነጋገር ይፈረዳል” ነውና ይህ መጽሐፍ ወደፊት ከዮሐንስ ብዙ እንድንጠብቅ ያደርገናል።የሞፈር አያያዙንና የማረሻውን አተካከል በውል ያወቀ ጀማሪ አራሽ ሞፈሩን ተከትሎ አድምቶ እንደሚያርስ ሁሉ በመጀመሪያ መድብሉ ላይ ያየነውን የብዕር ትጋት ይበልጥ አጠብቦ እንዲሄድ እንመኛለን።

ከፌስቡክ ገጾችና ከምረቃ ዝግጅቱ እንዳስተዋልኩት ዮሐንስ ጥሩ እንደሚጽፍ የሚያውቁ፣ የሚያበረታቱትና የሚያደንቁት በርካታ ወዳጆች አሉት። ይህ መልካም ማበረታቻ ነው። ነገር ግን አድናቆቱ በዝቶ ከብዕሩ ጥንካሬ እንዳያናጥበው መጠንቀቅ አለበት። ወዳጅ ጓደኞችም ምስጋናና አድናቆት ብቻ ሳይሆን የሒሳዊ ንባብ አስተያየታችሁን ለግሱት።

ዮሐንስ የሚቀጥለውን መጽሐፉን ሲያቀርብልን የሚያመጣውን ለውጥ የምናየው እነዚህን አስተያየቶች ተቀብሎ ምን ያህል በግጥም ገበታ ላይ እንዳደፋጨ ስናይ ነው። ውስጡ ትጋት እንዳለ ስላስተዋልኩ የሚቀጥለው መድብሉ የራሱን ወዝ፣ ስልት፣ ወጥነት፣ ቃላት አጠቃቀም የያዘ እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ።

በነገራችን ላይ የእኔ ፍቅር ላንቺ አንድ፣ ሁለ፣ ሦስት እና ፍቅሬ ሙዚቃዬ የተሰኙት ግጥሞች ከያዙት ጥልቅ መልዕክት በተጨማሪ ስሜትን የሚነካ ሙዚቃዊ ቃና ስላላቸው አንጀትን ሰርስሮ በሚገባ ዜማ ሚካኤል በላይነህ ወይም ቴዎድሮስ ካሳሁን እንዲዘፍኑት ቢሰጣቸው?

/ነፃነት ተስፋዬ የኮምዩኒኬሽን፣ የሚዲያና የሥነ ጽሑፍ ባለሞያ ነው።/

 

 

“የብርሃን ልክፍት”ን ለመግዛት (ለማዘዝ) ከታች ያለውን ይጫኑ።

Buy Now Button with Credit Cards

ባይገርምሽ 21

አፍ አስከፋች መልኳ፣… ውስብስብ ስሪቷ፣… አቀነባበሯ፣
አደንዛዥ ቀለሟ፣… አስፈንጣዥ ውበቷ፣… ልዩ አሰዳደሯ፣
አጃኢብ፥ ኩነቷ፣… ጉድ፥ አተካከሏ፣… ታምር፥ አሠራሯ፣
የተፈጥሪት መልኳ፤… ጥፍጥና፣ ጣዕሟ፣
የእግዜሩ እጅ ሥራ፣ ድብልቅልቅ ቀለሟ፥….

ፍንትው፥ ሲል ካ’ይኔ፤  ሀሳቡ ሲጠጋኝ፣ ሲከመር ካ’ናቴ፣
ውጭ ውስጧ ሲያሳሳኝ፣ ቁንጅና ተጭኖ፥ ሲኮለኮል ፊቴ፣
ውበት ሲያሸፍተኝ፣ ደምግባት ሲያቀልጠኝ፣ ሲርድ ሰውነቴ፣
ጭው ይላል ዓለሙ፥…. መላ ቅጥ አጣለሁ፤
ያንንም፥ ያንንም፥ በሆንኩ ያሰኘኛል፣ እንደማልችል ሳውቀው!

