የብርሃን ልክፍትን ስንመርቀው! …በነፃነት ተስፋዬ

xhfanበነፃነት ተስፋዬ
(netsatesfa@gmail.com)

“ዕንቁ” መጽሔት፣ ቅፅ 6 ቁጥር 92፥ ግንቦት 2005 ዓ/ም

ለራስ ሳይሆን ለሌላ ሰው ብርሃን ለመሆን መነሳት ትልቅ የሕይወት ውሳኔን ይሻል። ዕድሜ ልክን እንደ ጃማ ለሕዝብ አዳም ወ ሔዋን ብርሃን እየሰጡ እስከ መጨረሻዋ ጭላንጭል መትጋት፣ ከዚያም ቀልጦ መቅረትን። ይህን መታደል የሚያገኙትና የሚፈፅሙት ደግሞ ጥቂት ናቸው። ብርሃን ለመሆንም እኮ መታደግ ያስፈልጋል። ለሌላው ብርሃን ለመስጠት ሲሉ መጣር፣ መጋር፣ መፈተን፣ መከራን መቀበል ሁሉ አለ። አንዱ እንደ ሻማ ብርሃን ሰጥቶ ቀልጦ ሲያልቅ፣ ወይም እንደ አምፖል ሲቃጠል፣ በምትኩ ሌላ ሻማ ወይም አምፖል የሚሆን ሰው እየተተካ እዚህ ደርሰናል።

እኛ ደግሞ ብርሃን ሆነው መንገዳችንን ያመለከቱንን፣ ጨለማውን ያበሩልን እና ሕይወታችንን ያደመቁልንን ትጉህ ሰዎች ማሰብ፣ ማድነቅ፣ ማመሰገንና ማክበር አለብን። ልብ ያላቸው መቼና የት ቦታ ሆነው ብርሃን እንደለገሱን እንኳን የማናውቃቸው ስንት ሻማዎቻችን ነበሩ፤ አሉ።

ዮሐንስ ሞላ ታዲያ ብርሃን የሰጡንና እየሰጡን ያሉትን ከልቡ ጥፏቸው ኖሮ “የብርሃን ልክፍት ያለባቸው ናቸው።” አለና የግጥም መድብሉን “የብርሃን ልክፍት” ብሎ ሰየመው። ምክንያቱንም የመጽሐፉ የጀርባ ሽፋን ላይ እንዲህ በማለት ገልፆታል።

ለሌሎች ብርሃን የመሆን ፀጋ ተችሯቸው፤… ብርሃን በመሆን ምግባር ተለክፈው፤… ወይ ደግሞ እንዲሁ ጥሎባቸው፤… ለሰው ልጆች ጥቂት ብርሃን ለመስጠት በብዙ የመከራ እሳት ውስጥ አልፈዋል። በየቦታው የሚቃጠሉም አሉ። — ምናልባት ያሰቡትን ብርሃን በመሆንና ባለመሆን መሀል ግብራቸው በውል ሳይለይ በከንቱ!

ሌሎች ደግሞ ብርሃንን በማየትና በመፈለግ ተለክፈው፣ በመከራ ውስጥ ሳሉ እንኳን ‘የብርሃን ያለ…’ ብለው ዋትተው ስለ ብርሃን ብዙ ደክመዋል። በየጊዜውና በየሁኔታው የሚማስኑም አሉ።….– ምናልባት የፍለጋቸው ስምረት በሰዎች ተቃጥሎ የማብራትና የማለፍ ዋጋም ቢሆን ግድ ሳይሰጣቸው።…. — አንዳንዴ እየተሳካላቸው፤…. አንዳንዴ ደግሞ፥ እንዲሁ በከንቱ!

ልክፍት ነው! የብርሃን ልክፍት!

