አፍ አስከፋች መልኳ፣… ውስብስብ ስሪቷ፣… አቀነባበሯ፣
አደንዛዥ ቀለሟ፣… አስፈንጣዥ ውበቷ፣… ልዩ አሰዳደሯ፣
አጃኢብ፥ ኩነቷ፣… ጉድ፥ አተካከሏ፣… ታምር፥ አሠራሯ፣
የተፈጥሪት መልኳ፤… ጥፍጥና፣ ጣዕሟ፣
የእግዜሩ እጅ ሥራ፣ ድብልቅልቅ ቀለሟ፥….
ፍንትው፥ ሲል ካ’ይኔ፤ ሀሳቡ ሲጠጋኝ፣ ሲከመር ካ’ናቴ፣
ውጭ ውስጧ ሲያሳሳኝ፣ ቁንጅና ተጭኖ፥ ሲኮለኮል ፊቴ፣
ውበት ሲያሸፍተኝ፣ ደምግባት ሲያቀልጠኝ፣ ሲርድ ሰውነቴ፣
ጭው ይላል ዓለሙ፥…. መላ ቅጥ አጣለሁ፤
ያንንም፥ ያንንም፥ በሆንኩ ያሰኘኛል፣ እንደማልችል ሳውቀው!
አይመረመረው፥… — የአሠራሯ ጥበብ፣ የሠሪው ችሎታ፤
አወይ አፈጣጠር፣ ወየው ሰውነቷ…!
ለጥ ያለው ሜዳ ላይ አረንጓዴ ፈስሶ፣ የሣር ልብስ ተነጥፎ፣
ውበት ተደፍቶባት፣ ወዟ ችፍ ብሎ፣ አመዷ ተራግፎ፣
ሳያት እርዳለሁ፥ ከብትነት ያምረኛል፤
— በሬነት፣ በግነት፤ ላምነት ይለኛል፤
“ሂድ ጋጠው! … ሂድ ጋጠው! … ዋልበት ከመስኩ፣
እረኞች ያግዱህ፣… ካ’ጋጋጥህ ጋራ፣ ዜማ ይሰካኩ!
ጠግበህ ስትገባም፥ ከበረት አሽካካ፣
ጌጥ ይሁንህ ገመድ፥ ታስረህ አመሰኳ! ”
ይለኛል አንዳች ኃይል! …ሰቅዞ፣ …ለብቆ፤
ከልቤ ጆሮ ውስጥ፣ ከማላውቀው ጠልቆ፣
ምሪውን አርቅቆ፣ መልዕክቱን አድምቆ፣ ውሉን አጠባብቆ፤
ደግሞ ተራራዋን፣ ኮረብታዋን ሳያት፥ — እንዳ’ንዳች ተራቁታ፣
ብርድ ውርጭ ሲጠልዛት፣ ሙቀቱ ሲያነፍራት፣
…ስታሳዝን ጊዜ! … — ጡቷ ተዝረክርኮ፣ ተጋልጦ ደረቷ፣
አመዳይ ሲለብስ፣ ቀጭ ሲወራት ጉንጯን፣ ስትከስል መድይታ፥….
“ንፋሷን ባረገኝ፣… — በተኛሁ ከላይዋ፣… ሄጄ በሸፈንኋት፤
ባሟሟቅኋት ኖሮ፣ ባባረድኋት ኖሮ፣ (እንዳ’የሩ ጠባይ) በተንከባከብኋት፣
ኩታ፣ ጋቢ ሆኜ፣ በተደረብኩላት፣ ሄጄ ባለበስኋት፣ ጠርታኝ በተላበስን፣
በሀሴት በተላቀስን፤….
እርሷንም በሞቃት! እኔንም በሞቀኝ!
ዓለሙም እንዲሁ…. — ባ’ዱኛ ቢጎበኝ!
ለእኔና እርሷ መብራት፥….
ጀምበርን በሰደብን፥ — “ይች ጎታታ! ” ባልናት፣
ጨለማን በረገምን፤ — “ከቶ አትንጊ! ” ባልናት፤…
ያሰኘኛል ደርሶ!
