ዓለምዬ – “ናና”….

ዓለምዬ ናና ናና ናና…
አንተ ጉብል ናና፣
የአገሬ ልጅ ናና…

የሚለው የድምጻዊት መሰሉ ፋንታሁን አሪፍ ዘፈን ትዝ ብሎኝ፥ በስሜት ጆሮዬን imagesCA4BEEXZመምታቱን ተከትሎ፥ “ናና” ከረሜላ ባይኔ ላይ ዞረ። ….ናናዬ፣ ናና ገላ፣ ናንነት፣ ናኑ፣ የእኔ ቆንጆ፣ የእኔ ክብ ጠፍጣፋ፥ ጎማ መሳይ – ጉንፋን ከረሜላም ትባል ነበር – ….በ5 ሳንቲም ገዝተናት በልጅነታችን የ5 ብር ዓለም ታሳየን ነበር። ናና ከረሜላ (በወጣትነት የሴት ቻፓ ሰረቅ አድርገን አይተን ደስ እንደሚለን  🙂 ) ገና ሲያይዋት ጀምሮ ነበር የምታረካው። ….ለእኔ እንደዚያ ነበር።

ደግሞ አንዳንድ ጊዜ፥ ላይዋ ላይ የሆነ ጽሁፍ ይጻፍባት ነበር። ….ምን ነበር ዛሬ አግኝቼያት ባነበብኩት ኖሮ? ይኽኔ “የኔ አፍቃሪ ጩጬው ጆዬ፥ ዓላማዬ ዓለምህን ማጣፈጥና አንተን ከፍ ከፍ ማድረግ ነው።” ሊሆንም ይችላል’ኮ። ሄሄሄ…. ናና በእጅ ስትጨበጥም የልጅነት እጃችንን ሞልታ ታስጨንቀን ነበር። ….አትወድቅም እንጂ!፥ ድንገት አፈትልካ ከእጅ ላይ ብትወድቅ ደግሞ ቀድመናት መሬት ደርሰን፥ ተነጥፈን ነበር የምንጠብቃት። …በዚያ ላይ ‘ከእጅህ ወጥቼ ካልዋጥኸኝ’ ብላ ስትታገል። ትኩስ ምራቅ አፍን ሞልቶ በሀሳብ ሲጎትታት! ….ይምጣብኝ አቦ!….በዚያ ላይ ነጭነቷ። ምጵጣ! ምጵጣ!

ዓለምዬ ናና ናና ናና…
አንተ ጉብል ናና፣
የአገሬ ልጅ ናና…

የልጅነት ቀልባችን፥ ከረሜላይቱን…. ጣፋጭቱን…. መልከመልካሚቱን…. ማሪቱን….. ነጪቱን…. ክቢቱን…. ጎማ መሳይቱን…. ስኳሪቱን…. ወለላይቱን….. ናናይቱን……… በማየትና፥ በምላስ በኩል ለመቅመስ በመከጀል መካከል ሆኖ ሲሰቃይ፣ በአውራ እና በሌባ ጣቶች መካከል ጨምድደን ይዘናት፤ ከናካቴው ሳናስገባው — ኋላ እስክንኮረሻሽመው ድረስ — ምላሳችንን አሹለን እያወጣን ጎን ጎኗን ላስ ላስ እናደርጋትና የበለጠ እንጓጓ ነበር።

ጊዜዋ ደርሶ ጥቅልል ብላ ከአፋችን ስትገባ ደግሞ ጥፍጥናዋ ከመሬት ከፍ ያደርገን ነበር። ….ናና እየመጠጡ አየር ላይ መቅዘፍ ደስ አይልም? – እጥፍ ድርብ ሀሴት!ውይ ናና፥…. ወላ ልጅ እያለሁ “ህብስተ መና” ሲባል ናና ይመስለኝ ነበር። የሆነ ከሰማይ ወርዶ ለንጹሀን ሕፃናት የታደለች። ከንጹህ ልጅነት ትንሽ ከፍ ብዬ ብልጠት ምናምን ስጀማምርና ናና ከገበያ ስትጠፋ ሰሞን፥…. መጥፋቷ አጢሀት መስራት ስለጀመርን፥ መቀጣታችን ይመስለኝ ነበር።