አይመረመረው፥… — የአሠራሯ ጥበብ፣ የሠሪው ችሎታ፤
አወይ አፈጣጠር፣ ወየው ሰውነቷ…!
ለጥ ያለው ሜዳ ላይ አረንጓዴ ፈስሶ፣ የሣር ልብስ ተነጥፎ፣
ውበት ተደፍቶባት፣ ወዟ ችፍ ብሎ፣ አመዷ ተራግፎ፣
ሳያት እርዳለሁ፥ ከብትነት ያምረኛል፤
— በሬነት፣ በግነት፤ ላምነት ይለኛል፤

“ሂድ ጋጠው! … ሂድ ጋጠው! … ዋልበት ከመስኩ፣
እረኞች ያግዱህ፣… ካ’ጋጋጥህ ጋራ፣ ዜማ ይሰካኩ!
ጠግበህ ስትገባም፥ ከበረት አሽካካ፣
ጌጥ ይሁንህ ገመድ፥ ታስረህ አመሰኳ! ”
ይለኛል አንዳች ኃይል!  …ሰቅዞ፣ …ለብቆ፤
ከልቤ ጆሮ ውስጥ፣ ከማላውቀው ጠልቆ፣
ምሪውን አርቅቆ፣ መልዕክቱን አድምቆ፣ ውሉን አጠባብቆ፤

ደግሞ ተራራዋን፣ ኮረብታዋን ሳያት፥ — እንዳ’ንዳች ተራቁታ፣
ብርድ ውርጭ ሲጠልዛት፣ ሙቀቱ ሲያነፍራት፣
…ስታሳዝን ጊዜ! … — ጡቷ ተዝረክርኮ፣ ተጋልጦ ደረቷ፣
አመዳይ ሲለብስ፣ ቀጭ ሲወራት ጉንጯን፣ ስትከስል መድይታ፥….

“ንፋሷን ባረገኝ፣… — በተኛሁ ከላይዋ፣… ሄጄ በሸፈንኋት፤
ባሟሟቅኋት ኖሮ፣ ባባረድኋት ኖሮ፣ (እንዳ’የሩ ጠባይ) በተንከባከብኋት፣
ኩታ፣ ጋቢ ሆኜ፣ በተደረብኩላት፣ ሄጄ ባለበስኋት፣ ጠርታኝ በተላበስን፣
በሀሴት በተላቀስን፤….
እርሷንም በሞቃት!  እኔንም በሞቀኝ!
ዓለሙም እንዲሁ…. — ባ’ዱኛ ቢጎበኝ!
ለእኔና እርሷ መብራት፥….
ጀምበርን በሰደብን፥ — “ይች ጎታታ! ” ባልናት፣
ጨለማን በረገምን፤ — “ከቶ አትንጊ! ” ባልናት፤…
ያሰኘኛል ደርሶ!
— የሀሳብ ሙላት ፈልቶ፣ …ሰቅዞ፣ …ለብቆ፣
ከልቤ ጆሮ ውስጥ፣ ከማላውቀው ዘልቆ፣

ደግሞ በሌላ ቀን፥ ያ’ዋሮች ስብስብ ሜዳዋን ሲያለብሳት፥
“አፅዳላት” ይለኛል፤ ”ንፋሲቷን ሁን… ሁን… ሽው በል ካናቷ፣
አውሎ ሆነህ ንጎድ! …. ኮልኮሌውን ለቅመህ፥ አንሳላት ከፊቷ፣
ጠራርገህ ውሰደው፤ — ወስደህ አሳቃቸው፣ ከአቁሻሾች አይን ክተት፣
ሲጨናበሱ አይተህ፥ – ሲሸሹ፣ ሲሮጡ – ከ’ርሷ ጋር ተንከትከት! ”