በመድብሉ ውስጥ በመጽሐፉ ርዕስ የተሰየመ ግጥም ባይኖርም በብርሃን የመለከፍ ጠረን ያላቸው ግጥሞች አሉበት። በተለይ ”የእኔ ፍቅር ላንቺ“ በሚል ርዕስ የቀረቡት ግጥሞች የዚህ ቃና አላቸው። ዮሐንስ የግጥም መጽሐፉን ባስመረቀበት ድግስ ላይ ግን “የብርሃን ልክፍት” የተሰኘውን መድብሉ ውስጥ ያልተካተተ ግጥሙን ለእድምተኞቹ አንብቧል።

ብርሃን ሆነው ላደመቁን ሁሉ ይህን ክብር መስጠት ያኮራል። አርአያነትም ነው። ለዛሬው ማንነታችን መሠረት የሆኑንን ያውም በወጣት ገጣሚ ከሥነ ጽሑፍ በረከት ጋር ማመስገን ቢያውቁም ባያውቁም የሕሊና ሜዳሊያ እንደመሸለም ይቆጠራል። ገለታ ይግባህ።

ዮሐንስ ሞላ ማኅበራዊ ሚዲያን በተለይ ደግሞ ፌስቡክን ለሥነ ጽሑፍ ገበታነት እየተጠቀመ ያለው ንቁ ትውልድ አባል ነው። “ጠይም በረንዳ” የተሰኘ የፌስቡክ ገጽና የራሱ ብሎግ አለው። የብዕሩን ጠንካራነት ያየሁት በነዚህ ገጾች ላይ በሚያቀርባቸው ወጎች፣ ምልከታዎች፣ ግጥሞችና በመሳሰሉት ጽሑፎች ነው።

ይህ የማሕበራዊ ሚዲያ መድረክ በርካታ ወጣት ጽሐፊዎችን ያፈራ ሐሳብን በነጻነት የመለዋወጥ መድረክ የፈጠረ፣ በቀላሉ ሊታተሙ ያልቻሉ ጽሑፎችን በራሳችን ቋንቋ ያገኘንበት ነው። መድረኩ ልክ እንደ ሥነ ጽሑፍ ክበባት ተስፋ ያላቸው ጸሐፊዎችን እየፈጠረ መሆኑን አፌን ሞልቼ እናገራለሁ። የመጻፍ አቅማቸውን የሚያዳብሩበትን የጥበብ መጋሪያ እንዲያቁሙ አድርቿቸዋልና።

በዓይነ ሥጋ ተያይተው የማያውቁ ግን በብዕሮቻቸው የሚተዋወቁ ወጣቶች በተለይ በፌስቡክ ላይ በሚፈጠሩ የጥበብ ገጾች ላይ እያደረጉት ያሉት ተሳትፎ የሚደነቅ ነው። “የብርሃን ልክፍት” በተመረቀበት ዕለት በጽሑፎችቻቸው ብቻ የሚተዋወቁ ባለገጾች ዐይን ለዐይን ተገናኝተው ተጠፋፍተው እንደተገናኙ ዘመዳሞች ሠላምታ ተለዋውጠዋል። ይህንኑ ስሜታቸውን በምረቃው ምሽትና ዋዜማ በየፌስቡክ ገጾቻቸው ላይ አዝንበውታል።

በምረቃ በዓሉ ላይና ከዚያም በኋላ ድርሰቶቻቸውን አሳትመው በቅርቡ የሚያስመርቁ እንዳሉ ሰምተናል። ዮሐንስ ብዕሩን አትብቶ  ይህን የግጥም መድብል ለአንባቢያን ሲያቀርብ ለአገራችንም ሥነጽሁፍ አንድ ተጨማሪ መጽሐፍ አበርክቷል ማለት ነው። በድርሰቱ ይዘትና አቀራረብ ላይ ግንቦት 8 ቀን 2005 ዓ.ም. በተካሄደው የምረቃ ሥነሥርዓት ላይ ደረጀ በላይነህ ጥሩ አስተያየት ሰጥቷል።