— የሀሳብ ሙላት ፈልቶ፣ …ሰቅዞ፣ …ለብቆ፣
ከልቤ ጆሮ ውስጥ፣ ከማላውቀው ዘልቆ፣
ደግሞ በሌላ ቀን፥ ያ’ዋሮች ስብስብ ሜዳዋን ሲያለብሳት፥
“አፅዳላት” ይለኛል፤ ”ንፋሲቷን ሁን… ሁን… ሽው በል ካናቷ፣
አውሎ ሆነህ ንጎድ! …. ኮልኮሌውን ለቅመህ፥ አንሳላት ከፊቷ፣
ጠራርገህ ውሰደው፤ — ወስደህ አሳቃቸው፣ ከአቁሻሾች አይን ክተት፣
ሲጨናበሱ አይተህ፥ – ሲሸሹ፣ ሲሮጡ – ከ’ርሷ ጋር ተንከትከት! ”
“ደግሞም ዝናቧን ሁን፥… ፍሰስ ከገላዋ፣
አጣጥባት፣ አጠጣት፣… ይታይ ቁንጅናዋ፣
ይፅደቅ፣… ያብብ፣… ያፍራ፣… ለምለም ይሁን ዘርዋ! ”
ይለኛል አንዳች ኃይል! …ሰቅዞ፣ …ለብቆ፤
ከልቤ ጆሮ ውስጥ፣ ከማላውቀው ጠልቆ፣
ተንኳልሎ ሲወርድ፥ የምንጭ ውኀ ጠርቶ፣
መንገዱን ሲጠርግ፣ መስመር አበጃጅቶ፣
ተከትሮ ሳየው፥ — ኩሬ ሰርቶ፣ ‘ረግቶ፣
ፊት ሲያሳይ አጥርቶ፣ — “መልክህን ታይበት፣
ጠጣው! ” ያሰኘኛል! — “ጥም’ን ቁረጥበት፤
ወፍ ሆነህ ድረሰው፣ ትል ሆነህ ልበሰው! ”
ድንጋይ ገርፎ ሲወርድ፥ መገረፍ ያምረኛል፣
“ተጣጠብ” ይለኛል፥ — “ተለቃለቅበት፥
ዛቀው ከመነሻው፣ ጨልፈው ከምንጩ፣
አንተ ስትረካ፣ ያ’ልቻሉት ይንጫጩ! ”
ይለኛል አንዳች ኃይል! …ሰቅዞ፣ …ለብቆ፤
ከልቤ ጆሮ ውስጥ፣ ከማላውቀው ጠልቆ፣
ዛፏን ሳይ – ወፊቱን፥ መሆን ያሰኘኛል፣ ላይዋ ማረፍ – በርሮ፣
ቤት መሥራት መቀለስ፣ ጎጆ ማበጃጀት፣… መደላደል ሰፍሮ፣
እፎይ ብሎ ማደር፣ — ቅርንጫፏን ሰብሮ፣ ግንዷንም ቆርቁሮ፣
ምናምን ለቀማ፥ — የከብቶቹን ገላ፣ ያዞን ጥርስ መበርበር፣
ማደሪያ አበጃጅቶ፣ ታዛን አሽቀርቅሮ፣ ሐሳብ ጥሎ ማደር፤
…ሲነጋ ለመብረር —
— ካ’ንዱ ዛፍ፣ አንዱ ዛፍ፤ ካ’ንዱ ስጥ አንዱ ስጥ!
ደግሞ ጦጣ መሆን፣… ደግሞ ዝንጀሮነት፥….
ዓይን የሻውን መንጠቅ፤ ከሰው ማሳ ገብቶ፣ ብቃዩን አምክኖ፣
ሲጠግቡ መጫወት፣ በደቦ አጠፋፍቶ፣ መሬት ላይ በታትኖ፤
ሲደክመኝ — ሰውነት! መጠለል ከሥሯ፣ መምከር ተሰብስቦ፣
ከዛፏ ጥላ ሥር፣ ቁጭ ብሎ መደመም፣ መጫወት ተካቦ፤
ያምረኛል ክፉኛ! …ሰቅዞ፣ …ለብቆ፤
አንዳች ልዩ ስሜት፣ ከማላውቀው ጠልቆ፤
ወንዟን ካየሁማ…፥
ቁልቁል ስታሽላላ፣ ተንጋግታ ስትወርድ፣ ቀልታ እንዳ’ለላ፣
ከአፈር ተቀላቅላ፣ ስትሄድ ቀይ ወጥ መስላ፣
“አፈር ሁን” ይለኛል! እመር ተመሳሰል፣ ስመር ከውኅው ጋ፣
ካ’ንዱ ጥግ አንዱ ጥግ፥ ባንድነት ዝመቱ፣ አብረኻት ተላጋ!