“ደግሞም ዝናቧን ሁን፥… ፍሰስ ከገላዋ፣
አጣጥባት፣ አጠጣት፣… ይታይ ቁንጅናዋ፣
ይፅደቅ፣… ያብብ፣… ያፍራ፣… ለምለም ይሁን ዘርዋ! ”
ይለኛል አንዳች ኃይል!  …ሰቅዞ፣ …ለብቆ፤
ከልቤ ጆሮ ውስጥ፣ ከማላውቀው ጠልቆ፣

ተንኳልሎ ሲወርድ፥ የምንጭ ውኀ ጠርቶ፣
መንገዱን ሲጠርግ፣ መስመር አበጃጅቶ፣
ተከትሮ ሳየው፥ — ኩሬ ሰርቶ፣ ‘ረግቶ፣
ፊት ሲያሳይ አጥርቶ፣ — “መልክህን ታይበት፣
ጠጣው! ” ያሰኘኛል!  — “ጥም’ን ቁረጥበት፤
ወፍ ሆነህ ድረሰው፣ ትል ሆነህ ልበሰው! ”

ድንጋይ ገርፎ ሲወርድ፥ መገረፍ ያምረኛል፣
“ተጣጠብ” ይለኛል፥ — “ተለቃለቅበት፥
ዛቀው ከመነሻው፣ ጨልፈው ከምንጩ፣
አንተ ስትረካ፣ ያ’ልቻሉት ይንጫጩ! ”
ይለኛል አንዳች ኃይል!  …ሰቅዞ፣ …ለብቆ፤
ከልቤ ጆሮ ውስጥ፣ ከማላውቀው ጠልቆ፣

ዛፏን ሳይ – ወፊቱን፥ መሆን ያሰኘኛል፣ ላይዋ ማረፍ – በርሮ፣
ቤት መሥራት መቀለስ፣ ጎጆ ማበጃጀት፣… መደላደል ሰፍሮ፣
እፎይ ብሎ ማደር፣ — ቅርንጫፏን ሰብሮ፣ ግንዷንም ቆርቁሮ፣
ምናምን ለቀማ፥ — የከብቶቹን ገላ፣ ያዞን ጥርስ መበርበር፣
ማደሪያ አበጃጅቶ፣ ታዛን አሽቀርቅሮ፣ ሐሳብ ጥሎ ማደር፤
…ሲነጋ ለመብረር —
— ካ’ንዱ ዛፍ፣ አንዱ ዛፍ፤  ካ’ንዱ ስጥ አንዱ ስጥ!
ደግሞ ጦጣ መሆን፣… ደግሞ ዝንጀሮነት፥….
ዓይን የሻውን መንጠቅ፤ ከሰው ማሳ ገብቶ፣ ብቃዩን አምክኖ፣
ሲጠግቡ መጫወት፣ በደቦ አጠፋፍቶ፣ መሬት ላይ በታትኖ፤
ሲደክመኝ — ሰውነት! መጠለል ከሥሯ፣ መምከር ተሰብስቦ፣
ከዛፏ ጥላ ሥር፣ ቁጭ ብሎ መደመም፣ መጫወት ተካቦ፤
ያምረኛል ክፉኛ!   …ሰቅዞ፣ …ለብቆ፤
አንዳች ልዩ ስሜት፣ ከማላውቀው ጠልቆ፤

ወንዟን ካየሁማ…፥
ቁልቁል ስታሽላላ፣ ተንጋግታ ስትወርድ፣ ቀልታ እንዳ’ለላ፣
ከአፈር ተቀላቅላ፣ ስትሄድ ቀይ ወጥ መስላ፣
“አፈር ሁን” ይለኛል!  እመር ተመሳሰል፣ ስመር ከውኅው ጋ፣
ካ’ንዱ ጥግ አንዱ ጥግ፥ ባንድነት ዝመቱ፣ አብረኻት ተላጋ!
ደግሞም አጎንብሰህ፥… ከወንዙ ጠጣለት፣ ይገረም አለሙ፥
ከ’ርካታ ተዋወቅ፣ ጥምን ቆርጠህ ጣለው፥ እስከዘላለሙ! ”
ያሰኘኛል ደርሶ! የሀሳብ ሙላት ፈልቶ፣ …ሰቅዞ፣ …ለብቆ፣
አንዳች ኃያል ነገር፥ ከልቤ ጆሮ ውስጥ ከማላውቀው ዘልቆ፣
ምሪውን አርቅቆ፣ መልዕክቱን አድምቆ፣ ውሉን አጠባብቆ፤