የናና ነገር ከሱቅ መስኮት እስከቤት በራፍ ድረስስ የት ያስችልና?! ….በተለይ እንደ እኔ “መንገድ ላይ መብላት የሌባ ነው። ሰው ቤት ሲበላ የሚያሳፍረውን ነው መንገድ ላይ የሚበላው። ልክስክስ አትሁን….” እየተባለ ያደገና፥ አታድርግ የተባለውን ቢያደርግ “ያዝኑብኛል“ ብሎ የሚሰጋ ልጅ ላይ ስቃዩ ይበረታል። …..አቤት ከሱቅ እስከ ቤት ርዝመቱ (ይህን ያህል ነበር፥ > ——————————————————————————— ∞ )…. በጊዜ ከለካነው ደግሞ፥ ከሱቅ ቤት እስኪደረስ የነበረው ጊዜ፥ በሚጎትት ቴፕ እንኳን ሶስት “ዓለምዬ ናና” አዘፍኖ “ኮርናስሜ”ን ያስመርቅ ነበር፤…. ለያውም በአዩኝ አላዩኝ ላስ ላስ ታጅቦ ነዋ!……

ዓለምዬ ናና ናና ናና…
አንተ ጉብል ናና፣
የአገሬ ልጅ ናና….

ማጋነን እንደው ዴሞክራሲ መብታችን ነው! ሃሃሃ….

ኡኡቴ…..
ከሰው ሰምታ’ቴ፣….
ይህቺ ፈጣጤ፣
ኡመቴ፥
መጥታ ተኛች ከደረቴ!
ቴ ቴ….

ናና ከረሜላ ተመጥጦ ጣእሙ በጉሮሮ ሲወርድ ሕልም ይመስልና፥ ጉሮሮውን ሁሉ ገብቶ መላስ ያስመኝ ነበር። ናና የተጨበጠበት እጅ (በምራቅ ረጥቦ ከሆነ) መዳፍ ሳይቀር ያስልስ ነበር። ለእኔ እንደዚያ ነበረ።… ወላ የመጨረሻውን የናና ወለላ ከዋጥኩኝ በኋላ፥ በማጣጣም ምላሴንና ላንቃዬን (ምጵጣ! ምጵጣ! እያልኩ….) ሳማታና ወደ ውስጥ መጥጬ ስውጥ፥ ታፍኜ እንዳልሞት ሁላ እፈራ ነበር። (ብዬ ማጋነንና ማጋጋል መብቴ ነው። ሄሄሄ….)

የሰፈሩን እኩያ ቁጫጮች ለማስገበሩና ለማቁለጭለጩ ቢሆንስ፥ ማን እንደ ናናዬ? — ደጉ ዘመን በ5 ሳንቲም አለቃና ምንዝር ይበጁ የነበረበት! ፓ! ዛሬ “ናልኝ…. ናና…..” ቢሉት፣ ቢጠሩ ቢያንቆላጵሱት የት ሊሰማ? ….ኦ ልጅነት – ዓለም! ….ኦ ልጅነት – ጉብል! ….ኦ ልጅነት – የአገር ልጅ!

ዓለምዬ ናና ናና ናና…
አንተ ጉብል ናና፣
የአገሬ ልጅ ናና….

እኛ ቤት ደግሞ ናና ከረሜላ ለትንንሾቹ የደስታ ምንጭ ብቻ ሳትሆን፣ ለትልልቆቹም የጨጓራ ህመም መድኃኒት ነበረች። ከታላላቅ ወንድሞቼ አንዱ (ሶስተኛው) “ጨጓራዬን አመመኝ” ብሎ እርሷን ያስልክና፥…. ገና አፉ ስትገባ “እፎይ” ማለት ይጀምራል። (እኔን ሲልከኝ የናናው ዱቄት እጄ ላይ እንዲቀርልኝ መታ መታ አድርጌ፥ መዳፌን ልሼ ነበር የምሰጠው።) ….የናናን የፀረ አሲድነት ሀልዮት ቀድሞ ወደ ቤታችን ያመጣውም እርሱ ነው።

ከዚያ ሌሎቹ “ጨጓራዬን” ሲሉ አሳምኖ እያዘዘላቸው ተለመደች። ….ታዲያ ግን በ“ላንቺም አምጪ ለእኔም ስጪ” ዘይቤ ነበር። ለእነርሱ ያዝዝና ለራሱም ይመጣታል። ….የእኔ ናና፣ የእኔ anti-acid!– ይኸው ዛሬም ድረስ ሰው ጨጓራውን ሲታመም ትዝ ትለናለች።  ዛሬም ተልኬ እጄ ላይ ዱቄቷን አራፍጌና ሸቅቤ መስጠት ያምረኛል። አዬ… ዛሬ ማን ሸጧት ማን ሊሸቅብ?!