በበኩሌ፥ “የብርሃን ልክፍት” ጥሩ ግጥሞችን ይዟል እላለሁ። በውስጣቸው ጠንካራ ሀሳብ አለ። የደራሲው ጥብቅ ስሜት ይነበባል። አብዛኞቹ አገራዊ ጉዳይን የያዙ፣ የአገሬ ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ ናቸው። ረጃጅም ግጥሞቹ ርዕሰ ጉዳዩን በጥብቀት ይዳስሳሉ። በተለይም ጥሩ የቃላት አጠቃቀም አቅም አለው። የሚጠቀምባቸው ቃላት ቀላል፥ ግን እምቅ ሐሳብ የሚገልፁ  ናቸው። አዳዲስ ቃላትን ፈጥሮ መጠቀሙ፣ የግዕዝ ቃላትን እንደምስል መቁጠሪያ መገልገሉ፣ ድርጊት ገላጭ ቃላት በመደርደር ክዋኔን በቃላት ማሳየቱና የመሳሰሉት የአቋም ማሳያ ሆነው ሊጠቀሱ ይችላሉ። መንፈሳዊ ዕውቀቱ ለቀደም ጠቃሽ አጻጻፍ የግብአት ምንጭ ሆኗል።

ሥነ ቃላትን የግጥም አካላት ማድረጉ በታሪክ ላይ የተመሠረቱ ሁነቶች ላይ ተመርኩዞ ጉዳዩን ከአሁኑ ዘመን ሁነት ጋር እያነጻጸረ ማቅረቡ፣ የብዕር ጥንካሬውን ያመለክታል። “ከአያያዝ ይቀደዳል፣ ካነጋገር ይፈረዳል” ነውና ይህ መጽሐፍ ወደፊት ከዮሐንስ ብዙ እንድንጠብቅ ያደርገናል።የሞፈር አያያዙንና የማረሻውን አተካከል በውል ያወቀ ጀማሪ አራሽ ሞፈሩን ተከትሎ አድምቶ እንደሚያርስ ሁሉ በመጀመሪያ መድብሉ ላይ ያየነውን የብዕር ትጋት ይበልጥ አጠብቦ እንዲሄድ እንመኛለን።

ከፌስቡክ ገጾችና ከምረቃ ዝግጅቱ እንዳስተዋልኩት ዮሐንስ ጥሩ እንደሚጽፍ የሚያውቁ፣ የሚያበረታቱትና የሚያደንቁት በርካታ ወዳጆች አሉት። ይህ መልካም ማበረታቻ ነው። ነገር ግን አድናቆቱ በዝቶ ከብዕሩ ጥንካሬ እንዳያናጥበው መጠንቀቅ አለበት። ወዳጅ ጓደኞችም ምስጋናና አድናቆት ብቻ ሳይሆን የሒሳዊ ንባብ አስተያየታችሁን ለግሱት።

ዮሐንስ የሚቀጥለውን መጽሐፉን ሲያቀርብልን የሚያመጣውን ለውጥ የምናየው እነዚህን አስተያየቶች ተቀብሎ ምን ያህል በግጥም ገበታ ላይ እንዳደፋጨ ስናይ ነው። ውስጡ ትጋት እንዳለ ስላስተዋልኩ የሚቀጥለው መድብሉ የራሱን ወዝ፣ ስልት፣ ወጥነት፣ ቃላት አጠቃቀም የያዘ እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ።

በነገራችን ላይ የእኔ ፍቅር ላንቺ አንድ፣ ሁለ፣ ሦስት እና ፍቅሬ ሙዚቃዬ የተሰኙት ግጥሞች ከያዙት ጥልቅ መልዕክት በተጨማሪ ስሜትን የሚነካ ሙዚቃዊ ቃና ስላላቸው አንጀትን ሰርስሮ በሚገባ ዜማ ሚካኤል በላይነህ ወይም ቴዎድሮስ ካሳሁን እንዲዘፍኑት ቢሰጣቸው?

/ነፃነት ተስፋዬ የኮምዩኒኬሽን፣ የሚዲያና የሥነ ጽሑፍ ባለሞያ ነው።/

 

 

“የብርሃን ልክፍት”ን ለመግዛት (ለማዘዝ) ከታች ያለውን ይጫኑ።

Buy Now Button with Credit Cards

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s