ያ’ገሩ ገበሬ፣ ከእርሻ መሬቱ ላይ በሬ ጠምዶ ካየሁ፣
“ብረት ሁን! ” ይለኛል፥ ያች ማረሻይቱን መሆን ያሰኘኛል፤
“በከብቶች ጉተታ፣ በገበሬው ግፊያ፣ መሬቷን ቆፍራት፣
ዘልቀህ አተራምሳት፥ ቀድሞ እንዳልታረሰች፥ ሂድባት፣ ዝለቃት! ”
ይለኛል አንዳች ኃይል!  …ሰቅዞ፣ …ለብቆ፤
ከልቤ ጆሮ ውስጥ፣ ከማላውቀው ጠልቆ።

አፍ አስከፋች መልኳን፣… ውስብስብ ስሪቷን፣… አቀነባበሯን፣
አደንዛዥ ቀለሟን፣… አስፈንጣዥ ውበቷን፣… ልዩ አሰዳደሯን፣
አጃኢብ፥ ኩነቷን፣… ጉድ፥ አተካከሏን፣… ታምር፥ አሠራሯን፣
የተፈጥሪት መልኳን፤… ጥፍጥና፣ ጣዕሟን፣
የእግዜሩ እጅ ሥራ፣ ድብልቅልቅ ቀለሟን፥

ወፈ ሰማይ ሳይ ግን፥…
አንቺ የእኔ በራሪ፥ ትዝ ትይኝና፣ ወፍነት ያምረኛል!–
ሩቅ ይዞሽ መሄድ፣ መምጫሽን ጠብቆ፣
ሰማይ ላይ መከተም፣ ከመሬት ተላቅቆ፣
ቁልቁል መገላመጥ፣ ማንዣበብ ማማተር፣
ውድ አንቺን ፍለጋ!ውድ አንቺን ጥበቃ!
— ያሰኘኝን ሁሉ፥ ባንዴ’ምሆንብሽ፣
ሁሉንም ባንድ ላይ፣ ውድ አንቺን ስወድሽ፣
ካ’ንቺ ጋር ስገናኝ፣ ካ’ንቺ ጋር ስተይ፣
ከፍቅራችን ምድር፣ ከውዳችን ሰማይ፣
አፍ አስከፋች — አንቺ!
አደንዛዥ፣ አስፈንጣዥ፣ ልዩ ጥዑም — አንቺ!

ውድ አንቺን ስወድሽ….
ካ’ንቺ ጋር ስገናኝ፣ ካ’ንቺ ጋር ስተይ፣
ከፍቅራችን ምድር፣ ከውዳችን ሰማይ፣
ሳሮች ይዋባሉ! ምድር ታበራለች!
ከብቶች ይተኛሉ! እረኞች ያርፋሉ!
ተራራው ይናዳል! ኮረብታው ይፈርሳል!
ነፋሱም ያፏጫል! ዛፎች ያረግዳሉ!
ፀሐይ ትፈዛለች! ዝናብ ይጨፍራል!
ጨረቃ ታብዳለች! ከዋክብት ያፍራሉ!
ምንጮች ይረጋሉ! ቀጥ ይላል ዓለሙ!
ወንዞች ይቆማሉ! አህዋፍ ያዜማሉ!
መንጩም አደግዳጊ፣ ባሳየነው ተጓዥ!
ሳር ቅጠሉ ታዛዥ!