እንዲያውም ከእለታት ባ’ንዱ ቀን ‘ናና ኪኒን’ ክፉኛ አምሮኝ፥ “አይዞህ” ብለው ቢገዙልኝ ብዬ፥ “ጨጓራዬን አመመኝ” ብዬ ተንቆራጠጥኩኝ። አንቆራጠጡን አልቻልኩበት ሆኖ ነው መሰል ነቄ ብለው፥ “ምኑ ጋር ነው ያመመህ? ጨጓራ የቱ ጋር ነው? ” ብለው ማፋጠጥ፤…. እኔም ጉሮሮዬን ነክቶ ማሳየት! ወዲያው ቤቶቼ ከት ብለው ሲስቁና እኔ ሳለቅስ እኩል ሆነ። ‘ልጅ ስላለቀሰ ማባበል ያጨማልቃል’ የሚሉት ነገረ  ባትኖራቸው ኖሮ፥ ….ማባበያ፣ የእንባ ተከታይ ናና ይሆንልኝ ነበረ። ያን ቀን ግን እንዳማረኝ ቀረ።

ውሸት ይቅር ሲሉኝ፥
“አልሰማም አልኩና!”
አመለጠኝ ናና!….
እንባ ገዴ ናና፣
አረጣጥበኝና፥
አስገዛልኝ ናና! ሃሃሃ….

(እንደውም ግጥም የለመድኩት “ናና…ና” ስል ነው ምናምን ብዬ ልቀውጠው እንዴ? ሄሄሄ….)

ግን እኮ ያን ጊዜ ጨጓራዬን አሞኝ ነበረ። — የናና ጨጓራዬን አሞኝ ነበረ። አሁንም ናና ናፍቆኛልና ጨጓራዬን አሞኛል። ….ናና የጨጓራ መድኃኒት ከሆነ፣ የእኔ ጨጓራ ያለው ጉሮሮዬ ላይ መሆን አለበት። ….ናና የጨጓራ መድኃኒት ከሆነ፣ መላ የልጅነት አካላቴ ጨጓራ መሆን አለበት። ….መንፈስና ስጋዬ ጨጓራ መሆን አለበት። — እንዲያ ነዋ የሚያክመኝ። እንዲያ ነዋ የሚፈውሰኝ። አሁን ይህን ታይፕ ሳደርግም ጉሮሮዬ ላይ የሆነ ነገር ይላወሳል። ምላሴም ላደርስበት ይንጠራራል። – እንዲህ ነው ናና ትዝ ሲል!

ካደግሁኝ ወዲህ ዝም ብዬ ሳስበው ግን፥ ወንድሜ ምናልባት “እንደልጅ ከረሜላ ይመጣል” እንዳይባል የዘየደውና፣ ለሌሎቹ አቀብሏቸው፥ መሸሸጊያ ያደረጓት ታርጋ ትመስለኛለች። ….ወይ ደግሞ በናናው ረክተው “እፎይ” እያሉ አየር ወደ ውጭ ሲያስወጡ፥ የጨጓራቸው ህመም ቀለል እያለላቸው ሊሆንም ይችላል። ይሆናል። ….መቼስ አይሆንም አይባልም። ….ልጅ እንዳይበላው ሲፈለግ፥ ማርስ ያኮላትፍ የለ? ሄሄሄ…

ልጅ እያለሁ “ተስፋሁን” የሚባል ኮልታፋ የት/ቤት ጓደኛ ነበረኝ። ተስፋሁንን በጣም እወደው ነበር። ሲኮላተፍ ደግሞ የሆነ ከሌላ ዓለም የመጣ ነበር የሚመስለው። ….የገዛ ስሙን እንኳን “ሸሽፋሁን” ነበር የሚለው። (እንግዲህ እኔን ሲጠራ እንዴት ሊሆን እንደሚችል መጠርጠር ነው። ….የሆነ እንደተበላሸ ቴፕ “ሽሽሽሽ….” ይላል።) ….ከዚያ እኔ አማረልኝ ብዬ፥ የፍቅሬን “ሼሾ” አልኩት። ስሙም ሼሾ ሆኖ ቀረ። ያኔ… እኔማ የተኮላተፍኩ መስሎኝ ደስ ብሎኝ ነበር። ”ማር ያኮላትፋል” ሲባል ደስ ብሎኝ፥ ጓደኛዬን ልመስል ተደብቄ ማር መላስ ጀመርኩኝ።

ስልስ ስልስ ስልስ…. ከእለታት በአንዱ ቀን ከሌላ ኮልታፋ ከማይሉት ገመድ አፍ ጋር ተዋወቅሁኝ። ውይ ሲያስጠላበት። እኮላተፍ ብሎ ስም ያበላሻል። አስጠላኝ። ኮልታፍነትም አስጠላኝ። ….ናና ግን አላስጠላኝም። እንዲያውም በብስጭት የናና ሻይ ማፍያውን ተክል ተክዬ፥ ከስመ ሞክሼው ናና ሻይ ጋርም ፍቅር ያዘኝ። የናና ቅጠል መዓዛ ደግሞ ሌላ ነው። ….ኮልታፋና ማር ግን አስጠሉኝ። ከዚያ ከራሴ አልፎ ተርፎ ጓደኞቼን ሁሉ “ማር አትላሱ” እያልኩ እሰብክ ነበር።