ደግሞም አጎንብሰህ፥… ከወንዙ ጠጣለት፣ ይገረም አለሙ፥
ከ’ርካታ ተዋወቅ፣ ጥምን ቆርጠህ ጣለው፥ እስከዘላለሙ! ”
ያሰኘኛል ደርሶ! የሀሳብ ሙላት ፈልቶ፣ …ሰቅዞ፣ …ለብቆ፣
አንዳች ኃያል ነገር፥ ከልቤ ጆሮ ውስጥ ከማላውቀው ዘልቆ፣
ምሪውን አርቅቆ፣ መልዕክቱን አድምቆ፣ ውሉን አጠባብቆ፤
ያ’ገሩ ገበሬ፣ ከእርሻ መሬቱ ላይ በሬ ጠምዶ ካየሁ፣
“ብረት ሁን! ” ይለኛል፥ ያች ማረሻይቱን መሆን ያሰኘኛል፤
“በከብቶች ጉተታ፣ በገበሬው ግፊያ፣ መሬቷን ቆፍራት፣
ዘልቀህ አተራምሳት፥ ቀድሞ እንዳልታረሰች፥ ሂድባት፣ ዝለቃት! ”
ይለኛል አንዳች ኃይል! …ሰቅዞ፣ …ለብቆ፤
ከልቤ ጆሮ ውስጥ፣ ከማላውቀው ጠልቆ።
አፍ አስከፋች መልኳን፣… ውስብስብ ስሪቷን፣… አቀነባበሯን፣
አደንዛዥ ቀለሟን፣… አስፈንጣዥ ውበቷን፣… ልዩ አሰዳደሯን፣
አጃኢብ፥ ኩነቷን፣… ጉድ፥ አተካከሏን፣… ታምር፥ አሠራሯን፣
የተፈጥሪት መልኳን፤… ጥፍጥና፣ ጣዕሟን፣
የእግዜሩ እጅ ሥራ፣ ድብልቅልቅ ቀለሟን፥
ወፈ ሰማይ ሳይ ግን፥…
አንቺ የእኔ በራሪ፥ ትዝ ትይኝና፣ ወፍነት ያምረኛል!–
ሩቅ ይዞሽ መሄድ፣ መምጫሽን ጠብቆ፣
ሰማይ ላይ መከተም፣ ከመሬት ተላቅቆ፣
ቁልቁል መገላመጥ፣ ማንዣበብ ማማተር፣
ውድ አንቺን ፍለጋ!ውድ አንቺን ጥበቃ!
— ያሰኘኝን ሁሉ፥ ባንዴ’ምሆንብሽ፣
ሁሉንም ባንድ ላይ፣ ውድ አንቺን ስወድሽ፣
ካ’ንቺ ጋር ስገናኝ፣ ካ’ንቺ ጋር ስተይ፣
ከፍቅራችን ምድር፣ ከውዳችን ሰማይ፣
አፍ አስከፋች — አንቺ!
አደንዛዥ፣ አስፈንጣዥ፣ ልዩ ጥዑም — አንቺ!
ውድ አንቺን ስወድሽ….
ካ’ንቺ ጋር ስገናኝ፣ ካ’ንቺ ጋር ስተይ፣
ከፍቅራችን ምድር፣ ከውዳችን ሰማይ፣
ሳሮች ይዋባሉ! ምድር ታበራለች!
ከብቶች ይተኛሉ! እረኞች ያርፋሉ!
ተራራው ይናዳል! ኮረብታው ይፈርሳል!
ነፋሱም ያፏጫል! ዛፎች ያረግዳሉ!
ፀሐይ ትፈዛለች! ዝናብ ይጨፍራል!
ጨረቃ ታብዳለች! ከዋክብት ያፍራሉ!
ምንጮች ይረጋሉ! ቀጥ ይላል ዓለሙ!
ወንዞች ይቆማሉ! አህዋፍ ያዜማሉ!
መንጩም አደግዳጊ፣ ባሳየነው ተጓዥ!
ሳር ቅጠሉ ታዛዥ!
ከእኔና አንቺ ምድር፣
ከእኔና አንቺ ሰማይ፣
/ዮሐንስ ሞላ/
————
በዚያው ማስታወቂያ 🙂
በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥኑ 72፥ አጫጭርና ረዣዥም ግጥሞች የተካተቱባት መፅሐፌ፥ “የብርሃን ልክፍት” ገበያ ላይ ነችና አንብቧት። “የብርሃን ልክፍት”ን ለመግዛት (ለማዘዝ) ከታች ያለውን ይጫኑ።