ከእኔና አንቺ ምድር፣
ከእኔና አንቺ ሰማይ፣

/ዮሐንስ ሞላ/

————

 

 

በዚያው ማስታወቂያ 🙂

በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥኑ 72፥ አጫጭርና ረዣዥም ግጥሞች የተካተቱባት መፅሐፌ፥ “የብርሃን ልክፍት” ገበያ ላይ ነችና አንብቧት። “የብርሃን ልክፍት”ን ለመግዛት (ለማዘዝ) ከታች ያለውን ይጫኑ።

Buy Now Button with Credit Cards

የዮሃንስ ግጥሞች መዓዛ!በደረጀ በላይነህ

አዲስ አድማስ ጋዜጣ ግንቦት 17 ቀን 2005 ዓ.ም. xhfan

በዘመናችን ህይወት የሚላወስባቸው፣ እንደመብረቅ የሚያስደነግጥ መልእክትና ውበት ያላቸው ጥቂት ገጣሚያን ተወልደው ፣በአበባ ሳቅ፣በእምባ ጉንጉን አስደምመውናል፡፡በተዘለዘለ የእምባ ቋንጣ አስለቅሰው፣ትኩስ የውበት ወንዞችን በልባችን መልካዎች አፍስሰዋል፡፡

ምንም እንኳ በገዛ ዘመናቸው ኖረው በኛም ዘመን የሚኖሩ ገጣሚያን መጥረቢያ የማይነካቸው የአድባር ዛፎች ተደርገው፣ በአዲሱ ትውልድ ላይ በር ቢዘጋም፣ወደኋላ ሄደን ስናይ ግን አንዳንዶቹ ብዙ ሊገረዙ የሚገባቸው ጭራሮዎች ያንጨፈረሩ፣ከዛሬዎቹ የሚያንሱት ብዙ ስራዎቻቸው በፍርሃት ገደል ውስጥ እንዲደበቁ ተደርጓል፡ዛሬ በሃሳብ ልቀት የትኛውም ያለፈው ዘመን ገጣሚን የሚያስንቁ እጅግ ጥቂት ገጣሚያን አሉን፡፡ግን አንዱ በቋንቋ፣ሌላው በሃሳብ ይበላለጣል እንጂ ሰበብ ተጠቅሞ በዚሀ ዘመን ግጥም የለም የሚለው ጤናማነት የጎደለው በሽታ ነው፡፡ ምናልባትም የቀደሙት ገጣሚያን ግጥሞች በወጣትነታቸው ምን ይመስል እንደነበር ለማስታወስ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን የ50ኛ ዓመት የኮሌጅ ግጥሞች ማንበብ ጥሩ ነው፡፡እኔ ጆን ድራይደን እንደሚል “እያንዳንዱ ዘመን የየራሱ ጂኒየስ አለው ብዬ አምናለሁ፡፡ትናንት ገጣሚ ከነበረ፣ዛሬ የማይኖርበት ምንም ምክንያት የለም፡፡

ይሁንና ገጣሚያንን አናወዳድርም፤ምክንያቱም መልካቸውና ፍሰታቸው ስለሚለያይ፡፡እንግሊዛዊው ሳሙኤል ጆንሰን እንደሚለው አሌክሳንደር ፖፕ ከ ጆን ድራይደን የሚለይባቸው መልኮች አሉት፤ፖፕ ለህዝብ ቅርብ ልብ አለው፤ድራይደን ደግሞ የጠለቀ ምሁራዊነት ለድራይደን አለው፡፡ድራይደን የውስጡን ድምጽ ወጀብ ሲያዳምጥ፤ፖፕ ደግሞ ስለ አጻጻፍ ህግ ያምጣል፡፡ሁለቱም በየመንገዳቸው ሃሳቦችን እንደጧፍ ያቀጣጥላሉ፡፡