እናቴ “ማር ፀጉር ከተቀባ ያሸብታል። እንጂ ልጅ ቢልሰው አይኮላተፍም። ….የድሮ ሰው ራሱን ስለሚንከባከብና ልጆች ጣፋጭ ስለሚወዱ ልሰው እንዳይጨርሱበት የፈጠረው መላ ነው….” ብላ ከአባቴ ጋር ስትከራከርና ሲናደድ (ምናልባት ስለነቃችበት ይሆናል) ደስ አለኝ። እንዴት እንደተንተከተኩኝ አልረሳውም።…. በጣም ጣፋጭ ሳቅ ስለሳቅሁኝ የናና ጥርሶች የበቀሉልኝ መስሎኝ ነበር። ….ታዲያ ካላኮላተፈማ ከማር ጋር ምን ፀብ አለኝ ብዬ ልተወው? ….“ና ግባ በሞቴ” እያልኩ እልሰው ጀመር። እርሱን ሳስብ አሁንም ጥርሶቼ ባሉበት አረገዱ። አሁን ያማረኝ ማር  ግን ናና ነው። የመቀሌ ማር ዓይነት ነጭ፤ ግን ደረቅ ክብና ጠፍጣፋ። ናናዬ፥ የልጅነት ዓለሜ….  — ናና!

ዓለምዬ ናና ናና ናና…
አንተ ጉብል ናና፣
የአገሬ ልጅ ናና….

ናንዬን ግን የትኛው የከረሜላ ፋብሪካ ነበር የሚያመርታት? ማን ነበር የሚያስመጣት? አሁን ለምን ተዋት ታዲያ? ለነገሩ እዚህ አገር ደንበኞች እንደሚወዱት ከታወቀ ምርት ይቆማል። ለምሳሌ: አድጌ በጉሮሮዬ ሳንቆረቁራት ሙዚቃ የምጠጣ ይመስለኝ የነበረችው የላይኛው አዋሽ አግሮ ኢንዱስትሪ ያመርታት የነበረችው የቲማቲም ጭማቂ፥ ፈላጊዋ ሲጨምር (ምናልባትም እኔ ስለወደድዃት) ደብዛዋ ጠፋ። እኔም በናፍቆት ጉሮሮዬ እየተንቀጠቀጠ፣ በቅዳሜዎች እርሷን ፍለጋ ሱፐር ማርኬት ለሱፐር ማርኬት ሳስስ አረጀሁ። ….መቼስ ይሁና! እስኪ ናና ሻይ ፉት እያልን ብርዱን በ “ዓለምዬ ናና” ሙዚቃ እንሸውደውማ።

ዓለምዬ ናና ናና ናና…
አንተ ጉብል ናና፣
የአገሬ ልጅ ናና….

ኩታ ትወዳለህ መባሉን ሰምቼ፣
ይኸው እፈትላለሁ እንዝርቴን አንስቼ።
እንኳን ለሚወዱት አርሶ ለሚጭን፣
ለእንዝርት ይከፈታል የሸጋጎች ጭን።
ድማሙ መሸ እንግዲህ ደግሞ
ደማሙ ደህና እደር ወዳጄ….

የዘፈኑን ግጥም ቀጥሉልንማ። ወይ ደግሞ ዘፈኑን ወዲህ ክሉልኝ!DSC02890

ብታምኑም ባታምኑም:

ይህንን ጽፌ ጨርሼ ልለጥፈው ስል ለወዳጄ ፍፁም “ናፍቆኝ፥ ስለ ናና እየጻፍኩ ነው” ብያት ተሳስቀን፥ ሰው እንደሰጣት ነግራኝ ሃያ የሚጠጉ የናና ፍሬዎች አበረከተችልኝ። (ናንዬ Pepermunt በሚል ስም ታሽጋ ዓለሟን አይታ። ፍፄም ከሶስት እሽጎች አንዱን ለቀቀችብኝ) …..እኔ አሁንም አሁንም እየዋጥኹኝ አላበረክት አልኩት እንጂ!(በዚህች ቅፅበት እንኳን እጄ ላይ 11 ፍሬ ቀርቷል። – you see my hand?  🙂 ) ….የምንፈልገውን፣ የናፈቀንን ነገር እንጎትተዋለን ማለት እንዲህም አይደል? — ‘law of attraction’ ይልሃል ፈረንጅ!

ከናፈቃችሁት ጋር ያገናኛችሁማ!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s