ሎረንስ ፔሬኒ እንደሚሉት የታወቁ ገጣሚያንን ማውራት ጣጣ የለውም፤ግን ኣዳዲሶቹን እንዲህ ናቸው ብሎ ማለት ያስቸግራል፡፡ ስለዚህ ደፋር እንድንሆንና ትክክለኛ ግምት እንዲኖረን ጥሩ አንባቢና መመዘኛ ያለን ልንሆን ይገባል፡፡አዲስ ሰው መቀበል ልበሙሉነት ለጎደላቸው በጣም ዳገት ነው-በተለይ ለፈሪዎች፡፡በምክንያት ለማያምኑ ባይተዋሮች፡፡

አሁን የዮሃንስን ግጥሞች ስናይ በዚህ ስሜት ሊሆን ይችላል፡፡እኔ ግን እንዳየሁት፤ደጋግሜም እንዳነበብኩት ዛሬ የጀመረውን ከቀጠለ ረጂም መንገድ በውበት ይጓዛል፡፡ቋንቋው፣ሃሳቡ፣ፍሰቱ ፣ዜማው ሁሉ ለግጥም የተመቸ ነው፡፡

አንዳንዶቹ ግጥሞቹ ሲነበቡ የገጣሚው መልክና ዕድሜ ከሃሳቡ ጋር አልጣጣም ይልና እንዴት ይህን ነን ያህል አሰበ፡፡እንዴት ይህን ያህል የሚብከነከን ሆነ? ያሰኛል በርግጥ አንዳንድ ቦታ ወረድ ይላል፡፡ግን ያልወረደ ገጣሚ በምድር ላይ ማን አለ?…ያለቃላት በስሜት ብቻ ለሚያነብቡት በሳሎች ውስጥን ያንሾካሹካል የሚባለው ሼክስፒር እንኳ ትንንስ ቁልቁለቶች አሉበት፡፡ እኔ የማምነው ግን አክሱም ሃውልት አጠገብ ሄዶ ምን አይነት ጥበብ ነው እያሉ ረጂሙን በማየት ልካቸውን መለካት እንጂ ትንንሾቹን እያዩ እነዚህ ግን ቀሽሞች ናቸው በማለት አይደለም፡፡ሰማይ ነኩ ግጥሞች ያለው ገጣሚ ያንን ያህል ማሰቡ አቅሙን ያሳያል፡፡ልኩ ያ ነውና!

የዮሃንስ ግጥሞች አጫጭርም ረጃጅምም ናቸው።… ረጃጅሞቹ የመንገዱ ርቀት አቅም አልነሳቸውም፤ ትንፋሽ ጠብቀው ፈስሰዋል፤ ሳይንገዳገዱ ደርሰዋል፡፡ቃላት አያጥረውም፤ሃሳቡ አይደርቅም፡፡ ብዙ የፍቅር ግጥሞቹ ረዘም ይላሉ፡፡

አንዳንዶቹም ስነ ቃላዊ ግንድ ያላቸው፣ህዝባዊ ግጥሞች ናቸው፡፡ገጣሚው ብዙ ጊዜ ይህንን ዘይቤ ይጠቀማል፡፡ለምሳሌ ግርማ ሞገሳሟ‹ቴ‹፣”የኔ ፍቅር ላንቺ”…(ትንሽ ቢረዝምም) ምናልባት ለሃገራዊ እሴቶች ጆሮና ልብ የመስጠት ዝንባሌ ይሆናል ብዬ ገምቻለሁ፡፡ለውረንስ ፔረኒ እንደሚከፍሉት ይህ ዘይቤ በ3 ይከፈላል፡፡ …. 1. ታሪክ ጠቃሽ  2. ስነ-ጽሁፍ ጠቃሽ 3. መጽሃፍ ቅዱስ ጠቃሽ ናቸው፡፡

እስቲ “ጥምቀትና ሎሚ” ን እንይ፡- (ስለዚህ ስነ-ቃል የቃል ስነ ጽሁፍ ስለሆነ በዚህ ይካተታል፡፡)

ከአሲድ፣ ከዱላ፣
ከጥፊ፣ ከቢላ፣
የተረፈ ገላ….
በሎሚ ታክሞ፣ ጃንሜዳ ተበላ፤
ዳግም እስኪታመም፤–
…እስኪያገኘው ሌላ፡፡

* * *
በ‹ስሟ ለማርያም ከደጅሽ ታድሜ፤
ቁራሽ ልማጸንሽ፣ ከበራፍሽ ቆሜ፤
ካ’የሁሽ ጀምሮ፣…
ፍቅርሽ ሰቅዞኛል፣ ልብሽ ልቤ ገብቶ፤
ሐሳቤ ካንቺው ነው፣ ከደብሩ ሸፍቶ፤
ፍቀጅ እመቤቴ!…
ሎሚ መግዣ የለኝ፣ ውርወራ አላውቅ ከቶ፣
ጥምቀት ብዬ፣ ልንካሽ በ’ስክሪፕቶ፤

ይህ ግጥም የአሁኑን የፍቅር መግለጫ አሲድና የቀደመውን “ሎሚ ጣሉባት በደረትዋ፣የጌታ ልጅ ናት መሰረትዋን” ያስታውሳል፡፡ዮሃንስ የሁለቱም ትውልድና ቅርስ አድናቂ እንጂ ናቂ አይደለም፡፡

ውበትን አገላብጠው የሚስሙ ድንቅ የተቃራኒ ጾታ ፍቅር ግጥሞችም ቢኖሩት ከምስኪኖች ጋር ተቆራምደው የሚያለቅሱ የጉበኛ ልቦች አሉ፡፡አንዳንዴ ከደሃውና ከተጠቃው ምስኪን፣ወይም ከመላው ምስኪን ጋር ታገኙታላችሁ፡፡

….ግርማ ሞገሳሟ ቴ
ዛሬ እናን ባየሽን…
እንኳን ስሙን ጠርተን፣ ደርሰን ከሰፈሩ፣
ልኩን አስታጥቀነው፣ገጥመን ከግንባሩ፣…
እንዲሁም እንዲሁ ነን፣ ትርጁማን አናጣ፣
ያልነውን ተርጉሞ፣ ባላልነው ሚቀጣ፡፡
ብናለቅስ–“አበዱ!”፤ ጥለን ብንሄድ — “ፈሩ!”፣
ብንጠይቅ — “ጠገቡ!”፤ ብናውቅ–“አሸበሩ!”፤
የሚለን ብዙ ነው፣ ሚከሰን ዘርዝሮ፣
እንኳንስ ሊሸኘን፣ ካሳ ድርጎ ሰፍሮ፡፡

“ስንብት” አንዱ ራሮት ነው፤አንዱ የሩቅ ድምጽ፣ የሰቀቀን ዜማ ነው፡፡

ስንቱን የቀለም ቀንድ፣ ችኩል ጅብ ነካክሶ፣
ቀለሙን ደፋፍቶ፣ ጥበብን አራክሶ፤
አድርባይ ጤፍ ቆዪው፣ በዝቶ በመንደሩ፣
ጥራዝ-ነጠቅ እውቀት፣ ተስፋፍቶ ባገሩ፣
ብራና በረቀ፤…መቃ ብ‹ር ነጠፈ፤ ሊቃውንት ሰፈሩ፤
ፀሃፍት አንገት ደፉ፤ አበው ተሸበሩ፤ ጠቢባንም ፈሩ፡፡
ድጓ ጾመ ድጓ፣ ተሰቃቅለው ቀሩ፤
–እንደተደጎሱ…

* * *
ደጅ ሁሉ ተዘጋ፣ ሆድ ሁሉ ተከፋ፣
በግ ሁሉ ተነዳ፣ በተኩላ ተበላ፤… ቆዳው ሳይቀር ጠፋ፤
ወስፋቱን ሊያስተኛ፣ ደበሎሊደርብ፣ ተሜ ላይ ታች ለፋ፡፡
ምጣድ ይጥድ ሳይኖር፣ “የዕለት እንጀራዬን ስጠኝ” ባዩ በዛ፤
የበሰለ እንጀራም በበዮች ተከብቦ፣ በየጥጋጥጉ ሻገተ ጠነዛ፡፡…..

* * *
መንገድ እንዳትባክን፣ልቤ ካለ ልብዋ፣
“ይቅናህ ልጄ!”በይኝ!…ደህና ሁኝ እመዋ!
ደህና ሁን አስኳላ ! ደህና ሁን መምህሩ!
ደህና ሁን ባልንጀር! ደህና ቆይ መንደሩ!
–ጋራው ሸንተረሩ፤ አድባሩ፣ ደብሩ፣
ደህና ሁኑ እንግዲህ!… በችጋር ተገፋ፣ልቤማ ሰነፈ፤
ኑሮውን ሊረታ፣ ለከንቱ ብልጭልጭ ውበት ተሸነፈ፡፡

እዚህ ላይ የምናያቸው በርካታ ቃላት እማሬያዊ ብቻ ሳይሆኑ ፍካሬያዊም ፍቺ ያላቸው ናቸው፡፡…እነዚህ ደግሞ ለልብ የልብ ለመናገር ይሆናሉ፡፡

እስቲ እጅግ ከሚመስጡት የፍቅር ግጥሞቹ ጥቂት ስንኞች ልውሰድ፡-

መዋስዕት፣ምዕራፍ፣ድጓ፣ጾመ ድጓ፣
አቋቋም፣ዝማሬ፣–ቀልብ እንደሚያረጋ፣
እንደ ነፍስ ወጌሻ፣ እንደ ሥጋ አለንጋ፣
እንደምትቃርመው፣ መንፈሴ አደግድጋ፣
ሥጋ እንደሚሸሻት፣ ቤቱ ስትጠጋ፣
ካንቺ ከውዴ ጋ…ከስሜቴ ሲሳይ፤

….እያለ ይቀጥላል፡፡የቓላቱን ውበት እዚህ ጋ ማየት ይቻላል። አሻም ቴ እጅግ መሳጩና አስደኛቂው ግጥም ነው፡ ፡–ለኔ! ገጽ 19…

የዮሃንስ መጽሃፍ ውበት ከሽፋኑ ይጀምራል።…ቋንቋው በዚህ ዘመን ላለው የቃላት ድህነት እንደማስታገሻ ነው ማለት ይቻላል፡፡በዚያ ላይ አዳዲስ ቃላትን ኮይን ሊያደርግ የሚከረበት መንገድ የሚያበረታታ ነው፡፡….እንደ ችግር እንይ ካልን፣ አንዳንዶቹየግርጌ ማስታወሻዎች ብዙም ጠቃሚ ስላልሆኑና ባብዛኛው የሚታወቁ ስለሆኑ ቢቀሩ ጥሩ ነበር የሚል ሃሳብ አለኝ፡፡ከዚያ በተረፈ ባብዛኛው የተጠቀማቸው ጠቃሽ ዘይቤዎች አንዳንድ ቦታ ዝቅ ማለታቸው አይወደድም፡፡ለምሳሌ በህዝብ ዘንድ እጅግ የተለመዱት፤ግርማ ሞገሳሟ ቴ..ግጥሙን አጋምሶታል፡፡

ይህ ዘይቤ ታዲያ ከፍታው ጨምሮ ወደ ላይ ሲያንጠራራም፣ወደ ታች ዝቅ ብሎ ሲያስጎነብስም ጥሩ አይደለም፡፡ብቻ–ብቻ ዮሃንስ ትልቅ ልብ፣ትልቅ ምናብ አለው፡፡ይህንን አይውሰድበት!!

ምሁራዊ ከፍታቸው ጨምሮ ማንጠራራት ዝቅ ብሎ ሲያስጎነብስ አይወደድም፡፡ Over intellectualization

 

 

 

 

 

 

“የብርሃን ልክፍት”ን ለመግዛት (ለማዘዝ) ከታች ያለውን ይጫኑ።

Buy Now Button with Credit Cards